ሰዎች ተስፋ ለምን ይቆርጣሉ?
ተስፋ ለሰዉ ልጅ የተሰጠዉ ትልቁ ስጦታዉ ነዉ። ይህም ሰዎች ነገን እዲናፍቁ የሚያደርግ ነዉ፡፡
ለመኪና መንቀሳቀስ ጎማ እደሚያስፈልግ ሁሉ ተስፋም ለሰዉልጅ እንዲሁ ነዉ። ተስፋ ከሌለ ጨለምተኝነት ይበዛል፡፡
የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሰዉ ልጆች በተለይ በሕይወታቸዉ አስቸጋሪ ዉጣ ወረድ ዉስጥ ሲገቡ ወይም የማያልፉት የሚመስል ፈተና ሲገጥማቸዉ በዉስጣቸዉ የሚፈጠር ከፍርሀት፣ ከስጋት እና ከእምነት ማጣት የሚፈጠር እጅግ ከባድ ስሜት ነዉ፡፡
- ከዚህ ባለፈ ሰዎች ተስፋን በሶስት መንገድ ሊያጡ ይችላሉ፤ በሰዎች፤ በሃሳቦች፤ በነገሮች፡፡
- ተስፋ ብዙም ባይሆን ከድብርት እና ጫና ጋር የሚገናኝበት ባህርይም አለዉ፡፡
- አንዳንድ ጊዜም ይህ ነዉ የሚባል ምክንያት ሳይኖረን ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፡፡
- በአንድ ነገር ሰዎች ያልረኩ ከሆነና ከሚጠበቅባቸዉ ነጥብ በታች የሚያመጡ ከሆነ የዚህ ስሜት ተጠቂ የመሆን ዕድል ሊኖራቸዉ ይችላል፡፡
ታዲያ ይህ የስሜት ቀዉስ ከባድ በመሆኑ ከዚህ ስሜት ለመዉጣት ከፍተኛ ትግልና ረጅም ጊዜ የሚጠይቅ ነዉ፡፡
የተስፋ ማጣት መገለጫዎች፦የኃዘን ወይም የድብርት ስሜት፤ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና የእንቅልፍ እጦት፤ የራስን ጽዳት እና የጤንነት ሁኔታ ችላ ማለት ከቤተሰብ፣ ከጓደኞችና ከሚኖሩበት ማህበረሰብ መራቅ፣ በትምህርት፣ በሥራ እና በልዩ ልዩ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ አለመሆን፡፡
ከፍተኛ የጥፋተኝነትና የሃፍረት ስሜት መሰማት (ሕይወቴ ትርጉም የላትም፣ ለሌሎችም ሰዎች ሸክም ነኝ፣ በሥራዬም ውድቀት እንጂ አሸናፊነት አልቀዳጅም ብሎ ማሰብ) የተስፋ እጦት ከሚፈጠራቸዉ ስሜቶች መካከል የተወሰኑት ናቸዉ፡፡
ታዲያ የእነኚ ስሜቶች ድምር ራስን ወደ መጉዳት እና ከፍ ሲልም እራስን ለማጥፋት የተለያዩ መንገዶችን ወደ መፈለግ ይመራል፡፡
ከተስፋ መቁረጥ እንዴት እራስን መጠበቅ ይቻላል?- ችግርን በአግባቡ መረዳት
- ከትናንት መልካሙን እየወሰዱ ክፉዉን አርቆ መጣል እነዲሁም አዲሲ ነገር ለማወቅ፤ ለመስራት እራስን ለለዉጥ ዝግጁ ማድረግ ተገቢ ነዉ፡፡
- ተስፋ መቁረጥ ከተደጋጋሚና አሰልቺ ሕይወት የሚመነጭ ሊሆን ስለሚችል ሥራቹሁን፣ አካባቢያቹሁን ወይም ለነገሮች ያላቹሁን ዕይታ መለወጥ ከቻላችሁ የችግሩ ተጋላጭ አትሆኑም፡፡
- ይህ ማንኛዉም የሰዉ ልጅ የሚሰማዉ ነዉ ብሎ ማሰብ እና በእኛ ላይ ብቻ እንዳልተፈጠረ ማሰብ፡፡
በተጨማሪም ሁሉም አዲሲ ቀን የራሱ በረከት እናዳለዉ በማሰብ ትናንት የወደቃቹ ከሆነ ነገ እንደምትነሱ በማመን፣ ትናንት ከከሰራቹ ነገ እንደምታተርፉ በማሰብ፣ ትናንት ያጣቹትን ነገ እንደምታገኙት በማሰብ በአሉታዊ ሳይሆን በአዉንታዊ በማየት ነገን የተሸለ ማድረግ ይቻላል፡፡
በመጨረሻም እርዳታ መጠየቅ የበታችነት ባለመሆኑ፤ አንዱን የከበደዉ ቀንበር ላንዱ በመቅለሉ በዚህ የስሜት ቀዉስ ዉስጥ ያሉ ሰዎች ስነልቦና ባለሙያዎችን፤ እንዲሁም አጠገባቸዉ ያሉ ከነሱ በላይ ሰዎችን ማማከር ዕርዳታን መጠየቅ ይገባል፡፡
አቶ ልዑል አብረሃም (የስነልቦና ባለሙያ)
@melkam_enaseb