#ከዜናዎቻችን| የቢሾፍቱ ከተማ አብዛኛው ስፍራ ለዱባይ ባለሀብቶች በሊዝ እንደተሸጠ የተነገራቸው ነዋሪዎች በአንድ ሳምንት እንዲነሱ መታዘዛቸውን ተናገሩ
(መሠረት ሚድያ)- ከተማዋን 'በምስራቅ አፍሪካ የቱሪዝም ማዕከል' ለማድረግ እየተሰራ ካለው ስራ ጋር በተያያዘ በርካታ የከተማው ቦታ ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባለሀብቶች ሊሰጥ እንደሆነ በመጀመርያ የተሰማው የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ነበር።
"እስከ 80 ፐርሰንት የሚደርስ የከተማው ቦታ ለኤምሬትስ ኢንቨስተሮች ሊሰጥ ነው የሚል መረጃ አለን፣ በዛ ላይ ትንሽ የቤት እድሳት ለማድረግ እንኳን ስንሞክር በከተማው አስተዳደር 'እዚህ ብዙ ስለማትቆዩ ማደስ አትችሉም' እየተባልን ነው" ብለው ነዋሪዎቹ በወቅቱ ለመሠረት ሚድያ ተናግረው ነበር።
ይህን በተመለከተ መሠረት ሚድያ የቢሾፍቱ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሀላፊ የሆኑትን አቶ ገብሬ ዳቢን አነጋግሮ የነበረ ሲሆም "እኔ የከተማው ኢንቨስትመንት ቦርድ ውስጥ አባል ነኝ፣ ግን በዚህ ደረጃ እንዲህ አይነት ኢንቨስትመንት ይመጣል የሚል መረጃ የለኝም" ብለው ተናግረው ነበር።
ሀላፊው የቤት እድሳት ክልከላውም ምናልባት ከተማው ውስጥ ወጥነት ያለው የቤት አሰራር እንዲሆን ከሚሰራው ስራ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ገልፀው ነበር።
ነዋሪዎቹ ግን ትነሳላችሁ የሚለው ቃል ከመንግስት እስካሁን ባይወጣም ወደፊት ግን ሊነሱ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልፀው ነበር።
አሁን በደረሰን መረጃ መሰረት ደግሞ ከ15 እና 20 አመት በላይ በቢሾፍቱ የኖሩ ነዋሪዎች "ቦታው ለዱባይ ባለሀብት በሊዝ ተሽጧል፣ ስለዚህ በአንድ ሳምንት ውስጥ ልቀቁ ተብለናል" በማለት ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎ ለገበሬ ባለይዞታዎች ከሳ መክፈል እንደተጀመረ የታወቀ ሲሆን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ህዝቡን ሰብስበው የአየር ካርታ ላላቸው 105 ካሬ መሬት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
በአንድ ሳምንት ውስጥ ልቀቁ የተባሉት እነዚህ ነዋሪዎች የገበሬ ቤት የሆነውን አረንጓዴ ቀለም፣ የሌላውን ህዝብ ደግሞ ቀይ ቀለም እየቀቡ ለይተው እንደጨረሱ ታውቋል።
የኦሮሚያ ክልልም ሆነ የፌደራሉ መንግስት እስካሁን በግልፅ ምን ያህል መሬት ለኤምሬትስ ባለሀብቶች እንደሸጡ ይፋ አላደረጉም።
(#ከዜናዎቻችን በሳምንቱ በቪድዮ ዩትዩብ ላይ ያቀረብናቸውን የተመረጡ መረጃዎች ቆየት ብለን በድጋሜ በፅሁፍ የምናቀርብበት አምድ ነው)
መረጃን ከመሠረት!
@MeseretMedia