🔈#የመምህራንድምጽ
" መግለጫ እና ወሬ ሳይሆን የተግባር መፍትሄ እንፈልጋለን ፤ እኛ መኖር ከብዶናል !! " - ቃላቸውን የሰጡ መምህራን
ከሰሞኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር 37ኛ መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባውን አድርጎ ነበር።
የማህበሩ ስብሰባ ላይ ፦
➡ መምህራንን እየተፈታተነ ያለው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣
➡ ረጅም ጊዜ አገልግሎት ያላቸው መምህራን የደረጃ እድገት ወይም የእርከን ጭማሪ አለመኖር፣
➡ በአንዳንድ ክልሎች የመምህራን ደሞዝ በጊዜ አለመከፈል ብሎም እየተቆራረጠ በፐርሰንት መከፈል፣
➡ ያለመምህራን ዕውቅናና ፈቃድ በተለያዩ ምክንያቶች የደሞዝ መቆረጥ፤ ይሄንን የሚቃወሙትን ደግሞ ማዋከብና ማንገላታት፣
➡ ቀደም ብሎ የተጀመረው የመምህራን የመኖሪያ ቤት እና የመሥሪያ ቦታ በሚፈለገው ፍጥነት እየተከናወነ ያለመሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ደግሞ ጭራሽ አለመጀመሩ፣
➡ በትርፍ ሰዓት ክፍያ ላይ ተደራራቢ ግብር መቆረጡ፣
➡ የመጽሐፍትና ሌሎች ግብአቶች እጥረት፣ የክረምት መምህራን ስልጠናና ያጋጠሙ ችግሮች ...ወዘተ በተሳታፊዎች በአስተያየት እና በጥያቄ መልክ ተነስተው ነበር።
በቀረቡት ጥያቄዎች ዙሪያ የትምህርት ሚንስቴር አመራሮች ተገኝተው ምላሽ እንደሰጡ በማህበሩ ተገልጿል።
ስብሰባው የአቋም መግለጫ በማውጣት ነው የተጠናቀው።
ይህንን የማህበሩን ስብሰባ መደረግ የሰሙና ማህበሩም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሰጠውን ቃል ያነበቡ በርካታ መምህራን መልዕክታቸውን ልከዋል።
ቃላቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጡ መምህራን ፥ " እኛ መግለጫና የማይጨበጥ ወሬና መስማት ሰልችቶናል የተግባር መፍትሄ እንፈልጋለን " ብለዋል።
" እኛ መኖር ከብዶናል !! ስብሰባ ከዛ መግለጫ ምን ይሰራልናል ? ምን ያህል ዋጋ እየከፈልን እንዳለን እኛ ነን የምናውቀው ልጅ ማሳደግ ፣ ቤተሰብ ማስተዳደር እጅጉን ፈተና ከሆነብን ሰንብቷል " ሲሉ ገልጸዋል።
" ይህ ማህበር በየጊዜው መግለጫ ነው የሚሰጠን ምንድነው ጠብ የሚል ስራ የተሰራው ? ይሄን ይመልሱልን " ሲሉ ጠይቀዋል።
" መግለጫና ወሬ ምንድነው የሚሰራልን ? ችግራችንን ደጋግሞ መናገር መፍትሄ ከሌለው ጥቁሙ ምን ላይ ነው ? የማይታወቅ ችግር ያለ ይመስል ሁሌ አንድ አይነት ነገር መናገር ያሰለቻል ደክሞናል " ብለዋል።
" መብታቸውን የእንጀራ ጥያቄያቸውን የላባቸውን ደመወዝ ስለጠየቁ ብቻ መምህራን መታሰራቸውን ሰምተናል ይህ ሲሆን እንኳን መፍትሄ እየተሰጠ አይደለም " ሲሉ አማረዋል።
ቃላቸውን የሰጡ መምህራን ፥" በሚዲያው መግለጫ ሳይሆን ተግባራዊ መሬት ላይ የሚወርድ መፍትሄ ብቻ ነው የምንፈልገው " ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
" ሰራተኛው ኑሮው ቢከድበውና የሚጮኽበት እዲሁም ችግሩን ሰምቶ መፍትሄ የሚሰጠው ቢያጣ ነው ወደሚዲያ የሚቀርበው ስለዚህ እባካችሁ ድምጻችንን ይሰማና መፍትሄ ስጡን " ሲሉ አክለዋል
[ዘገባው የቲክቫህ ኢትዮጵያ ነው]
ለጥቆማ 👉
@atc_newsbot➡️
https://t.me/atc_news