ኢትዮቴሌኮም እንደ አማዞን፣ አሊባባ እና ኢ-ቤይ አይነት የዲጂታል ገበያን ወደ ኢኮኖሚው አስገባ።
ይህ የዲጂታል ገበያ ወይም ማርኬት ፕሌስ “ዘመን ገበያ“ ይሰኛል።
በብሔራዊ ደረጃ የዚህ የዲጂታል ገበያ ባለቤት ኢትዮ ቴሌኮም ነው።
ኩባንያው ዘመን ገበያ የተሰኘ ፤
ሀገር አቀፍ የዲጂታል የገበያ ሜዳ ዛሬ በይፋ አስጀምሯል።
ኢትዮ ቴሌኮም ለኢኮኖሚ እድገት ያግዛሉ ያላቸውን ምዕራፎች በመለየት በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ በማድረግ፤ ውጤታማና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በቴክኖሎጂ በማስታጠቅ ገበያውን በብርቱ እያገዝኩ ነው ብሏል።
ኢትዮ ቴሌኮም የዘረጋው የዲጂታል መሰረተ ልማቶች እና ፈጣን ኢንተርኔት ግንኙነት፣ የክላውድ፣ ሞጁላር ዳታ ሴንተር እና የቴሌብር ዲጂታል ክፍያ ሥርዓት መስፋፋት ይህን ዲጂታል ገበያ ወደ ፊት ይገፈትረዋል ተብሏል።
ኢትዮ ቴሌኮም በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ የኤሌክትሮኒክ ንግድን ማእዘን፣ ብሔራዊ የዲጂታል ግብይት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሜዳ ፈጥሬያለሁ ብሏል።
ኩባንያው ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ የዲጂታል ግብይት ሥርዓት እውን እንዲሆን እና የሰፊውን ገበያ ጉልበት እጠቀማለሁ ብሏል።
ይህን በማድረግም የዲጂታል ኢኮኖሚ ውጤቶችን በመዘርዘር ፤ በመቁጠር አስተማማኝ በተባለ ደህንነቱ በተጠበቀ እና ማእከላዊ ዲጂታል በተባለለት ገበያ ''ዘመን የዲጅታል ገበያን “ ወደ ኢኮኖሚው ወርውሮ ተግባራዊ ለማድረግ በብርቱ ሲደክም እንደነበር የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል።
በመሆኑም ኩባንያው የዲጅታል ግብይትን አንድ ወደፊት የሚያዘምነውን ሥርዓት ወደ ኢኮኖሚው ዛሬ በይፋ አስገብቷል ተብሏል።
ይህ ዘመን የተሰኘው የዲጂታል ገበያ ሜዳ፣ምርት እና አገልግሎት አቅራቢዎች ከሸማቾች ይገናኙበታል መባሉን ሰምተናል።
በተለይም በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ድርጅቶች ከሸማቾች ጋር በቀላሉ ለማገናኘት እድል ይሆናል ተብሏል።
አዳዲስ የገበያ እድል በመፍጠርም የዲጂታል ኢኮኖሚን ለማፍታታት እንደሚያግዝ ሰምተናል።
ዘመን ገበያ ንግድን በማቀላጠፍና ከአነስተኛ ጀምሮ እስከ ትላልቅ የንግድ ድርጅቶች በማገናኘት፣ የገበያ ተደራሽነትን በማስፋት፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲጨምር፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርና አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል።
በሎጅስቲክስ፣ በዲጂታል አገልግሎቶች፣ በዲጂታል ገበያ፣ በችርቻሮና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የሀገር ውስጥ የሥራ ዕድሎችን በማነቃቃት ዘላቂ የኑሮ መተዳደሪያንና የማኅበረሰብ እድገትን ይደግፋል ተብሎለታል።
ዘመን የዲጅታል ገበያ የከተማና የገጠር ማህበረሰቦችን በማገናኘት በመላው ኢትዮዽያ በዲጂታል ንግድ ውስጥ እኩል ተሳትፎ እንዲኖር ያስችላል መባሉን ከዛሬው ጉባኤ ሰምተናል።
ይህ ጅምር፤ የድንበር ተሻጋሪ የንግድ ዕድሎችን በማመቻቸት ፤ ወደፊት የአገር ውስጥ አምራቾችና ነጋዴዎች ዓለም አቀፍ ገበያዎችን እንዲያገኙ በማገዝ ፤ ለውጪ ንግድ ዝግጁነትን ከፍ በማድረግ ለኢኮኖሚው በብርቱ ያግዛል ተብሏል።
@seledadotio @seledadotio