አንድ ለማድረግ የተለጎሙ በታኝ ምላሶች!
የአንዳንድ ወንድሞች አካሄድ የበዛ ግብታዊነት የሚስተዋልበትና ለትግላችን የማይጠቅም ነው። በቂ መረጃ ሳይኖራችሁ፣ የትግል ሜዳ ላይ ያሉ ጓዶችን ለማጠልሸት መኳተን ትርፉ እራስን ትዝብት ላይ መጣል ብቻ ነው።
አንድ ለማድረግ የሚሰራ እንጅ ትግላችንን ለመበተንማ ከብልፅግና ሰዎች እስከኛዎቹ ውሽልሽል እንክርዳዶች መች አጣን። መገፋፋት ትግላችን ሲጎዳ እንጅ ሲያቀና አላየንም። ለትግል ጓዶችና መሪዎች ከለላ መሆን ሲገባ ነጠላ እየፈተሉ ለሃሜት መቀመጥን የእኛ ከምንላቸው ሰዎች ስናይ እጅጉን ያማል።
እያወራን ያለነው በኢንጅነር ማንችሎት ዙሪያ አንዳንድ ወንድሞች የጻፉትን ስላየን ነው። እንኳን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአማራ ፋኖ በጎጃም ወሳኝ ኃላፊነትን ወስዶ እየሰራ የነበርን ወንድማችንን ይቅርና በግላጭ በሌላ ጎራ ተሰልፈው የነበሩትን ወንድሞቻችን ወግደረስ ጤናውንና ዶ/ር እንዳላማውን ከመግፋት ማቅረቡ ብሎም እንደታቀደው ተገቢ የአመራር ኃላፊነት መስጠቱ የብልህ አካሄድ ነው ብለን እናምናለን።
ማንቼም እንደማናችንም ሊሳሳት የሚችል ሰው ነው፤ ቢሳሳት እንኳን የሚመክሩና አስተዳደራዊ እርምጃ የሚወስዱበት ወንድሞችና አለቆች አሉት። ነገር ግን በይሆናል ብቻ ወይም በግል ጥላቻ ወይም ግልፅ ባልሆነ ምክንያት፣ ወንድማችንን የሚዲያ አፍ ማሟሻ ለማድረግ መሞከር ትንሽነትን መሸቀጥ ነው።
ኢ/ር ፋኖ ማንችሎት እሱባለው በሰሜኑ ጦርነት ጋሸና ድረስ በመዝለቅ የአካል መስእዋትነት ከመክፈል ጀምሮ ብዙ ተጋድሎ ያደረገና የአማራ ፋኖ በጎጃምን ከመመስረት ጀምሮ ከወንድሞቹ ጋ ትልቅ መስእዋትነት የከፈለና ለባህር ዳር ትግል መነቃቃት ትልቅ ድርሻ ያለው እንዲሁም ከ5 በላይ ቤተሰቦቹን ለዚህ ትግል የገበረ የነገ ትልቅ መሪ እና አታጋይ ይሆናል ብለን የምንጠብቀው ጀግናችን መሆኑን ሊሰመርበት ይገባል።
ይህንምም መስዕዋትነት ከፍሎልን፣ መስመር ከሳተ ግን ለመገሰፅ ከፊት ከሚገኙ ውስጥ እሆናለሁ። ነገር ግን ለአንድነት ቀናዒ የሆነውን፣ ስልጣን የማያጓጓውንና አሁንም ከቀድሞ ወንድሞቹ ጋር በትግል ሜዳ ላይ ያለውን መሪያችንን ባልዋለበት ማጠልሸቱ ያሳፍራል፤ ጥቂት ሞቅታሞች አብረው ቢያጨበጭቡም፣ ብዙሃኑን ግን ስቆበትና ተሸማቆ እንዲያልፍ የሚያደርግ ነው።
እናም አንዳንድ ወንድሞቻችን መጀመሪያ በቂና እውነተኛ መረጃ ኖሯችሁ ጻፉ። ቀጥሎ ደግሞ እኛ አልጋ ላይ ሆነን በስማ በለው የጻፍናት ቃል፣ እውነተኛ ታጋዮችን የምትሰብር ልትሆን እንደምትችል መገንዘብ ያስፈልጋል። ሚዲያው ላይ የመኖራችን ምክንያት የወገንን አንድነት ለማጠናከርና ለመጠገን እንጅ አንድነት ለመሸርሸር ወይም ስንጥቅ ለመፍጠር መሆን የለበትም።
እናስተውል!
ፎቶው [ ኢ/ር ፋኖ ማንችሎት በሰሜኑ ጦርነት ጋሸና ላይ ቆስሎ ህክምና ሲደረግለት የተወሰደ ነው]
ታጋይ አምሓራ
ነፃነት በትግል እንጂ በልመና አይገኝም!
11/4/2017 ዓ.ም