" በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ዳግም የመሬት ናዳ እና ጎርፍ ተከስቶ በሰዉና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል " - የአከባቢው ነዋሪዎች የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከሰሞኑ በአከባቢያቸዉ ነፋስ ቀላቅሎ እየጣለ ያለዉ ከባድ ዝናብ የመሬት ናዳ እና ጎርፍ በማስከተሉ በሰዉ ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።
ከሚያዚያ 9/2017 ዓ/ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በአከባቢዉ እየጣለ ያለዉ ዝናብ በተለይም ፦
- ጎሬ ኦዳ፣
- ጃዉላ ዉጋ ማሽታሌ፣
- ኤላ፣
- አማሮ ሻጌ፣
- ቡልቂ በተባሉ አከባቢዎች ባስከተለዉ ከባድ ነፋስ፣ ከፍተኛ የዉሃ ሙላት እና የመሬት መንሸራተት የ3 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ከ4 በላይ ቤቶች በመሬት ናዳዉ መስመጣቸዉንና፤ የእርሻ ማሳዎች እንዲሁም የቤት እንስሳት ጭምር በመሬት መንሸራተቱ መወሰዳቸዉን ነዋሪዎቹ አስረድተዋል።
በወረዳዉ ሰሞኑን በተከሰተዉ ዳግመኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በጎዶ አንደኛ ትምህርት ቤት እና በአንድ የሃይማኖት ተቋም ግቢ ተጠልለው እንደሚገኙ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ የዝናብ ሁኔታዉ ቀጣይነት ያለዉ ስለሚመስል አሁንም ከፍተኛ ስጋት ዉስጥ መሆናቸዉን ተናግረዋል።
" በወረዳዉ የዛሬ ዓመት በተከሰተዉ የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መሉ በሙሉ መልሶ የማደራጀቱ ስራ ባልተጠናቀቀበት ይህ መከሰቱ ስጋታችንን ከፍ ያደርገዋልም " ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገራቸዉ የገዜ ጎፋ ወረዳ አደጋ ስጋት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ማስረሻ ማናዬ በበኩላቸው በአካባቢው እየጣለ ባለዉ ከባድ ዝናብ በወረዳዉ አራት ቀበሌያት በሰዉ፣ በንብረትና በቤት እንስሳት ላይ ጉዳት ማድረሱን አስታዉቀዋል።
ተጨማሪ አደጋዎች እንዳይከሰቱ የወረዳዉ መንግስት በልዩ ተኩረት እየሰራ ነዉ ያሉት አቶ ማስረሻ ጉዳት የደረሰባቸውን ነዋሪዎች የማቋቋም ስራም እንደሚሰራ ገልፀዋል።
ባሳለፍነዉ ዓመት በአከባቢዉ የተከሰተዉ መሰል የመሬት መንሸራተትና ናዳ ምክንያት በርካታ ሰዎች መሞታቸዉ የሚታወስ ሲሆን አሁንም ድረስ በአከባቢው በስጋት የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ሙሉ በሙሉ መልሶ የማቋቋም ስራዉ አለመጠናቀቁን በቅርቡ የአካባቢው ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸው ነበር።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሀዋሳ
#TikvahEthiopiaFamilyHW
@tikvahethiopia