💉 ከሰሞኑ የተስተዋለው ለሰመመን ህክምና የሚውሉ መድኃኒቶች እጥረት የህክምና ባለሞያዎች ከፍተኛ ደረጃ በሚባል መልኩ ለሰመመን ህክምና የሚውሉ መድኃኒቶች በመጥፋታቸው ታካሚሞች ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ ይገኛሉ ሲሉ እየገለጹ ይገኛሉ።
ዶ/ር መዝገብ ገደፌ (ዩሮሎጂስት) ለሀኪም ፔጅ በጻፉት ጹሑፍ ''ላለፉት ጥቂት ሳምንታት ሁሉም በሚባል ደረጃ የመንግስት ሆሰፒታሎች በማደንዘዣ መድሃኒቶች እጥረት ምክንያት መደበኛ የኦፕሬሽን አገልግሎት አቁመዋል፡፡'' ሲሉ ችግሩን ያስረዳሉ።
አብዛኛው ሆስፒታሎች የኦፕሬሽን አገልግሎት አቁመው ዜጎች እየተጉላሉ ጤናቸውም አደጋ ላይ እየወደቀ ነው፤ ሰለዚህ የማደንዘዣ መድሃኒቶች የምናገኝበት መንገድ ባስቸኳይ ይፈለግ ሲሉም ጠይቀዋል።
በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ ጤና ተቋማት የግብአቶችን ምጠና በማድረግ በግዥ የሚያቀርበው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በበኩሉ ከማቀርባቸው ከአስራ ሁለት (12) አይነት በላይ ለሰመመን ህክምና ከሚውሉት ግብአቶች ውስጥ ከሰክሳሚቶኒየም (Suxamethonium) በስተቀር በሌሎቹ ላይ እጥረት የለም ሲል ገልጿል።
የአገልግሎቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ንጉሴ መድሀኒቱን ከሚመረትበት ሀገር በዘላቂነት በማስመጣት እንዲሁም አሁን የተፈጠረውን የአቅርቦት መቆራረጥ ችግር በአስቸኳይ ለመቅረፍ በአየር ትራንስፖርት ከጎረቤት ሀገር ኬኒያ ለማስገባት እየተሰራ ሲሆን በዚህ ሳምንት ውስጥ እጥረቱ ለተከሰተባቸው ጤና ተቋማት እንዲሰራጭ እናደርጋለን ብለዋል።
ቀሪ 11ዱ ለሰመመን ህክምና የሚውሉ ግብአቶች በበቂ መጠን በክምችት ያሉ ሲሆን እነዚህን መድኃኒቶችን በመላው ሀገሪቱ ባሉ 18 ቅርንጫፎቻችን ላይ የሚገኙ መሆናቸውን እንዲሁም በየ ሁለት ሳምንቱ የክምችት ትንተና ሪፖርት በሚደረገዉ የFILL-IFS reporting system በማቅረብ ማግኘት እንደሚቻል ኃላፊው ገልፀዋል።
ከጤና ባለሞያዎች በተለይ ከመድኃኒት አቅርቦትና ግብዓት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች ተገቢውን ትኩረት አግኝተው አፋጣኝ ምላሽ ሲሰጥባቸው አይስተዋልም፥ ይህም ባለሞያውን እያማረረ ሲሆን በዚህ ምክንያትም ዜጎች ህይወታቸው እያለፈ ይገኛል።
@tikvahethmagazine