Walia bookstore gallery


Channel's geo and language: Ethiopia, Amharic
Category: Edutainment


Books

Related channels  |  Similar channels

Channel's geo and language
Ethiopia, Amharic
Category
Edutainment
Statistics
Posts filter






ከሀገሪቱ መዲና የተነሳው አሮጌ ፎርድ መኪና፤ ባለደማቅ ቀለሟን ግን አለም አደብዝዟት ፍዝ ያደረጋትን ቤርሳቤህን፣ በህይወት ላይ አቂሞ በመኖር ላይ ያኮረፈውን ምንተስኖት፣ ከሚታየው ይልቅ የመንፈሱ አለም ተማራኪ የሆኑት ሁለት ሆነው ግን በነገረ ስራቸው እንደ አንድ በእና ተዳርተው የሚጠሩ መሪጌታ ሐብቴ እና ኢዩኤልን ጨምሮ ከተለያየ የህይወት ልምድ፣ አስተዳደግ፣ የህይወት ፍልስፍናና አስተሳሰብ የተሰበሰቡትን ዘጠኝ ሰዎችን አሳፍሯል። መራሄ ሙዚቃው ሳያሻቸው ሙዚቃ መሳሪያዎቻቸውን እንደመቃኘት ፣ መፈተሽ የጀመሩት ሙዚቀኞች ገና በጉዞ ላይ ወደመግባባት ይደርሳሉ። ከመቃኘትና ከመግባባት አልፈው ስልቱን አስይዘውን ጆሮዋችንን ይይዛሉ። መዳረሻቸውን ደብረሰምራ ለማድረግ ያሰቡት እቅዳቸው ተጨናግፎባቸው መራሄ ሙዚቃቸውን "አልይ" ላይ አገኙት።
ወትሮም የጃዝ ሙዚቃ ስልተምት የመዘግየት አይነት አሞዛዘቁ ስልቱን አወሳስቦትም ቢሆን የሙዚቀኞቹም የሕይወት ልምድ የየቅልነቱ የመራሄ ሙዚቃውን ድካም ያከፋዋል።
ተሰናስሎ የመጣው ታሪካቸው አማሃይ ላይ ሲደርስ መተርተር ይጀምራል። እራሳቸውን ችለው በመድረኩ ላይ መከየን ይጀምራሉ። መድረኩም አንዱን ሲጥል ሌላውን ያነሳል። ክዋኔው አስተሳስሯቸው እጅ ለእጅም ይያያዛሉ።
በአስራ አራተኛው ምራፍ የመድረኩ ላይ ክዋኔ ተጠናቆ ሙዚቀኞቹ ወደየኑሮ መስመራቸው መጓዝ ይጀምራሉ። የመራሄ ሙዚቃው ፍትሃዊ መሪነትም ብዝሃ ከዋኞችን ክዋኔው ሳይደበዝዝ እዲመራ አስችሎታል።
ሳጠቃልልም ጃዛዊው የትረካ ስልት በዚህ መጽሐፍ ላይ ለግልጋሎት መዋሉ አንድም የሐሳብ ሰፊነት፣ የመጽሐፉ ይዘትም ይፈቅድለታል። የተራኪዮቹ በሀሳብም ፣ በህይወት ልምድም ብዝሃነት እምሮቫይዜሽን የአተራረክ ስልት እንዲጠቀም አስገድዶታል። በልቦለዱ ላይ የመሪ ገፀባህርይ አለመኖር ፣ የክዋኔውን አማሃይ ለሁሉም በእኩል ደረጃ ከፍሎ ሐሳባቸውን እኩል ለማስተጋባት አስችሎታል።


የ "ሲጥል"ን ልቦለድ አጻጻፍ ከጃዝ የሙዚቃ ስልት አንጻ...
በትሬዛ ዮሴፍ
የዚህ ጽሑፍ አብይ አላማ የደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ደርሰት የሆነውን "ሲጥል" ረጅም ልቦለድ ከጃዝ ሙዚቃ የትረካ ስልት አንጻር መፈተሽ ነው። ጃዝ ሙዚቃ የመድረክ ላይ በቅጽበት የመፍጠርና፣ ታሪክን በሙዚቃ የመናገር ስርዓት (Improvisation) ወደሥነጽሐፉ አለም ደራሲው እንዳለጌታ ከበደ በ"ሲጥል" ረጅም ልቦለድ አማካኝነት አምጥቶታልና የሙዚቃውን ጽንሰሐሳብ ከሥነጽሑፉ ጋር እያዋዛን ዳሰሳ እናደርጋለን።
"After you initiate the solo, one phrase determines what the next is going to be. From the first note that you hear, you are responding to what you've just played: you just said this on your instrument, and now that's a constant."
— Max Roach
ይህ የማክስ ሮች አባባል ለመዝለቂያችን ብንጠቀም አንድም ውብ ነው፤ደግሞ ገላጭም ነው። "ሲጥል" ልቦለድ በጃዛዊው የእምፕሮቫይዜሽን ስልት በመተረኩም ለመፈተሻነትም ይሆነናል። እናም የደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ስራ የሆነውን "ሲጥል" ረጅም ልቦለድ በጃዝ ሙዚቃ መንፈስ ሆነን እያንዳንዳችን ደራሲው በሰጠን የክየና ነጻነት በመድረኩ ላይ መከየንም እንችላለን። የጃዝ ሙዚቃ ትልቁ መገለጫም የመፍጠር ነጻነት ነውና፣ ፈጠራችን በእምፕሮቫይዜሽናችን ነው የሚገለጠው።
እምፕሮቫይዜሽን በጃዝ ሙዚቃ ክየና ወቅት የሙዚቃው ቀማሪ በሚሰጣቸው ነጻነት በተናጠል በመድረኩ ላይ የመፍጠር ችሎታቸውን ተጠቅመው በቅፅበቱ የሚከይኑበት ነው። በሙዚቃው ጅማሮ ሁሉም ተሳታፊ የሚጫወት ሲሆን ለየአንዳንዱ ሙዚቀኛ ደግሞ የመፍጠር ነጻነት የሚሰጥበት ጊዜ አለ። በዚህ ጊዜ ሙዚቀኞች የሙዚቃ ቀማሪና መሪው በሚሰጣቸው መንደርደሪያ ሀሳብ ተነስተው የራሳቸውን ሀሳብ የሚያሳድጉበት ነው። በሙዚቃው ክየና ጊዜ እንደ ሙዚቃው ቅንብር የሙዚቃ መሳሪያዎቹ ቅደም ተከተሉን ደልድሎ ለያንዳዱ በየአስፈላጊው ቦታ እድል የሚሰጠውም እንዲሁ የሙዚቃ ቀማሪው ነው። በተሰጠው እድል እምፕሮቫይዘሩ አቅሙን ይፈትሽበታል። ሀሳቡን ያጋባል።
በጃዝ ሙዚቃ አካሄድ ስልተምት (Rhythm) ከሌሎች የሙዚቃ ዘውጎች የመወሳሰብ ባህሪይም አለው። ለምሳሌ፥ ሌሎች የሙዚቃ ዘውጎች በአብዛኛውን እንደ ልብ ምታችን፣ እንደ አረማመዳችን ከተፈጥሮ ላይ የተቀዳ ቀጥተኛ ስልት ሲጠቀሙ ጃዝ ሙዚቃ ግን እኝህን ቀጥተኛ ስልተምቶችን ቲንሽ ጎተት በማድረግ፣ በማዘግየት(ከፍጥረትም ስልት ዘግይቶ) የራሱን አካሄድ ይፈጥራል። ያም ከሌሎቹ የሙዚቃ ስልቶች ውስብስብ ስልተምት (Rhythm) እንዲኖረው አስችሎታል።
ይህ በተፈጥሮው ውስብስብ የሆነው የስልቱ አካሄድ ወደ ትረካ ለማምጣት የደራሲውን ችሎታ ይጠይቃል። እኛም አንባቢያን በደራሲው መሪነት ክየናውን ተቀላቅለን የበትረሙዚቃውን አካሄድ በትኩረታችን ስር አውለን እየከየንንም ሙያው በሚሰጠን ገደብ የምንዳስስም ይሆናል። መራሄ ሙዚቃው እንዳለጌታ በትረሙዚቃውን በወዘወዘልን መጠን ተከትለነው እንሞዝቃለን።
በጃዝ ሙዚቃ አተራረክ (story telling) ስልት አንድ ሙዚቀኛ እድሉ ሲሰጠው የሙዚቃው መሪ የፈቀደለትን መነሻ ሀሳብ ሳይለቅ በተሰጠው ገደብ ውስጥ የራሱን የመፍጠር ነጻነት ተጠቅሞ ሀሳቡን መተረክ አለበት። የታሪክ ነገራው ምን ያህል ነጻነትና የጊዜ ርዝመት እንዳለውም መረዳት ይጠበቅበታል። ስለዚህ አጀማመሩ ይህን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆን ይጠበቅበታል።
You can leave some spaces in the music. You're not going to start off a solo double-timing. You start off just playing very simply and, as much as possible, with lyrical ideas. And as the intensity builds, if it does, your ideas can become a little more complicated. They can become longer.
Kenny Barron
ይህን የኬኒ ባሮንን ሀሳብ የአተራረክ አካሄዱን ለመመልከት ያበጃል። መንደርደሪያችን ግባችንን ይወስነዋል እንደማለት። "ሀ" ሲል ታሪኩን የጀመረው በ "ሀ" ፊደል ቤቶች ስለምን እንደሚያወጋ መንደርደሪያ ያስይዘናል። ሙዚቃ ሊከየን ዘንደ አማሃይ ሊኖር ይገባል። ይህን አማሃይ (መድረክ) ለማበጀት በየራሳቸው ምክንያት በአንድ መኪና የተገናኙ ተሳፋሪዎች ወደ አማሃያቸው አንደረደራቸው። ወደ ክዋኔው መድረክ። ደግሞም ለመድረኩ ታስበው ብቻ ሳይሆን ኑረቱ (ይዘቱም) የመድረኩን አስፈላጊነት ይነግረናል። ጃዝ ሙዚቃ ላይ ሁሉም ታሪክ ነጋሪዮች የየራሳቸውን ፈጠራ እንዲያሳዩ በመድረኩ ላይ እኩል እድልና ጊዜ ይሰጣቸዋል። በዚህ መጽሐፍ ላይም ሁሉም ገጸባሕሪያት በመድረኩ ላይ የየራሳቸው ታሪክ ኖሯቸው በአንድነት ስለሚከይኑ የጃዝ አተራረክ አስፈላጊ ነበር። ለምን ጃዛዊው መድረክ ለአተራረክ ተመረጠ? የሚለውን ጥያቄም ይመልስልናል። የብዙ ከያኒዎችን ሀሳብ በአንድነትና በተናጠል ለማጋባት የጃዛዊው የትረካ ስልት በጣም ምቹም ነው።
ከክዋኔው አማሃይ በፊት ገጸባህሪያቱ ስለህይወት ልምዳቸው፣ አስተዳደጋቸው፣ አስተሳሰባቸው ሁሉ መንደርደሪያ ያስይዙናል። በሚጋሩት መድረክ ምን ሊከይኑልን እንደሚችሉ እንገምታለን። ትረካውን በአንድነትም በተናጠልም እየወሰዱና እየመለሱን ቅኝቱን ይከስቱልናል። ስለዚህ እኝህ ከያኒያን መድረክ ላይ ምን ሊከይኑልን እንደሆነ መገመትና መንደፍ እንችላለን ማለት ነው። ይህም በጃዛዊው "እምሮቫይዜሽን" የመፍጠር ነጻነቱ በመድረኩ ላይ ድንገት ሲሰጠን የህይወት ልምዳችንን ነው ለታዳሚው የምንተርከውና ይህን ለማሳየት ነው የስብስቡን ልምድ ቀድሞ ያጋራን። ይህም የጃዝ "እምፕሮቫይዜሽን" የክየና ጽንሰ ሀሳብን በደምብ ያሟላ ነው ማለት ይቻላል።
"እምሮቫይዘሮቹ" ስለራሳቸው በተወሰነ ስላወጉን የታሪኩ ዳራ ምን ላይ ትኩረቱን ሊያደርግ እንደሚችል መገመት ችለናል። ታሪኩ የተሰናሰለ መሆን፣ ሰበዞች በአንድ መሰፋት ሰፌድን እንደሚፈጥረው፤ ገጸባህሪያቱ የየራሳቸውን ታሪክ ይዘው መተው እንደሰበዞቹ ሰፌድ ይሰሩና አንድ መድረክ ይኖራቸዋል። ይህ የታሪክ ነገራ አካሄድ እጅጉን የጃዛዊው እምፕሮቫይዜሽን የተቀነበበ መሆኑን ያሳየናል።
ከፍጥረት ላይ የመዘግየትን የመሰለ ፣ ውስብስብ የሆነውን የጃዝ ሙዚቃ ስልተምት (Rhythm) ተጠቅሞ በ"አልይ" መድረክ ላይ በትረሙዚቃውን አቅንቶ እንደያዘ ከመሃል ሀገር የተነሱትን ተጓዦች በመጠባበቅ ላይ ይገኛል መራሄ ሙዚቃው።




ኤመረተስ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ‹የአመቱ በጎ ሰው› እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ‹የህይወት ዘመን አገልግሎት ተሸላሚ› የሆኑ ዕውቅ ምሁር ናቸው፡፡ ከምርምር፣ የማስተማር ሥራዎቻቸውና ተቋማት ከመመስረት በተጨማሪ በጸሐፊነት የሚታወቁ ጉምቱ ሙያተኛና የሥነጽሑፍ አፍቃሪ ናቸው፡፡ ‹ከጉሬዛም ማርያም እስከአዲስ አበባ፡ የህይወት ጉዙ እና ትዝታዬ›፣ ‹የስንኝ ማሰሮ›፣ ‹ሕያው ፈለግ› በተባሉና በሌሎችም መጽሐፎቻቸውም ይታወቃሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ ሳይንስን ለማሃዘብ የተለያዩ መጣጥፎችን በልዩ ልዩ ጋዜጦችን መጽሔቶች በመጻፍም በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡


"ሲጥል" የእንዳለጌታ ከበደን ልብወለድ በጨረፍታ
ሽብሩ ተድላ (ኤመረተስ ፕሮፌሰር)
በእንዳለጌታ ከበደ (PhD.) የተደረሰው "ሲጥል" ተብሎ የተሰየመው ልብወለድ፣ ርእሱን ያገኘው፣ በመጽሐፉ ውስጥ የተወሱ ገጸ-ባህርያት፣ "ደብረ ሠምራ" ለመሄድ አስበው "ዐሊይ" ወደ ምትባል ትንሽ የገጠር ቀበሌ ስለተጓዙ ይመስለኛል፣ ያንን ዓይነት ስያሜ (ቀን ሲጥል ዓይነት) የተሰጠው፡፡ ደራሲው አሥራ ሁለት ገደማ በሆኑ ቀጥተኛ ገጸ-ባህርያት፣ በተጓዳኝ የጎላ ሚና ያሏቸው ስድስት ገደማ እና በጨረፍታ የሚወሱ አሥር ገደማ የሚሆኑ ገጸ-ባህርያት፣ አጠቃላይ የማኅበረሰቡን በጎ እንዲሁም ኋላ ቀር ተብለው የሚፈረጁ ጎኖችን ሁሉ ያመላክታል፡፡
በ"ሲጥል" ልቦለድ ያልተዳሰሰ የሰው ልጅ ባህርይ ያለ አይመስልም፡፡ ባህርያቱ ሁሉ የሚገለጡት ለሃያ አንድ ቀናት ሳይፈልጉ አብረው በሰነበቱበት ሁኔታ ነው፡፡ ማታ ማታም፣ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ባለመኖሩ፣ እማምሻ ሻይ ቤታቸው ተሰባስበው ዕጣ እየተጣጣሉ፣ በደረሳቸው ዕጣ አማካይነት በትረካ መሳተፋቸው፣ እርስ በርስ የመተዋወቅ አድማሶቻቸውን አስፍቶላቸዋል፡፡
በቆይታቸው ከተሜዎችን የገጠር አባባል ዘይቤዎች ሳያስገርሟቸው አልቀሩም፣ የገበሬ ማኅበር ሊቀመንበሩ "ቢከፋም ቢለማም አታምሹ"፣ "ቢከፋም ቢለማም ከፀጉረ-ልውጦች ጋር አትገናኙ...."፣ "ቢከፋም ቢለማም…."፡፡ የሴቶች ፀጉር አሠራርም ከእድሜ ጋር የተቆራኘ መሆኑን አንዷ ለገጠር እንግዳ ስታስረዳት ስናነብም ባህል በየፈርጁ…ያስብለናል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርት ቤታቸው አጥር ሳይኖረው፣ አጥር እንዳለው አድርገው አስበው ለትምህርት ቤቱ ደንብ መገዛታቸው…የዐሊይ ማኅበረሰብ ለመራቂነትና አስታራቂነት የሚመርጠው ከዚህ ቀደም ወንጀል ሰርቶ በበቂ ፍርዱን ጨርሶ የወጣ ሰው መሆኑ… ‹‹ተፈርዶበት ከሆነና ቅጣቱን በሰላም ማጠናቀቁ ከተረጋገጠ ማኅበረሰቡ ለእሱ አድሮበት የነበረውን ቅሬታ ማንሳቱን የሚያሳምነው እንዲህ ባለው አጋጣሚ ከበሬታ ሲቸረው ነው፡፡›› ይለናል "ሲጥል"፡፡ ሌላም ሌላ…ያልተለመዱ አኗኗሮችና ጥልቅ ህይወት ፍልስፍናዎች…
ገጸ-ባህርያቱ የየራሳቸው የዓለም እይታ አላቸው - ዓለም ጉራማይሌ ናት እንደሚባል፡፡ እንዲያም ሆኖ የሚያገናኛቸው ጉዳዮች አሉ፣ በጉዞ ላይ የነበረ ሥጋትና በባልፈለጉት ቦታ አንድ ላይ መገኘታቸው፡፡
የተለያዩ ገጸ-ባህርያትን ለምሳሌ ፍቅርና ጥላቻ፣ ሃይማኖታዊ እምነትና በአንፃሩ ምትሃታታዊ አምልኮት፣ የወቅቱ የመታገት ስጋት፣ ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት ወሲባዊ፣ አንዲሁም በስልጣን መባለግ፣ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የብሔር ጋብቻ፣ ክፋትና ደግነት፣ መከፋትና መደሰት፣ አክብሮትና ንቀት፣ በራስ መተማመን እና በራስ እምነት ማጣት፣ የወገን ፍቅር ጥማት (ራሷ እየገዛች የምትለብሰውን ወንድሜ የላከልኝ ነው እያለች ለጎረቤት የምታሳውቀዋን እናት ልብ ይሏል)፣ ሌሎችም የእኛ መጥፎ እድል ገጥሟቸዋል ብሎ የምስራች ማብሰር መሯሯጥ፣ ወዘተ፣ የሚወክሉ ግለሰቦችም በውይይት ላይ ባህሪዎቻቸውን ገላጭ የሆኑ አረፍተ ነገሮች ሲሰነዝሩ፣ እንደ ተራ ጉዳይ፣ የቀን ተቀን ሁኔታ፣ ተግባር አድርገው ነበር የሚያወሩ፡፡
ግለሰቦች ቦድነው በማይረባ ጉዳይ መነታረክ፣ "የቴዎድሮስ ሳልሳዊ ጉዳይ"፣ የኛ ነው የኛ ነው የማለት ብሎም ስር የሰደደ ጸብ መቀስቀስ፡፡ በፖለቲካ ተዋናይነት ከሚገባ በላይ ራሱን አንቱ ብሎ፣ ያንን ለዘላለም ሲያነሱ መገኘት አንዱ የዘመናችን ችግር ነው፣ ያም ተወስቷል (አቶ ሥዩም በሟች በአቶ ዘላለም ተነጠቅሁ የሚሉት ዝና)፡፡ የፍቅር መግለጫ ሆኖ የተሰነደው ቤርሳቤህ ለተለያት ፍቅረኛዋ ለምንተስኖት ጥላለት የሄደችው፣ እሱ ይወደው የነበረ እርሷም የምትኩራራበትን ዘንፋላ ፀጉሯን ተላጭታ ከመቃብሩ አፈር ጋር ቀላቅላ መሰናበቷስ? ሁሉንም ሁኔታዎች ደራሲው በአጫጭር አረፍተ ነገሮች፣ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡
ለአዲሱ ትውልድ እንግዳ ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ኋላ ቀር እምነቶችም ተወስተዋል፣ ለምሳሌ የመሪጌታ ሐብቴ እና የኢዩዔል ተግባራት፣ "የትኩስ የመቃብር አፈር በመበተን የተኛን ከእንቅልፉ እንዳይነቃ ማድረግ"፣ "ጅብ ጋላቢ ቡዳ"፣ "የድመት ቂመኝነት፣ እንዲሁም መጥፎ ዕድል አመልካችነት"፣ "ለአንድ ግለሰብ የመጣን የሞት እጣ ወደ ሌላ ግለሰብ ማሸጋገር"፣ "ትላልቅ ወንዞች የመናፍስት ሰፈሮች ስለመሆናቸው"፣ የሞተን ሰው ቀስቅሶ እንዴት እንደተገደለ ራሱን ሟቹን ቀስቅሶ ስለመጠየቅ …ወዘተ፡፡ አንዱ ኩነት፣ ኩነቱ በሚነካቸው ገጸ-ባህርያት ላይ የተለያዩ ተጽእኖዎችን ማድረስ፣ ለእናት የስጋት ምንጭና ምስጢራዊነት፣ ላልወለደ አባት የጥንካሬ ምንጭ፣ ልጁ የእሱ አለመሆኑን እያወቀ ሚስቱን እንዳይከፋት፣ ብሎም ልጇን ይዛበት እንዳትሄድ፣ እንዳላወቀ ሆኖ መታየት፣ ለልጅ የዘላለም ጠንቅ ሆኖ የዘለቀ፣ በመጨረሻ ራሱን ለማጥፋት ምክንያት መሆን፡፡
ብዙ ፍልስፍና አዘል ጥልቅ አስተያየቶችም ቀርበዋል፣ ለምሳሌ "ከቁርበት ጋር መምከር (ይደር እንደማለት)"፣ ለማኙ ለተለማኝ የወረወረው አረፍተ ነገር "አንተ እንድትረዳኝ የግድ መዝረክረክ፣ መንገፍገፍ.....መቆሸሽ... ነበረብኝ?" … "መዋደድ ብቻውን አብሮ ለመኖር በቂ አይደለም"፣ "ፍቅር ብቻውን ግጥም የሌለው ዜማ ነው"፣ "ያልተፈተነ አያልፍም"፣ የደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር "የነፃነት" ግንዛቤ፣ ወዘተ፡፡
ብዙ ዱብዳዎችም ተወስተዋል፡፡ ለብዙ ዓመት እናቷን ያላየች ልጅ፣ እናቷን ስታገኛት የእናቷን ሴት አዳሪ መሰል ሆና መታየት፣ ያም ሁኔታ በቅናት መንስዔ በራሷ ጓደኛ የተቀናጀ ሴራ መሆኑን ከጊዜ በኋላ መገንዘብ… ከሃያ ዓመት በላይ አባቴ እገሌ ነው ብሎ የኖረ ልጅ፣ ድንገት አይቶት የማያውቀው ሰው አባትህ ነኝ ብሎ መምጣት ወዘተ፡፡
አልፎ አልፎ አረፍተ ነገሮች፣ ሙዚቃ አዳባሪ መሰል፣ ከሩቅ የሚሰማ አታሞ/ከበሮ ድምጽ ስሜትን በአንባቢው ላይ ይጭራሉ፡፡ "ድፍረት እንደ አንበሳ፣ ስርቆት እንደ ቁራ፣ ፍጥነት እንደ ንስር…"፣ "የተፋታ ሁሉ የተጣላ፣ አብሮ የሚኖር ሁሉ ፍቅረኛ…"፣ "ከምላስ ላይ ምራቅ፣ ከአንገት ላይ ንቅሳት…"፣ "እናቷን ስታገኝ፣ የዛገ ብረት እንደማሽተት፣ የሻገተ እንጀራ እንደመብላት፣ ክፍቱን ያደረ ውሃ እንደመጠጣት ዓይነት ስሜት…" ... መሰል የቃላት ስብጥሮች፡፡
አንዳንድ ለየት ያሉ ሁኔታዎችም ተወስተዋል፡፡ "ቀውስጦስ" የተባለ መልዓክ፣ የፈጣሪውን ትዕዛዝ፣ ለመፈጸም ርህራሄው ስለገታው በአምላክ ተቀጣ፤ ክንፉ ተሰበረ፤ ብሎም የመብርር አቅሙን ተነጠቀ፤ በአማላጅ ከዓመታት በኋላ በፊት እንደነበረው ለመሆን በቃ፡፡ ይህን ስናነብ ምነው ብዙ "ቀውስጦስ" መሰሎች የፈጣሪ መልእክተኞች በዚህ ዓለም ቢኖሩ ኖሮ? ያሰኛል፡፡
አንባብያን የእንዳለጌታ ከበደን "ሲጥል" በጥሞና ካነበቡ፣ ስለ ሕይወት ገጠመኞች ብዙ ግንዘቤ፣ ብሎም ስለ ማኅበረሰባዊ ግንኙነቶች የሕይወት መመሪያ ሊሆን የሚችል ዕውቀት እንደሚያገኙ አምናለሁ፡፡ መጽሐፉን ማንበብ ይጠቅማል፤ ይበጃልም፣ እላለሁ!
ከአዘጋጁ፡-







10 last posts shown.

4 110

subscribers
Channel statistics
Popular in the channel