አደፍርስ
አብዬ አደፍርስ የሚስታቸውን ግልምጫ ያመልጡበት፣የልጆቻቸውን ሆድ ይሞሉበት መላው ቸግሯቸዋል።የዛሬ አራት ወር ገደማ በጥበቃነት ይሰሩበት የነበረው ባንክ የዘረፋ ሙከራ ተደርጎበት የነበረ ጊዜ ዘራፊዎቹን በጉልበታቸው መመከት እንደማይችሉ ሲያውቁት በድረሱልኝ ጥሪ ቢዘርሯቸውም የባንኩ ማናጀር እሳቸውን አባሮ በቦታቸው ከሳቸው በእድሜ አነስ የሚል ጎልማሳ ከመቅጠር ወደኋላ አላለም።ይኸው ከተባረሩ አንስቶ ሁሌ ማለዳ ማለዳ ከስራ ሰዓት ቀደም ብለው ያደረ ሽንታቸውን ከቤት ይዘውት ይወጡና ባንክ ቤቱ አጥር ስር ሲደርሱ ነው ቀበቷቸውን የሚፈቱት።
ስጋ ለበስ ብትራቸውን አራግፈው ከሱሪያቸው ስር እየወሸቁ
"ኡኡ ባልኩ?እንደ ሴት ጮሄ ባስጣልኩ?" ይላሉ።አሁን አሁን ግን ረሀቡ ጠናባቸው።የሶስት ልጆቻቸው አንጀት እግርና እግራቸውን ተብትቦ ይዞ አላራምድ አላቸው።ሚስታቸው ከጉሊት ውለው ሲመጡ ከሬሳ የከረሰሰ ሽሮ ያቀርቡላቸውና
"አንቱ የሴት ገንዘብ ምን ምን ይላል?እስቲ ቀምሰው ይንገሩኝ" ይሏቸዋል።
ሁለመናው ከትዕግስታቸው ቋት እየፈሰሰ አልሆን ሲላቸው ሂሩትን አማከሯት...የመንደራቸውን አድባር።ሂሩት በመንደሩ ብቸኛዋ አጭር ቀሚስና ሂል ጫማ የምትለብስ የመንግስት ሰራተኛ ናት።እንዳማከሯትም አላሳፈረቻቸውም ማንበብና መፃፍ የሚችል ሰው ሁሉ ሊሰራው የሚችል ስራ አገኘችላቸው።አላምናት ብለው
"አየ ሂሩት...ይኸን ሽማግሌ ልቀልድበት ብለሽ ነው መቸም"
"አባቴን ይንሳኝ የምሬን ነው!"
"እንዴት ያለ ነው ስራው?"
"አልጋ ቤት ነው የሚሰራው አብዬ...አንድ ቀን በቀን ፈረቃ ሌላ ቀን በማታ ሆኖ አልጋ የሚይዘውን ሰው መታወቂያ ይዘው ስም እየመዘገቡ ብር ተቀብሎ ማሳደር ነው።የማታ ሲሆኑ ማደሪያዎትን ቆንጆ አልጋ ይዘጋጅልዎታል።"
"አልጋ ቤት?"አሉ ቅሬታ በተሞላ ድምፀት።
"አዎ...መንገደኛና የሰው አገር ሰዎች...ነጋዴዎች አልጋ ተከራይተው ሲያድሩ እነሱን መመዝገብ ነው አብዬ።"
"እንዴት ነው እነሱ ተኝተው እኔ ስጠብቃቸው ላድር ነው?ተይ ተይ ቤቱን ዘርፈውት የሄዱ እንደሁ በጉዴ እወጣብሻለሁ ሂሩቴ"
"ኧረ ቤቱ የራሱ ጥበቃ አለው!የርስዎ ስራ መዝግቦ መተኛት ነው"ስትላቸው እያቅማሙም ቢሆን ተስማሙ።
የመጀመሪያውን ቀን በቀን ፈረቃቸው አቀላጥፈው ሰሩ።ይጠፉብኛል ብለው የፈሯቸው ፊደላት ሁሉ እንደ ይስሐቅ ታዘዟቸው።ያሞጨሞጩ አይኖቻቸውም የዋዛ አልነበሩምና ከየሰዉ መታወቂያ ላይ ጥቁሩን ከቀዩ፣ጠይሙን ከቀይ ዳማው አበጥረው ለዩት።አመስግነው ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው ከወትሮው በተለየ በትኩስ ሽሮ ተቀበሏቸው።አቦል ይሁን በረካ ባይለይም ቡና ተፈልቶላቸው አንድ ሲኒ ጠጡ።ለወትሮው ጀርባቸውን ይሰጧቸው የነበሩት እመይቴ አማረች ጡትና ጡታቸው መሃል አስተኝተው ራሳቸውን ሲዳብሷቸው አመሹ።
በሁለተኛው ቀን በማታ ፈረቃቸው ሰዓታቸውን አክብረው ተገኙ።አንድ ሶስት መንገደኞችን መዝግበው ቁልፍ ከሰጡ ወዲያ ሁለት ወጣቶች ተቃቅፈው መጡና አጠገባቸው ቆሙ።ሲታዩ እድሜአቸው እምብዛም አይራራቅም።ሴቲቱ ከማውራት ይልቅ ፈገግታና መሽኮርመም ይቀናታል።ወንዱ የጤና በማይመስል ሁኔታ ይቁነጠነጣል...ችኩል ችኩል ይላል።
"እ ፋዘር...አልጋ አለ ኣ?"
"አለ...ሁለት ነው አንድ የፈለጋችሁ?"
"ኧረ ቆጥበን እንጠቀማለን ሃሃሃ...ባለ አንዱ ስንት ነው?"
"ሁለት መቶ ብር"
"ሁለ'መቶ?" አለና ግንባሩን ክስክስ አድርጎ አጠገባቸው ያለውን አልጋ እያየ
"እንደዚህ ነው እንዴ አልጋው?"ጠየቀ።
"ኧረ ይች የኔ የብቻየ ስለሆነች ነው...ውስጥ ያለው ሰፋፊ ነው"አሉ እያፈሩ።ልጅቷ የልጁን ጎን በስስ ቦክስ ነካ አርጋ በዝግታ "አንተ አታፍርም?"ትላለች።
" ሀዬ በቃ መዝግቡና ፋዘርዬ" አለ መታወቂያውን ፍለጋ ኪሱን እያመሰ።ወዲያው ነገር በድንገት ብልጭ እንዳለለት ሰው እያደረገው
"ውውውውውይ በናትሽ!...ለካ አይ.ዲ.ዬን ያ ዘበኛ እንደያዘው ነው...ያንቺን አምጪው በቃ" ሲላት ቅር እያላት መታወቂያዋን አውጥታ ሰጠች።አብዬ አደፍርስ ፎቶዋን አበጥረው አዩና ወደ ስሟ ወረዱ።ለአፍታ ከመረመሩት በኋላ የሚያውቁት ፊደል ሲያጡ ቀና አሉና።
"ማነው ስምሽ"? አሉ።
"የኋላ'ሸት"
"እና ምነ በአማርኛ ቢፃፍ?" አሉና ስሟን ሊመዘግቡ ፊደላቱን ከአዕምሯቸው ጓዳ ያተራምሷቸው ጀመር።እየተንቀጠቀጡ ስሟን ፅፈው ሲጨርሱ
"የአባትሽስ?"
"ይበልጣል"
አሁንም እየተንቀጠቀጡ ሊመዘግቡ ሲያቀረቅሩ ልጁ ትዕግስቱ ተሟጦ
"ፋዘር እኔ ልመዝግበው የፈጠነ?"
"እ?"
"የፈጠነ...እኔ ፃፍ ፃፍ ላርገው?"
"ቆይ እስቲ...ይ...በ...ል...ጣ...ል...ይበልጣል"አሉና ቀጠል አርገው
"ስራ?"
"ተማሪ ነን"
"ተ...ማ...ሪ...ተማሪ"ይህንንም በዘገምታ አስፍረው ስልክ ቁጥር ከመዘገቡ በኋላ ክፍያ ተቀብለው ቁልፉን አስረከቧቸው።ለክፋቱ የዚያን ቀን የቀረው ብቸኛ ክፍል ከሳቸው ምኝታ ቤት ቀጥሎ ያለው ነበር።
አገር አማን ብለው ሊያሸልባቸው ሲል ከመሬት መንቀጥቀጥ ያልተናነሰ መናወጥ ከሰመመናቸው አባነናቸው።ተገስ እስኪል ጠበቁና ወደ ክፍሏ በር ጠጋ ብለው አንኳኩ።
"የኔ ልጅ"
"ምንድነው ፋዘር?"
"እንደው አደራህን የኔ ዓለም የአልጋው ብሎን እንዳይረግፍ...ደሃ ነኝ የምከፍለውም የለኝ...ወይ ፍራሹን ታወርዱት"?
"ሀዬ በቃ ይወርዳላ!"
ወደምኝታቸው ተመልሰው ፀሎታቸውን እያነበነቡ በድጋሚ ሊያሸልባቸው ሲል የድረሱልኝ ጥሪ የሰሙ መስሏቸው ብርግግ ብለው ተነሱ። ጆሯቸውን ቀስረው ሲያዳምጡ ጩኸቱ ከጎረቤት ነው።ጭንቅ ሲላቸው የስልካቸውን ራዲዮ ከፍተው ወደ ጆሯቸው ለገቡት።
"እንግዲህ አድማጮቻችን ከምሽቱ 12:00 የጀመረው የመዝናኛ ዝግጅቻችን እንደቀጠለ ነው።በያላችሁበት እጅግ ያማረ ጊዜን እያሳለፋችሁ እንደሆነ አንጠራጠርም።ታሪኳ ይነበብ ከሞጣ 'አትጠገቡም' ብላናለች።...ሆዴ ሞላ ከደጀን...እግዜሩ ባይከዳኝ ከጎንደር...ብርአልጣ ዘለዓለም ከማርቆስ 'ዝግጅታችሁ ተወዳጅ ነው' ብለውናል።ከኤፍሬም ታምሩ ሙዚቃ በኋላ ተመልሰን የምንገናኝ ይሆናል።አብራችሁን ቆዩ"
"...ወይ ዘንድሮ(2X)...ወይ ዘንድሮ(2X)
ወይ ዘንድሮ አያልቅም ተነግሮ"
ሙዚቃው ሲያልቅ የስልካቸውን ራዲዮ እየዘጉ
"ወይ የአንት ያለህ!!!እንዴት ያል ዘመን መጣብና?ወንዱ እንደ ሴት እየጮኸ? ኧረግ የእንድማጣው!ቱ!ቱ!ቱ! ሞት ይሻል የለም ወያ አንድ ፊቱን!"እያሉ ይብሰለሰሉ ጀመር።ለሊት ከሞቀ እንቅልፋቸው ሶስቴ ተቀስቅሰው፣አልጋው ረገበ አልረገበ በስጋት ተሰቅዘው አደሩና እንዳይነጋ የለ ነጋላቸው።ልጆቹ መታወቂያ ሊወስዱ ሲመጡ አብዬ አደፍርስ አልጋውን ሳላይ ገመድ ባንገቴ አሉ።አገላብጠው ካዩትና ከመረመሩት በኋላ
"እውነትም ላያስችል አይሰጥ!"ብለው አልጎመጎሙና ልጆቹን አሰናበቷቸው።በቀን ፈረቃ የሚሰራው ተተኪ ሰራተኛ እስኪመጣ ጠብቀው ስራ መልቀቃቸውን ነግሩትና ወደ ቤታቸው አዘገሙ።እመይቴ አማረች ወሬውን ቀድመው ከሂሩት ሰምተውት ኖሮ መሸት ሲል መጥተው የከረሰሰ ፊት ከከረሰሰ ሽሮ ጋር አቀረቡላቸው።
"አንቱ የሴት ገንዘብ ምን ምን ይላል?እስቲ ቀምሰው ይንገሩኝ "
ዘማርቆስ
@wogegnit@wegoch@wegoch@wegoch