የሴት የትምህርት አመራሮችን አቅም ለማጎልበት እና ወደ አመራርነት ለማምጣት የሚያስችል ስልጠና ተሰጠ።
(መጋቢት 6/2017 ዓ.ም) ስልጠናው በሁሉም የመንግስት አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ዋና እና ምክትል ርዕሳነ መምህራን በዘርፉ ልምድ ባላቸው አካላት መሰጠቱን ከመርሀ ግብሩ አዘጋጆች ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የዘርፈ ብዙና ቀዳማይ ልጅነት ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ በላይነሽ የሻው በስልጠናው መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት በትምህርት ዘርፉ የሚገኙ ሴት አመራሮችን አቅም የማጎልበትና ወደ አመራርነት የማምጣት ስራ በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው የዛሬው የስልጠና መርሀግብር ቢሮው በትምህርት ሴክተሩ ብቃት ያላቸው እና በራስ መተማመናቸው ከፍተኛ የሆነ ሴት የትምህርት አመራሮችን ለማፍራት ያስቀመጠው ግብ ስኬታማ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ቡድን መሪ አቶ ይልማ ተሾመ በበኩላቸው ስልጠናው በትምህርት ሴክተሩ ብቃታቸው የተረጋገጠና ተጽኖ ፈጣሪ ሴት አመራሮችን ለመፍጠር የሚያስችል መርሀግብር መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ትምህርት ቢሮ ድረስ ለሚገኙ ሴት የትምህርት አመራሮች ተመሳሳይ ስልጠና የሚሰጥ መሆኑንም አመላክተዋል።
ስልጠናውን በአዲስ አበባ ዩኒ ቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ በሚገኙት እና በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባላቸው ወይዘሮ ሩት ሹሜ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ በመጡት ወይዘሮ ሰላማዊት በላቸው መሰጠቱን የስልጠናው አስተባባሪዎች አስታውቀዋል።
መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት ማሰፈንጠሪያውን ይጫኑ!
https://linktr.ee/aacaebc