እግዚአብሔር ለምን መቅሰፍት ያመጣል?
(አባ ገብረኪዳን)
በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ስሙ ይክበርና ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔር ፍጥረቱን ለመጥቀም ስለ ሦስት ነገር መቅሰፍትን ያመጣል።
፩. " ከመ መቃብር ክሡት ጎራዒቶሙ - ጉረሯቸው እንደተከፈተ መቃብር ነው " ለሚላቸው ሰዎች። ማለት መቃብር ቢቀብሩበት ቢቀብሩበት
በቃኝ እንደማይል ኃጢአትን በቃኝ ለማይሉ ፥ መመለስን ለማያስቡ መመለስንም ለማይፈልጉ ሲል መቅሰፍትን ያመጣል። ሰው ኃጢአትን
ከመደጋገሙ የተነሳ ኃጢአት ወደ ልማድ ይለወጣል። በልማድ ከመታሰሩ የተነሳ ልቡ ይደነድናል። ልቡ ከመደንደኑ የተነሳ ጽድቅን ይጠላል ፥
ኃጢአት ይጣፍጠዋል ። ከዚህ በኋላ ጽድቅን ሁሉ ይቃወማል። " እስመ ግዘፈ ልብ ዘልፈ ይትቃዎሞ ለጽድቀ እግዚአብሔር - የደነደነ ልቡና
ዘወትር የእግዚአብሔርን እውነት ይቃወማል " እንዲል ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ። ከዚህ ሲያልፍ ምሕረት እንኳ ያስጠላዋል። መጨረሻ ላይ
ለማይረባ አዕምሮ ተላልፎ ይሰጣል ። ከዚህ ወዲያ በግብሩ አውሬ ወይም ሰይጣን ይሆናል ። አንድ ሰው በዚህ ግብር ለመያዙ የደዌው
ምልክት ምንድን ነው ቢሉ በኃጢአት አለማፈር ና በግፍ መደሰት ፤ ከዚህም አልፎ በግፍ መኩራት ይታይበታል። ቀደም ብለን እንዳነሣነው
እጁጉን በሽታው እንደጸናበት የፍጻሜ ምልክቱ ደግሞ ምሕረትን መስማትም አለመፈለግ ነው ። እንዲህ አይነት ሰው ደግ መሥራትቱስ
ይቅርና ሃይማኖቱን እንኳ እስከማጣት ይደርሳል። "የሌለውን ያንኑ ይወስዱበታል " የተባለው ይኸው ነው።
ሊቁም " ኢይትከሃሎ ለብእሲ ለእመ ኢያግኀሰ ርእሶ እምግዕዘ ልማድ - ሰው ከፈቃደ ልማድ ማእሰር ራሱን ካላራቀ ሃይማኖታዊ ምእመን
መሆን አይቻለውም " ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትርጓሜ እብራውያን ፳፪
መመለስን ለማይሻ ፣ ምሕረት ለማይፈልግ ፣ ልቡ ለደነደነ ፣ አዕምሮው ለተነሣው ፣ ሕሊናው ለከዳው " እሰማው ዘንድ እግዚአብሔር ማን
ነው " በሚል እንቢተኛ ልብ ለጸና ሰው መቅሰፍት ይታዘዝልታል ። ለምን ቢሉ ምሕረተ እግዚአብሔርን ላልተጠቀመባት ሰው ፍትሑ
ትፈርድበታለችና።
ይህ ሰው ሞቱ ሁለት ጥቅም አለው። መጀመሪያ "ወባሕቱ በአምጣነ ኢትኔስሕ ትዘግብ መቅሰፍት ለርእስከ - ነገር ግን ንስሐ
እንዳለመግባትህ ለራስህ ፍዳን ታከማቻለህ " እንዳለው ሐዋርያው ቆይቶ ፍዳን ከሚጨምር መሄዱ ይሻለዋልና ስለዚህ ነገር
እግዚአብሔር ይቀስፈዋል። ሌላው ደግሞ ንስሐ ለመግባት ያለቀውን የተሰጠውን ዘመንና ትምህርት ላልተጠቀመበት ሰው መቆየቱ
ለሌላው ስቃይ እንዳይሆን ስለዚህም ይቀስፈዋል። አስር ምክር ተሰጥቶት ላልተመለሰ ፈርዖን ቢቆይ በሕዝበ በእስራኤል ላይ ስቃይ
ከመጨመር በቀር እርሱ እንደማይመለስ ባወቀ ገንዘብ እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ እንዳሰጠመው ማለት ነው። እኛንም " ወይእዜኒ አመ
ሰማዕክሙ ቃሎ ኢታጽንዑ ልበክሙ - አሁንም ቃሉን ብትሰሙ ልባችሁን አታጽኑ " ያለን ዕድል ፈንታችን ጽዋ ተርታችን እንዲህ እንዳይሆን
ነው።
፪. ሁለተኛ መቅሰፍት የሚመጣው " ቅን ልቡና ላላቸው ፣ የተንኮል ጥበብ ለሌለባቸው ፣ እግዚአብሔርን ለማይሸነግሉ ፣ በብልጠት
መጽደቅ ለማይፈልጉ ፣ በቅን መንገድ ሆነው ፣ ድካማቸውን ተረድተው " ኢታብአነ እግዚኦ ወስተንሱት - አቤቱ ወደ የፈተና አታግባን "
ለሚሉ ሰዎች እግዚአብሔር ደዌውን ሞትን ያመጣል። የፈተና ቀን ምንድን ነው ቢሉ መከራ ፈርተው ክርስቶስን የሚክዱባት ቀን ናት ይላሉ
አበው። ስለዚህ በጭንቅ ቀን የእምነት ትጥቃችን እንዳይላላ በክንፈ ርድኤትህ ከልለን ፤ ለሚሉና
"አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለ ዛ ዓለም ወከአዉ ደሞሙ በእንተ እግዚአብሔር ፥ ወተዐገሡ ሞተ መሪር በእንተ መንግሥተ ሰማያት
ተሣሃለነ በከመ ዕበየ ሣሕልከ - ሰማዕታት በእውነት የዚህችን ዓለም ጣዕም ናቁ ። እግዚአብሔርን ስለ መውደድም ሰውነታቸውን
ለሕማም ለሞት አሳልፈው ሰጡ ደማቸውንም አፈሰሱ። ስለ ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሡ። አቤቱ እኛ ግን እንደ
ሰማዕታት እሳቱን ስዕለቱን ፥ እንደ ባሕታውያን ድምፀ አራዊቱን ጸብዓ አጋንንቱን ፥ እንደ መነኮሳት ዕፀብ ገዳሙን ፣ ፍትወታት ርኩሳት
ኃጣውእ ርኩሳቱን ታግሠን መጽደቅ አትቻለንምና እንደ ምሕረትህ መጠን ማረን " እያሉ የሚለምኑትን እግዚአብሔር በመከራ ጽናት
እንዳይናወጹ በጊዜው ይወስዳቸው ዘንድ መቅሰፍትን ያመጣል። ይህን የሚያደርገው መቆየታቸው ያለቻቸውን ጥቂት ምግባር
እንዳያሳጣቸው ሃይማኖታቸውን እንዳያስክዳቸው ነው።
ከኢትዮጵያውያን ጻድቃን እንዷ እናታችን ቅደስት ወለተ ጴጥሮስ ይህንን አድርጋለች። በሚቀጥሉት ጊዜያት መከራ እንደሚመጣ በጸጋ አውቃ
ከመንፈሳዊ ልጆቿም ጥቂቶቹ በድካማቸው ካሉበት መንፈሳዊ ሕይወት መከራው እንዲያናውጻቸው በተረዳች ጊዜ ፤ አርድእቶቿን በሞት
እንዲወስድላት እግዚአብሔርን ለምና እንዲሞቱ አድርጋለች። ቆይተው በመከራው ተናውጸው ሲኦል ከሚወርዱ ያለቻቸውን በጎ ሕይወት
ይዘው የምድሩ እድሜ ቀርቶባቸው ዘለዓለም ቢኖሩ የተገባ ነውና ። እግዚአብሔርንም እንዲህ በሚለው የቅዱስ ዳዊት መዝሙር ነበር
የለመነችው " እስመ ይኄይስ እምኀይው ሣሕልከ - አቤቱ ከሕይወት ቸርነትህ ይሻላል "። ይህ ማለት በምድር ኃጢአት ሊጨምሩ ከመኖር
የምድሩ እድሜ ቀርቶ አጥሮ በቸርነትህ የዘለዓለም ሕይወትን መውረስ ይሻላልና ማለት ነው ። ነቢዩ በሌላም ስፍራ " አቤቱ በኃጥኣን
ድንኳን ከመኖር ይልቅ በአንተ ቤት መጣል ይሻላል " ። በዚህ ዓለም ቆይተን ኃጢአትን ጨምረን ኪፈረድብን በሞት ተጥለን ዘለዓለም
ብንኖር በእውነት ይሻለናልና ። ይህንን ማድረግ የሚቻለው ግን እርሱ ባለቤቱ ሕያው እግዚአብሔር እንጅ ማንም አይደለም ። ራሱን የፈጠረ
ሰው እንደሌለ ማንም ራሱን ቢገድል ራሱን ጣዖት ማድረጉ ነው።
፫. ሦስተኛው ደግሞ እግዚአብሔር በሚያመጣው መቅሰፍት የሚጠቀሙ ሰዎች እድሜ ለንስሐ የተሰጣቸው ናቸው ። ክብር ይግባው ስሙ
ይመስገንና አቡሃ ለምሕረት እግዚአብሔር ካልዘራበት አያጭድም ካልበተነበት አይሰበስብም ። ማለት ሳያስተምር አይፈርድም። ስለዚህ
ሰውን በብዙ መንገድ ለድኅነት ይጠራል ። መምህራንን ለሚሰማ በመምሕራን ፥ በትሑት ሰብእና በቅን ልቡና በበጎ ሕሊና ሆነው
ሊሚፈልጉት በመጻሕፍት ፥ ይህ ሁሉ ላልተሳካላቸው በሥነ ፍጥረት " ወኩሉ ዘተፈጥረ ለመፍቅደ ነባብያን ቦ እምኔሆሙ ለምሕሮ ወቦ
እምኔሆሙ ለአንክሮ ወቦ እምኔሆሙ ለተዘክሮ - የተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ በነፍስ ለባውያን ነባብያን ሕታዋን ሆነው ለተፈጠሩ ለሰዎች
የተፈጠረ ነው። ከተፈጠሩትም ፍጥረታት ለትምህርት የተፈጠሩ አሉ። ለአድናቆት የተፈጠሩ አሉ ፤ እግዚአብሔርን ለማሰብ የተፈጠሩ አሉ "።
እንዳለ አረጋዊ መንፈሳዊ
በስነፍጥረት ላልተማረም በአዕምሮ ጠባይዕ ያስተምራል ። በዚህ ሁሉ ለላልተመለሰም በተአምራት ያስተምረዋል ።
ይህንን ሁሉ አልፎ ወደ እግዚአብሔር ያልተመለሰ ሰው በመቅሰፍት ይማራል ። ፈጣሪ የለም የሚል ሰነፍ ልቡ እንኳን ቢሆን በመቅሰፍት
እግዚአብሔር እንዳለ ያውቃል። ለሚጨነቁት የማያዝኑ ሲጨንቃቸው ርኅራኄን ይለምዳሉ ። ፍርድ የጎደለው ድኻ ተበደለ የማይሉ
ባለሥልጣናት ፈራጅ እንዳለ ያውቁ ዘን መቅሰፍት ይመጣል። ክንደ ብርቱ ነን ብለው ቋንጃ የሚቆርጡ ፥ ደም የሚያፈሱ ........
..... ቤት የሚተኩሱ ፦ ከእግዚአብሔር ጸባዖት - ከአሸናፊው የሠራዊት ጌታ ከሕያው እግዚአብሔር ክንድ በታች ሥር መሆናቸውን
ተረድተው ይመለሱ ዘንድ መቅሰፍት ይመጣል ።
@yaltenegeru_mistroch@yaltenegeru_mistroch@yaltenegeru_mistroch