ብልጽግና ፓርቲ በመጪው ጠቅላላ ጉባኤው የከፍተኛ አመራሮች ምርጫ ሊያካሄድ ነው!ከመጪው አርብ ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በሚካሄደው የገዢው ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ፤ ፓርቲውን የሚመሩ ከፍተኛ አመራሮች እንደሚመረጡ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ።
ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ፤ የፓርቲው ፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ የስራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ እንደሚካሄድ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
ከአርብ ጥር 23 እስከ እሁድ ጥር 26 በአዲስ አበባው የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በሚካሄደው በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ፤ በፓርቲው ፕሮግራም እና ደንብ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች የሚጸድቁበት እንደሆነ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ባለፈው ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች አፈጻጸም በአሁኑ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚገመገም አቶ አደም ተናግረዋል። እስከሚቀጥለው ጉባኤ ድረስ ፓርቲውን የሚመሩ ከፍተኛ አመራሮችም በዚሁ ጉባኤ ላይ እንደሚመረጡ አቶ አደም አክለዋል።
በሁለተኛው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ፤ የፓርቲው ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች ምርጫ እንደሚካሄድ ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ከእነዚህ ከፍተኛ አመራሮች በተጨማሪ የስራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ በተመሳሳይ መልኩ እንደሚካሄድ ምንጮቹ ገልጸዋል።የፓርቲው የኢንስፔክሽን እና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን አባላትም በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚመረጡ ምንጮች አክለዋል።
Via Ethiopia Insider
@YeneTube @FikerAssefa