ቤተ ዝማሬ መላእክት ዘደብረ ገነት


Channel's geo and language: Ethiopia, Amharic
Category: not specified


ይህ ምኅላፍ (channel ) በየጁቤ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት የተከፈተ ሲሆን ፡በዚህ ምኅላፍ(channel ):-
✍ ያሬዳዊ መዝሙሮች
✍ ከ ስንክሳር ዕለታዊ የቅዱሳን
ገድል
✍ የቤተክርስቲያናችንን አስተምህሮ
የምናጠናበት እና የምንማርበት ነው፡፡

Related channels

Channel's geo and language
Ethiopia, Amharic
Category
not specified
Statistics
Posts filter




✝ በስመ፡ አብ፡ወወልድ ፡ወመንፈስ ቅዱስ ፡አሃዱ ፡አምላክ ፡አሜን✝
የዚህ ቻናል ተከታታይ በሙሉ ሀሳብ አስተያየት ያላችሁ @zedebregenet @dagimdd @seasamson
If you have comments from all the followers of this channel


።በዚህ መሰረት የሌሎችንም እንመልከት
ኢይወርድ.......ኢየዐርግ
የነነዌ ጾም.............ጥር 17........የካቲት 21
ዓቢይ ጾም..............የካቲት 1......መጋቢት 5
ደብረ ዘይት.............የካቲት 28....ሚያዝያ 2
ሆሳእና....................መጋቢት 19...ሚያዝያ 23
ስቅለት...................መጋቢት 24....ሚያዝያ 28
ትንሳኤ..................መጋቢት 26.....ሚያዝያ 30
ርክበ ካህናት.........ሚያዝያ 20.......ግንቦት 24
ዕርገት..................ግንቦት 5..........ሰኔ 9
ጰራቅሊጦስ............ግንቦት 15.......ሰኔ 19
ጾመ ሐዋርያት...........ግንቦት 16.......ሰኔ 20
ጾመ ድኅነት.............ግንቦት 18..........ሰኔ 22
የበዓላትና የአጽዋማት ኢየዐርግና ኢይወርድ ይህንን ይመስላል።
ጸሎተ አስርቆት
ውዳሴ ማርያምም ይሁን ሌላ ጸሎት ከአሥርቆት
በኋላ ነው።አሥርቆቱም ይህ ነው።
ሃሌ ሉያ በዘንዜከር ሐሳባተ ሕጉ ወትእዛዛቲሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ
ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐሳበ ነቢያት ወሐዋርያት ሐሳበ ጻድቃን ወሰማእት
ሐሳበ ደናግል ወመነኮሳት ሐሳበ ኄራን መላእክት እንዘ ሀሎነ በዘመነ ቅዱስ
ማቴዎስ ወንጌላዊ (አስተውል ማቴዎስ ጸሎት እያደረግክበት ያለው ዘመን ነው)
ቡሩክ ያብጽሐነ እስከ ዘመነ ማርቆስ ዜናዊ።ካልክ በኋላ ያለህበትን ዘመን ዓመተ
ምህረት ዓመተ ዓለም አስበህ በ፸፻ወ፭፻፲፫ ኮነ ዓመተ ዓለም።በ፶፻ወ፭፻ ኮነ
ዓመተ ኩነኔ ዓመተ ፍዳ።በ፳፩፲፫ ኮነ ዓመተ ምሕረት።ትልና በመቀጠል
ያለህበትን ወር አንስተህ ለቀጣዩ ወር በሰላም ያድርሰኝ ለማለት ዮም ሠረቀ ለነ
ወርኀ መስከረም (በመስከረም ወር ከሆነ እየጸለይክ ያለኽው) ቡሩክ ያብጽሐነ
እስከ ወርኀ ጥቅምት በሰላመ እግዚአብሔር አብ አሜን ትላለህ።በመቀጠል
የእለቱ ሠርቀ መዓልት ሠርቀ ሌሊት እና ሠርቀ ወርኅ አስበህ እንዲህ
ትላለህ።መስከረም 1 ላይ ከሆነ እየጸለይክ ያለኽው አሚሩ (፩) ሠርቀ መዓልት።
አሡሩ ወተሱኡ (፲፱) ሠርቀ ሌሊት (19ኝን ያገኘነው አበቅቴ+ሠርቀ መዓልት
+ሕጸጽ አድርገን ነው) እሥራ ወሠሉሱ (፳፫) ሠርቀ ወርኅ።ሠርቀ ወርኅን
ያገኘነው ሠርቀ ሌሊት ላይ 4 በመጨመር ነው።ከዚያ እየጸለይክ ያለኽው ረቡእ
ከሆነ አሚሩ ጥንተ ዖን ረቡዑ ሠርቀ ዕለት ሰቡኡ ጥንተ ቀመር ብለህ ዝ ጸሎት
ወዝ አስተብቁዖት ይዕርግ በእንተ ስመ አብ ወበእንተ ተዝካረ ወልዱ ለእግዚእነ
ኢየሱስ ክርስቶስ ወበእንተ ስሙ ለመንፈስ ቅዱስ ጰራቅሊጦስ ወበእንተ ስማ
ለእግዝእትነ ማርያም ወላዲተ አምላክ አሜን ብለን እንጨርስና ይህም ጸሎት
ነው ከዚያ ወደ ሌላው ጸሎት እንገባለን ማለት ነው።የምትጸልየው
ረቡእ ከሆነ ጥንተ ዖን 1 ጥንተ ቀመር 2 ጥንተ ዕለት 4 ይሆናል።
ሐሙስ ከሆነ ጥንተ ዖን 2 ጥንተ ቀመር 3 ጥንተ ዕለት 5 ይሆናል።
አርብ ከሆነ ጥንተ ዖን 3 ጥንተ ቀመር 4 ጥንተ እለት 6 ይሆናል።
ቅዳሜ ከሆነ ጥንተ ዖን 4 ጥንተ ቀመር 5 ጥንተ እለት 7 ይሆናል።
እሑድ ከሆነ ጥንተ ዖን 5 ጥንተ ቀመር 6 ጥንተ እለት 1 ይሆናል።
ሰኞ ከሆነ ጥንተ ዖን 6 ጥንተ ቀመር 7 ጥንተ እለት 2 ይሆናል።
ማክሰኞ ከሆነ ጥንተ ዖን 7 ጥንተ ቀመር 1 ጥንተ እለት 3 ይሆናል።
በዚህ መሰረት ዘመኑን እያስታወስን እግዚአብሔርን እያመሰገንን እንኖራለን።
አነሳስቶ ላስጀመረን
አስጀምሮ ላስፈጸመን
ልዑል እግዚአብሔር
ምስጋና ይገባል
አሜን።
ሊቀ ማዕምራን መዓዛ ፈንታሁን የባሶ ሊበን ወረዳ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ
የጁቤ


የባሕረ ሐሳብ ትምህርት
ክፍል ሁለት
©® ዓመተ ምሕረትና ዓመተ ኩነኔ©®
ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ክርስቶስ የተጸነሰበት ጊዜ ያለው ዓመት ዓመተ
ኩነኔ ይባላል።መጠኑም 5500 ዓመት ነው።ክርስቶስ ከተፀነሰበት ጀምሮ ወደዚህ
ያለው ዘመን ደግሞ ዓመተ ምሕረት ይባላል።መጠኑም መስከረም 1 ጀምሮ
2013 ዓመተ ምሕረት ነው።
ዓመተ ዓለም=ዓመተ ኩነኔ+ዓመተ ምሕረት
=5500+2013 =7513 ዓመት ይህ ማለት ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ እስካሁን ያለው እድሜ 7513 ዓመት ነው ማለት ነው።
ዓመተ ወንጌላዊ
ወንጌላውያን 4 ናቸው።ወንጌልን ለ4 ተካፍለው እንደጻፉት ሁሉ።ዘመናትንም ለ4
ተካፍለው ይመግቡታል።ስለዚህ በሚቀጥለው ዓመት ዘመኑ ዘመነ ማን ነው የሚለውን ለማወቅ ስንፈልግ ዓመተ ዓለሙን ለ4 አካፍለን
ቀሪው 1 ከሆነ ዘመነ ማቴዎስ
ቀሪው 2 ከሆነ ዘመነ ማርቆስ
ቀሪው 3 ከሆነ ዘመነ ሉቃስ
ያለ ቀሪ ከተካፈለ ዘመነ ዮሐንስ ነው።
ስለዚህ በዚህ መሰረት።7513÷4=1878 ቀሪ 1 ይሆናል።1878 ወይም ደራሹ
መጠነ ራብዒት ይባላል። ስለዚህ ቀሪው 1 ከሆነ ማቴዎስ ነው እንዳልነው ቀጣይ
ዓመት ዘመኑ ዘመነ ማቴዎስ ይባላል።
የዓመቱ መስከረም 1 ቀን መቼ መቼ ትውላለች?
መስከረም አንድ ቀን መቼ እንደምትውል ለማወቅ ዓመተ ዓለምን ከመጠነ
ራብዒት ጋራ ደምረን በእለታቱ መጠን በ7 አካፍለን
ቀሪው 1 ከሆነ ማክሰኞ
ቀሪው 2 ከሆነ ረቡእ
ቀሪው 3 ከሆነ ሐሙስ
ቀሪው 4 ከሆነ አርብ
ቀሪው 5 ከሆነ ቅዳሜ
ቀሪው 6 ከሆነ እሑድ
ያለ ቀሪ ከተካፈለ ሰኞ ይውላል።
ስለዚህ አሁን ቀጣይ መስከረም 1 መቼ ይውላል የሚለውን ለማወቅ።
(7513+1878)÷7=1341 ቀሪ 4 ይሆናል።
ቀሪው 4 ከሆነ አርብ
ይውላል።ስለዚህ መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም አርብ ይውላል ማለት ነው።
መስከረም 1 በዋለበት ሚያዝያ 1 ይውላል
ጥቅምት 1 በዋለበት ግንቦት 1 ይውላል
ህዳር 1 በዋለበት ሰኔ 1 ይውላል
ታሕሣሥ 1 በዋለበት ሐምሌ 1 ይውላል
ጥር 1 በዋለበት ነሐሴ 1 ይውላል።
ይህም ማለት ለምሳሌ መስከረም 1 ቀን አርብ ከዋለ ሚያዝያ 1 ቀንም አርብ
ይውላል ማለት ነው።ታህሣሥ 19 ሰኞ ከዋለ ሐምሌ 19ም ሰኞ ይውላል ማለት ነው።
የ2013 መጥቅእ እና አበቅቴን እንዴት እናገኛለን??
ዓመተ ዓለምን በንኡስ ቀመር ወይም በ19 ብናካፍለው።ይህም ማለት
7513÷19=395 ቀሪ 8 ይሆናል።አሐደ አእትት ለዘመን እንዲል 8-1=7
ይሆናል።ይህ 7 ወንበር ይባላል። አበቅቴውን ለማግኘት ይህንን ወንበር በጥንተ
አበቅቴ ስናባዛው ማለትም 7×11=77 ይሆናል። ይህንን ቁጥር ለ30
ስናካፍለው 2 ጊዜ ደርሶ 17 ይተርፋል። ይህ 17 የቀጣዩ ዓመት ማለትም የ2013
አበቅቴ ነው።
መጥቅእን ለማግኘት አጭሩ መንገድ ከ30 ላይ 17 ስንቀንስ 13 እናገኛለን
ስለዚህ የ 2013 ዓ.ም መጥቅእ 13 ነው።በሌላ መልኩ ወንበሩን በጥንተ
መጥቅእ ስናባዛው 7×19=133 ይሆናል ይህንን ለ30 ስናካፍለው 4 ጊዜ ደርሶ
13 ይተርፋል።ይህ መጥቅዕ ይባላል። መጥቅዕ 14ን አይነካም ከ14 በላይ
ከዋለ በመስከረም ይውላል።ከ14 በታች ከዋለ በጥቅምት ይውላል።በዚህም
ምሳሌ ዘንድሮ መጥቅእ 13 ከሆነ ከ14 በታች ስለሆነ በጥቅምት ይውላል
ማለት ነው።ስለዚህ የዘንድሮ መጥቅእ ጥቅምት 13 ይውላል።መስከረም 1 ቀን
አርብ ከዋለ ጥቅምት 1 ቀን እሑድ ይውላል።ጥቅምት 8 እሑድ ይውላል።9 ሰኞ
10 ማክሰኞ 11 ረቡእ 12 ሐሙስ 13 አርብ ይውላል።ስለዚህ ጥቅምት 13 ቀን
አርብ ይውላል ማለት ነው።

መባጃ ሐመር
መባጃ ሐመር አጽዋማትና በዓላት መቼ እንደሚውሉ የሚያሳውቀን ሲሆን
የምናገኘውም መጥቅዕ+ መጥቅዕ የዋለበት የእለት ተውሳክ ነው ።ይህም
13+የአርብ ተውሳክ =13+2 ይህም 15 ይመጣል።15 መባጃ ሐመር ነው።
መጥቅዕ በጥቅምት ከዋለ የነነዌ ጾም በየካቲት ትጀምራለች።ይህም የካቲት 15
ቀን 2013 ዓ.ም የነነዌ ጾም ይገባል ማለት ነው።መጥቅዕ በመስከረም ከዋለ
እና መባጃ ሐመሩ ከ30 በታች ከሆነ በጥር ይገባል። ከ30 በላይ ከሆነ ግን ገድፎ
በየካቲት ይውላል።
የእለታት ተውሳክም እንደሚከተለው ነው።
የቅዳሜ ተውሳክ 8
የእሑድ ተውሳክ 7
የሰኞ ተውሳክ 6
የማክሰኞ ተውሳክ 5
የረቡእ ተውሳክ 4
የሐሙስ ተውሳክ 3
የአርብ ተውሳክ 2
ነው።ይህ ከመጥቅእ ጋር መጥቅእ የዋለበት እለት ተደምሮ መባጃ ሐመርን
ለማግኘት ይጠቅመናል።
መጥቅእ በዓላትና አጽዋማት መቼ እንደሚውሉ ሲያሳውቁን አበቅቴ ደግሞ
ሠርቀ ወርኅ እና ሠርቀ ሌሊትን ለማግኘት ይጠቅመናል።

© ሠርቀ መዓልት የሚባለው ራሱ ቀኑ ነው።ለምሳሌ የመስከረም 1 ሠርቀ መዓልት ራሱ 1 ነው።
© ሠርቀ ሌሊት=አበቅቴ+ሠርቀ መዓልት+ሕፀፅ
=17+1+1
=19
© ሠርቀ ወርኅ=ሠርቀ ሌሊት+4
=19+4
=23
ሕጸጽ ያልነው።
የመስከረምና የጥቅምት 1
የህዳርና የታህሳስ 2
የጥር እና የየካቲት 3
የመጋቢት እና የሚያዝያ 4
የግንቦትና የሰኔ 5
የሐምሌና የነሐሴ 6 ነው።
የበዓላትና የአጽዋማት ተውሳክ።መባጃ ሐመር 15 ከሆነ እይኸውም የካቲት 15 ቀን የነነዌ ጾም ትገባለች ማለት ነው።ሌሎቹ
መቼ እንደሚውሉ ለማወቅ ይህን መባጃ ሐመር ከተውሳኮቻቸው ጋር እየደመርን
እናገኘዋለን።የአጽዋማትና የበዓላት ተውሳክ እነሆ
የዐቢይ ጾም ተውሳክ 14
የደብረ ዘይት ተውሳክ 11
የሆሳእና ተውሳክ 2
የስቅለት ተውሳክ 7
የትንሳኤ ተውሳክ 9
የርክበ ካህናት ተውሳክ 3
የዕርገት ተውሳክ 18
የጰራቅሊጦስ ተውሳክ 28
የጾመ ሐዋርያት ተውሳክ 29
የጾመ ድኅነት ተውሳክ 1
ነው።ስለዚህ እኒህን ተውሳኮች ከመባጃ ሐመሩ ጋር እየደመርን በዓላቱ እና አጽዋማቱ መቼ እንደሚውሉ ያሳውቁናል።
ስለዚህ ዐቢይ ጾም=14+መባጃ ሐመር
=14+15
=29 ዓቢይ ጾም የካቲት 29 ይውላል ማለት ነው። መጥቅዕ ጥቅምት ውሎ
በ2013
ዐቢይ ጾም የካቲት 29 ይውላል።
ደብረ ዘይት=11+መባጃ ሐመር
=11+15
=26
መጋቢት 26 ደብረ ዘይት ይውላል ማለት ነው
ሆሣዕና=2+መባጃ ሐመር
=2+15
=17
ሚያዝያ 17 ሆሳእና ይውላል ማለት ነው።
ስቅለት=7+መባጃ ሐመር
=7+15
=22
ሚያዝያ 22 ስቅለት ይውላል ማለት ነው
ትንሳኤ=9+መባጃ ሐመር
=9+15
=24
ሚያዝያ 24 ትንሳኤ ይውላል ማለት ነው።
ርክበ ካህናት=3+መባጃ ሐመር
=3+15
=18
ግንቦት 18 ቀን ርክበ ካህናት ይሆናል ማለት ነው
ዕርገት=18+መባጃ ሐመር
=18+15
=33
33 ከ30 በላይ ስለሆነ በ30 ስንከፍለው አንድ ደርሶ 3 ይተርፋል።ይህም ዕርገት
ሰኔ 3 ይሆናል ማለት ነው።ከ30 በላይ ባይሆን ግንቦት ላይ ይውል ነበር።
ጰራቅሊጦስ=28+መባጃ ሐመር
=28+15
=43
ይህ ከ30 በላይ ስለሆነ በ30 ስናካፍለው 1 ደርሶ 13 ይተርፋል።ስለዚህ
ጰራቅሊጦስ ሰኔ 13 ይውላል ማለት ነው።
ጾመ ሐዋርያት=29+መባጃ ሐመር
=29+15
=44
ይሆናል በ30 ስንገድፈው 1 ጊዜ ደርሶ 14 ይተርፋል።ስለዚህ ሰኔ 14 ጾመ
ሐዋርያት ይገባል ማለት ነው።
ጾመ ድኅነት=1+መባጃ ሐመር
=1+15
=16
ስለዚህ ጾመ ድኅነት ሰኔ 16 ይጀምራል ማለት ነው።
©® ኢየዐርግ እና ኢይወርድ ©®
እነዚህ በዓላት ኢየዐርግ (አይወጣም) ናን ኢይወርድ (አይወርድም) አላቸው
ለምሳሌ የነነዌ ጾም ቢወርድ ቢወርድ ጥር 17 ይሆናል እንጂ ጥር 16
አይሆንም።እንዲሁም ቢወጣ ቢወጣ የካቲት 21 ይሆናል እንጂ የካቲት 22 ሊሆን
አይችልም።ይህ ማለት የነነዌ ጾም ከጥር 17 እስከ የካቲት 21 ባለው ብቻ
ይውላል ማለት ነው


ት እንድታነቡት በጥብቅ ማስገንዘብ እወዳለሁ
ሊቀ ማዕምራን መዓዛ ፈንታሁን
የባሶ ሊበን ወረዳ ቤተ ክህነት
የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ


ደግሞ 1 ሰዓት 2.5
ኬክሮስ ነው ማለት ነው።ስለዚህ ይህንን ካየን ካልዒትን ወደ ሣልሲት እንዲሁም
አንዱን ወደ አንዱ መለወጥ አያቅተንም ማለት ነው።
እንደሚታወቀው ፀሐይ ዓመቱን ሙሉ ብርሃኗን ትሰጣለች።በአንጻሩ ጨረቃ በቀን
በቀን ከፀሐይ 1 ኬክሮስ ከ 52 ካልዒት ከ31 ሣልሲት በአነሰ መጠን
ታበራለች።ይህንን እያንዳንዱን እንመልከተው።
በቀን 1 ኬክሮስ በ30 ቀን 30 ኬክሮስ ይሆናል።በ2 ወር 60 ኬክሮስ
ይሆናል።60 ኬክሮስ ደግሞ 1 እለት ስለሆነ።በ2 ወር 1 እለት በ12 ወር 6 እለት
ይገኛል። 52 ካልዒት 31 ሣልሲት በ12 ወር 5 ቀንና 15 ኬክሮስ ከ1 ሣልሲት
ይሆናል።52 ካልዒት×30 ቀን×12 ወር=18720 ካልዒት ይገኛል።ይህንን ወደ
ኬክሮስ ስንለውጠው 312 ኬክሮስ ይመጣል።በመቀጠል 30 ሣልሲት×30
ቀን×12 ወር 10800 ሣልሲት ይመጣል ይህንን ወደ ኬክሮስ ስንቀይረው 3
ኬክሮስ ይሆናል።ከላይኛው ጋር 312+3=315 ኬክሮስ ይሆናል።ይህንን ወደ
እለት ስንቀይረው 5 ቀን ከ15 ኬክሮስ ይሆናል።
ይህች 5 ቀን ጷግሜን ናት።ከዝያ 15 ኬክሮስ በ4 ዓመት 4×15=60 ኬክሮስ
ወይም አንድ እለት ይሆናል። በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ጳጉሜን 6 የምትሆን
በዚህ ምክንያት ነው።አንዷ ሣልሲት በ600 ዓመት 1 ቀን ትሆናለች።ይኽውም 1
ሣልሲት×30 ቀን×12 ወር×600 ዓመት 216000 ሣልሲት ይገኛል ይህንን ወደ
ኬክሮስ ስንቀይረው 60 ኬክሮስ ይሆናል።60 ኬክሮስ ደግሞ አንድ ቀን ወይም
እለት ነው። ስለዚህም በ600 ዓመት አንድ ጊዜ ጳጉሜን 7 ትሆናለች ማለት ነው።

የዓለም እድሜ ስንት ነው በሚልየን ይቆጠራል ወይስ እንዴት ነው? ለሚለው
ብዙ አስተያየቶች አሉ።እኒህን ከስር መሰረቱ እንመልከት እንግዲህ ይህች ዓለም
የተፈጠረች በእለተ እሑድ ነው።ይህም እሁድ ጥንተ እለት ወይም የእለታት
መጀመሪያ ይባላል።ማክሰኞ ጥንተ ቀመር ይባላል።ረቡዕ ደግሞ ጥንተ ዖን
ይባላል።ዖን ማለት ፀሐይ ማለት ነው።ፀሐይ የተፈጠረች በዕለተ ረቡዕ
ስለሆነ።ጥንተ ዖን ማለት ፀሐይ የተፈጠረችበት የመጀመሪያ እለት እንደማለት
ነው ጥንተ ዖን ማለት።ዓለም የተፈጠረ መጋቢት 29 እሑድ ቀን ነው።ፀሐይ
የተፈጠረች ረቡዕ ስለሆነ ከረቡዕ በፊት ያለው ቀን በፀሐይ አቆጣጠር
ስላልተቆጠረ ምናልባት በሚልየን በቢልየን የሚቆጠር ዘመን ሊሆን ይችላል
ወይም በአንጻሩ በሰከንድ በደቂቃ የሚቆጠር ሊሆን ይችላል የሚሉ አሉ።ነገር
ግን ከረቡዕ በኋላ ያለውን ቀንና ከረቡዕ በፊት ያለውን ቀን ማታም ሆነ ጠዋትም
ሆነ አንድ ቀን እያለ ቀን በማለት ስለሚያስተባብረው ምንም እንኳ ፀሐይ ረቡእ
ብትፈጠርም ከረቡዕ በፊትም ጨለማንና ቀንን የሚለይ ብርሃን ነበረ።ስለዝህ
ተመሳሳይ አቆጣጠር ይኖረዋል።ይህ በእንዲህ እንዳለ። አዳም በእለተ አርብ
ተፈጠረ።ከ40 ቀን በኋላም ወደ ገነት እግዚአብሔር አስገባው።አዳምም
የእግዚአብሔርን ሕግ እየጠበቀ 7 ዓመት ከ3 ወር ከ17 ቀን በገነት
ተቀመጠ።ከዚያ በኋላ አትብላ የተባለውን እጸበለስ ስለበላ ተፈረደበት። አዳምም
ንሥሓ በገባ ጊዜ እግዚአብሔር ከ5500 ዘመን በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ
አድንሀለሁ የሚል ተስፋ ሰጠው።የአዳም ልጆችም ይህን ይዘው ጌታ ሰውን
ለማዳን የሚመጣበትን ጊዜ በፀሐይ በጨረቃ በከዋክብት እየቆጠሩ ይኖሩ
ነበር። የዘመን ቁጥር የተጀመረበት ምክንያቱ ይህ ነው።ጌታም
1.ኛ በ5500 ዘመን በዘመነ ዮሐንስ መጋቢት 29 እሑድ ቀን በ3 ሰዓት
ተፀነሰ
2.ኛ በ5501 ዘመን ወይም በ1 ዓመተ ምሕረት ዘመነ ማቴዎስ ታህሳስ 29
ማክሰኞ መንፈቀ ሌሊት ተወለደ።
3.ኛ 31 ዓመተ ምሕረት ዘመነ ሉቃስ ጥር 11 ማክሰኞ መንፈቀ ሌሊት
ተጠመቀ።
4.ኛ በ33 ዓመተ ምሕረት ዘመነ ማቴዎስ ነሐሴ 13 እሑድ ቀን በቀትር ጊዜ
ብርሃነ መለኮቱን ለሐዋርያት በደብረ ታቦር ገለጠ።
5.ኛ በ34 ዓመተ ምሕረት ዘመነ ማርቆስ መጋቢት 27 አርብ በቀትር ጊዜ ተሰቀለ።
6.ኛ በ34 ዓመተ ምሕረት በዘመነ ማትቆስ መጋቢት
29 እሑድ በመንፈቀ ሌሊት ተነሣ

©©አበቅቴ እና መጥቅእ©©
ከዚህ በኋላ መልአኩ አበቅቴን እና መጥቅእን ለዲሜጥሮስ ገለጸለት።አበቅቴ
ማለት ተረፈ ዘመን ማለት ነው።ይህም ማለት ጨረቃ ከፀሐይ ባነሰ የምታበራበት
የጊዜ መጠን ነው።ፀሐይ በዓመት 365 ቀን ከ15 ኬክሮስ ከ1 ሣልሲት
ታበራለች።ጨረቃ ደግሞ 11 ቀን አንሳ 354 ቀን ታበራለች።በሁለቱ መካከል
ያለው ልዩነት አበቅቴ ይባላል።መልአኩ ለዲሜጥሮስ የገለጸለት አበቅቴ ዓለም
ከተፈጠረ የመጀመሪያውን ዓመት ነው።ስለዝህ 11 ጥንተ አበቅቴ
ይባላል።ሌላው መጥቅዕ ማለት ነጋሪት ደወል ማለት ነው።ደወል ሲመታ ከሩቅ
ያሉት ተሰብስበው መጥተው እንዲገኙ ይህ መጥቅእም አጽዋማትን እና በዓላትን
የሚያስገኝ ስለሆነ ነው።መልአኩ ለዲሜጥሮስ የገለጸለት ጥንተ መጥቅእ 19
ነው።አበቅቴ እና መጥቅእ ሁለቱ ተደምረው ሁልጊዜም 30 ይሆናሉ።
ስለዚህ በመጀመሪያው ዓመት 11 አበቅቴ ከሆነ በሁለተኛው 22 ይሆናል
በሦስተኛው 33 ይሆናል።ከ30 በላይ ሲሆን በ30 አካፍለን ቀሪውን እየያዝን
አበቅቴን እናወጣለን ስለዚህ 3 ይሆናል።ከዚያ በአራተኛው 14 እያለ
ይሄዳል።አበቅቴና መጥቅእ ሁለቱ ተደምረው 30 ስለሚሆኑ አንዱ ከተገኘ
ሌላኛውን ከ30 በመቀነስ እናገኘዋለን።ምሳሌ አበቅቴ 6 ከሆነ መጥቅእ 24
ይሆናል ማለት ነው።

©©ሰባቱ አዕዋዳት®®
1ኛ ዓውደ እለት፦ይህ ከእሑድ እስከ ቅዳሜ ያሉት እለታት ናቸው።ይህም
ማለት ቅዳሜን መልሰን የምናገኘው ከሰባት ቀን በኋላ ነው።
2ኛ ዓውደ ፀሐይ፦በየ 28 ዓመቱ የሚገኝ ሲሆን ይህም ዕለትና ወንጌላዊ
ይገናኙበታል። ይህም ማለት ለምሳሌ ዛሬ ጳጉሜን 3 ማክሰኞ ቀን ዘመነ ዮሐንስ
ተመልሶ ይኸው ቀን ማለትም ጳጉሜን 3 ቀን ዘመነ ዮሐንስ እለተ ሠሉስ/ማክሰኞ
የሚገኘው የዛሬ 28 ዓመት ነው ማለት ነው።
3ኛ ዓውደ ወርኅ፦በፀሐይ 30 ቀን በጨረቃ አንድ ጊዜ 29 አንድ ጊዜ 30
የሚሆነው ነው። ይህም ማለት ለምሳሌ ሐምሌ 29 በዓለ ወልድን ከ30 ቀን በኋላ
ነሐሴ 29 እናገኛታለን ይህ ዓውደ ወርኅ ይባላል።
4ኛ ዓውደ ዓመት፦ይህ በፀሐይ 365.25 ቀን ነው። ይህም ማለት ለምሳሌ
ጳጉሜን 3ን መልሰን የምናገኘው ከ365.25 ቀን በኋላ ነው ማለት ነው።
5ኛ ዓውደ ንኡስ ቀመር ወይም ዓውደ አበቅቴ የሚባለው ደግሞ ከ19
ዓመት በኋላ የሚመላለስ ነው። ይህም ማለት ለምሳሌ ዛሬ ይህን በምታነብበት
ጊዜ ፀሐይም ካለችበት ቦታ ጨረቃም ካለችበት ቦታ በዚያው ቦታ የሚገኙት
ከ19 ዓመት በኋላ ነው። ከዚያ በፊት ግን ፀሐይ ባለችበት ብትገኝ ጨረቃ
ከሌላ ።ጨረቃ ባለችበት ስትገኝ ፀሐይ በሌላ እየሆኑ ይኖራሉ። በየ19 ዓመት ግን
መጀመርያ ከየነበሩበት ይገናኛሉ።
6ኛ ዓውደ ማእከላዊ ቀመር ወይም ዓውደ ማኅተም፦ይህ በየ 76 ዓመቱ
ይከሰታል። በዚህም ለምሳሌ በዘመነ ዮሐንስ ጳጉሜን 3 ቀን ፀሐይ እና ጨረቃ ካሉበት ቦታ መልሰን ማግኘይት ይምንችለው ዘመኑም ዘመነ ዮሐንስ ሆኖ የሚገኘው ከ76 ዓመት
በኋላ ነው። ይህም 4×19=76 ነው
7ኛ ዓውደ ዐቢይ ቀመር፦ ይህ ደግሞ 532 ዓመት ሲሆን በዚህ ወንጌላዊ
እለት እና አበቅቴ ይገናኙበታል።ይህም ማለት ለምሳሌ ጳጉሜን 3 ቀን ማክሰኞ ቀን ዘመነ ዮሐንስ ላይ አሁን ወጥታችሁ ብትመለከቱና ፀሐይም ያለችበትን ቦታ ጨረቃም
ያለችበትን ቦታ የምትይዘው ። ከዛሬ በኋላ እለቱም ምክሰኞ ቀኑ ጳጉሜን 3 ዘመኑ ዘመነ ዮሐንስ ሊሆን የሚችለው ከ532 ዓመት በኋላ ነው።
.....ክፍል ሁለት ይቀጥላል።
ማሳሰቢያ
ለግሩፑ ተከታዮች በሙሉ ይህን ጽሑፍ በትኩረ


የባሕረ ሐሳብ ትምህርት
ክፍል አንድ
ባሕረ ሐሳብ ማለት፤ መርሐ ዕውራን ማለት ነው አ አላዋቂዎችን መርቶ ወደ ዕውቀት የሚያደርስ ስለኾነ፤ ሐሳብ ቊጥር ነው ብፁዓን እለ ተኃድገ ሎሙ ኀጢአቶሙ ወለእለ ኢኃሰበ ሎሙ ኲሎ ጌጋዮሙ እንዲል፤ ባሕረ ሐሳብ አለው ባሕር
እስኪ ለምዱት ድረስ ያስፈራል ይገርማል፤ ከለመዱት በኋላ በልብ ተኝቶ ይውሏል ይኽም
መጽሐፍ እስኪ ለምዱት ድረስ ያስፈራል ይገርማል ከለመዱት በኋላ ብዙ ምስጢር አስታውቆ
ደስ ያሰኛልና፤ አንድም ባሕር ከለመዱት በኋላ ከመሠረቱ ወርዶ አሸዋ ይዞ ይወጧል ይኽም
መጽሐፍ ከለመዱት በኋላ ብዙ ምስጢር ያስታውቃል ያስመርምራል፤ አንድም የባሕር አዟሪቱ
መንገዱ ብዙ ነው የዚኽም መጽሐፍ መንገዱ ስልቱ ብዙ ነውና፤ አንድም ሐሳበ ባሕር
ባሕር ዘመን ነው ሠፈራ ለባሕር በመሥፈርት ወደለዋ ለዓለም በመዳልው መኑ ዘአእመረ ስፍሐ
ሰማይ ወዕመቀ ቀላይ እንዲል በባሕር ውስጥ ያለውን እግዚአብሔር እንጂ ሰው
እንዳያውቀው በዘመንም ኹሉ የሚደረገውን እግዚአብሔር እንጂ ሰው አያውቀውምና፤ ኢኮነ
ለክሙ ታእምሩ መዋዕለ ወአዝማነ ዘሠርዐ አብ እንዲል፡፡
ባሕረ ሀሳብን የአጽዋማትና የበዓላት መውጫ እንዲሆን የደረሰው ቅዱስ ድሜጥሮስ ነው
ዲሜጥሮስ ማለት መጽሔት ማለት ነው፤
አንድም ፀሓይ ማለት ነው
ሰውን በትምህርቱ ብሩህ ያደርጋልና የድሜጥሮስ ትውልዱ ነገዱ ከአዝማደ እስክንድርያ ነው ጥንተ
ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ ያባቱ ወንድም ያጐቱ ሴት ልጅ ነበረችው አባቷ ሲሞት ልጄን ከልጅህ
አትለይብኝ አደራ ብሎት ሞተ፤ አብረው አደጉ አካለ መጠን አደረሱ ዘመኑ መናፍቃን የበዙበት
ነበርና ርሱንም ከሌላ ብናጋባው ርሷንም ለሌላ ብንድራት ከሃይማኖት ይወጣሉ ከምግባር
ይጎድላሉ ሕንጻ ሃይማኖት ከሚፈርስ ሕንጻ ሥጋ ይፍረስ ዕርስ በርሳቸው እናጋባቸው ብለው መከሩ
መክረው አልቀሩም ሠርግ አደረጉ፤ ሥርዓተ ከብካቡ ሲፈጸም ሥርዓተ መርዓዊና ሥርዓተ መርዓት
ያድርሱ ብለው ከጫጉላው ቤት አግብተዋቸው ሄዱ፡፡
❖ ርሷን አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስ አነሣሥቶ ድሜጥሮስ ያንት ወንድምነት ለኔ የኔ እኅትነት
ላንተ አልበቃ ብሎ የባዕድ ሥራ እንሥራ አልህን አለችው፤ እኔስ የናት ያባቴን ፈቃድ
ማፍረስ ይሆንብኛል ብዬ ነው እንጂ ፈቃዴም አይደል ፈቃድሽ ካልሆነ አንተወውምን አላት
እንተወው አለችው፤ እንኪያስ የተለያየን እንደኾነ አንችን ለሌላ ወንድ እኔንም ለሌላ ሴት
ያጋቡናልና መስለን እንኑር አላት እንኑር አለችው፤ በአንድ ቤት በአንድ አልጋ እየተኙ 48
ዘመን ኖሩ፤ ርሱን መልአኩ ቀኝ ክንፉን ርሷን ግራ ክንፉን እያለበሳቸው ያድራል፤ ሲነጋ
በመስኮቱ በአምሳለ ርግብ ወጥቶ ሲሄድ ያዩታል ስለምን ቢሉ በቅተዋልና አንድም
በንጽሕናቸው ይትጉበት ብሎ::
በዘመኑ የተሾመው ሊቀ ጳጳስ ሉክዮስ/ሉክያኖስ ይባላል አረጀ ደከመ፤ ሕዝቡ ተሰብስበው
አባታችን አንተ አረጀህ ደከምህ ካንተ ቀጥሎ የሚሾመውን ንገረን አሉት፤ እናንተም ወደ
እግዚአብሔር አመልክቱ እኔም ወደ እግዚአብሔር አመለክታለሁ ብሎ ቀን ቀጥሮ ሰደዳቸው
ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጣ ስሙ ድሜጥሮስ የሚባል ያለጊዜዋ ያፈራች የወይን
ዘለላ ይዞ ካንተ ሊባረክ ይመጣል ካንተ ቀጥሎ የሚሾመው ዕርሱ ነው አለው፤ ሕዝቡም
በቀጠራቸው ቀን መጡ አገኛችኹት አላቸው እኛስ አላገኘንም አሉት እኔ አገኘሁላችሁ
አላቸው፤ ስሙ ድሜጥሮስ የሚባል ያለጊዜዋ ያፈራች የወይን ዘለላ ይዞ ሊባረክ ይመጣል ከኔ
ቀጥሎ የሚሾመው እርሱ ነው ለጊዜው እንቢ ይላችኋል ግድ ብላችሁ ሹሙት አላቸው፡፡
ይኸም ድሜጥሮስ ተክል አጽድቆ ዕርፍ አርቆ የሚኖር ገበሬ ነበር ይላሉ፤ ከዕለታት በአንድ
ቀን ተክል ለመጎብኘት ከተክል ቦታ ገብቶ ሳለ ያለጊዜዋ ያፈራች የወይን ዘለላ አገኘ ይህንስ
ከሊቀ ጳጳሱ ወስዶ ሊባረኩበት ይገባል ብሎ በንጹሕ ዕቃ አድርጎ ይዞ ሄዶ ንገሩልኝ አለ፤
እንዲህ ያል ይዞ የመጣ ሰው ከደጅ ቁሟል ብለው ነገሩት እንዲህ ያል ይዞ የመጣውን ከደጅ
ያቆሙታልን ያገቡታልን እንጂ ግባ በለው አለው፤ ገብቶ ተባርኳል፤ ከኔ ቀጥሎ የሚሾመው
ይህ ነው ብሏቸው ወዲያው ዐረፈ፤ ቀብረው ሲመለሱ ሕዝቡ ተሾምልን አሉት በማርቆስ
ወንበር የሚቀመጥ የተማረ ነው ደግሞም ንጹሕ ድንግል ነው፤ እኔ እንደምታውቁኝ ሕዝባዊ
ነኝ ደግሞም ሥጋዊ ነኝ እንደምን አድርጎ ይሆናል አላቸው፤ እኛስ አባታችን ያዘዘንን ትተን ሌላ
አንሾምም አሉት፤ ርሱም እንደማይተውት ዐውቆ ሊቀ ጳጳሱ ሲሾም ምን ያደርግላችሁ ነበር
አላቸው አንቀጸ አባግዕን አንብቦ ይተረጒምልን ነበር አሉት ወንጌል አምጡልኝ አለ፤
አመጡለት እንኳን ትርጓሜውን ንባቡን አያውቀው የነበረ መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት
ተርጒሞላቸዋል፤ ይህም ብቻ አይደለም ብሉይና ሐዲስ ተርጒሟል፡፡
ከዚህ በኋላ ከደጀ ሰላም ቆሞ አንተ በቅተሃል ተቀበል አንተ አልበቃህም ቆይ እያለ
ከልክሏቸዋል፤ ሕዝቡም ቆንጆ ሚስቱን ከቤቱ አስቀምጦ እኛን ይከለክለናል ብለው
አምተውታል፤ መልአኩም ኢትፍቅድ አድኅኖ ርእስከ ወብእሲትከ አላ አድኅኖ ሕዝብከ አለው፤
እርሱም ዕንጨት እየያዛችሁ ተሰብሰቡ ብሎ ዐዋጅ ነገረ ምእመናኑም ዕንጨት እየያዙ
ተሰበሰቡ ደመራ አሠርቶ በእሳት አቃጥሎ ልብሰ ተክህኖውን ለብሶ ሊቀድስ ገባ ጸሎተ
ቅዳሴውን ፈጽሞ ልብሰ ተክህኖውን እንደለበሰ በእሳቱ መካከል እየተመላለሰ ያጥን ጀመር፤
ሚስቱም ከዚያ ነበረችና ስፍሒ አጽፈኪ ልብስሽን ዘርጊ አላት ዘረጋች እሳቱን እየታፈነ ከልብሷ
ላይ አደረገላት ልብሷ ሳይቃጠል ቀርቷል ሕዝቡም አባታችን ይህን ተአምራት ያደረግኸው
ስለምን ነው አሉት፤ አምታችሁኝ አላቸው፤ አላበጀንም በድለናል ይቅር በለን አሉት፤ ይፍታሕ
ወይኅድግ ያንጽሕ ወይስረይ ብሎ ናዟቸዋል፤ ኑዛዜ ከዚያ ወዲኽ ተጀምሯል፡፡ ዲሜጥሮስም 11ኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ሁኖ ተሹሟል።
ታሪክ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ ሳይውል ሳያድር ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዶ 40 ቀን ጾመ።
ይህም ማለት ጥር11 ተጠምቆ
ጥር 12 ጀምሮ እስከ የካቲት 21 ድረስ ጾመ ይህን ጾም ጌታ የጾመው በመሆኑ ዐቢይ ጾም ወይም ጾመ ኢየሱስ እንለዋለን።
ከሐዋርያት ጀምረው እስከ 241 ዓመተ ምሕረት ድረስ አካባቢ ምእመናን ዐቢይ ጾምን ጥር
12 ጀምረው የካቲት 21 ድረስ ይጾሙና።እንደገና ሰሙነ ሕማማትን ከመጋቢት
22 እስከ መጋቢት 27 ይጾሙ ነበረ።ትንሳኤንም ሰኞም ይሁን ማክሰኞም ይሁን
ብቻ መጋቢት 29 ቀን በዋለበት ቀን ያከብሩ ነበር።ሐዋርያት ግን በድድስቅሊይ
የትንሳኤ በዓል እሑድን መልቀቅ የለበትም ብለው ስርዓት ሰርተው ስለነበር
ቅዱስ ድሜጥሮስ የነነዌ ጾም የዐቢይ ጾም እና ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ።ደብረ
ዘይት ሆሳእና ትንሳኤ ጰራቅሊጦስ ከእሁድ።ስቅለት ከአርብ።ዕርገት
ከሐሙስ።ርክበ ካህናት፥ጾመ ድኅነት ከረቡዕ ባይወጡ በወደድኩ ነበር።ብሎ
ተመኘ።መልአኩም መጥቶ ባሕረ ሀሳብን ገለጸለት።

በመሆኑም ቤተክርስቲያን ከሰከንድም ከማይክሮ ሰከንድም እጅግ በጣም የረቀቀ የዘመን
የጊዜ መለኪያ አላት
1ኛ ሳድሲት ይህ ቁጥር 0.00000185 ሰከንድ ነው።አስበውማ ከሰከንድ
እጅግ ያነሰ መለኪያ ነው።
2ኛ ኀምሲት ይህ ቁጥር 0.00011 ሰከንድ ነው።
3ኛ ራብዒት ይህ ደግሞ 0.0067 ሰከንድ ነው።
4ኛ ሣልሲት ይህ ደግሞ 0.4 ሰከንድ ነው።
5ኛ ካልዒት ይህ ደግሞ 24 ሰከንድ ነው
6ኛ ኬክሮስ ይህ ደግሞ 24 ደቂቃ ነው።

በሌላ አገላለጽ
60 ሳድሲት=1 ኃምሲት
60 ኃምሲት=1 ራብዒት
60 ራብዒት=1 ሣልሲት
60 ሣልሲት=1 ካልዒት
60 ካልዒት=1 ኬክሮስ
60 ኬክሮስ=1 ዕለት ወይም 24 ሰዓት ነው። ይህ ማለት


የግዕዝ ትምህርት
ፈተና/2 መልስ
1,ከሚከተሉት መካክል ሰያፍ የሆነነ ----ነው
ሀ፡ገብርኤል √
ለ፡ሶልያና
ሐ፡ሚካኤል
2,ተናባቢ የሆነው የቱ ነው?
ሀ፡ኢሳይያስ
ለ፡መድኃኔ ዓለም √
ሐ፡ሙሴ
3,ወዳቂ የሆነው የንባብ ዓይነት የቱ ነው?
ሀ፡አብ
ለ፡ ወልድ
ሐ፡ ሥላሴ √
መ፡ሁሉም
4,ከሚከተሉት ጠብቆ የሚነበብ ማን ነው?
ሀ፡ ቀደሰ √
ለ፡ ቀተለ
ሐ፡ ተንበለ
5,ሲጠብቅናሲላላ 2 ትርጉም ያላው ማን ነው?
ሀ፡ ንጉሥ
ለ፡ መካን √
ሐ፡ ቅዳሴ
6,-----ከተነሽ የንባብ ዓይነት ይመደባል።
ሀ፡ ጸዋሚ
ለ፡ ጾም
ሐ፡ጾመ √
7, እፎ ወአልኪ-------?
ሀ፡እምየ √
ለ፡ አቡየ
ሐ፡ እኁየ
8,----- ሆረ ኀበ ቤተ ክርስቲያን።
ሀ፡ ንህነ
ለ፡ ውእቱ √
ሐ፡ አንተ
9,ዋና ዋና/ዓበይት የንባብ አይነቶችን ጻፍ/ጻፊ
1,ተነሽ 2, ተጣይ 3,ሰያፍ 4, ወዳቂ ናቸው
10,ከንዑሳን ንባባት መካከል 2ቱን ጻፍ/ጻፊ
1.ተናባቢ 2,ማጥበቅ 3,ማላላት 4,መቁጠር 5,መዋጥ 6,መጠቅለል ናቸው
ቦነስ
11, ከአስሩ መራህያን 5ቱን ጻፍ/ጻፊ
አነ፡አንተ፡አንቲ፡ውእቱ፡ይዕቲ፡ንህነ፡አንትሙ፡አንትን፡ውእቶሙ፡ ውእቶን ናቸው
ማሳሰቢያ
ለግሩፑ አባላት ሁላችሁም ትምህርቱን እና ፈተናውን በትኩረት የማትከታተሉ ከሆነ ትምህርቱን ለማቋረጥ የምገደድ መሆኔን በጥብቅ ማስገንዘብ እወዳለሁ !!!
ሊቀ ማዕምራን መዓዛ ፈንታሁን
የባሶ ሊበን ወረዳ ቤተ ክህነት
የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ
የጁቤ


የፈተናው ማጠናቀቂያ ሰዓት ወደ አርብ 7፡30 ስለተራዘመ ሁላችሁም እንድሠሩት በጥብቅ አሳስባለሁ


የግዕዝ ትምህርት
ፈተና/2 ምርጫ
1,ከሚከተሉት መካክል ሰያፍ የሆነ ----ነው
ሀ፡ገብርኤል ለ፡ሶልያና ሐ፡ሚካኤል
2,ተናባቢ የሆነው የቱ ነው?
ሀ፡ኢሳይያስ ለ፡መድኃኔ ዓለም ሐ፡ሙሴ
3,ወዳቂ የሆነው የንባብ ዓይነት የቱ ነው?
ሀ፡አብ ለ፡ ወልድ ሐ፡ ሥላሴ መ፡ሁሉም
4,ከሚከተሉት ጠብቆ የሚነበብ ማን ነው?
ሀ፡ ቀደሰ ለ፡ ቀተለ ሐ፡ ተንበለ
5,ሲጠብቅና ሲላላ 2 ትርጉም ያላው ማን ነው?
ሀ፡ ንጉሥ ለ፡ መካን ሐ፡ ቅዳሴ
6,-----ከተነሽ የንባብ ዓይነት ይመደባል።
ሀ፡ ጸዋሚ ለ፡ ጾም ሐ፡ ጾመ
7, እፎ ወአልኪ-------?
ሀ፡እምየ ለ፡ አቡየ ሐ፡ እኁየ
8,----- ሖረ ኀበ ቤተ ክርስቲያን።
ሀ፡ ንህነ ለ፡ ውእቱ ሐ፡ አንተ
9,ዋና ዋና/ዓበይት የንባብ አይነቶችን ጻፍ/ጻፊ
10,ከንዑሳን ንባባት መካከል 2ቱን ጻፍ/ጻፊ
1.-------------------------2.--------------------
ቦነስ
11, ከአስሩ መራህያን 5ቱን ተከተል ጻፍ/ጻፊ




መምህር ማዕዛ:
ውድ የዚህ ግሩፕ የግዕዝ ት/ት ተከታታዮች ነገ ሐሙስ በ7፡30 የግዕዝ ፈተና የምትፈተኑ መሆኑን ከወዲሁ እየገለጽሁ ሁላችሁም ወደ ኋላ የተለቀቁትን ጽሑፎች በትኩረት እንድታነቡ ማሳሰብ እወዳለሁ።

ሊቀ ማዕምራን መዓዛ ፈንታሁን
የባሶ ሊበን ወረዳ ቤተ ክህነት
ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ
የጁቤ


ትምህርተ ሃይማኖት
ክፍል 5
❖ ሥነ ፍጥረት
ልዑል እግዚአብሔር በእውቀቱ ሰማይን ምድርን እንዲሁም በእነርሱ ውስጥ የሚገኙትን ሁሉ ከምንም ወይም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ብቁና ንቁ የሆኑ ሥነ ፍጥረታትን የፈጠረበትን ሁኔታና ሥርዓት የምንማርበት ትምህርት ሥነ ፍጥረት ይባላል፡፡
❖ ሥነ ፍጥረት ማለት፡- የፍጥረታት መበጀት/መሠራት ማለት ነው፡፡ይህ የሚታየው ዓለምና በውስጡ ያለው ሁሉ ከዚህ ከሚታየው ዓለም ውጭም ያለው የማይታይ ዓለምና በውስጡ ያሉት ረቂቃን ፍጥረታት ሁሉ በእግዚአብሔር ተፈጥረዋል። / ዘፍ1:1 መዝ 101:25 ኢሳ 66:1-2 ዕብ 11:3/
❖እግዚአብሔር ግዙፉንና ረቂቁን ዓለም የፈጠረው ከምንም ተነስቶ የሚያገናኛቸውና የሚያዋሕዳቸው ነገር ሳይኖረው /እም ኀበ አልቦ ኀበ ቦ / ካለ መኖር ወደ መኖር ነው፡፡
/መዝ 32:9 2ኛመቃ 14:10 ጥበብ11:18 የሐዋ ሥራ 17:24 መዝ 148:5/::
❖ እግዚአብሔር ፍጥረታትን የፈጠረው ሰውንና መላእክትን ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ ሲሆን ሌሎችን ፍጥረታት ደግሞ ለአንክሮ ለተዘክሮ ለምግበ ሥጋና ለምግበ ነፍስ ነው/መዝ 148:1-13 ራዕ ይ4:11 ሮሜ 1:20/::
❖ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ሁሉ ፈጥሮ ያከናወነው በስድስት ቀናት ውስጥ ነው፡፡/ዘፍ 1 እና 2 ዘፍ 20:9-11/
በነዚህ ቀናት የተፈጠሩት ፍጥረታት እያንዳንዳቸው ቢቆጠሩ ፍጡር ተናግሮ አይፈጽማቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን በባህርያቸውና በአኗኗራቸው በ22 ይመደባሉ፡፡ኩፋሌ 3:9
የተፈጠሩትም በ3 መንገድ ነው ይኸውም፡-
1 በአርምሞ/በዝምታ/:- አራቱ ባሕርያተ ሥጋ ጨለማ፡መላእክት ሰማያት
2 በነቢብ/በመናገር/:- ብርሃን ጠፈር ፡እንስሳት፡ ዕፅዋት፡፡
3 በገቢር /በመስራት/:- ሰውን ብቻ፡፡
❖ የስድስቱ ቀናት ፍጥረታት
እግዚአብሔር በመጀመርያ ቀን 8 ፍጥረታትን እም ኀበ አልቦ ኀበ ቦ አምጥቶ የፈጠረ ሲሆን እነርሱም፡-
1,እሳት
2,ነፋስ
3,ውኃ
4,አፈር/መሬት/
5,ጨለማ
6,ሰማያት
7,መላእክት
8,ብርሃን ናቸው፡፡ /ዘፍ1:1/ እሳት፡ነፋስ ውኃና መሬት አራቱ ባሕርያተ ሥጋ ይባላሉ፡፡
ሰማያት ሰባት ናቸው፡፡/መዝ 18: 1 ማቴ 3:17 2ኛቆሮ 12:3 ዮሐ14:2 ዕዝ ሱቱኤል 4:4/።
ማሳሰቢያ
ለአንባብያን በትኩረት እንድትከታተሉት እና ከቻላችሁ ባላችሁበት ቦታ በማስታወሻ ማለትም በኖት ቡክ ኮፒ እያደረጋችሁ እንድታነቡ በጥብቅ ማስገንዘብ እወዳለሁ
ሊቀ ማዕምራን መዓዛ ፈንታሁን
የባሶ ሊበን ወረዳ ቤተ ክህነት
የስብከተ ወንጌል ልፍል ኃላፊ
የጁቤ


ማሳሰቢያ ለግሩፑ ተከታዮች በሙሉ
ዛሬ ከምሽቱ 2፥00 ላይ ትምህርተ ሃይማኖት ክፍል 5 ስለ ሚለቀቅ ሁላችሁም online ሁናችሁ እንድትጠብቁ በጥብቅ አሳስባለሁ።
ሊቀ ማዕምራን መዓዛ ፈንታሁን
የባሶ ሊበን ወረዳ ቤተ ክህነት
የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ


...ንዑሳን ንባባት ከሚለው የቀጠለ...
​2,ማጥበቅ
ከንዑሳን ንባባት መካከል ሁለተኛው ንዑስ ንባብ ማጥበቅ ይባላል፡፡
ይህ የንባብ አይነት በግሱ መካከል የሚገኙትን ቃላት ጠበቅ አድርገን የምናነብበት የንባብ ዓይነት ነው።

# ጠብቀው የሚነበቡ ግሶች ምሳሌ ፡-
ግስ = ትርጉም = የሚጠብቀው ፊደል
ቀደሰ = አመሰገነ = "ደ" ጠብቆ ይነበባል
ዘመረ = ዘመረ = "መ" ጠብቆ ይነበባል
ነጸረ = ዓየ = "ጸ" ጠብቆ ይነበባል
ፈነወ = ላከ = "ነ" ጠብቆ ይነበባል
ለበወ = ልበኛ ሆነ = "በ" ጠብቆ ይነበባል
ሐወጸ = ጎበኘ = "ወ" ጠብቆ ይነበባል
መ'ነ'ነ = ናቀ = "ነ" ጠብቆ ይነበባል
ወደሰ = አመሰገነ = "ደ" ጠብቆ ይነበባል
ተዘከረ = አሰበ = "ከ" ጠብቆ ይነበባል
ተዐገሠ=ትዕግስተኛ ሆነ="ገ" ጠብቆ ይነበባል
ጸውዐ = ጠራ = "ው" ጠብቆ ይነበባል
ጸለየ = ለመነ = "ለ" ጠብቆ ይነበባል
ከላይ ያየናቸውን የመመሳሰሉት ሁሉ ጠብቀው ይነበባቡ በተለይ የቀደሰ ቤት ግሶች ለሚጠብቁት እንደ ማስረጃ ሊሆኑ ይችላሉ።

3,ማላላት
ከንዑሳን ንባባት መካከል ሦስተኛው ንዑስ ንባብ ማላላት ይባላል፡፡
ይህ የንባብ አይነት በግሱ መካከል የሚገኙትን ቃላት ላላ አድርገን የምናነብበት መንገድ ሲሆን የማጥበቅ ተቃራኒ የሆነ የንባብ ዓይነት ነው።
# ላልተው የሚነበቡ ግሶች ምሳሌ ፡-
ግስ = ትርጉም = የሚላላ ፊደል
ቀተለ = ገደለ = "ተ" ላልቶ ይነበባል
ሰረቀ = ሰረቀ = "ረ" ላልቶ ይነበባል
ተለወ =ተከተለ = "ለ" ላልቶ ይነበባል
ፈቀደ = ፈቀደ = "ቀ" ላልቶ ይነበባል
ሐቀፈ= አቀፈ = "ቀ" ላልቶ ይነበባል
ነበረ =ተቀመጠ= "በ" ላልቶ ይነበባል
ወለደ= ወለደ = "ለ" ላልቶ ይነበባል
ወረደ= ወረደ = "ረ" ላልቶ ይነበባል
ወሀበ= ሰጠ = "ሀ" ላልቶ ይነበባል
ሰከበ = ተኛ = "ከ" ላልቶ ይነበባል
መጽአ= መጣ = "ጽ" ላልቶ ይነበባል
ፈተወ = ወደደ = "ተ" ላልቶ ይነበባል
ተከለ= ተከለ = "ከ" ላልቶ ይነበባል
ከላይ ያየናቸውን የመመሳሰሉት ሁሉ ላልተው ይነበባቡ በተለይ የቀተለ ቤት ግሶች ላልተው ለሚነበቡት እንደ ማስረጃ ሊሆኑ ይችላሉ።

#በግእዝ ቋንቋ ውስጥ አንድ ቃል ሲጠብቅና ሲላላ የተለያየ ትርጉም ሊኖረው ይችላል፡፡
ምሳሌ ፡ -
√ሰበከ ("ከ"ሲጠብቅ) ➜ አስተማርህ
√ ሰበከ ("ከ" ሲላላ) ➜ አስተማረ
√መካን ("ካ" ሲጠብቅ) ➜ የማትወልድ ሴት
√መካን ("ካ" ሲለላ) ➜ ቦታ
√አጥመቀ ("ቀ"ሲጠብቅ) ➜ አጠመቅህ
√አጥመቀ ("ቀ" ሲላላ) ➜ አጠመቀ ይላል

ማሳሰቢያ
ለአንባብያን በትኩረት እንድትከታተሉት እና ከቻላችሁ ባላችሁበት ቦታ በማስታወሻ ማለትም በኖት ቡክ ኮፒ እያደረጋችሁ እንድታነቡ በጥብቅ ማስገንዘብ እወዳለሁ
ሊቀ ማዕምራን መዓዛ ፈንታሁን
የባሶ ሊበን ወረዳ ቤተ ክህነት
የስብከተ ወንጌል ልፍል ኃላፊ
የጁቤ


1,ተናባቢ
ከንዑሳን ንባባት መካከል የመጀመሪያው ንዑስ ንባብ ተናባቢ ይባላል፡፡
ይህ የንባብ አይነት የተለያዩ ቃላትን በማጣመር የሚነበብ የንባባብ ዓይነት ሲሆን ተናባቢ መሆን የሚችሉት የመሻው ቃል የመጨረሻ ፊደል፡-
ሣልስ
ራብዕ
ሐምስ
ሳድስና
ሳብዕ ሲሆን ብቻ ነው
በምሳሌ እንመልከታቸው
በሣልስ
ብእሲ = ብእሴ-እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ሰው)
ወሃቢ= ወሃቤ-ሰላም (ሰላምን የሚሰጥ)
ፈጣሪ= ፈጣሬ-ዓለማት( ዓለምን የሠራ)
በላዒ= በላዔ-ሰብ (ስምዖን)
በራብዕ
ዜና = ዜና-አበው (የአማቶች የምሥራች)
ደመና= ደመና-ሰማይ (የሰማይ ደመና)
ሰረገላ=ሰረገላ-አሚናዳብ(የአሚናዳብ ሰረገላ)
በሐምስ
ዝማሬ= ዝማሬ-መላእክት(የመላእክት ዝማሬ)
ውዳሴ= ውዳሴ-ማርያም(የማርያም ምስጋና)
ቅዳሴ = ቅዳሴ-እግዚእ(የጌታ ምስጋና)
በሳድስ
መሠረት=መሠረተ-ሕይወት( የሕይወት መሠረት)
መንግሥት=መንግሥተ-ሰማያት
ገነት=ገነተ-ትፍስሕት(የደስታ ገነት)
ቤት=ቤተ-ክርስቲያን
ሊቀ=ሊቀ-ካህናት (የካህናት አለቃ)
ገብር=ገብረ-ሥላሴ(የሥላሴ አገልጋይ)
ወለት=ወለተ-ማርያም(የማርያም ወዳጅ)
በሳብዕ
መሰንቆ=መሰንቆ-ዳዊት(የዳዊት መሰንቆ)
አዕምሮ=አዕምሮ-መጻሕፍት(መጻሕፍትን ማወቅ)
ጸልዮ=ጸልዮ-ጸሎት( ጸሎት መጸለይ) ይላል።
ማሳሰቢያ
ለአንባብያን በትኩረት እንድትከታተሉት እና ከቻላችሁ ባላችሁበት ቦታ በማስታወሻ ማለትም በኖት ቡክ ኮፒ እያደረጋችሁ እንድታነቡ በጥብቅ ማስገንዘብ እወዳለሁ
ሊቀ ማዕምራን መዓዛ ፈንታሁን
የባሶ ሊበን ወረዳ ቤተ ክህነት
የስብከተ ወንጌል ልፍል ኃላፊ
የጁቤ


ሰላም ለኪ


​ የግዕዝ ት/ት
ክፍል ሃያ ሁለት
ንዑሳን የንባብ አይነቶች 6 ናቸው።
እነርሱም፡ -

1,ተናባቢ

2,ጠብቆ የሚነብብ

3,ላልቶ የሚነበብ

4,መቁጠር

5,መዋጥ

6,መጠቅለል

ናቸው ዝርዝራቸው ይቀጥላል።
💚💛❤️በሊቀ ማዕምራን መዓዛ ፈንታሁን💚💛❤️


ትምህርተ ሃይማኖት
ክፍል 4
የእግዚአብሔር የባህርይ ቅጽል ስሞች
በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እግዚአብሔር መኖር በብዛት ከመጻፍም በላይ ስለ እርሱ የተሰጡ ባሕርዩን የሚገልጡ ቅጽል ስሞች አሉት፡፡እነሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ቅዱስ፡-
እግዚአብሔር በባህርዩ ቅዱስ ነው፡፡እርሱ ራሱ (እኔ ቅዱስ እንደሆንሁ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ፡፡) ሲል ተናግሯል፡፡ዘሌ 19፥2 1ኛ ጴጥ 1፥16 ኢሳ 6፥3 ሉቃ 1፥35
2.ጻድቅ፡- ማለት እውነተኛ ማለት ነው
እግዚአብሔር በሁሉ እውነተኛ ነው፡፡በእውነተኛነቱ ለሁሉ በትክክል ይፈርዳል፡፡1ኛ ሳሙ 2፥2 2ኛጢሞ4፥8 መዝ 114፡5 መዝ11:7 ዮሐንስ አቡቀለምሲስም
/በራዕዩ 16:7/ አዎን አቤቱ ሁሉን የምትገዛ እግዚአብሔር ሆይ ፍርድህ እውነትና ቅንነት ነው ብሏል፡፡
3. አኃዜ ኩሉ፡- /ሁሉን ያዥ/
ሰው እንቁላልን በመዳፉ እንደሚይዝ እግዚአብሔር አለምን በመዳፉ የያዘ የሁሉ ገዥ ሁሉን የሚያውቅ ሁሉን የሚችል በሁሉ ቦታ የሚኖር አምላክ ነው፡፡ሐዋርያት አመክንዮ በተባለው ቀኖና ሃይማኖት
(አእመርናሁ በኦሪት ወበነቢያት ከመ ውእቱ አኃዜ ኩሉ ወሥሉጥ ላዕለ ኩሉ ፍጥረት ) ብለዋል፡፡
4. አምላከ አማልክት ፡/የአማልክት አምላክ/ እግዚአብሔር አምላክነቱ የባሕርዩ ነው፡፡የሰዎች አማልክት መባል ግን የጸጋ ነው፡፡የጸጋ አማልክት የሚባሉትም የእግዚአብሔርን ቃል ለህዝቡ የሚያስተምሩ መምህራን ካህናት ናቸው እንጂ ጣዖታት አይደለም፡፡መዝ 81:6 ዮሐ 10፥34-36
5. እግዚአ አጋእዝት፡-የጌቶች ጌታ ፡
እግዚአብሔር ጌትነቱ የባሕርዩ ነው የሰዎች ጌቶች መባል ግን የጸጋ ነው፡፡ጌቶች የሚባሉትም መምህራን ናቸው፡፡
ስለ እግዚአብሔር የባህርይ ጌትነት ነብዩ ዳዊት (እግዚአብሔር እግዚእ አስተርአየ ለነ)ይላል፡፡ መዝ117፥27 ዮሐ20፥28 1ኛጢሞ 6፥15 ዕብ 13፥17
6. ኤልሻዳይ፡- ሁሉን ቻይ
ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር ፈጽሞ የለም ሁሉን ማድረግ ይቻላል እግዚአብሔረ ራሱ ለአብርሃም (ሁሉን ቻይ ነኝ፡፡)/ኤልሻዳይ/ነኝ ብሎ ገልጦለታል/ዘፍ17፥1 , 18፥14 ሉቃ 1፥13 ኢሳ 40፥26 ዳን 4፥35 ኢዮ42፥2
7 ንጉሠ ነገሥት፡- የነገሥታት ንጉሥ፡ እግዚአብሔር ንጉሥነቱ /መንግስቱ/ የባህርዩ ነው የሰዎች ነገሥታት መባል ግን የጸጋ ነው፡፡ዳን 4፥3 መዝ 23፥7 ኢሳ 9፥7
8. በሁሉ ቦታ ምሉዕ፡-
እግዚአብሔር በዚህ አለ በዚህ የለም የማይባል በመለኮታዊ ሥልጣኑ ምሉዕ ሰፉህ ነው፡፡እግዚአብሔር በሚታየውም በማይታየውም ዓለም አለ ቅዱስ ዳዊት /ከመንፈስህ ወዴት እሔዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ?/ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ ነህ ወደ ሲዖልም ብወረድ በዚያ አለህ እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ እስከ ባህር መጨረሻ ብበር በዚያ እጂህ ትመራለች ቀኝህም ትይዘናለች ብሏል፡፡መዝ138፥1-10 1ኛነገ 8፥27 2ኛ ዜ ና6፥18 ኢሳ 66፥1
9. ሁሉን አዋቂ፡-
እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ከመሆኑ በፊት ያውቃል። ነገሮችን ሁሉ ከመታሰባቸው ከመመሥረታቸው በፊት ያውቃቸዋል።
መዝ 138፥1-5 ዮሐ 2፥25 ኤር 17፥10 1ኛ ቆሮ 2፥11 ሕዝ 11፥5 1ኛ ሳሙ 16፥6
10. አልፋ ወዖ፡- ዘለዓለማዊ
እግዚአብሔር ከዘመን በፊት ነበር ዘመናትንም አሳልፎ የሚኖር ነው መዝ 89፥1
በአጠቃላይ እግዚአብሔር መጀመሪያ እና መጨረሻ የለውም ራሱ አነ ውእቱ አልፋ ወዖ
ቀዳማዊና ደኃራዊ እኔ ነኝ ራዕ 22፥13
አንተሰ አንተ ክመ አንተ ግን አንተ ነህ ወአመቲከኒ ዘኢየሀልቅ መዝ 101፥27
ማሳሰቢያ
ለመደበኛ ኮርስ ተማሪዎች ነገ ማክሰኞ የሚሰጠው ትምህርት ይህ ስለ ሆነ ኖት ጽፋችሁ እና አንባችሁ እንድትመጡ በጥብቅ ማስገንዘብ እወዳለሁ
ሊቀ ማዕምራን መዓዛ ፈንታሁን
የባሶ ሊበን ወረዳ ቤተ ክህነት
የስብከተ ወንጌል ልፍል ኃላፊ
የጁቤ


ትምህርተ ሃይማኖት
ክፍል 3
ሀልወተ እግዚአብሔር/ የእግዚአብሔር አኗኗር
ሃይማኖት ያላቸው ፍጥረታት ሰው እና
መላእክት ብቻ ሲሆኑ እነርሱም ስሙን ለመቀደስ እና ክብሩን ለመውረስ ተፈጥረዋል። ስለዚህ የእግዚአብሔርን መኖር በምን እናውቃለን???
# የፈጣሪን መኖር የሚያስረዱን የሚከተሉት ናቸው ።
1ኛ ሥነ ፍጥረት
ሕንጻ ካለ አናጺ ፣ስዕል ካለ ሰዓሊ ፣ፍጡር ካለ ፈጣሪ አለ ።
ያለ ሰዓሊ ስዕል ፣ያለ አናጺ ሕንጻ ፣ያፈጣሪ ፍጡር አይኖርም ።ስለዚህ ፈጣሪ
አለ? ብለን ከምንጠይቅ ፍጡር አለ?ብለን ብንጠይቅ ይቀላል ፍጡር ካለ
ፈጣሪም አለ ማለት ነው ፍጡር መኖሩን ለማወቅ ደግሞ ፊደል መቁጠር
አይጠይቅም ።
ሌላው ሥነ ፍጥረትን ብንመለከት ብዙ የሚነግሩን ነገር አለ ።
ለምሳሌ ፦አራዊት በሌሊት ፣ሰው በቀን እንዲሰለጥን ሰው እና አራዊት በዚህ
ጉዳይ ላይ አልተፈራረሙም ግን ይኸንን ሥርዓት ጠብቀው ለዘለዓም ይኖራሉ ።
መጽ ምሳ 30 ፥27 ይላል ።
በተጨማሪም ፦ሰው እና እፅዋት ምንም ሳይፈራረሙ በመለኮታዊ ቃል ኪዳን
ብቻ የሰውን የተቃጠለ አየር እፅዋት ይወስዳሉ ፣ የእፅዋትን ደግሞ የሰው ልጅ
ይወስዳል ።
እንዲያውም ይህንን ሰጥቶ የመቀበል ሕግ እምቢ ብሎ የሚያምጽ እንዳይኖር
እግዚያብሔር በአምላካዊ ጥበቡ የሕይወት ጉዳይ አድርጎታል ።አንድ ሰው
የእኔን ለእፅዋት አልሠጥም ፣የእፅዋትንም መቀበል አልፈልግም ቢል በራሱ ላይ
የግድያ ሙከራ እያደረገ (እያመፀ )ነው ማለት ነው ።
ስለዚህ ይህንን ሁሉ የፈጠረ ፣ የሚያስተዳድር አንድ አምላክ (ፈጣሪ) እንዳለ
ግልፅ ነው ።የማይታየው እግዚያብሔር በሥራው ይታያል ።እሱ አይታይም
ጨለማን እና ብርሃንን ሲያፈራርቅ ግን በሥራው አይተነዋል ።
ስለዚህ ፍጥረታት የፈጣሪን መኖር ያስተምሩናል መዝ 18 ፥1

2ኛ መጽሐፍ ቅዱስ
ቅዱሱ መጽሐፍ ሥራውን የሚጀምረው የፈጣሪን መኖር በማስረዳት ነው። ዘፍ 1፥1

3ኛ የኅሊና ምሥክርነት ነው
ኅሊና ማለት ፦ነፋስ ምርቱን ከገለባ እንደሚለይ የሚጠቅም እና የሚጎዳውን
የምንለይበት በተፈጥሮ የተሰጠን ታላቅ ፀጋ ነው ።
ለምሳሌ አንድ ህጻን እንደተወለደ ከእናቱ ጋር በቋንቋ አይግባባም ።
የጡትን ጥቅም ማንም ሳይነግረው ይጠባል እንደተወለደ ማንኛውም ህጻን
ዐይኑን አይጠነቁልም ይልቁንም በመዳፉ ያሸዋል እንጅ ።ታዲያ ይኸ በተፈጥሮ
የተሰጠን የኅሊና ኅግ ነው በመጽሐፍ ሳይጻፍ ጠብቀነው የምንኖር ነው ።
ዘፍ 4 ÷4 ቃኤል አትግደል የሚለው ሕግ ሳይሰራ ነው ወንድሙን የገደለው ግን
የመጽሐፍ ሕግ ባይሰጥም ኅሊና እግዚያብሔር የሰዎችን ልብ ብራና አድርጎ
የሚጽፍበት የተፈጥሮ ሕግ ስለሆነ ቃኤል ተቅበዝባዥ ሆነ ።
ኅሊናው አሳደደው ።
ኅሊና ፦ብቻውን ይከሳል፣ይመሠክራል፣ይፈርዳል።
ይ.ቀ.ጥ.ላ.ል
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ይቆየን
ማሳሰቢያ
ለአንባብያን በትኩረት እንድትከታተሉት እና ከቻላችሁ ባላችሁበት ቦታ በማስታወሻ ማለትም በኖት ቡክ ኮፒ እያደረጋችሁ በትኩረት እንድታነቡ በጥብቅ ማስገንዘብ እወዳለሁ
ሊቀ ማዕምራን መዓዛ ፈንታሁን
የባሶ ሊበን ወረዳ ቤተ ክህነት
የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ

20 last posts shown.

110

subscribers
Channel statistics