WARA BETHEL 2025
የመሐል ሲዳማ ቅርጫፍ ሰበካን ልዩ ከሚያደርጉት አንዱ ከመላ አገሪቱና ከአለም ዙሪያ የሚመጡ ምዕመናን የሚሳተፉበት ታላቁ አለም አቀፍ ጉባኤ የሚካሄድበት ሰፊው የዋራ ሜዳ የሚገኝበት መሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን በዚያ ሜዳ ላይ በብሎኬት የታጠረ ሰፊ ቦታ አላት፤ በቦታው የኮንፍራንስ ማዕከል ተገንብቶ አለም አቀፍ ጉባኤ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በየአመቱ እየተካሄደ ይገኛል።
ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ወጥቶ ወደ ካራን ሲሄድ ድንጋይ ተንተርሶ የተኛበትን "ሎዛ" የምትባለውን ስፍራ እግዚአብሔር ተገልጦለት ካነጋገረው ቦኃላ ይህ የእግዚአብሔር ደጅ ነው ስል "ቤቴል" ብሎ እንደጠራት፣ እንዲሁ በዋራ አከባቢ እግዚአብሔር እራሱ እንዲመለክበት በደሙ ለዋጃት ቤተከርስቲያን አሳልፎ ሰጥቶ በዚያ ስፍራ እውነቱን ስላበራ ቤተክርስቲያን "ዋራ ቤቴል" ብላ ጠራችው።
የዋራ ኮንፍረንስ ማዕከል በኢየሩሳሌም ከተማ ምሳሌ የተሰራ ቅጥርና መሰረት አለው። ቅጥሩ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ሆኖ በአራቱም አቅጣጫ እያንዳንዱ ሶስት ሶስት በሮች በድምሩ አስራ ሁለት በሮች አሉት። የዋራ ቤቴል የኮንፍራንስ ማዕከል 12 ትላልቅ ሼዶች የተገነቡለት የተንጣለለ ሰፊ ሜዳ ነው።
ከመጋቢት 5 ቀን 1984 ዓ.ም ጀምሮ ህዝቡን በበረከትና በምህረት እየጠበቀና እየጎበኘ፣ በድንቅና የሰው ልብና አዕምሮ ልገምተው ከምችለው በላይ ብዙ አስደናቂ ነገሮችን ያከናወነበት ዋራ ቤቴል የአምላካችን የእግዚአብሔር ተአምራት የሚገልጽ ነው።
ዋራ ሜዳ ላይ የማያቋርጥ ሃሌሉያና እልልታ በሽብሸባ ታጅቦ አስተጋባ። ግማሹ ይሰግዳል፣ ግማሹ ያመሰግናል፣ ሌላው ኢየሱስ እያለ ይጮሃል፤ እጆቹ ተዘርግተው ሞትን ለዘላለም የዋጠውን ኢየሱስን ያመሰግናሉ። ከኢየሱስ ፈውስ፣ በረከትንና ምህረትን የሚሹ ሁሉ ኢየሱስን ዝቅ ብለው፣ ሜዳ ላይ ተንበርክከው እንዲሰማቸው ይማጸኑታል።
በዚህ የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን የሰማይ መላዕክት ጭምር በተገኙበት ቢሾፕ ተክለማርያም ገዛኸኝ "ኢየሱስ በመካከላችን ነውና ምስጋናን አታቋርጡ" ብሎ ሲናገር የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በዋራ ቤቴል ፈሰሰ። በህመም ስሰቃዩ የነበሩ ተፈቱ፣ "አምላኬ ዛሬስ አያልፈኝም የእስራቴን ገመድ ይበጥሳል" ብለው የሚጠብቁ ነፍሳት ዘመናትን በአጋንንት እስራት ያሳለፉ ተፈትተው ለምስጋና እጃቸው ሲዘረጉ ታየ።
እግዚአብሔር የጠራው ጉባኤ ለመሆኑ መንፈሱን እያፈሰሰ በደዌና በሕመም የታሰሩትን እየፈታ በዋራ ቤቴል አምላካችን በሕዝቡ መካከል እንደነበረ መሰከረ።
በብሉይ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔር ህዝብ አንድም ሳይቀር በእግዚአብሔር ፊት ሊታይ ከነቤተሰቡ ይወጣ እንደነበርና እግዚአብሔርም ለህዝቡ ህጉን ያስተምርና ይባርክ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክርልናል።
ዛሬም በአዲስ ኪዳን የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ሕዝቡን በጉባኤ ሰብስቦ መንፈስ ቅዱስ እያፈሰሰ ሲባርክና የደመና ዓምድ ሲያወርድ የሚታይበት ጉባኤ አዘጋጅቷል።
ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከምስራቅና ከምዕራብ የሃገሪቱ ክፍሎች የተሰበሰቡ በደሙ የተዋጁ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ልጆች በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራበት ስም ሁሉ በላይ የሆነውን የታላቁን የአምላካችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም እየጠሩ በፊቱ ሲሰግዱና ሲዘምሩ፣ በደዌና በአጋንንት የታሰሩ ሲፈቱ፣ ያየንበት፣ ከዚህ ጨለማ ዓለም አንዱን አምላክ ከምያስክድ ክፉ ትምህርት ሰዎች በንስሐ ሲመለሱ የታየበት ድንቅ ጉባኤ ነው።
ብቻውን በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ያለውን አንዱን አምላክ በአንድ ልብና በአንድ መንፈስ ከተሰበሰበ ህዝብ ጋር ማምለክ ምንኛ መታደል ነው! ህዝቡም በአንድ ልብ እጁን ዘርግቶ በመካከሉ ያለውን አምላክ ሲያመሰግን ማየትም ነፍስን በሃሴት የሚሞላ ድንቅ ትዕይንት ነው። እግዚአብሔር የሚገለጥበት ጉባኤ!!
ለ34ኛው ዋራ ቤቴል አለማቀፍ ኮንፍረንስ እንኳን ጌታ ኢየሱስ በሰላም በጤና አደረሰን! ጉባኤም ከመጋቢት 5-7/2017 ዓ.ም ይካሄዳል። ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ተጋብዛችኋል።
@zemeru@zemeruበማስተዋል ዘምሩ Telegram Channel JOIN US for more Updates!