አልፎካከርም!
ከራስ ጋር ንግግር፦ "ብርቱ ስራ አለብኝ፣ ፋታ የማይሰጥ፣ እንቅልፍ የማያስተኛ፣ ስንፍናን የማይቀበል፣ ለተስፋ መቁረጥ ቦታ የሌለው ብርቱ ስራ አለብኝ።
ስራዬን እወደዋለሁ ለዛም ነው ፈጣሪዬ ሁሌም ከጎኔ ሆኖ እንዲያበረታኝ የምማፀነው። አቅም እንዳለኝ አውቃለሁ፣ ጠንካራ እንደሆንኩ አውቃለሁ፣ የተሰጠኝ ፀጋ ብዙ እንደሆነ አውቃለሁ ነገር ግን ዛሬም ቢሆን የምመካው በተሰጠኝ ነገር ሳይሆን በሰጠኝ አምላኬ ነው። በእርሱ ተመክቼ አፍሬ አላውቅም፣ እርሱን ተማምኜ አንገት ደፍቼ አላውቅም፣ እርሱን አስቀድሜ ወድቄ አላውቅም።
በገለጠልኝ መጠን የፈጠረኝን አውቀዋለሁ፣ የሰጠኝን ቦታ አውቀዋለሁ ለዚህም ነው የማልፎካከረው፣ ለዚህም ከማንም ጋር እራሴን የማላነፃፅረው። እራሴን ከመናቅ በላይ የፈጠረኝን መናቅ አልፈልግም፣ እራሴን ከማዋረድ በላይ ወደ ምድር ያመጣኝን ማዋረድ አልፈልግም። ሌላ ትልቅ ስራ ሰርቼ አምላኬን ባላኮራውም በፍፁም ግን እንዲያፍርብኝ የሚያደርገውን ተግባር አልፈፅምም። ራስን የመሆን ስራ ስጥቶኛልና ሁሌም ቢሆን ራሴን ለመሆን መስራቴን እቀጥላለሁ።
አዎ! አልፎካከርም! ዋጋዬን የሚያሳንስ ተግባር ላይ አልሳተፍም፣ የሚያስንቀኝን ስራ በፍፁም አልሰራም። እኔ ክብሬን ስጠብቅ፣ እኔ ራሴን ስሆን፣ እኔ ራሴን ሳሻሽል፣ በተሰጠኝ መክሊት ፍሬ ሳፈራ የሚከብርብኝ ፈጣሪ አለኝ፤ ሌላ በረከትን የሚያድለኝ አምላክ አለኝ።
ሁሌም ቢሆን ፉክክሩ እኔና እኔ መሃል እንደሆነ ገብቶኛል። ራሴን ማሸነፍ ዋንኛው አጀንዳዬ ነው፤ ከትናንቴ ተሽሎ መገኘት ትልቁ ተልዕኮዬ ነው። እግዚአብሔርን ያወቅኩት ከሰው ለመሻል፣ ሰውን ለመብለጥ ስጥር ሳይሆን ከራሴ ለመሻል ስሞክርና ራሴን በማሻሻል ጉዞዬ ውስጥ ነው። ለአንድ ሌላ ሰው የተሰራን መነፅር ልጠቀም ብል ምናልባትም ማየት የምፈልገውን ነገር ለእርሱ እንደሚያሳየው በጥራት ላያሳየኝ ይችላል። ምክንያቱም መነፅሩ የተሰራው ለርሱ እንጂ ለእኔ ስላልሆነ። የሰው የሆነን ነገር መመኘቴም ከዚህ የተለየ ትርፍ እንደማይሰጠኝ ገብቶኛል። የሰው ነገር የሰው ነው። የእራሴን ጥዬ የሰውን ነገር ለማንሳት አልጥርም። የሌሎች ስኬት እኔን እንዲያሳንሰኝ አልፈቅድም። የነርሱ መንገድ የራሳቸው ነው፣ የእኔም መንገድ የእራሴ ነው።"
አዎ! ጀግናዬ..! ሰው እንዲንቅህ እንደማትፈልገው አንተም ራስህን አትናቅ። ከብርህን የሚያሳንስ ተግባር እያደረክ አትገኝ። ራሱ ጋር ያለውን ነገር ሳያውቅ ሰው በር ላይ ያለን ነገር ከሚያማትር ሰው በላይ ደረጃውን የሚያወርድና ራሱን የሚንቅ ሰው የለም። እንትናን በሆንኩ እያልክ አንተነትህን ቦታ አታሳጣው፤ የማይመለከትህን ነገር አርቀህ እየተመለከትህ ራስህን ባዶ አታድርገው። አንተ ጋር ብዙ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፣ ማንንም ሳትመለከት አንተ ራስህ ማስተካከል ያሉበህ ነገሮች አሉ። ብዙዎችን ተመልከት፣ ከብዙዎች ተማር፣ ከእነርሱም ልምድ ውሰድ በስተመጨረሻ ግን ትኩረትህን ራስህ ላይ አድርግ። ፉክክር በጣም አስፈላጊና ጥሩ ነገር ነው። ነገር ግን መሆን ያለበት ከራስ ጋር ብቻ ነው። ራስህን ተቀበል፣ የገዛ ቤትህን አድምቅ፣ ውስጥህን አረጋጋ፣ ለራስህ ሰላም ስጥ፣ የሰላሙ አለቃም እንዲነግስብህ አድርግ።
ግሩም ድንቅ ቀን ይሁንልን! 🏞🌞🌅
በየቀኑ ጠቃሚ መልእክቶችን፣ መጽሐፍት ፒዲኤፍ፣ በነፃ የምታገኟቸው አሪፍ የኮምፒውተር ሶፍትዌሮች፣ የቢዝነስ ሃሳቦች እና የገንዘብና የተለያዩ ሽልማቶችን ለማግኘት ገጾቻችንን ይቀላቀሉ።
📱ቴሌግራም👉
@Beleqe_boostup📱ፌስቡክ ገጽ👉
https://SuperBoostUp📱ዌብሳይት 👉
https://superboostup.com/ 📱ቲክቶክ👉
tiktok.com/@superboostup