"ኧረ ሙልዬ ልጅ በእንጨት አይመታም...."....ብላ ለትንሿ ልጇ የሰነዘረችውን ማማሰያ አሰጣለቻት....እናቴ ናት....ትክ ብዬ አየዋት....አይኗን በደንብ አየሁት....የምሯን ነበር....
ታዲያ እኔን ከአራተኛ ክፍል ጀምሮ በመወልወያ እንጨት የመታችኝ እኩያዋ መስያት ነበር... አልገባሽ አለኝ።
እናቴ በማማሰያ መምታት አትወድም.... 'የልብ አያደርስም' የምትለው ነገር አላት....ፍልጥ ነገር ትወዳለች....ለማገዶ የሚገዛው እንጨት ከመንደዱ በፊት እኔን ያነደኝ እንደነበር ትዝ ይለኛል....
ከቁጥጥሯ በላይ የሆነ ንዴት አለባት....አንድ ሁለቴ የምትከትፈውን ሽንኩርት ትታ እኔን ለመክተፍ ቢላ ወርውራለች....ንዴቷን 'ትናደዳለች' የሚለው ቃል አይገልፀውም.....
አኩራፊም ናት....እናቴን ማባበል ቋሚ ስራዬ ነበር....
አንድ ቀን እንደውም እሷን ለማስደሰት የጓደኞቼን የሙያ እርዳታ ጠይቄ አራት አይነት ወጥ ሰርቼ ጠበኳት.....ስትናደድ በያዘችው ነገር መምታት ይቀናታል....በያዘችው ሶስት ሊትር ጀሪካን አናቴን ስትለኝ ማንነቴ ጠፋብኝ....
"ዘይቴን ልትጨርሺ.....አምስት አይወጣ ካንቺ....እግዚኦ አቃጥለሽ ልደፊኝ....አቃጥያት ብለው ነው የላኩሽ....".....አለችኝ....ከማን እንደተላኩ የማላውቀው እኔ አንገቴን እንደቀበርኩ ተጠቅልዬ ተኛሁ....
አባቴን የምታውቀው እሷ ብቻ ናት።
የምንተኛው ከእሷ ጋር ነው...
ስተኛ ጠብቃ እኔ በምተኛበት በኩል ከቁም ሳጥኑ ጀርባ የሚገባውን ብርድ በውስጥ ልብሷ ትደፍንልኛለች....የተኛሁ መስዬ አያታለሁ...
አልገባትም እንጂ ከብርዱ በላይ የምታሳምመኝ እሷ ነበረች....
ራስጌ እና ግርጌ ስንተኛ አትወድም....አጠገቧ ስተኛ ነው ደስ የሚላት...እንቅልፍ ከወሰዳት በኃላ በሰመመን ታቅፈኛለች....ምቾት አይሰማኝም....በውኗ አቅፋኝ አታውቅም....የማላውቃት ሴትዮ ያቀፈችኝ ይመስለኝና ሽክክ ይለኛል...ሸርተት ብዬ ከእቅፏ እወጣለሁ....
እንደምትኮራብኝ ያወቅኩት በቅርቡ ነው....ስመረቅ....ያኔ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ፈገግ ብላ ያየቺኝ....የኩራት ፊቷን ለማየት ድፍን 23 አመት ጠብቄያለሁ ብል ማን ያምነኛል....
" ከእርሱ ጋር መኖር እፈልጋለሁ....እናቴን አልፈልጋትም" ብዬ የፃፍኩትን ዲያሪ የሰፈር ሰው ለቡና በተሰበሰበበት አንብባ 'አይን ይብላሽ' ተብያለሁ....ምን አጉድላብኝ ከሰፈር ወጠጤ ጋር ለመኖር መመኘቴን አልጠየቀችኝም....
የገዛ እናቴ አደባባይ ላይ ስታሰጣኝ ማየት ሞት ነበር....በፊቷ ከንፈር ይመጡላታል....ከንፈር መጠጣ ጤፍ ይሸምትላት ይሆን እንጃ ትወደዋለች....
"አሳዳጊ የበደላት" በሚለው ትዝብት ውስጥ በዳይ መባሏን አታስተውልም።
"ባንቺ ምክንያት በረኪና ልጠጣ ነው....አይገባሽም እንዴ" ....ብዬ ቢጫውን ብልቃጥ ሳሳያት እርግት ብላ ነበር ያዳመጠችኝ....
"መጠጣት የሚፈልግ ሰው ሲወጣለት ጠብቆ ነው የሚጠጣው"....ብላ እንዴት እንደሚሞት ስትነግረኝም ተረጋግታ ነበር...
ሳይውል ሳያድር ደግሞ ደንቦችን ሰብስባ መጣች...."አንድ ልጄ ልትሞትብኝ ነው ምከሩልኝ"....ብላን ነው የመጣነው አሉ.....ደስ እያለኝ አመንኳቸው....
መካሪዎቹ እግራቸው እንደወጣ "ከቤቴ ሬሳ ቢወጣ እኔ ተጠያቂ አይደለሁም...ፖሊስ አጥቼ ነው ደንቦችን ያመጣሁት"....ብላ ደስታዬን ከአፈር ጨመረችው።
ከአንዴም ብዙ ጊዜ ልረዳት ሞከርኩ....ፍቅሯን በፊቴ የማታደርገው ለምን እንደሆነ ግን 50 አመትም ብኖር የምረዳት አልመስልሽ አለኝ...
ነገሯ ሁሉ 'አውቆ የተኛ' ሆነብኝ....ለምን ልትገለጥልኝ እንደማትፈልግ እንጃ ....እኔ ውስጥ ማንን እንደምታይ እንጃ...ለምን ጨለማ ጠብቃ እንደምትወደኝ እንጃ....
✍Shewit
https://t.me/shewitdorkahttps://t.me/shewitdorkahttps://t.me/shewitdorka