የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባንኮች በምሽት እንዲሰሩ ያወጣው መመሪያ እስካሁን ተቀባይነት እንዳላገኘ ተገለፀ፡፡
በከተማው ንግድ ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ ፊርማ የወጣው ደብዳቤ ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ሁሉም የከተማው ንግድ ቤቶች እስከ ምሽቱ ሶስት ሰአት ተኩል ክፍት መሆን እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡
ከተጠቀሰው ሰአት በፊት የዘጋ አስር ሺ ብር መቀጫ እንደሚጣልበትም የሚገልፅ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይህ ጉዳይ በከተማው የሚገኙ ባንኮችን የሚያጠቃልል ቢሆንም እስካሁን ግን በጉዳዩ ላይ ስምምነት ሊደረስ እንዳልቻለ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የንግድ ቢሮው ባንኮች ይህንን መመሪያ ተግባራዊ እንዲደርጉ የሚል ትእዛዝ ብሄራዊ ባንክ እንዲያስተላልፍ ጥያቄ ማቅረቡ ተገልጿል፡፡
ይሁንና እስካሁን ድረስ የብሄራዊ ባንክ ሀላፊዎች በዚህ ላይ ውሳኔ ላይ አልደረሱም፡፡ የባንክ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ብሄራዊ ባንክ እንደዚህ አይነት ትእዛዝ መስጠት የሚያስችል መብት የለውም፡፡
አንድ ባለሙያ ሲናገሩ ‹‹እንዲህ አይነት ውሳኔ የሚመራው በገበያው ፍላጎት እንጂ በባለስልጣናት ትእዛዝ አይደለም፡፡ ብሄራዊ ባንክ የባንኮችን እንቅስቃሴ ይቆጣጠራል እንጂ የስራ ሰአታቸውን የመወሰን መብት የለውም›› ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም አንዳንድ ባንኮች የስራ ሰአታቸውን በማራዘም እስከ ምሽት ይሰሩ እንደነበር የጠቀሱት ባለሙያው ይሁንና የዲጂታል ባንኪንግ ስርአት እየተስፋፋ ከመምጣቱ ጋር ይህ እንደቀረ አስረድተዋል፡፡
@Ethio_fastnews🤩
@Ethio_fastnews🤩