ምሳላዊ መረጃ፦ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጪው ጥር አጋማሽ ገደማ የስልጣን መንበራቸውን ሲረከቡ በሀገሪቱ ጊዜያዊ ጥበቃ የተሰጣቸውን ጨምሮ በህገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ ናቸው የተባሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በገፍ ለማስወጣት እቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
አሜሪካ ካለፈው ዓመት ጥር እስከ መስከረም ባሉት ወራት ብቻ፤ 271,000 ገደማ ስደተኞችን ወደ 192 ሀገራት በግዳጅ መልሳለች። ከእነዚህ መካከል 27ቱ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ መሆናቸውን የአሜሪካ የኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ አስፈጻሚ መስሪያ ቤት ዓመታዊ ሪፖርት ያሳያል።
በተቋሙ መረጃ መሰረት፤ በ2024 ወደ ኢትዮጵያ የተጠረዙ ሰዎች ቁጥር ባለፉት ሶስት ዓመታት ከተመዘገቡት ከፍተኛው ነው። በ2019 አሜሪካ 32 ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ የመለሰች ሲሆን አሃዙ በቀጣዩ ዓመት ወደ 43 ከፍ ብሎ ነበር።
ከኢትዮጵያ ጎረቤቶች በ2024 ብዛት ያላቸው ዜጎቿን ከአሜሪካ የተቀበለችው ሶማሊያ ነች። ሶማሊያ በተጠቀሰው ዓመት ከአሜሪካ በግዳጅ የተመለሱ 64 ሰዎች ተቀብላለች።
ከኢትዮጵያውያን እና ሶማሊያውያን በተጨማሪ 48 ኬንያውያን፣ 34 ኤርትራውያን እና 5 ሱዳናውያን በዓመቱ ወደ ሀገራቸው በግዳጅ እንደተመለሱ የተቋሙ ዓመታዊ ሪፖርት ይጠቁማል።
በ2024 አሜሪካ በግዳጅ ወደ ተለያዩ ሀገሮች የላከቻቸው ሰዎች ቁጥር ባለፉት አስር ዓመታት ከነበረው ሁሉ ከፍተኛው ነው። በአሜሪካ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ወይም በጊዜያዊ ጥበቃ የሚኖሩ 11 ሚሊዮን ገደማ ስደተኞች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚገመት የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ይጠቁማሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
@EthiopiaInsiderNews