➕➕➕ ሰሙነ ሕማማት እና የቀናት ስያሜዎች ➕➕➕
የዐብይ ጾም የመጨረሻው ሳምንት ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ያሉት ቀናት ሰሙነ ሕማማት ይባላሉ። በነዚህ ቀናት የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም የሚታሰብ ሲሆን፤ ካህናትና ምእመናን በቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ተሰብስበው የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ በማዜም ቀኑን ሙሉ በስግደትና በጸሎት ያሳልፋሉ።
ካህናተ ቤተክርስቲያን ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፤ ምክንያቱም ጌታችን የደረሰበትን መከራና ስቃይ እንዲሁም የሰው ልጅ አምስት ሺህ 500 ዘመን በጨለማ ግዞት ይኖር እንደነበር ለማዘከርም ጭምር ነው። በዚህ ሳምንት ከክርስቶስ ልደት በኋላ የመጡት የድኅነት ምልክቶች አይደረጉም። ከሰኞ እስከ ትንሳኤ ዋዜማ ያሉት ስድስቱ የሰሙነ ሕማማት ዕለታትም ትርጉም ተሰጥቷቸው ይታሰባሉ፡፡
☄️
ሰኞ:- ርግመተ በለስ እና አንጽሖተ ቤተመቅደስ ትባላለች።በዚህ ዕለት ኢየሱስ ክርስቶስ ከቢታኒያ ሲወጣ ተራበ። ቅጠል ያለባትን በለስ ተመልክቶ ወደ በለሲቱ ቢቀርብ ከቅጠል በቀር ምንም ነገር ባለማግኘቱ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ምንም ካንቺ ፍሬ አይበላ” በማለት ስለረገማት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል። ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሄዶ በቤተመቅደሱ የሚሸጡትን እና የሚለውጡትን “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” በማለት ከቤተመቅደስ ገርፎ ያስወጣበት ዕለት ነው።
☄️
ማክሰኞ:- የጥያቄና የትምህርት ቀን ትባላለች።ሰኞ ዕለት በቤተመቅደስ ሲሸጡ እና ሲለውጡ የነበሩትን ሁሉ እየገረፈ በማባረሩ ምክንያት ለሰው ልጅ ሹመትንና ስልጣንን የሰጠ ጌታ በምን ስልጣን ይህንን ታደርጋለህ? ተብሎ በፈሪሳውያን ተጠይቋልና የጥያቄ ቀን ይባላል። በዕለተ ማክሰኞ በቤተመቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ የትምህርት ቀንም ትባላለች።
☄️
ረቡዕ፡- ምክረ አይሁድ፣ የመልካም መዓዛ እና የእንባ ቀን ይባላል። ረቡዕ እለት የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የመከሩበትና ውሳኔ ያሳለፉበት ቀን በመሆኑ ምክረ አይሁድ ይባላል።የመልካም መዓዛ ቀንም መባሉ ደግሞ በለምጻሙ በሰምዖን ቤት ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት (ባለሽቶዋ ማርያም) ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ የአልባጥሮስ ሽቱ አምጥታ በራሱ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባቸው ነው።
ባለሽቱዋ ሴት (ማርያም እንተ እፍረት) ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት እየለመነች በእግሩ ስር ተደፍታ በእንባዋ እግሩን አርሳለችና ማየእንባ ቀን ይባላል።
☄️
ሐሙስ:- ፀሎተ ሐሙስ፣ ህጽበተ ሀሙስ፣ የምስጢር ቀን፣ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ እና የነጻነት ሐሙስ ይባላል።ፀሎተ ሐሙስ ጌታ ለአይሁድ ተላልፎ ከመሰጠቱ በፊት በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሲጸልይ በማደሩ ጸሎተ ሐሙስ ይባላል። ጌታችን የደቀመዛሙርቱን እግር በፍጹም ትህትና ዝቅ ብሎ ያጠበበት ዕለት በመሆኑም ሕጽበተ ሐሙስ ይባላል። የምስጢር ቀን ይባላል፡- ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ የቅዱስ ቁርባን ምስጢር በዚህ ዕለት ተፈጽሟልና የምስጢር ቀን ይባላል። የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡- መሥዋዕተ ኦሪት /በእንስሳት ደም የሚቀርብ መሥዋዕት/ቀርቶ ለአለም ድኅነት ራሱን ያቀረበበት ቀን በመሆኑ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል። የነጻነት ሐሙስ ይባላል፡- ለኃጢአትና ለዲያቢሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱን እንዲሁም የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነም የነጻነት ሐሙስ ይባላል።
☄️
ዓርብ:- የስቅለት ዓርብ እና መልካሙ ዓርብ ይባላል።ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ የዋለበት ዕለት ነውና የስቅለት ዓርብ ይባላል። ከጌታ ስቅለት በፊት በተለይም በሮማውያን ህግ የወንጀለኛ መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል ጌታ በደሙ ቀድሶ የምህረት፣ የሕይወት አርማ፣ የዲያቢሎስ ድል መንሻ ስላደረገው፤ በሞቱ መልካሙን ሕይወት ስላገኘን መልካሙ ዓርብ ይባላል።
☄️
ቅዳሜ:- ቅዳም ስዑር፣ ለምለም ቅዳሜ እና ቅዱስ ትባላለች።ይህች እለት ከድሮ በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረች ቅዳሜ ትባላላች። ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት በመሆኑም ለምለም ቅዳሜ ይባላል። ምዕመናንም ይህንን ለምለም ቀጤማ እስከ ትንሣኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል። ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ያረፈበት ቀን ሲሆን፤ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ስራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ በነፍሱ ወደ ሲዖል ወርዶ ሲኦልን በርብሮ ባዶዋን ሲያስቀራት በዚያ የነበሩትን ነፍሳት የዘላለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል።
Credit: GazettePlus
@Ethiopian_Digital_Library@Ethiopian_Digital_Library