"ባለትዳሮቹ.. ቀድመው ይስተናገዳሉ" የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ለመስጠት ነዋሪዎችን በማኅበር የማደራጀት ሥራውን ሊጀምር መኾኑን ማሳወቁ ይታወሳል።
ከሚያዝያ ስድስት ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ የጸጥታ ሃይሎችን እና የከተማ ነዋሪዎችን እንደ ቅደም ተከተላቸው የምዝገባ እና የማደራጀት ሥራ እየሠራ ነው።
ነዋሪዎች በማኅበር ሲደራጁ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመቅረፍ እና ሥራውን ለማቀላጠፍ ከተማ አሥተዳደሩ ባለ ትዳር ኾነው የሚደራጁትን እንደሚያበረታታ እና ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተገልጿል።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብርሐም ወርቁ በሰጡት ማብራሪያ ለመደራጀት የሚመጡ ሰዎች በሀሰት ፍቺ ወይም ላጤነት የመቅረብ ዝንባሌዎች መኖራቸው ተገምግሟል ብለዋል።
የሚደራጁ ሰዎች ኹኔታ በዝርዝር ከተገመገመ በኋላ ትዳር እና ልጅ ያላቸውን ግለሰቦች ችግራቸውን ለመቅረፍም ሲባል ትዳር ያላቸውን ማበረታታት ተገቢ ነው ብለዋል አቶ አብርሐም።
ለባለትዳሮች ቅድሚያ ይሰጣል ማለት የሌሎችን ለማጣራት የሚወስደውን ያህል ጊዜ አይወስድም ማለት መኾኑንምም ገልጸዋል።
ትክክለኛ ጋብቻ የሌላቸው እና በትክክለኛ ፍች የፈጸሙት እስኪረጋገጥ በጋብቻ ላይ ያሉት እንዳይጉላሉ የተወሰደ መፍትሄ ነው ብለዋል።
ሲጣራ በትክክልም ላጤ የኾኑ (በትዳር ላይ ያልኾኑ) ይኖራሉ፤ የነሱ መብትም እንደተጠበቀ ነው ብለዋል።
ተቋማት ትክክለኛ መረጃ የመስጠት እና የቤት ሥራ ማኅበራትም ተገቢ ያልኾኑ ተደራጂዎችን የመታገል ውስንነቶች እንዳሉባቸው አቶ አብርሐም ጠቅሰዋል።
መረጃ ሰጪ ተቋማት ትክክለኛ መረጃ የመስጠት እና ማኅበራትም በውስጣቸው የሚደራጅን ሰው መስፈርት አውቀው የማደራጀት ኀላፊነት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ መሬት የሕዝቡ የጋራ ሀብት ነው ያሉት ኀላፊው ይህንን ሀብት በፍትሐዊ መንገድ ለመጠቀም ሁሉም ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
በማደራጀት ሥራው ከሚታዩ ዝንባሌዎች ውስጥ አንዱ የሀሰት ላጤነት ነው ብለዋል። ይህንን ለመከላከል በሚደረግ የማጣራት ሂደት እውነተኞቹ እንዳይጉላሉ ባለትዳሮቹ ቀድመው የሚያገኙበትን አሠራር ነው የተቀመጠው ብለዋል።
በላጤነት የሚደራጁትን ደግሞ ከተቋማቸው እና ከማኅበራቸው ጋር መረጃ በማጥራት ትክክል ኾነው ሲገኙ ተደራጅተው ቦታ ያገኛሉ ነው ያሉት።
Via:አሚኮ
@Ewun_Mereja1@Ewun_Mereja1