Фильтр публикаций




#_ነገ_በጸሎተ_ሐሙስ_በቅዱስ_ቁርባን_እንቀደስ!

የቆረባችሁም ያልቆረባችሁም የነገው እለት እንዳያመልጣችሁ!

በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

ሼር በማድረግ ለሁሉም አዳርሱ!

ተወዳጆች ሆይ ነገ ጸሎተ ሐሙስ ነው። ይህ ቀን ብዙ ስያሜ ቢኖረውም አንዱ ስያሜው የምስጢር ቀን ይባላል። ምክንያቱም በዚህ እለት ጌታችን የቅዱስ ቁርባንን ምስጢር ለቅዱሳን ሐዋርያት ያካፈለበት፣ ሥርዓተ ቅዱስ ቁርባንን የመሠረተበት ታላቅ ቀን ነው።

ስለዚህ ቅዱስ ቁርባን በመቀበል የምትኖሩ ነገ በጸሎተ ሐሙስ ቅዱስ ቁርባን ተቀበሉ። ንስሐ ገብታችሁ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል ያሰባችሁም ከንስሐ አባታችሁ ጋር ተመካክራችሁ ነገ በጸሎተ ሐሙስ እለት ቅዱስ ቁርባን ተቀበሉ።

ቅዱስ ቁርባን ያልተቀበላችሁ ደግሞ፣ ጌታችን ሥርዓተ ቅዱስ ቁርባንን በመሠረተበት፣ ለቅዱሳን ሐዋርያት ምስጢርን ባካፈለበት በዚህ እለት ተገኝታችሁ አስቀድሳችሁ በቅዳሴው ተቀደሱ።

በጸሎተ ሐሙስ እለት ጌታች "እንኳችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው፣ ይህ ደሜ ነው ጠጡ" ብሎ እራሱን ብሉኝ ጠጡኝ ብሎ ሰጠን።

የሚገርመው ጌታችን በማቴ 26፥27 ላይ "ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው" በማለት ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን ለሁላችን ሰጠን።

እንድ ሰው የሚወደውን ሰው በእንግድነት ቤቱ ቢጠራው የሚወደውን ምግብ እና መጠጥ ሊጋብዘው ይችላል። ጌታችን ግን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንድንመጣ ሲጋብዘን የሚሰጠን እራሱን ነው። የሚጋብዘን ቅዱስ ሥጋውንና ክብር ደሙን ነው።

ሰው ሰውን ቢጋብዝ የራሱን ነገር ነው የሚሰጠው። ጌታችን ግን እራሱን ነው የሰጠን። የሚደንቀው ደግሞ "ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ" አለ። ኃጥአን ፃድቃን ሳይል፣ የበቃ ያልበቃ ሳይል፣ ድንግል ዘማዊ ሳይል፣ ሕፃን ወጣት ጎልማሳ አዛውንት ሳይል፣ ግን ንስሐ የገባውን ሁሉ ሥጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ አለ። አንዴት መታደል ነው!

ቅዱስ ቁርባንን በየትኛውም እለት ልትቀበሉ ትችላላችሁ ግን በጸሎተ ሐሙስ ቅዱስ ቁርባንን መቀበል እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታ እጅ መቀበል ነው።

በጸሎተ ሐሙስ ቅዱስ ቁርባንን በማስታወስ መቀበል የቅዱስ ቁርባንን በዓል አስቦ መቀበል ነው። ጸሎተ ሐሙስ ለመጀመሪያ ጊዜ ጌታችን ቅዱስ ቁርባንን የሰጠን እለት ስለሆነ በዚህ እለት ቅዱስ ቁርባንን መቀበል የቅዱስ ቁርባንን የምሥረታ በዓል አስቦ መቀበል ነው።

በጸሎተ ሐሙስ ቅዱስ ቁርባን መቀበል እኛ ቆራቢዎች እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ነን፤ ቀድሰው የሚያቆርቡን ክቡራን ካህናት ደግሞ እንደ ጌታችን ናቸው።

በጸሎተ ሐሙስ ቅዱስ ቁርባን መቀበል፣ በምሥጢር እለት ምስጢር መሳተፍ ነው።

እስኪ አስቡት! በጸሎተ ሐሙስ እናንተ እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ክቡራን ካህናት እንደ ጌታችን ሆነን በጸሎተ ሐሙስ በቅዳሴ ስንገኝ! ግሩም ነው!

ስለዚህ በቅዱስ ቁርባን ሕይወት ያላችሁም፣ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል በንስሐ የተዘጋጃችሁም፣ ይህቺ የምስጢር እለት አታምልጣችሁ! ደግሜ እናገራለሁ ለመቁረብ አንዳች ምክንያት እስካልከለከላችሁ ድረስ የቻላችሁ ቅዱስ ቁርባን ተቀበሉ።

እራሱ ጌታችን "ሥጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ" ብሎ አዞናል። በነገራችን ላይ ቅዱስ ቁርባን መቀበል የጌታችን ትዕዛዝ ነው። በቃ አዞናል። በንስሐ ሆኖ ቅዱስ ቁርባን መቀበል ለጌታ መታዘዝ ነው። ቅዱስ ቁርባን አለመቀበል ለጌታ አለመታዘዝ ነው።

በእርግጥ እንደ ኃጢአታችን ላይቻለን ላይሆንልን ይችላል። በንስሐ ሆነን እንደ ቸርነቱ ይቻለናል። ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል እኔ አላዛቹ፣ መምህራን እና ካህናት አያዛቹ። እኛ ማስታወስ ብቻ ነው። ተቀበሉ ያላችሁ የቅዱስ ቁርባኑ ባለቤት ጌታችን ነው። ባለቤቱ ካዘዘ ደግሞ በንስሐ እና በትህትና ሆነን መቀበል ነው።

ቅዱስ ቁርባን የሚቀበል ሰው ዘላለማዊ ሕይወት፣ ጸጋ መለኮት፣ የእግዚአብሔር በረከት፣ የኃጢአት ሥርየት እና መንፈሳዊ ኃይል ወዘተ ይኖረዋል። ስለዚህ ቅዱስ ቁርባን በመቀበል እነዚህን ጸጋዎች እንቀበል።

እንዲሁም ቅዱስ ቁርባን ያልተቀበላችሁም በምስጢር እለት ተገኝታችሁ ጌታችንን "ከዚህ ምስጢር እንድካፈል አብቃኝ" ብላችሁ በቅዳሴው ተማጸኑ።

በያላንብ የጌታችን ቸርነት የወለላይቱ እመቤት ጸሎት አይለየን!

ሚያዝያ 8-8-17 ዓ.ም

አዲስ አበባ






#_ለክርስቶስ_ዓላማ_እንደ_አህያ_ተመችተነዋል?

በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

ሼር በማድረግ ለወዳጆ አዳርሱ!

ከጥንት ጀምሮ አህያ ለሰው ልጆች ሕይወት ትልቅ ባለውለታ ብትሆንም፤ ሰዎች ጉልበቷን እየተጠቀሙ ስሟን ስድብ አደረጉት። በብርቱዋ፣ ዕቃ ተሸከሚዋ፣ ታዛዥዋ አህያ እርባና ለሌለው ሰው፣ የሚሉትን ለማይሰማ ሰው ስሟ ስድብ ሆነ።

ለጠንካራና ለታታሪ ሰው "አህያ" የሚለው ስም እንደ ነውር ይቆጠራል። ግን አህያ ሰው በቀላሉ የማያየውን መልአክ ለማየት፤ ዘባነ ኪሩብን ተክታ ጌታዋን ለመሸከም የበቃች ፍጡር ነች። /ዘኁ 22÷23—34, ዮሐ 12÷15/

ጌታችን በሥጋ ተገልጦ በነበረበት ጊዜያት ከሰው ያልተናነሰ አህያ በሰው መሃል ጌታዋን አገልግላለች። እኛስ ጌታችንን በሰው መሃል አገልግለናል? ጌታችን አህያዋን "ፍቱና አምጡልኝ" ሲል ሐዋርያትን ሳትራገጥ፣ ተፈትታም ሳትፈረጥጥ ወደ ጌታዋ መጥታ አገልግላለች።

እኛ ግን ጌታችን መምህራንን ካህናትን ልኮልን ከታሰርንበት የኃጢአት ማሰርያ ፈተው ወደ ጌታ ሊወስዱን ሲሉ የኃጢአቱን ገመድ እያጠበቅን፣ ከአህያ አንሰን አልፈታም ብለን ሸሸኝ፤ ጌታችንንም ለማገልገል እንቢኝ አልን። አህያ ባልተለመደ መልኩ ልብስ ለበሰች፤ እኛ ደግሞ የጌታችንን ጸጋ መልበስ አቃተን። ማቴ 21÷7

አህያ ጌታ ሲመሰገን ክብሩን በዓይኗ አይታለች፣ ለጌታ የተነጠፈውን ዘንባባ በኮቴዋ ረግጣለች። እኛ የጌታን ክብር በማህሌቱ በቅዳሴው ሳናይ፣ የጸጋ ዝንጣፊ የተነጠፈበትን የእግዚአብሔርን ደጅ ዘወትር ሳንረግጥ፣ እንደ ሰነፍ አህያ የጌታችንን ጸጋ ለመሸከም ስናለምጥ፣ ነፍሳችን በኃጢአት ስትላቁጥ ስንት ዓመት ሆነን? በእውነት በሕይወታችን ለክርስቶስ አላማ እንደ አህያ ሳንመቸው ከኖርን፣ ከአህያ አነስን ማለት ነው።

‹‹ከክርስቶስ ጋር እንዴት እንኑር›› ከሚለው መጽሐፌ የተወሰደ፡፡

መልካም የሆሳዕና በዓል

ሚያዝያ 5/8/17 ዓ.ም
አዲስ አበባ










#_ደህና_ነኝ_ከአውሮችላኑ_አልወርድም!

የጉዞ ማስታወሻ!

በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

ዊኒፒግ ይቀዘቅዛል የሚል ቃል አይገልጸውም። የዊኒፒግ ቅዝቃዜ ዊኒፒግን ምድራዊ ሲኦል አስመስሏታል። ዊኒፒግን የበረዶ ቅርጫት ይሏታል። በካናዳ ካሉት ከተሞች እንደ ዊኒፒግ የሚቀዘቅዝ ከተማ የለም።

ከተፈጠርኩ በሕይወቴ እንደ ዊኒፒግ ያለ ቅዝቃዜ ገጥሞኝ አያውቅም። ያሉት የሚኖሩት በቴክኖሎጂ ነው። ትንፋሻቸው ማብራት ነው። አንድ ቀን እንደ እኛ ሀገር ማብራት ቢጠፋ በሞት ይጠፋሉ። ቅዝቃዜው ይገድላቸዋል። ውጪው ሰውነትን ድንጋይ የሚያደርግ ቅዝቃዜ አለ። ቤት ውስጥ ደግሞ ውጪውን የማያስረሳ ሙቀት አለ።

በዊኒፒግ ማኒቶባ ሙዝየም የሚባል አለ። ሙዝየሙን ለማየት እና ለመጎብኘት ወደ ሙዝየሙ የተወሰነ ርቀት በእግሬ ሄጄ ነበር። በዛች ደቂቃ እጄ በረዶ ሆነ። እጄ ደነዘዘ፣ የደም ዝውውሬ የቆመ ነው የሚመስለው። ተሯሩጩ ሙዝየም ገባሁ። በዛች ደቂቃ የተሰማኝን ቅዝቃዜ ልገልጽላችሁ አልችልም።

በዊኒፒግ የነበረኝን ቆይታዬን አብቅቼ በጠዋት ተነስቼ ወደ ኤርፖርት ሄድኩኝ። ጣጣዬን ጨርሼ አውሮፕላን ውስጥ ገባሁ። አውሮፕላኑ ወደ መንደርደሪያው ሄዶ ለመነሳት ሲዘጋጅ ከኋላዬ የተቀመጠ ተለቅ የሚል ሰው ድንገት ታሞ ተዝለፍልፎ ላብ አጥምቆት አይኑ ተገለባብጦ አየሁት።

ሚስቱ ተደናግጣ ሆስተሶችን ጠራች። እኔ የሚገርመኝ የእነሱ ሀገር ሆስተሶች ናቸው። ሆስተሶቹ እንደ ኢትዮጲያ አየር መንገድ ወጣቶች ሳይሆኑ አብዞኛቹ በእድሜ ትልቅ ናቸው አንዳንዶቹማ አያት ናቸው።

ሆስተሶቹ መጡ! እኔ ሰውዬውን አይቼ ተደናገጥኩ እነሱ ግን ምንም አልመሰላቸውም። የለመዱት ነገር ይመስላል። ሰውዬውን ወደ ላይ ቀና አድርገው ቢጠሩት አይሰማም አይለማም።

ወደ ፖይተሉ ደውለው ሰው ታሟል ብለው ነገሩት። እሱም በማይክ "መንገደኞቻቸን ሰው ታሞብናል የእርዳታ ሠራተኞች እስኪመጡ ዶክተሮች ካላችሁ እባካችሁ እርዱልን" ብሎ ተናገረ።

አንድ ጎልማሳ ሰው መጥቶ "ዶ/ር እከሌ እባላለሁ ልረዳው እችላለሁ" አለ። ሆስተሶቹ የህክምና መርጃ መሣሪያዎች ይዘው መጡና ለዶክተሩ አሳዩት። እሱም ማዳመጫውን ጆሮው ላይ እና የታመመው ሰው ላይ አድርጎ አዳመጠ። ከዛ አነስ ያለች የሱኳር መለኪያ መሣሪያ ሰጡትና በዛ ሱኳሩን ለካው።

እንዲህ እየሆንን አውሮፕላኑ ከመንደርደሪያው ተመልሶ ወደ ጫነን ቦታ ሄዶ ቆመ። ድንገተኛ የሕክምና እርዳታ ሠራተኞች መጡ። እርዳታ የሰጠውን ዶክተር ጠየቁት። ዶክተሩም "ስኳሩ ከፍ ብሏል የደም ግፊቱም ጨምራል" አለ።

ይሄንን የሰሙት ድንገተኛ የሕክምና ሠራተኞች ሰውዬውን "ወርደህ የሕክምና እርዳታ ማግኘት አለብህ" አሉት። የታመመውም ሰው "ደህና ነኝ ቀለል ብሎኛል" አላቸው። እነሱም "ደህና ልትሆን ትችላለህ ግን የሕክምና እርዳታ ማግኘት አለብህ ሱኳርህም ደምህም ከፍ ብሏል" አሉት።

እሱም ንክች ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ ብሎ "ኖ በፍጽም አልወርድም ደህና ነኝ" ብሎ ተሟገተ። የሕክምና እርዳታ ሰራተኞቹም እንደማይሆንና የሕክምና እርዳ ካላገኘ እንደሜይሄድ ነገሩት። እሱም "አልወርድም" አለ። ባለፈው እኛ ሀገር አንድ ወጣት ከአውሮፕላን አላወርድም ብሎ ነበር። ይሄ "አልወርድም" ለካ እኛ ሀገር ብቻ አይደለም ያለው ብዬ ተገረምኩ።

የድንገተኛ የሕክምና ሠራተኞች የታመመውን ሰው በትህትና ቀስ ብለው አግባቡት። እንዲህ ሆኖ ቢበር ለሕይወቱ አደጋ እንደሆነ አባብለው ነገሩት። ሆስተሷም በሚቀጥለው ፍላይት እንደሚሄድ ነገረችው። ብቻ ታከም ሳይሆን ታመም የተባለ ይመስል እያቅማማ እሺ አለ። ዊልቸር ላይ አስምጠውት እየገፉት ወሰዱት።

ካናዳ የሕክምና ነገር ይገርማል። ሕክምና በነፃ ነው። ሕክምና በነፃ ቢሆን በጣም ነው የማያካቡዱት። ሆስፒታል ሆዳቹ ጉኔን ወጋኝ ካላችሁ ሲቲ ስካን፣ ኤም አር አይ ወዘተ ታዞላችሁ ሙሉ ምርመራ ተደርጎላችሁ ወጋኝ ስላላችሁ ብቻ ለበረከት አንድ መርፌ ተወግታችሁ የአንድ ወር መድኃኒት ይዛችሁ ልትመለሱ ትችላላቹ።

አንድ ወዳጄ ወድቃ እጇን ወለም አላት። ወለምታው አውራ ጣቷን ሲያሳብጠው ሆስፒታል ሄደች። ሆስፒታልም ተረባርበው ምርመራ አድርገው ደም ስሯ እንደዞረና በዞረው ደም ስሯ ምክንያት አውሯ ጣቷ እንዳበጠ እና አደገኛ እንደሆነ ነገሯት።

ግርም ነው ያለኝ። እኛ ድሮ ትምህርት ቤት እያለን እንደ አህያ ስንላፋ በኳስ ስንጋፋ አይደለም ጣታችን አንገታችን እየዞረ፣ ጣታችን እየወለቀ እንደ ተርምኔተር የወለቀውን እያስገባን የዞረውን እና የተጣመመውን እያስተካከልን ነው ያደግነው። ስንቶቻችን የእጅ እና የእግር ደም ስራችን እየዞረ ደም ስራችንን አዙረን መልሰናል!

እንጦጦ ማርያም ጸበል እያጠመኩ አንዷን አጋንንቱ ልጆቷን እንዳይጥላት ስታገል ድንገት የቀኝ አውራ ጣቴ ወለቀ። አንድ የማውቃቸው እናት ናቸው የወለቀውን መልሰውልኝ በማግስቱ ጣቴን አስሬ ያጠመኩት። የካናዳ ሐኪሞች ይሄንን ታሪኬን ቢሰሙ ሪሰርች ይሰሩብኝ ነበር።

ወደ ልጅቷ ልመለስና "ደም ስርሽ ዞሮ ጣትሽ ስላበጠ ለአንድ ወር ስራ እንዳትሰሪ" አለቻት። ከአንድ ወር በኋላ ያበጠው ተስተካክሎ መጣች። ሐኪሟም ድጋሚ መርምራት "የሚያሳይ ነገር አለ ደም ስርሽ ወደ ቦታው አልተመለሰም ስለዚህ ሪስክ ነው ለአንድ ዓመት በዚህ እጅሽ ሥራ እንዳትሠሪ" ብላ በጤነኛ አውራ ጣቷ ተከራክራት ወደ ቤት ላከቻት። እሷም በአውራ ጣቷ ምክንያት ለአንድ ዓመት በእረፍት አሳለፈች።

የታመመው ሰው ከአውሮፕላን ከወረደ በኋላ ወደ ቶሮኖቶ ጉዞ ጀመርን። አጠገቤ የተቀመጠችው ነጭ ጎልማሲት ሴት ናት። "Think Twice" የሚል መጽሐፍ ታነባለች። የመጽሐፉን ዋጋ ሳየው 66.6 ዶላር ነው። ወደ እኛ መታውት። በእኛ መጽሐፉ ከስድስት ሺ ብር በላይ ነው። እነሱ መጽሐፍ ለመግሻት ዓይናቸውን አያሹም!

በተመስጦ ነው የምታነበው። አውሮፕላኑ በታመመው ሰው ምክንያት አንድ ሰዓት ከግማሽ ሲዘገይ እሷ መጽሐፏን ታነባለች። ከዊኒፒግ ቶሮንቶ እስክንደርስ ሁለት ሰዓት ከግማሽ አንብባለች።

ፈረንጆቹ መጽሐፍ እጅጉን ያነባሉ። በየሄድኩበት ሀገር የታተመ ጽሐፍ ይዘው ያነባሉ። በስልካቸው እና በአይፖድ ያነባሉ። እኛ ደግሞ የማንበብ ልምድ የለንም። ከመጽሐፍ እና ከእውቀት ጋር ጠበኞች ይመስል አንነካካም አናነብም።

የአእምሮ ምግብ መጽሐፍ ነው ወይም እወቀት ነው። ሰው በተለያየ መልኩ እውቀት ቢያገኝም አንዱ መንገድ መጻሕፍትን በማንበብ ነው እውቀት የሚያገኘው። የሚጠቅሙንን መጻሕፍት ማንበብ የአእምሮ ቀለብ ነው። አንብቡ...

ፈረንጇ "አለባበስህ የተለየ ነው ግሬስ አለህ" አለችኝ። አመስግኜ እንደ ኳስ ተጫዋች የሰቀልኩትን እንግልጣሬን/እንግሊዘኛዬን አውርጄ ያጠራቀምኳቸውን ውድ ቃላቶቼን ጨማምሬ ካህን እንደሆንኩና ቤተ ክርስቲያን እንደማገለግል ነገርኳት።

በነገራችን ላይ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን እንግሊዘኛ እንግልጣር ነው የሚባለው። ደብዳቤም ሲጻፍ ለእንግልጣር ንጉስ ይባል ነበር። በጊዜ ሂደት ነው እንግሊዝ እና እንግሊዘኛ ያልነው።

ፈገግታዋና ደስታዋ የውሸት ይሁን የእውነት ባላውቅም በጣም ደስተኛ እና የተደነቀ ፊት አሳየችኝ። ፈረንጆቹ እንደ እኛ ፊታቸውን ግስላ አያስመስሉም። ሰላም ሲሏችሁ፣ ሲያናግሯችሁ፣ እናንተ ሰላም ባትሏቸው፣ ብልጭ ብሎ ድግርም የሚል ፈገግታ ያሰይዋቹሃል።

ያለኝን እንግሊዘኛ ጨምቄ እና ሕሊናዬንም አስጨንቄ ስለ ታመመው ሰውና አንዳንድ ነገሮች በጥቂቱ አወራን።

ቶሮኖቶ ደረስን ...... ወዳጆቼን አገኘሁ ሰላም ሁኑ!

መጋቢት 29-7-17 ዓ.ም

ቶሮንቶ ካናዳ
















#_በአንዲት_ዓለም_ሁለት_ዓለም!

እኛ ሀገር በዚህን ጊዜ በጋ ነው! በካናዳ በቅዝቃዜዋና በበረዶዋ የምትታወቀው በማኒቶባ የምትገኘው የዊኒፔግ ከተማ ክረምቱ የተባዘተ ጥጥ በመሰለ በረዶ ተሸፋኗል!

እግዚአብሔር ሥራው ግሩም ነው! አንዱን አህጉር በጸሐይ ያሞቃል፣ አንዱን አህጉር በበረዶ ይሸፍናል! እኛ በእኛ ሀገር የአየር ጠባይ እናማርራለን። እነሱ ለሕይወት አስጊ በሆነው የአየር ጠባይ ተስማምተው ይኖራሉ።

በአንዲት ዓለም እየኖርን የአየሩ ጠባይ ሁለት ዓለም ያለ ያስመስላል! ለማንኛውም በማኒቶባ የምትገኘው ዊኒፔግ አየሩ ይህንን ይመስላል!

ቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

ካናዳ ዊኒፔግ

መጋቢት 19-7-2017 ዓ.ም





Показано 20 последних публикаций.