ኢትዮ ቴሌኮም የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ህትመት አገልግሎት መስጠት ጀመረ
ኩባንያችን የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ዘርፈ-ብዙ የመሠረተልማት ማስፋፊያ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ይህንን ስትራቴጂ እውን ለማድረግ ከሚያስፈልጉ አስቻይ ሲስተሞች ውስጥ አንዱ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ሲሆን፣ ለአካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት በሀገር አቀፍ ደረጃ እስከ 2018 ዓ.ም ድረስ 90 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ለማዳረስ በመደረግ ላይ ያለውን መጠነ ሰፊ ጥረት በመደገፍ የብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የመመዝገቢያ መሳሪያዎችን በመግዛት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአገልግሎት ማዕከላቱን በመጠቀም እና የሰው ኃይል በማሰልጠን የምዝገባ ስራ በስፋት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
አገልግሎት ደህንነቱ አስተማማኝ፣ ደረጃውን የጠበቀ እና ጥራት ያለው ካርድ በቀላሉ ለማቅረብ የሚያስችል ሲሆን ደንበኞች በቴሌብር ሱፐርአፕ ብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ የካርድ ህትመት መተግበሪያ ወይም በድረገጽ
https://teleprint.fayda.et/ በመግባት፣ የፋይዳ ተለዋጭ ቁጥር (FAN) በማስገባት፣ በአጭር ጽሑፍ የሚላከውን የማረጋገጫ መለያ ኮድ በማስገባት፣ የአገልግሎት ፍጥነት፣ ካርድ የመረከቢያ ቀን እና ቦታ እንደፍላጎታቸው መምረጥ ይችላሉ፡፡
የአገልግሎት ክፍያን በተመለከተ ደንበኞች በተለያየ የህትመት ማድረሻ ፍጥነት አማራጮች (delivery time) ማለትም ለመደበኛ በ7 የሥራ ቀናት (345 ብር)፣ ለፕሪሚየም በ6 የስራ ቀናት (600 ብር) እና ለኤክስፕረስ አስቸኳይ (800 ብር) በቀላሉ በቴሌብር በመፈጸም አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉ ይሆናል፡፡