✞ ጥር 4 የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ዓመታዊ በዓል
የወንጌላዊ ዮሐንስ ድንቅ ታሪክን አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ለዮሐንስ በደረሰለት ውዳሴ
ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ኮከብን ብለን ጠራንህ፤ የጽድቅ ፀሓይ ያሳደገህ ባጠገቡ (በጉያውም) ያስቀመጠህ ኮከብን ብለን ጠራንህ፤ በአፉ የሳመኽ በመታጠቂያውም ያስታጠቀኽ ኮከብን ብለን ጠራንኽ፤ የተሰወረውን ምስጢር ያሳየኽ የጸጋውን ወንጌል የሰጠኽ ኮከብን ብለን ጠራንኽ፤ ዮሐንስ እንዳንተ ያለ ማን ነው ታማልደን ዘንድ ማለድንኽ።
√ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በዚህ ክፍል ላይ ተጋድሎው ሕይወቱ እንደ ኮከብ የደመቀውን ዮሐንስን አመስግኖታል፤ ይህ ዮሐንስ ቊጥሩ ከ12ቱ ሐዋርያት መካከል ሆኖ የዘብዴዎስ እና የሰሎሜ ልጅ ሲሆን በእኛ ትውፊት እናቱን ማርያም ባውፍልያ ይላታል።
√ ጌታችን ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በታንኳ መረባቸውን ሲያበጁ ዐየ፤ ጠራቸውም እነርሱም ወዲያው ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከትለውታል። [ማቴ. 4፥21-22]
√ ጌታም ኹለቱን ወንድማማቾችን ቦአኔርጌስ ብሏቸዋል፤ ትርጓሜውም የነጐድጓድ ልጆች ማለት ነው። [ማር. 3፥17]
√ ጌታችን ምስጢረ መንግሥትን ለመግለጽ ወደ ታቦር ተራራ ይዞት ወጥቷል፤ በጌቴሴማኒም ምስጢረ ጸሎትን ሲያሳይ ከጌታ ጋር ነበርና "የምስጢር ሐዋርያ" ይባላል።
√ ጌታችን ይወድደው የነበረው ደቀ መዝሙር ርሱ ነውና "ፍቁረ እግዚእ" (የጌታ ወዳጅ) ሲባል በምሴተ ኀሙስም ምስጢረ ቊርባንን ሲመሠርት ከጐኑ የተጠቀመጠው ርሱ ዮሐንስ ነበርና ሊቁ “የጽድቅ ፀሓይ ያሳደገኽ ባጠገቡ ያስቀመጠኽ” ብሎታል፡፡
√ ጌታችን ሲጠራው የ25 ዓመት ወጣት እንደ ነበር ሄሬኔዎስ የተባለ ደቀ መዝሙሩ ጽፏል፡፡
√ ቅዱስ ጳውሎስ “Pillars of the Church- አዕማደ ቤተክርስቲያን” ብሎ ከሚጠራቸው ሐዋርያት አንዱ ዮሐንስ ነው። [ገላ. 2፥9]
[ሊቁ ዮሐንስ አፈ ወርቅና አውግስጢኖስ ስለ ዮሐንስ ሲመሰክሩ]
√ “ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን እስከ መስቀል ድረስ የተከተለ ብቸኛ ሐዋርያ ነውና ጌታም ዮሐንስ ካሳየው ፍቅር ከ100 (መቶ) ዕጥፍ በላይ እናቱን እናት አድርጎ ሰጠው፡፡ ምንኛ የታደለ ሐዋርያ ነው” ይላሉ፡፡ [ዮሐ. 19፥20-27]
√ ጌታችን በጸሎተ ኀሙስ ለደቀ መዝሙርቱ ትሕትናን ሊያስተምር ከእራት በኋላ ተነሥቶ ልብሱን አኑሮ “ወነሥአ መክፌ ዘለንጽ ወቀነተ ሐቌሁ” ይላል ዘርፍ ያላት ዝናር አንሥቶ ወገቡን ታጠቀ ሥራ የምታሠራ የምታስጌጥ ስትኾን ኢዮአብ ወደ ሰልፍ ሲገባ እየለበሳት ይገባ እንደነበረች ያለች ናት፤ ልብሰ መንድያ ይላታል በሺሕ ዘሓ (ድር) የተሠራች ናት።
√ “ወወደየ ማየ ውስተ ንብቲራ ወአኀዘ ይሕጽብ እገሪሆሙ ለአርዳኢሁ ወመዝመዘ በውእቱ መክፌ ዘቀነተ” በመታጠቢያው ውሃ ጨመረ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ ይላል።
√ ይህቺ የታጠቀበትን ለዮሐንስ ወንጌላዊ ሰጥቶት ጌታ በታጠቀበት ቢታጠቅ ሕገ ሥጋ ጠፍቶለታል ፍቁረ እግዚእ ያሰኘው ይኽ ነውና ሊቁ “በመታጠቂውም ያስታጠቀኽ” በማለት አመስግኗል፡፡
√ “በአፉ የሳመኽ” ማለቱ የሮሙ ንጉሥ ጢባርዮስ ቄሳር የጌታን ነገር አይሁድ በግፍ ጠልተው ተመቅኝተው ሰቅለውት እንደሞተ እንደተነሣ እንዳረገ ሰምቶ የጌታዬን እናት ማን ባመጣልኝ እኔ ቋሚ ለጓሚ፤ ሚስቴ ገረድ ደንገጥር በኾንላት ብሎ ተመኘ፤ ተመኝቶም አልቀረ “ወለአከ ኢየሩሳሌም ሰራዊተ ወሐራ ወአዋልደ ብዙኃተ ወኅጽዋነ” ይላል ወደ ኢየሩሳሌም ብዙ ደንገጥሮች ሰራዊትና ጭፍራ እንደዚሁም የሴት ደናግልና ባለሟሎችን በክብር አጅበው ያመጧት ዘንድ ላከ።
√ ጌታም የእናቱን ተድላ ነፍስ እንጂ ተድላ ሥጋን አይሻምና
እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም መንግሥት ክብር የሚበልጥና የሚያስደንቅ የጌትነቴን ክብር ታዪ ዘንድ በጎ ዕረፍት ወዳለበት ወደ ሰማይ አሳርግሽ ዘንድ ተነሥተሸ ቁሚ አላት፤ ከዚያም ወደ ገነት አግብቶ በገነት ላሉ ነፍሳት መድኀኒታችኊ እነኋት ርሷን አመስግኑ ብሏቸው አመስግነዋታል፡፡
በእርሱም ሐዘን እንዳይጸናበት ዮሐንስ ወንጌላዊን ላከለት ከዚያም ንጉሡን ስለ ጌታችን ሥጋዌ አስተማረው፤ ንጉሡም የሚቻልህም ከሆነ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እንዳየኸው ሥዕሉን ሥለህ አሳየኝ አለው፤ ዮሐንስም ንጉሥ ሆይ እሺ በርሱ ላይ የተፈጸመውን ሁሉ ሥዬ አሳይሆለኊ አለው፤ ከዚያም ዮሐንስ በዕለተ ዐርብ ጌታን እንደሰቀሉት አድርጎ ሣለው።
ብፁዕ ዮሐንስም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥዕል ሠርቶ ከፈጸመ በኋላ ራሱን ወደታች ዝቅ አድርጎ የሕያው እግዚአብሔርን ልጅ ሥዕል ተሳለመ፤ በዚችም ዕለት የዚሆ ሥዕል ከናፍር ከብፁዕ ዮሐንስ ከናፍር ጋር ለብዙ ሰዓት ተያይዞ ቆየ ይህም ጽንዐ ፍቅራቸውን ለማጠየቅ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የመድኅን ጌታ ሥዕል ንጉሥና በዚያም የቆሙ ሁሉ እያንዳዳንዳቸው እየሰሙት ወዳጄ ዮሐንስ ዮሐንስ እያለ ድምፅ አሰምቷልና ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ይኽነን ተናገረ፡፡
[ሊቁ አባ ጊዮርጊስ በዚኽ መጽሐፉ ላይ]
የተሰወረውን ምስጢር ያሳየኽ የጸጋውን ወንጌል የሰጠኽ ኮከብን ብለን ጠራንኽ በማለት ለዮሐንስ የተገለጸለትን ሰማያዊ ምስጢር ተናግሯል። ይኸውም ቅዱስ ዮሐንስ ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ነፍስ፣ ንጽሐ ልቡና ተሰጥቶት ሰማያዊ የአንድነት የሦስትነት ምስጢር ተገልጾለት።
“በመጀመሪያው ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” እያለ ወንጌሉን ሲጽፍ መልአኩ ከውቅያኖስ አስኳሉ በወጣለት እንቊላል እየቀዳ ውሃውን ሲያፈስስ ዐየው።
ዮሐንስም በአድናቆት ሆኖ “ምን ያደርግልኻል” ብሎ መልአኩን ጠየቀው፤ “ይህንን ውሃ በዚኽ እየቀዳኊ አፍስሼ ለማድረቅ ነው” አለው፤ ዮሐንስም “ያልቅልኻልን” አለው፤ መልአኩም “ይኽስ ፍጡር ነው ቁም ነገር የለውም ይፈጸማል፤ አንተስ የማይፈጸመውን ባሕርየ እግዚአብሔርን እፈጽማለኊ ብለኽ ጀምረህ የለም” አለው፤ ያን ጊዜ ዮሐንስ “ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ” በማለት ወንጌሉን መጻፍ ጀምሯል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ከወንጌል በተጨማሪ ሦስት መልእክታትን ሲጽፍ፤ በ98 ዓ.ም በፍጥሞ ደሴት ሳለ የዓለም ፍጻሜ ነገር ተገልጾለት ራእዩን ከጻፈ በኋላ ጥር 4 እንደተሰወረ ይነገራል፤ የቅዱስ ዮሐንስ በረከት በዝቶ ይደርብን፡፡
ማጣቀሻ
መጽሐፈ ሰዓታት ንባቡና ትርጓሜው ከመጋቤ ሐዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ
@yetewahedofera@yetewahedofera@yetewahedofera