በዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ የሚገኘው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት "በኢትዮጵያ መልቀቂያ የብሔራዊ ፈተና ውጤት የቅርብ ጊዜ ተለዋዋጭነት ግምገማ" በሚል ርዕስ ለአንድ ዓመት የቆየ ጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል።
ኢንስቲትዩቱ ካቀረባቸው የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች መካከል፣ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ የሚገኘው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይሰጥ የሚለው ይገኝበታል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የማኅበራዊ ልማትና አካታችነት ማዕከል ኃላፊና ከፍተኛ ተመራማሪ ደሳለኝ አንጭሶ (ዶ/ር)፥ የተማሪዎች ውጤት እንዲቀንስ ካደረጉ ቁልፍ ምክንያቶች መካከል የፈተና አሰጣጥ ስርዓቱ መቀየር በተለይ ከከተሞች ራቅ ካሉ አካባቢዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚመጡ ተማሪዎች ላይ የፈጠረው የስነ-ልቦና ችግር ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተፈጠረው የስነ-ልቦና ችግር ምክንያት ጥሩ ውጤት ማምጣት የነበረባቸው ተማሪዎች ውጤት ሳያመጡ መቅረታቸው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡
"ተማሪዎች የባዮሜትሪክ መረጃዎች እንዲሞሉ በማድረግ እንዲሁም በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የደኅንነት ካሜራዎችን በመግጠም የቁጥጥር ስራ በመስራት፣ ተማሪዎች ከሚኖሩበት አካባቢ ሳይርቁ ፈተናውን እንዲፈተኑ ትምህርት ሚኒስቴር የረዥም ጊዜ ዕቅድ ይዞ እንዲሠራ" ምክረ ሐሳብ መቅረቡን ገልፀዋል።
የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ማሻሻል እና ከታች ጀምሮ ጥራት ላይ ሊሰራ እንደሚገባ የገለፁት ኃላፊው፤ የትምህርት ቤት አመራሮች ዕውቀትን መሠረት ባደረገ ሁኔታ ሊመደቡ እንደሚገባም ምክረ ሐሳብ መቅረቡን ተናግረዋል።
በማኅበረሰቡ ዘንድ "ትምህርት ምን ያደርጋል" የሚል ዕሳቤ መቀየር ላይ አፅንኦት ሰጥቶ የለውጥ ሥራ መስራት ይገባል የሚለው በጥናቱ የተለየ ምክረ ሐሳብ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ጥናቱ በፀጥታ ችግር ምክንያት የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎችን እንዳላካተተ ተገልጿል። #Reporter
source :- tikvahuniversity
🌐JOIN : @QesemAcademy