የፍርድ ቤት ውሎ!
በእነ ዶክተር ወንደሰን አሰፋ መዝገብ ስር በሽብር ወንጀል በተከሰሱ ተጠርጣሪዎች ላይ የምስክር ቃል መሰማት ተጀመረ፡፡
የሽብር ወንጀል ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/12 አንቀጽ 3/2 ሀ ላይ የተደነገገውን ህግ ጥሰዋል በሚል የሽብር ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው 51 ተጠርጣሪዎች ላይ የምስክሮች ቃል መሰማት ዛሬ ተጀምሯል፡፡
የምስክር ቃል መሰማት የተጀመረው በአዲስ አበባ ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት ሲሆን በእስር ላይ ካሉት 23 ተከሳሾች ውስጥ አራቱ ማለትም ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እና ዶክተር ገብረአብ አለሙ በህመም ምክንያት እንዲሁም ዮርዳኖስ አለሜ እና ረዳት ፕሮፌሰር ማዕረጉ ባያበይን የታሰሩበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ደግሞ ታራሚዎችን ከቦታ ቦታ እያዘዋወርኩ ነው ማለቱን ተከትሎ ችሎቱ ላይ ሳይቀርቡ መቅረታቸውን የተከሳሾች ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ መናገራቸውን የዘገበው አል አይን ነው፡፡
እንደ ጠበቃ ሰለሞን ገለጻ በዛሬው ችሎት አቃቢ ህግ በሶስት ተከሳሾች ላይ ማለትም ዳዊት እባቡ ፣ሞላልኝ ሲሳይ እና አብርሃም ጌትነት ላይ አምስት ምስክሮችን አቅርቧል፡፡
አምስቱ ምስክሮች በችሎቱ ተገኝተው ቃለ መሀላ የፈጸሙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ሶስቱ ምስክሮች የደረጃ ምስክር ቃላቸውን ወይም የእማኝነት ምስክር ቃል ሰጥተዋል ተብሏል፡፡
ከመስካሪዎች ውስጥ አንዱ የፖሊስ ባልደረባ ሌላኛው ተመሳሳይ ምስክር ደግሞ የተከሳሽ መኖሪያ ቤት አከራይ ሲሆን በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት ቤት ሲፈተሸ ያልተመዘገበ ሽጉጥ መያዙን ለችሎቱ ማስረዳታቸውን፣ ነገር ግን ተያዘ የተባለው ሽጉጥ የክሱ አካል እንዳልሆነ እና በኢግዚቢትነት አለመቅረቡን ጠበቃ ሰለሞን አክለዋል፡፡
አቃቢ ህግ ሁለቱ ቀሪ ምስክሮቹ ከሶስቱ የተለየ የምስክርነት ቃል አይሰጡልኝም በሚል ቃላቸውን እንዳይሰጡ ለችሎቱ ማስረዳቱን ተከትሎ ቃላቸውን እንዳልሰጡም ጠበቃ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡
የአቃቢ ህግ 96 ምስክሮች ቃል መሰማት ቀጠሮ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 17 ቀን 2017 ድረስ እንዲሰሙ ችሎቱ የፈቀደ ሲሆን ነገ እና በቀጣዮቹ ቀናት በተከሳሾች ላይ የምስክሮች ቃል መሰማቱ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡
https://t.me/Tamrinmedia