ቻይና የክብደት መጠናቸው ከ50 ኪሎ ግራም በታች የሆኑ ዜጎቿ ከመኖሪያቸው እንዳይወጡ አሳሰበች
*
በቻይና ሰሜናዊ ክፍል ዝናብ የቀላቀለ ከባድ ነፋስ መከሰቱን ተከትሎ የሰውነት ክብደት መጠናቸው ከ50ኪሎ ግራም በታች የሆኑ ዜጎቿ ከመኖሪያቸው እንዳይወጡ አሳስባለች።
ከሀገሪቱ ደቡባዊ አዋሳኝ ሞንጎሊያ መነሻውን ያደረገው ነፋስ በሰዓት 150 ኪሎ ሜትር በመሸፈን ቤጂንግ፣ ቲያንጂንን እና ሄበይን ጨምሮ የቻይናን ሰሜናዊ ክፍሎች እየመታ ይገኛል።
የነፋስ ጥንካሬ ከ1 እስከ 17 ባለ ደረጃ የሚለካ ሲሆን አሁን ላይ የተከሰተው ከባድ ንፋስ ባለፉት 10 ዓመታት ከተመዘገቡት የመጀመሪያው መሆኑ ተገልጿል።
የተከሰተው ከባድ ንፋስ ደረጃ 13 ሲሆን ዝናብ ፣ በረዶ እና ነጎድጓድ የቀላቀለ መሆኑን የቻይና የአየር ትንበያ ኤጀንሲ ጠቁሟል።
በሁነቱ በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደሌለ ያመላከተው ኤጀንሲው፤ ከ300 በላይ ግዙፍ ዛፎች ተገንድሰው መውደቃቸውን ጠቁሟል።
ይህን ተከትሎ የሰውነት ክብደታቸው ከ50 ኪሎ ግራም በታች የሚመዝኑ ዜጎች በንፋሱ እንዳይወሰዱ በማሰብ ነው ከመኖሪያቸው እንዳይወጡ ማስጠንቀቂያው የተሰጠው።
እንዲሁም ንፋሱ የባሰ አደጋ እንዳያስከትል አስቸኳይ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛል። ዛፎች በቀላሉ እንዳይነቀሉ ማጠናከር ብሎም መቁረጥ፣ ፓርኮች እንዲዘጉ እንዲሁም ወሳኝ እና አስፈላጊ ያልሆኑ በረራዎች እንዲሰረዙም ተደርጓል።
ክስተቱን ተከትሎ የቤጂንግ እና ሌሎች የቻይና ሰሜናዊ አካባቢ ጎዳናዎች ጭር ብለው መዋላቸውን አርቲ በዘገባው አመላክቷል።
@Zena_Adis_Ethiopia