ባንኮች ኒቃብ ለባሽን አናስተናግድም አላሉም። ሴት ፈታሽ አስቀምጠዋል። ንግድ ባንክ ኒቃብ ለባሽ ሴቶችን አስፈላጊ ሲሆን ከመታወቂያ ጋር አይቶ ማመሳከሪያ ክፍል ሁሉ አዘጋጅቷል። መስገጃ ክፍል ጭምር አዘጋጅቷል። ውድድር ያለበት የገንዘብ ጉዳይ ላይ ፖሊሲ ተከልሶ ጭምር ሳይወዱ አማራጮች ሲመቻቹ እያየን ነው። እነዚህ ሁኔታዎች በትምህርት ተቋማት ለሚፈጠረው ችግር መንስኤው የቅንነት ችግር እንጂ ለሽፋንነት የሚቀርቡት ማመሀኛዎች እንዳልሆኑ ያሳያሉ። አዎ የኒቃብ ጉዳይ የሚፈልገው ቅንነት ብቻ ነው። በቅንነት ለተመለከተ ለምንም ነገር እንቅፋት አይሆንም። ለማንም ስጋት አይሆንም። በምእራቡ ዓለም በርካታ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ኒቃብ ሊከለከል ቀርቶ መነጋገሪያ አጀንዳም አልሆነም።
በነገራችን ላይ በኒቃብ ጉዳይ ትልቁ ፈተና ሳይነቁ እንደነቁ የሚያስቡ አንዳንድ ሙስሊሞች ናቸው። ጉዳዩ የመብት ጉዳይ መሆኑን እያወቁ ግላዊ ፍላጎታቸውና ምርጫቸውን እየሰነቀሩ ለጠላት ድንጋይ ያቀብላሉ። ለእርቃን ሩብ ጉዳይ ሴቶች በነፃነት በሚርመሰመሱባቸው ህዝባዊ ተቋማት ውስጥ ኒቃብ ለባሽ ሙስሊማት ተለይተው የመድሎ ሰለባ እየተደረጉ እንደሆነ እያዩ "ኒቃብ ሙስተሐብ ነው" የሚል ፈትዋ ሊሰጡ ከነ እርገጤ ዘንድ ይርመጠመጣሉ። ሰው እንዴት በዚህ ደረጃ የሚኖርበትን ዋቂዕ ይዘነጋል? እንዲህ አይነቱ አካሄድ ጥግ የደረሰ ነፈዝነት ነው። ካልሆነ ግን የተቋማትን አግላይ አካሄድ ለቡድናዊ ምርጫ የመጠቀም ርካሽ ስልት ነው። እነዚህ አካላት በተራ የግለሰብ የዩቲዩብ የግል ሚዲያ ላይ በዚህ መልኩ አንገት የሚያስደፋ ንግግር የሚናገሩ ከሆነ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት ቢሮ ውስጥ ሲገኙ ሊናገሩ የሚችሉትን መገመት ይሰቀጥጣል። ብቻ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ፈተና ብዙ ነው። ከጠላት በፊት አምርሮ ሊፋለማቸው የሚገባቸው ብዙ የራሱ ነ ሆ ለ ሎ ች አሉት። ቢሆንም ተስፋ መቁረጥ አይገባም። መብት በልመና አይገኝምና በልበ ሙሉነት መጋፈጥ ይገባል። ደግሞም - ኢንሻአላህ - አንድ ቀን ይሳካል። በዚህ ላይ ፈፅሞ አልጠራጠርም። በዚህ ላይ ደግሞ ከታዋቂዎች ልፍስፍስ አቋም በላይ የስም የለሽ ወጣቶች ተጋድሎ የበለጠ ውጤት ያመጣል።
Ibnu Munewor
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor