ማለት በልምላሜ ተሸፍነው ደስ ያሰኛሉ ማለት ነው። በምሥጢር ስለክርስቶስና ስለትሩፋን የሚተረጎምበት መንገድም አለ። (የበለጠ አንድምታ ዳዊትን ይመልከቱ)።
▶️፴፫. "ሰማያዊ ንጉሥ በላይዋ ባዘዘ ጊዜ በሰልሞን ላይ በረዶ ዘነበ። የእግዚአብሔር ተራራ የለመለመ ተራራ ነው። የጸና ተራራና የለመለመ ተራራ ነው። የጸኑ ተራራዎች ለምን ይነሣሉ? እግዚአብሔር ይህን ተራራ ያድርበት ዘንድ ወደደው። በእውነት እግዚአብሔር ለዘላለም ያድርበታል" ይላል (መዝ.68፥14-17)። የዚህ ንባብ ትርጓሜው ምን ይሆን?
✔️መልስ፦ ይህ ማለት እግዚአብሔር ሰልሞን በሚባል ሀገር ላይ በረዶን አዘነበ ማለት ነው። የእግዚአብሔር ተራራ፣ የጸና ተራራ፣ የለመለመ ተራራ የተባሉ ትሩፋን ናቸው። በሌላ አተረጓጎም ምእመናን ናቸው። እግዚአብሔር በትሩፋን እስራኤላውያን በረድኤት እንዳደረ ለምእመናን ደግሞ ልጅነትን ሰጠ ማለት ነው።
▶️፴፬. "ወጣቱ ብንያም በጕልበቱ በዚያ አለ። ገዦቻቸው የይሁዳ አለቆች የዛብሎን አለቆችና የንፍታሌምም አለቆች። አቤቱ ኃይልህን እዘዝ። አቤቱ ይህንም ለእኛ የሠራኸውን አጽናው" ይላል (መዝ.68:27-28)። ይህ መቼና ሰለምን የተዘመረ ነው?
✔️መልስ፦ ከብንያም ነገድ የሚወለዱትን ሁሉ ብንያም ብሎ መጥራት በመጽሐፍ ቅዱስ የተለመደ ነው። የይሁዳ አለቆች፣ የዛብሎን አለቆች፣ የንፍታሌም አለቆች ያላቸውም በዳዊት ዘመን የነበሩ ከእነርሱ ተወልደው ነገዱን በአለቅነት የሚመሩትን ሰዎች የሚያመለክት ነው። የተዘመረው በዳዊት ነው። ለምን ተዘመረ ለሚለው በእርሱ ዘመን ለነበሩ ለእነዚህ ነገድ ተወላጅ ሰዎች ነው።
▶️፴፭. "አቤቱ ውኃ እስከ ነፍሴ ደርሶብኛልና አድነኝ። በጥልቅ ረግረግ ጠለቅሁ መቋሚያም የለኝም። ወደ ጥልቅ ባሕር ገባሁ ማዕበልም አሰጠመኝ። በጩኸት ደከምሁ ጕሮሮዬም ሰለለ። አምላኬን ስጠብቅ ዓይኖቼ ፈዘዙ" ይላል (መዝ.69፥1-3)። ትርጓሜው ምንድን ነው?
✔️መልስ፦ ይህ ስለመቃብያን የተነገረ ነው። ከላይ የተጠቀሱት ሁሉ ከባድ መከራ ደረሰብኝ ለማለት የተገለጹ ናቸው። አምላኬን ስጠብቅ ዓይኖቼ ፈዘዙ ማለት ረድኤቱን ስጠባበቅ ቆየሁ ማለት ነው።
▶️፴፮. "በከንቱ የሚጠሉኝ ከራሴ ጠጕር በዙ። በዓመፅ የሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ በረቱ። በዚያን ጊዜ ያልቀማሁትን መለስሁ" ይላል (መዝ.69፥4)። በዚያን ጊዜ ያልቀማሁትን መለስሁ ሲል ምን ማለት ነው?
✔️መልስ፦ ያልተበደርኩትን ተበድረሀል እያሉ አስከፈሉኝ ማለት ነው። ወይም ያልቀማሁትን ቀምተሀል ብለው አስከፈሉኝ ማለት ነው።
▶️፴፯. "ስለ አንተ ስድብን ታግሻለሁና እፍረትም ፊቴን ሸፍናለችና። ለወንድሞቼ እንደ ሌላ ለእናቴ ልጆችም እንደ እንግዳ ሆንሁባቸው። የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቋልና። ነፍሴን በጾም አስመረርኋት ለስድብም ሆነብኝ። ማቅ ለበስሁ ምሳሌም ሆንሁላቸው። በደጅ የሚቀመጡ በእኔ ይጫወታሉ ወይን የሚጠጡ እኔን ይዘፍናሉ" ይላል (መዝ.69፥7-12)። ይህን ንባብ ቢያብራሩልኝ።
✔️መልስ፦ ይህ ስለመቃብያን የተነገረ ነው። መቃብያን ስለእግዚአብሔር ስም ስድብን እንደታገሡ፣ እፍረትን እንደተቀበሉ ያስረዳል። እንዲሁም በሦስቱ ከሓድያን ካህናት መከራ መቀበላቸውን ለመግለጽ ለወንድሞቼ እንግዳ ሆንኩባቸው ብለዋል። መቃብያን አንጥያኮስ በቤተ መቅደስ የጣዖት መሥዋዕት ሲሠዋ አይተው ለእግዚአብሔር ሕግ መቅናታቸውን ለመግለጽ የቤትህ ቅንዐት በላኝ አሉ። በደጅ የሚቀመጡ በእኔ ይጫወታሉ ወይን የሚጠጡ እኔን ይዘፍናሉ ማለት የአንጥያኮስ ወገኖች ወይን እየጠጡ ሲጫወቱ በመቃብያን ይተርቱ ነበርና ነው።
▶️፴፰. "እንዳይውጠኝ ከረግረግ አውጣኝ፤ ከሚጠሉኝና ከጥልቅ ውኃ አስጥለኝ። የውኃው ማዕበል አያስጥመኝ። ጥልቁም አይዋጠኝ። ጕድጓድም አፉን በእኔ ላይ አይዝጋ" ይላል (መዝ.69፥14-15)። ትርጓሜው ምንድን ነው?
✔️መልስ፦ ይህ ስለ መቃብያን የተነገረ ነው። ረግረግ፣ ጉድጓድ፣ ጥልቅ የተባሉ አንጥያኮስና ሠራዊቱ ናቸው። እነዚህ ከሚያመጡት መከራ አድነን እያሉ መቃብያን ይጸልያሉ ማለት ነው።
▶️፴፱. "ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ። ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ። ማዕዳቸው በፊታቸው ለወጥመድ ለፍዳ ለዕንቅፋት ትሁንባቸው። ዓይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ። ጀርባቸውም ዘወትር ይጕበጥ። መዓትህን በላያቸው አፍስስ። የቍጣህ መቅሠፍትም ያግኛቸው። ማደሪያቸው በረሃ ትሁን በድንኳኖቻቸውም የሚቀመጥ አይገኝ" ይላል (መዝ.69፥21-25)። ይህን ንባብ ቢያብራሩልኝ።
✔️መልስ፦ ይህ ስለክርስቶስ የተነገረ ነው። ክርስቶስ ሰውን ለማዳን በመስቀል በተሰቀለ ጊዜ አይሁድ ሐሞት እንዳጠጡት ያመለክታል። ከዚያ ቀጥሎ ያለው እርግማን በክፉዎች አይሁድ ይድረስባቸው ማለት ነው። ይህም ብዙው በ70 ዓመተ ምሕረት በጥጦስ ደርሶባቸዋል።
▶️፵. "ነገር ግን ክብሬን ይሽሩ ዘንድ መከሩ በጥሜም ሮጥሁ" ይላል (መዝ.61፥4)። በጥሜም ሮጥሁ ይልና ዕብራይስጡ ሐሰትን ይወድዳሉ ይላል የትርጉም ለውጥ አያመጣም?
✔️መልስ፦ በጥሜም ሮጥኩ ማለት በደል ሳልሠራ ወደ ጽርዕ ተማረክሁ ማለቱ ነው። ማየ ኃጢአትን አለመጠጣቱን በጽምእ መስሎ ተናገረ። ዕብራይስጡ ሐሰትንም ይወዳሉ ያለው በምሥጢር ክብሬን ይሽሩ ዘንድ መከሩ ካለው ጋር አንድ ስለሆነ የትርጉም ለውጥ አያመጣም።
▶️፵፩. "አቤቱ ፈትነኸናልና ብርንም እንደሚያነጥሩት አንጥረኸናልና። ወደ ወጥመድ አገባኸን። በጀርባችንም መከራን አኖርህ። በራሳችን ላይ ሰውን አስረገጥኸን። በእሳትና በውኃ መካከል አለፍን ወደ ዕረፍትም አወጣኸን" ይላል (መዝ.65፥10-12)። የዚህ ንባብ ትርጓሜ ምንድን ነው?
✔️መልስ፦ ዳዊት ስለእስራኤላውያን ከቀድሞ ጀምሮ የነበረውን እያወሳ ይናገራል። ስለዚህ ብርን እንደሚያነጥሩት አንጥረኸናል ማለት በመከራ ፈትነኸናል ማለት ነው። ወደ ወጥመድ አገባህን ማለት ወደ ግብፅ ወሰድከን ማለት ነው። በጀርባችን መከራን አኖርክ ማለት በዚያ መከራን እንድንቀበል አደረግከን ማለት ነው። በእሳትና በውሃ መካከል አለፍን ወደ እረፍትም አወጣህን ማለት ባሕረ ኤርትራን አሻግረህ ወደ ከነዓን አገባህን ማለት ነው።
▶️፵፪. "ከዕጣንና ከወጠጤዎች ጋራ ለሚቃጠል መሥዋዕት ፍሪዳን አቀርባለኹ። ላሞችንና ፍየሎችን እሠዋልኻለኹ" ይላል (መዝ.65፥15 )። ወጠጤ ምን ማለት ነው?
✔️መልስ፦ ወጠጤ የሚባለው ከግልገልነት ከፍ ያለ ከአውራነት ያነሠ መካከለኛው ወንድ ፍየል ነው።
▶️፵፫. "እግዚአብሔር ይማረን ይባርከንም ፊቱንም በላያችን ያብራ" ይላል (መዝ.66፥1)። ፊቱንም በላያችን ያብራ ሲባል ምን ማለት ነው?
✔️መልስ፦ ፊቱን በላያችን ያብራ ማለት ረድኤቱን ይግለጽልን ረድኤቱን ይስጠን ማለት ነው።
▶️፵፬. "እግዚአብሔርን በጉባኤ ጌታችንንም በእስራኤል ምንጭ አመስግኑት" ይላል (መዝ.67፥26)። በእስራኤል ምንጭ ሲባል ምን ማለት ነው?
✔️መልስ፦ ከዚህ የእስራኤል ምንጭ ያለው የኤርትራ ባሕርን ነው። ስለዚህ ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ ያሻገረ እግዚአብሔርን በጉባኤ አመስግኑት ማለት ነው።
© በትረ ማርያም አበባው
✝️የዩቲዩብ ቻናሌ:- ንሕነ ዘክርስቶስ
https://youtube.com/@edenawizechristos?si=6V4y-73OM3LTzhAf ነው።
🌻የፌስቡክ ገጼ Betremariam Abebaw
https://www.facebook.com/profile.php?id=100075547015721 ነው።