ሞባይል ስልክ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ አገልግሎቱን ለማግኘት ያስፈልጉ የነበሩት አስገራሚ መስፈርቶች (ከ
Wasihune Tesfaye የFacebook ገፅ የተወሰደ)
ግንቦት 9, 1991 ዓ.ም ቴሌ ለወራት ሲያስተዋውቅ የከረመውን የሞባይል ስልክ አገልግሎት መስጠት የሚጀምርበት ቀን ነበር።
እና በዚያን እለት ግንዛቤው የነበራቸው ባለሃብቶች ለኢትዮጵያ አዲስ የሆነውን ሞባይል ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ወደ ቴሌ ቢሮዎች በጠዋት መምጣት ጀምረዋል።
በቢሮው መግቢያ ላይ አንድ ማስታወቂያ ተለጥፏል። ሲም ካርድ ለመውሰድ ሲመጡ ኦሪጅናል እና ኮፒ የመኖሪያ ቤት ካርታ ይዘው መምጣት እንዳለባቸውና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን የቤት ካርታቸውን ማስያዝ እንዳለባቸው የሚገልጽ ማስታወቂያ ።
በነገሩ የተስማሙና ቀድመው መረጃውን ያገኙ ሰዎች የቤት ካርታቸውን እያስያዙ ለሲም ካርዱና ቴሌ በብቸኝነት ያስመጣው የነበረውን ይህን በፎቶው የሚታየውን ትልቅ የኢሪክሰን ቀፎ 5ሺ ብር አካባቢ እየከፈሉ መውሰድ ጀመሩ። የዚያኑ እለትም የመጀመሪያዎቹ ባለሞባይሎች በአዲስ አበባ ከተማ ይታዩ ጀመር።
እነዚህ ጥቂት የከተማችን ባለሞባይሎች በሱሪያቸው ቀበቶ ላይ በታሰረ የቆዳ ቦርሳ ያንጠለጠሉትን ትልቅ ሞባይል እያየ ማን ያልተገረመ ነበር። በነገራችን ላይ ከነዚህ ቴሌ ከሚያስመጣቸው ስልኮች ውጭ በሌላ ቀፎ መጠቀም ፈፅሞ የተከለከለ ሲሆን በኢትዮጵያ ብቸኛው የሞባይል ቀፎ ሻጭ ቴሌ ብቻ ነበር ።
ቆየት ብሎ ታድያ የሞባይል ስልክ መጠቀም ፈልገው ነገር ግን የቤት ካርታ የሌላቸው ባለሃብቶች ቅር መሰኘታቸውን የተረዳው ቴሌ የቤት ካርታ ላላቸው የተመዘገቡ ባለሃብቶች ስልክ ሰጥቶ እንደጨረሰ ካርታ ለሌላቸው መስመር ፈላጊዎች 50 ሺህ ብር በማስያዝ ሲም ካርድ መውሰድ እንደሚችሉ አስታወቀ።
በጥቂት ወራት እድሚው የሞባይል ስልክን አስፈላጊነቱን የተረዱ ሰዎች በርከት በማለታቸው 50 ሺ ብር አስይዞ ሞባይል የሚወስደው የ አዲስ አበባ ባለሃብት ተበራከተ።
በዚያን ጊዜ የሞባይል አገልግሎት የሚሰራው በ 100KM ራዲየስ ብቻ ነበረና የሞባይል ስልክ ብቸኛ መናሃሪያ አዲስ አበባ ከተማ ብቻ ነበረች። ( ከአዲስ አበባ ከመቶ ኪሎ ሜትር በላይ ከራቀ ሞባይሉ አይሰራም።) 🤔
ከዚህ በሁዋላ ቴሌ ለብዙ ወራት ሲም ካርድ መሸጥ አቁሞ ላሉት ጥቂት ባለሞባይሎች አገልገሎቱን ለማዳረስ ኔት ወርክ በማስፋፋት ስራ ላይ ተጠምዶ ከቆየ በሁዋላ ከአዲስ ማስታወቂያ ጋር ብቅ አለ።
ቴሌ በአዲሱ ማስታወቂያው ብዛት ያላቸውን ሲም ካርዶች ያለምንም ማስያዣ በቀበሌ መታወቂያ ብቻ መስጠት ሊጀምር እንደሆነና በተጨማሪም የሞባይል ተጠቃሚው ቴሌ በብቸኝነት ከሚሸጠው ኤሪክሰን ስልክ ውጭ በፈለገው ስልክ መጠቀም እንደሚችል ገልጾ ምዝገባ ጀመረ። በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች አገልግሎቱን ለማገኘት በመመዝገባቸውም ሲም ካርድ ለማገኘት ከ6 ወር እስከ አንድ አመት መጠበቅ ግድ ነበር ።
በዚህ ወቅት የሲምካርድ ዋጋ ከአምስት ሺህ ብር ወርዶ 550 ብር ከዚያም 440 ብር፣ 365 ብር፣ 169 ብር ይሸጥ ነበር። ይህን ተከትሎም የሞባይል ቀፎዎች በግለሰብ ሱቆች ውስጥ መሸጥ ጀመሩ ።
ዛሬ ላይ ሁሉ ነገር ቀላል ሆኖ ከየትኛውም ሱቅ ልንገዛው የምንችል እቃ ከመሆኑ በፊት ሲም ካርድ ተመዝገበው ደርሷቸው የቀፎ መግዣ ካጡ ሰዎች ሲሙን በወር ከ70 እስከ 100 ብር መከራየት ይቻልም ነበር ።
እናንተስ መጀመሪያ የያዛችሁት ስልክ ምን አይነት ነበር? ለመጀመሪያ ቀን ስልክ ስታወጡ የነበራችሁ ስሜት?
በመጀመሪያ ቀን የት ደወላችሁ? ከሞባይል ጋር በተያያዘ ያጋጠማችሁ?
Source link
click_here