🟢 🟡 🔴
የካቲት 23 | በዚህች ቀን #ቅዱስ_ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት አባቶቻችንን አድዋ ላይ የረዳበት ነው።በ1854 ዓ.ም ጀግናው ገበየሁ ጣልያንን ካሸነፉ በኋላ እንደገና ቅኝ ለመግዛት፣ ሃይማኖት ለማጥፋት የጣልያን ሰዎች መጡ።
በ1888 ዓ.ም መስከረም 7 ቀን፥ ሣህለ ማርያም (አጤ ምኒልክ) አዋጅ አስነገሩ። በኋላም ወደ አድዋ ተጓዙ።
በዚያም የሣህለ ማርያም ሚስት ወለተ ሚካኤል (እቴጌ ጣይቱ) በንጉሥ ትእዛዝ ታቦተ #ቅዱስ_ጊዮርጊስን አስይዘው ከካህናቱ ጋር ሔዱ።
በዚያም ጊዜ የአክሱም ጽዮን መነኰሳትና ካህናት የእመቤታችንን ሥዕል ይዘው ወደ ንጉሡ ወደ ምኒልክ መጥተው ከሊቀ ጳጳሱ ከነአቡነ ማቴዎስ ጋር ተቀላቀሉ ከዚያም ሌሊቱን ሙሉ ጸሎት ምሕላ ሲያደርሱ አደሩ።
ቅዳሜ ማታ ለእሑድ አጥቢያ የካቲት 22 ቀን፥ ንጉሡ ሣህለ ማርያም (ምኒልክ) የጦር ልብሱን ለብሰው ከሠራዊቱ ጋር ወደ ጦር ግንባር ሄዱ። ከዚያም ከሮማውያን የጠላት ጦር ጋር ተገናኝቶ ከሌሊቱ ዐሥራ አንድ ሰዓት ጦርነቱን ጀመረ።
በዚያም ጊዜ ንጉሡ ሣህለ ማርያም (ምኒልክ) በጦርነቱ መካከል ሳለ ሊቀ ጳጳሱ አባ ማቴዎስ እንዲሁም የአክሱም መነኰሳትና ሌሎቹ ካህናት በሙሉ ታቦተ ጊዮርጊስንና ሥዕለ ማርያምን ይዘው ከንጉሡ በስተኋላ በደጀንነት ቆመው ጸሎተ ምህላ ያደርሱ ነበር።
ንግሥቲቱ ወለተ ሚካኤል (እቴጌ ጣይቱም) በጸሎት ጊዜ በመዓልትም በሌሊትም ከእነርሱ አትለይም ነበር። የጽዮን አገልጋዮችም በእግዚአብሔር የሕጉ ታቦት ፊት መለከት ይነፉ ነበር።
በየካቲት 23 ቀን በሮማውያንና በኢትዮጵያውያን መካከል ከፍተኛ ጦርነት ሆነ። በዚህም ጊዜ በሰማይ ታላቅ ተአምር ተደረገ። የቀስተ ደመና ምልክት ታየ። ከዚያም ከቀስተ ደመናው ውስጥ መልኩ አረንጓዴ የመሰለ ጢስ ይወጣ ነበር። ከዚህም ጢስ ውስጥ እንደ ክረምት ነጎድጓድ ያለ ድምጽ ተሰማ።
ከዚህም የነጎድጓድ ድምጽ የተነሣ በሮማውያን ወታደሮች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤና ሽብር ሆነ ለመዋጋት አልቻሉም። ይልቁኑ ኃያሉ ገባሬ ተአምር ማር ቅዱስ ጊዮርጊስ በአምባ ላይ ፈረሱ ተቀምጦ ከነፋስ ሩጫ ይልቅ እየተፋጠነ በአየር ላይ በተገለጸ ጊዜ በግንባራቸው ፍግም እያሉ ወደቁ።
"
የኢትዮጵያ ሕዝብ አምላካቸው ሊረዳቸው መጣ እንግዲህ ማን ያድነናል" አሉ፤ ምድርም ጠበበቻቸው።
በዚህን ጊዜ የኢትዮጵያ ሠራዊት የሮምን የጦር ሠራዊት ፈጁዋቸው የተረፉትንም ማረኳቸው ፈጽመውም እስኪያጠፏቸው ድረስ በሮማውያን ላይ በእግዚአብሔር ሥልጣን የኢትዮጵያውያን እጅ እየበረታ ሄደ።
ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሣህለ ማርያም (ምኒልክ) በእግዚአብሔር ኃይልና በተአምራት አድራጊው በቅዱስ ጊዮርጊስ ተራዳኢነት የሮማውያንን የጦር ሠራዊት ድል አድርገው የድል አክሊል ተቀዳጅተው ተመለሱ።
ምንጭ፦ ተአምረ ቅዱስ ጊዮርጊስ
T.me/Ewnet1Nat