#ስለ_ወንድማችን_አክሊል_አንዳንድ_ነገሮች!
#ወንድማችን_አክሊል_ጌታችን_ካረገ_በኋላ_አብን_ያመልካል_አላልኩም_የሚል_መልእክት_ስለላከልኝ_ዋናው_ጉዳይ_መስተካከሉ_ስለ_ኾነ_አንሥቼዋለሁኝ🙏
በመጀመሪያ አክሊልን ያወኩት በቲክቶክ ሲያስተምርና ለመ*ና*ፍ*ቃን መልስ ሲሰጥ ነው። በዚህ ረገድ በጣም የሚበረታታ ሥራን ሠርቷል፤ እየሠራም ይገኛል። በሚያቀርባቸው የሃይማኖት ትምህርቶች በቲክቶክ የሚከታተሉትን በውጭም በሀገር ውስጥም ያሉ ብዙ ምእመናንን አጽንቷል፤ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንዲረዱ ረድቷቸዋል። ይህም ብቻ ሳይኾን በኑ*ፋ*ቄ እሳት የነደዱትን መ*ና*ፍ*ቃንንም ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱ የበኩሉን አስተዋጽዖ አበርክቷል፤ አሁንም እያበረከተ ይገኛል። ይህን አገልግሎቱን የተረዳ ሰው ይጸልይለታል፤ እግዚአብሔር ከክፉ እንዲጠብቀው ያስበዋል።
እንደሚታወቀው አንድ ሰው አንድ መልካም ሥራ ሊሠራ ሲነሣ ብዙ ፈተናዎች ሊገጥሙት እንደሚችል ግልጽ ነው። ይህ ፈተና በመጀመሪያ ከራስ የሚመነጭ ነው። ይኸውም ስለ ራስ ያለ ቦታና ደረጃ ለወጥ እያለ የመሄድ ፈተና ቀዳሚው ነው። ይህ በእንዲህ ዓይነት ትጉህ አገልግሎት ላይ ባሉ ኹሉም ላይ ማለት እስኪቻል ድረስ የሚመጣ ፈተና ነው። ይህን ፈተና ተፈታኞቹ አንዳንዴ ላይረዱት ኹሉ ይችላሉ፤ አደገኛ የሚያደርገው ደግሞ ይህ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በምናቀርበው ነገር የተደሰቱ አካላት የሚያቀርቡልን ገነን ያለ ምስጋናና አክብሮት ሌላው የሕይወት ፈተና ይኾናል። ከእነዚህ ጋር ተያይዞ ደግሞ የበጎ ነገር ኹሉ ጠላት የኾነ ሰይጣን የሚያመጣብን ሰወር ያለ ወይም ግልጽ የኾነ ፈተና ይኖራል። ይህን መረዳት ተገቢ ነው። እንግዲህ ይህን በአጭሩም ቢኾንም ከግምት ውስጥ በማስገባት በአገልግሎት ላይ ላሉ ወንድሞቻችን ልንጸልይና ከእኛ እንደ ክርስቲያን የሚጠበቅብንን ልናደርግ ይገባል።
ኹለተኛው ነጥቤ - የወንድሜን አኬን አካሄድ ማዕከል ያደረገ ይኾናል። ይኸውም በአንድ በኩል አንድን ነገር ለማስረዳት የሚገልጽበት መንገድ ጸነን ማለት ሲኾን በሌላ በኩል ተደጋጋሚ ጊዜ ያቀረባቸውን የስሕተት ትምህርቶችን የሚመለከት ነው። እኔ ከእርሱ ጋር በአካል በተደጋጋሚ ጊዜ ባወራን ጊዜ ያገኘኹትና እንደ ወንድም ደጋግሜ መክሬው ግን እስካሁን አቋም አድርጎ የያዛቸው የስሕተት ትምህርቶችን በቅደም ተከተል ላስቀምጥ፦
1) ነገረ ክርስቶስን በተመለከተ ያቀረበው ስሕተት ነው።
ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋው ወራት አብን አምልኳል የሚለው ነው። ይህን በተመለከተ እጅግ ስላስደነገጠኝ በጣም ለምኜዋለሁኝ። እባክህን ይህ ክሕደት ነው ተስተካከል ብዬዋለሁኝ በጓደኞቹ ፊት በጉዳዩ የምችለውን ኹሉ ለማለት ሞክሬያለሁኝ። እርሱ ግን ሚዲያ ላይ ከእንግዲህ ወዲህ አላነሣውም ቢኾንም ግን አቋሜ ነው ብሎኝ ነበር። ለዚህ ስሕተት መነሻ ያደረገውም ዮሐ 4፥21-22 ላይ ቅዱስ ቄርሎስ ያብራራውን እና አምብሮስ ዘሚላን ያለውን ነበር። በአቅሜ ለማስረዳት ሞክሬ ነበር። ያልኩትን አሁን አሻሽሎት ከኾነ ተመስገን ነው የምለው። ካልሆነ ግን በፍቅርና ክርስቲያናዊ በኾነ መንገድ እንዲያስተካክል ተማኅጽኖዬን በትሕትና በአደባባይ አቀርባለሁኝ።
2) ለኢየሱስ ክርስቶስ ከተዋሕዶ በኋላ አብ አምላኩ ነው የሚል አንዲት አጠር ያለች ቪዲዮ ሠርቶ ያ ቪዲዮ በብዙዎች ዘንድ ውዝግብን ፈጥሮ እንደ ነበር አስተውሳለኹኝ። ሙስሊሞችም አኬ ማለት ባልፈለገው መንገድ አጣመው ሲያራግቡት ነበር። ወንድማዊ በኾነ መንገድ በተደጋጋሚ ይህንም ጉዳይ በተመለከተ አውርተናል። ቪዲዮውንም እንዲያጠፋ ጽኑ ልመናዬን ከተግሣጽ ጋር በአካል አቅርቤለታለሁኝ። ኋላ ሌሎች መምህራንም ኾነን ተሰብስበን መክረነው ያን ቪዲዮ እንዳጠፋ ነግሮኝ ነበር። አቋሙ ግን እንደ ጸና ቀጥሏል። አብ ለኢየሱስ ከተዋሕዶ በኋላም አምላኩ ነው ማለት ምን ማለት ነው? ሥግው ቃል አንድ ከኾነና ሥጋን በመዋሐዱ ምክንያት ሥግው ቃል ፍጡር ነው የማይባል ከኾነ እንዴት ለሥግው ቃል አብ አምላኩ ሊባል ይችላል? በመጻሕፍት አምላኩ የተባለውን በጥንቃቄ ኾነን ቃል የተዋሐደው ሥጋ ፍጡር መኾኑንና ከተዋሕዶም በኋላ ያ ሥጋ አለመለወጡን ለማስረዳት መኾኑን እንገልጻለን እንጂ ከተዋሕዶ በኋላ ቃል የተለየው ዕሩቀ መለኮት የኾነ ሥጋ እንዳለ አድርገን አናምንም።
ወንድሜ አክሊል ግን "ቃል የተዋሐደው ሥጋ ስላልተለወጠ አሁንም ያንሳል" ብሎ እንደሚያምን ነግሮኝ ነበር። አምላኬም ያለው በሥጋው ነው፤ ሥጋው ያንሣልና ብሎኝ ነበር። ይህ ደግሞ ምንታዌ ነው። ሥጋ ምንም እንኳን ፍጡርነቱን ባይለቅም ከተዋሕዶ በኋላ ከቃል ስለማይለይ ያንሣል አይባልም። ያንሣል የሚለውን ስሑት ትምህርት አባቶቻችን አውግዘዋል። አባ ጊዮርጊስ በመጽሐፈ ምሥጢር፤ ሊቃውንት በመዝገበ ሃይማኖት ይህ ትምህርት የልዮናውያን እንደ ኾነና በኛ ዘንድ ተቀባይነት እንደ ሌለው አንሥተዋል። ሥጋው ያንሣል ማለት በአንድ በኩል ከመለኮቱ ተለይቷል የሚያሰኝ ሲኾን በሌላ በኩል ያመልካል እንጂ አይመለክም የሚያሰኝ ነው። ይህ ደግሞ ተቀባይነት የለውም። በቀጥታ ምንታዌን የሚያስረዳ ነውና ይልቅስ በአበው ትምህርት ያለው ሥጋ ያለመለያየት በተዋሕዶ ከቃል ጋር አንድ ስለ ኾነ ይመለካል የሚል ነው።
3) ከመ*ና*ፍ*ቃን ጋር ሲወያይ "ለሥግው ቃል አንድ ፈቃድ እንዳለው ነገር ግን የሥጋ ፈቃድ ለመለኮት ፈቃድ ለዘላለም ሲገዛ እንደሚኖር" በተደጋጋሚ ጊዜ አንሥቶ ስምቼዋለሁኝ። ይህም የምሥራቅ ኦርቶዶክሶች ትምህርት ነው። እነርሱ ኹለት ፈቃድ አለ፤ አንዱ ገዥ (የመለኮት ፈቃድ) ሌላኛው ተገዥ (የትስብእት ፈቃድ) ብለው ያምናሉ። መነሻቸው የባሕርይ ተዋሕዶ ስለሌለ ከኹለት ባሕርይ ኹለት ፈቃድና ኹለት ግብር ይመነጫል የሚል አቋም ስላላቸው እንዲያ ብለው ያምናሉ። እኛ ግን ከኹለት ፈቃድ የተገኘ አንድ ፈቃድ ብለን ስለምናምን በሥግው ቃል ውስጥ የምንከፋፍለው ፈቃድ የለም። ፈቃዱ ከኹለት የተገኘ አንድ ነው። ይሄ የመለኮት ይህ ደግሞ የትስብእት ተብሎ ተለያይቶ ፈጽሞ አይነገርም። ይህን አድማሱ ጀንበሬና በመድሎተ አሚን፤ አለቃ አያሌው መች ተለመደና ከተኩላ ዝምድና በሚል መጽሐፋቸው አንሥተውታል። አንዳንድ ቅዱሳን ሊቃውንት በጥንቃቄ የሥጋ ፈቃድ እንዳልጠፋ ለማስረዳት ያነሡት እንጂ እንደ ኬልቄዶናውያን ከፋፍሎ አንዱ ገዥ ሌላው ተገዥ በሚያሰኝ መንገድ እንድንረዳ ለማድረግ ፈጽሞ አይደለም።
4) "ቃል የተዋሐደው የጎሠቆለ ሰውነትን ነው" ብሎ አውርተንበት ነበር። ይህን የሚመስል አገላለጽ ያቀረቡ ሊቃውንትን ሐሳብ እንዴት መረዳት እንዳለብን አስረድቼው በጊዜው ከዲያቆን ብርሃኑ አድማስም ጋር እንዲያወሩ አድርጌ መ/ር ብርሃኑ በዚህ እና በእመቤታችን ጉዳይ (የጎሠቆለ ሰውነትን ለብሳለች አልለበሰችም በሚለው) ጽሑፍ ጽፎ በቴሌግራም ልኮለት ነበር። እኔም ከመ/ር ብርሃኑ አስቀድሜ ተው አክሊል አካሄድህ ጥሩ አይደለም ብዬ ረዘም ያለ የማብራሪያ ጽሑፍ ከዓመት ከስድስት ወር በፊት ልኬለት ነበር፤ በተጨማሪ መምህር ግርማ ባቱን ጉዳዩን ነግሬያቸው ተገናኝተው እንዲነጋገሩ አሳስቤ የላኩለትንም ጽሑፍ ለመምህር ግርማ አያይዤ ልኬ አሳይቼው ነበር። ወንድሜ አክሊል ግን እስካሁን ከአቋሙ አልተንቀሳቀሰም።
✨✨✨✨✨✨
✝️#
ድምፀ_ተዋህዶ✝️
✨✨✨✨✨✨