ገብርኤል መልአክ - የመሲሑ ምስክር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስማቸው የተጠሩና በስም የታወቁ መላእክት ኹለት ብቻ ናቸው፤ እነርሱም ሚካኤል (ዳን. 10፥13፤ ይሁ. 9፤ ራእ. 12፥7) እና ገብርኤል (ዳን. 8፥16፤ 9፥21)። ከእነዚህ መላእክት ውጭ በስም ተጠቅሰው የሚታወቁ ሌሎች መላእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሉም። እኒህ መላእክት በቀደመው ኪዳን ሕዝብ ውስጥ እጅግ የታወቁና ስሞቻቸው በተደጋጋሚ የተጠቀሱ መላእክት ናቸው።
ገብርኤል ማለት የስሙ ትርጓሜ “እግዚአብሔር የእኔ ጀግና ነው” ወይም “የእግዚአብሔር ኃያል ሰው” ወይም “የእግዚአብሔር ሰው” ማለት ነው። ይህንም ትርጓሜ ሊያገኝ የቻለው በሰው አምሳል ለሰዎች የተገለጠ የእግዚአብሔር መልአክ በመኾኑ ሊኾን ይችላል፤ መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ገናም በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ፤” (ዳን. 9፥21 አጽንዖት የእኔ) እንዲል።
በብሉይ ኪዳንም ኾነ በአዲስ ኪዳን፣ የዚህ መልአክ አገልግሎት የተገለጠ ነው።
1. ለነቢዩ ዳንኤል የእግዚአብሔር ቃል ለመተርጐምና የሚመጣውን ለመግለጥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፤ (ዳን. 8፥15-26፤ 9፥21-27)። በዚህ ክፍሎች ላይ ዳንኤል ያየው ራእይ የንጉሠ ነገሥት ግዛቶች በጦርነት ላይ፣ ቅድስቲቱን ከተማ ለማግኘት በሚያደርጉት ውጊያ ውስጥ ያሉትን ክንውኖች ዳንኤል እንዲረዳ ያብራራለታል ወይም ይተረጉምለታል።
በተለይም በክርስቶስ ቀዳማይ ምጽአትና ዳግማይ ምጽአት ጋር በተገናኘ ስለሚነሡ ተቃዋሚዎች ለዳንኤል በምሳሌያዊ መንገድ የተነገሩትን እያብራራ ይነግረዋል። በምዕራፍ ስምንትና ዘጠኝ ላይ ለዳንኤል የሚተረጕማቸው ራእያት መጠቃለያ ዐሳባቸው፣ የመሲሑ ተቃዋሚዎች ምንም ያህል ብርቱና ኃያላን፣ አሸናፊዎች ቢመስሉም፣ ነገር ግን በፍጻሜያቸው በመሲሑ ይሸነፋሉ፤ ይደመሰሳሉ የሚል ነው።
2. የመጥምቁ ዮሐንስን መወለድ አብስሮአል። መልአኩ ስለሚወለደው የዘካርያስ ልጅ ሲናገር እንዲህ ይላል፣
“ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል።” (ሉቃ. 1፥16) ይላል፤ አባቱ ዘካርያስም ልጁ በተወለደ ጊዜ እንዲህ ብሎ ተናገረ፣ “አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤” (1፥76)።
ምንም እንኳ የመጥምቁ ዮሐንስ እናትና አባት ማለትም ኤልሳቤጥና ዘካርያስ፣ በስተእርጅናቸው ልጅን በመውለድ የእግዚአብሔርን ተአምራት በሕይወታቸው በማየት እምነታቸው እጅግ ቢያድግም፣ ትልቁ ናፍቆትና ጥማታቸው ግን የመሲሑ መምጣትና የእስራኤልን ተስፋ መፈጸም ማየት ነበር። የመልአኩም የዘካርያስም መሻት መሲሑ ፈጥኖ በመምጣት ሕዝቡን ይቤዥና ያድን፣ ደግሞም የሕዝቡን ፊት ወደ እግዚአብሔር ይመልስ ዘንድ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት፤ … ለእነርሱም ከሰማይ በተላከ በመንፈስ ቅዱስ ወንጌልን የሰበኩላችሁ ሰዎች አሁን ባወሩላችሁ ነገር እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው፤ ይህንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ።” (1ጴጥ. 1፥10፡ 12) እንዲል፣ የመላእክት የዘወትር መሻት በክርስቶስ የእኛን መዳን እንደ ኾነ ይነግረናል።
3. ኢየሱስን ትወልድ ዘንድ ለማርያም አበሠራት። ሉቃስ ወንጌላዊው የመልአኩ ገብርኤልን ስም ጠቅሶ በመጻፍ ቀዳሚ ነው፤ መልአኩ በተናቀችውና በተጣለችው በናዝሬት ገሊላ ትኖር ለነበረችው ለማርያም፣ “እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ … ” (1፥31-32) ብሎ አበሠራት።
የኪዳኑ ሕዝብ ይጠብቅ የነበረውን የተስፋ ብርሃን ያበሠረው መልአኩ ገብርኤል ነበር። ለዘለዓለም የተጠበቀውን ተስፋ፣ የሰው ልጆች ኹሉ ሊያዩት የሚገባውን ብርሃን፣ በጨለማ ለሚሄዱ ኹሉ የሚያበራውን ፋኖስ፣ ለቅዱሳን ኹሉ የቅድስና ምንጭ የሚኾናቸውን መሲሕ ብላቴና … ሊወለድ እንዳለ ለቅድስት ድንግል ያበሠረው ይኸው መልአክ ነው። ስለ መሲሑ ሲናገር እንዲህ ይላል፣ “ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።” (1፥35)።
መልአኩ ገብርኤል ለተገለጠላቸው ኹሉ በሚሰማ ድምጽ የሚናገረው፣ ስለ አሸናፊው፤ ድል ነሺው ክርስቶስና ማንነቱ ነው። ለዳንኤል እንደ ተረጐመለት መሲሑ ጠላቶቹን ኹሉ ይመታል፤ ያሸንፋል፣ ይደመስሳል። ዘካርያስ እንደ ተናገረው፣ ከዘካርያስ የሚወለደው ልጅ የዚህ ታላቅ መሲሕ መንገድ ጠራጊና ሰዎች ኹሉ ወደ መሲሑ እንዲመጡ መንገድ ደልዳይ እንደ ኾነ ይናገራል። ለቅድስት ድንግልም እንደሚናገረው ከእርስዋ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ኾነና የአባቱን የዳዊት ዙፋን ወራሽና የጸና ዘላለማዊ መንግሥት እንዳለው ይናገራል።
እንኪያስ እኛም የመልአኩ እውነተኛ ወዳጆች ዛሬም እንዲህ እንላለን፤ መሲሑን ትሰሙትና በእርሱ ሕይወት ይኾንላችሁ ዘንድ ወደ መሲሑ ተመለሱ እንላለን፤ ለሚያስጨንቃችሁ ጠላት፣ ለሚያሳድዳችሁ ኀጢአት መድኃኒትና ሞትን የዋጠ አሸናፊ አለላችሁ፤ የኀጢአትን ኃይል የሰበረ፣ የገሃነምን ደጅ ያፈረሰ ጀግና እርሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ አለላችሁ! በእርሱ እመኑ፤ የገብርኤልን አምላክ ውደዱና ዕረፉ፤ አሜን!
የብሎግ አድራሻ -
http://abenezerteklu.blogspot.com/2023/12/blog-post_28.html#more