ሰ/መ/ቁ 199400 03/02/2014 ዓ.ም የማይንቀሳቀስ ንብረት የአጻጽፍ ስርዓትና የምዝገባ ልዩነት
ውል ለማዋዋል ስልጣን በተሰጠው አካል ፊት ያልተደረገ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል በፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 2878 አግባብ የተመዘገበ ቢሆንም እንኳን ውሉ መደረጉ ከተካደ በሻጭና ገዥ መካከል ህጋዊ ውጤት የለውም።
ምዝገባ በፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 1723/1 ስር የተደነገገውን የፎርም ስርዓት የሚተካ ካለመሆኑም በላይ የተዋዋዮቹን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የተዘረጋ ስርዓት አይደለም።
የተያዘውን ጉዳይ አስመልክቶ ችሎቱ እንዳለው፥
ዉሉ በማዘጋጃ ቤት በሚገኝ ማህደር ዉስጥ ስለሚገኝ እንደተመዘገበ ይቆጠራል ብለዉ ያቀረቡት ክርክርም ቢሆን ይሕ ተግባር ተፈጽሞ ቢሆን እንኳን በፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 1723/1 ስር የተደነገገዉን የፎርም ስርዓት የሚተካ ካለመሆኑም በላይ ይህ ተፈጸመ ያሉት ስርዓት የተዋዋዮቹን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የተዘረጋ ስርዓት ባለመሆኑ ይህ መከራከሪያቸዉ በክልሉ ፍርድ ቤቶች ተቀባይነት በማጣቱ የተፈጸመ ስህተት አላገኘንም፡፡
በፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 1723/1 ስር የተደነገገዉ ፎርማሊቲ በተዋዋዮች መካከል በፀና አኳኋን የተደረገ ዉል መኖሩን ለማረጋገጥና በዋናነት የተዋዋዮቹን መብት ለመጠበቅ የተደነገገ ሲሆን በፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 2878 እና በሌሎች ከላይ በተጠቀሱት ድንጋጌዎች የተመለከተዉ ምዝገባ (Registration) ደግሞ ተዋዋዮች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ለማስተላለፍ ወይም ባንድ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የአላባ ጥቅም መብት ወይም የመያዣ ወይም የሌላ አገልግሎት መብት ለመቋቋም ወይም በድንጋጌዎቹ ላይ የተመለከቱትን ሌሎች መብቶችን ለመመስረት ዉል በመዋዋላቸዉ የሦስተኛ ወገኖች መብትና ጥቅም እንዳይነካ ለሦስተኛ ወገኖች ጥበቃ ለማድረግ ነዉ፡፡ይህ አይነት ምዝገባ (Registration) የሚከናወነዉም ንብረቱ ተመዝግቦ በሚገኝበት አስተዳደር አካል ዘንድ በሚገኘዉ የማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ ላይ ነዉ፡፡
በመሆኑም ተዋዋዮች የቤት ሽያጭ ዉል የለም በሚል ዉሉን ተካክደዉ በሚከራከሩበት ጊዜ በእርግጥም በፀና አኳኋን የተደረገ ዉል ማድረግ አለማድረጋቸዉን ? ዉሉ የተደረገዉ መቼ ነዉ? የሽያጭ ዉል ከሆነ በምን ያህል ዋጋ ነዉ የተደረገዉ? ለዉሉ ምክንያት የሆነዉ ምን ዓይነት ንብረት ነዉ? የትስ የሚገኝ ነዉ? የሚሉና ንብረቱን ለማስተላለፍ መብት ባለዉ ሰዉ መፈረም አለመፈረሙን የሚመለከትና መሰል የይዘት ክርክሮች የተነሱ እንደሆነ ይህን ለማጣራት ሊቀርብ የሚገባዉ ማስረጃ ዓይነትም በፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 1723/1 ስር በተደነገገዉ አግባብ በጽሑፍ ሆኖ ዉል ለማዋዋል ሥልጣን ባለዉ አካል ፊት የተደረገ ዉል ሊሆን ይገባል፡፡
ይህን አስመልክቶም ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁጥር 78398 በሰ/መ/ቁጥር 188881 እና በሌሎችም ላይ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡
https://t.me/ethiolawtips