#በዓለ_ሥሉስ_ቅዱስ (ጥር 7)
ጥር ሰባት በዚች ቀን በዓለ ሥላሴ የሚከበረው ስለ ሁለት ምክንያቶች ነው:: ቀዳሚው ሕንጻ ሰናዖርን ማፍረሳቸው ሲሆን ሌላው ደግሞ ቅዳሴ ቤታቸው ነው::
#ሕንጻ_ሰናዖር
ሰናዖር ከሺዎች ዓመታት በፊት በአሁኗ ኢራቅ አካባቢ እንደ ነበረ የሚነገርለት ግዛት ሲሆን ስሙ ለሃገሪቱም: ለንጉሡም በተመሳሳይ ያገለግል ነበር:: ከናምሩድ ክፋት በሁዋላ ሰናዖርና ወገኖቹ ከሰይጣን ተወዳጁ::
ከጥፋት ውሃ (ከኖኅ ዕረፍት) በሁዋላ በሥፍራው በአንድነት ይኖሩ ነበርና እርስ በርሳቸው "ኑ ሳንበተን ስማችን የሚጠራበትን ሕንጻ እንሥራ:: በዚያውም አባቶቻችን በውሃ ያጠፋ እግዚአብሔርን እንውጋው" ተባባሉ::
ቀጥለውም ሰማይ ጠቀስ ፎቅን ገነቡ:: ከሕንጻው መርዘም የተነሳ በጸሐይ አብስለው በልተዋል ይባላል:: ቀጥለውም ጦር እያነሱ ፈጣሪን ሊወጉ ወርውረዋል::
መቼም የእነዚህን ሰዎች ክፋትና ቂልነት ስንሰማ ይገርመን ይሆናል:: ግንኮ ዛሬ ሰለጠንኩ በሚለው ዓለም እየተሠራ ያለው ከዚህ የከፋ ነው:: ቸርነቱ ቢጠብቀን እንጂ እንደ ክፋታችንስ ጠፊ ነበርን::
ርሕሩሐን ሥላሴ ግን የሰናዖር ሰዎች የሠሩትን አይተው ማጥፋት ሲችሉ አላደረጉትም:: የባሪያቸውን የኖኅን ቃል ኪዳን አስበዋልና:: ይልቁኑ "ንዑ ንረድ ወንክአው ነገሮሙ ለከለዳውያን-ቁዋንቁዋቸው እንደባልቀው" አሉ እንጂ::
ከለዳውያን ልሳናቸው ተደበላልቆ 71 ቁዋንቁዎች ተፈጠሩ:: እነርሱም ስምምነት አጥተው ተበተኑ:: ሥላሴም ያን ሕንጻ በነፋስ ትቢያ እንዲሆን በተኑት:: ስለዚህም እስከ ዛሬ ሥፍራው "ባቢሎን (ዝሩት)" ሲባል ይኖራል::
#ቅዳሴ_ቤት
ልክ የዛሬ 324 ዓመት አድያም ሰገድ ኢያሱ በኢትዮዽያ በነገሡ በ10ኛው ዓመት (በ1684 ዓ.ም) በጐንደር ከተማ ንግሥተ አድባራት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተሰርታ ተጠናቃለች::
ጥር 7 ቀንም ሊቁ ክፍለ ዮሐንስን ጨምሮ በርካታ ምዕመናን ሠራዊት መሣፍንትና ሊቃውንት ባሉበት ቅዳሴ ቤታቸው ተከብሯል። በዕለቱም ታላቅ ሐሴት ተደርጉዋል። ኢያሱ አድያም ሰገድ ኃያል ደግ ጥበበኛ አስተዋይ መናኝ ንጉሥ ነውና።
ቤተ ሥላሴን አስጊጿታልና ከዚህ ቀን ጀምሮ ጥር ሥላሴ በድምቀት የሚከበር ሆኗል:: ነገር ግን በተሠራች በ16 ዓመቷ ደጉ ኢያሱ ከተገደለ በሁዋላ ቤተ ክርስቲያኑ በአደጋ ፈርሷል:: ዛሬ የምናየው በ1708 ዓ.ም በልጁ በአፄ ዳዊት ሣልሳዊ የታነጸውን ነው::
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።
(ስንክሳር ዘተዋሕዶ)
@Ewuntegna@Ewuntegna@Ewuntegna