Meseret Media


Гео и язык канала: Эфиопия, Амхарский
Категория: Новости и СМИ


መሠረት ሚድያ በኢትዮጵያ ለበርካታ አመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የሰሩ ባለሙያዎች ወቅታዊ መረጃዎችን ለህዝብ ለማድረስ በማለም ያቋቋሙት ዲጂታል ሚድያ ነው።

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Гео и язык канала
Эфиопия, Амхарский
Категория
Новости и СМИ
Статистика
Фильтр публикаций


መንግስት ንብረታቸውን ሊወስድ እየተዘጋጀ መሆኑን አቶ ልደቱ አያሌው አስታወቁ

(መሠረት ሚድያ)- ባሳለፍነው ሰኞ ጠዋት ከአሜሪካ ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ለመጓዝ በአትላንታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቢገኙም እንዳይሳፈሩ የተደረጉት ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው መንግስት ንብረታቸውን ሊወስድ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታወቁ። 

ፖለቲከኛው ለበርካታ አለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ተቋሟት ዛሬ በፃፉት እና ለመሠረት ሚድያ በቀጥታ ባጋሩት ደብዳቤያቸው ላይ "ጠ/ሚር አብይ አህመድ ወደ ሀገር መመለስ እንደማልችል በአንድ ስብሰባ ላይ በይፋ ተናግረዋል" ብለዋል።

አቶ ልደቱ አክለውም ወደ ሀገር ቤት እንዳይመለሱ የታገዱት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ወደ ኢትዮጵያ በሚበሩ አየር መንገዶች ጭምር መሆኑን ጠቁመዋል።

"ይህ ድርጊት የሚያሳየው የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉንም ተፃራሪ ድምፆች ለማፈን ቁርጠኛ መሆኑን ነው። እነዚህ ድርጊቶች እየተፈፀሙ ያሉት ካለ ምንም የህግ አግባብ ስለሆነ በግዜው ካልተስተካከለ በርካታ ኢትዮጵያውያን ላይ ጭምር ሊፈፀም ይችላል" በማለት በደብዳቤያቸው ላይ አስፍረዋል።

አቶ ልደቱ ከኢትዮጵያ ውጪ ሌላ ዜግነት እንደሌላቸው አፅንኦት ሰጥተው በደብዳቤያቸው ላይ ያስረዱ ሲሆን የኢትዮጵያ ህገ-መንግስትም ሆነ ሌሎች የሀገሪቱ ህጎች ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደማይችሉ የሚገልፅ ድንጋጌ እንደሌላቸው አንስተዋል።

የአቶ ልደቱ ደብዳቤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን፣ የአፍሪካ ህብረትን፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልን፣ ሂውማን ራይትስ ዋችን እና የአሜሪካ ኤምባሲን ጨምሮ ለ32 ድርጅቶች የተፃፈ ነው።

"ወደ ሀገሬ መሄድ ማንም ሊከለክለኝ አይችልም፣ ሀገሬ ከሄድኩ በኋላ ግን ማሰር ይችላሉ" የሚሉት ፖለቲከኛው ከአመታት በፊት ለህክምና ከሀገር ሲወጡ መንግስት ከልክሏቸው እንደነበር፣ አሁን ደግሞ ሊመለሱ ሲፈልጉ መከልከሉ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ባሳለፍነው ሰኞ ለመሠረት ሚድያ ተናግረው ነበር።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

18.6k 0 28 44 370



አንዳንድ እድሜያቸው የገፋ መኪናዎች ወደ ቦሌ አቅጣጫ እንዳይንቀሳቀሱ እየተደረጉ እንደሆነ ታወቀ

(መሠረት ሚድያ)- ከአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ጋር በተያያዘ አንዳንድ እድሜ ጠገብ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ቦሌ አቅጣጫ የመንቀሳቀስ እገዳ እየተደረገባቸው እንደሆነ ታውቋል።

ከባለፈው አርብ እለት ጀምሮ በርካታ የእነዚህ ተሽከርካሪዎች ባለቤቶች ለመሠረት ሚድያ ባደረሱት ጥቆማ ከቦሌ ብስራስ፣ ቦሌ አትላስ፣ ከአራት ኪሎ እና ከኡራኤል አቅጣጫዎች በመነሳት ወደ ዋናው የቦሌ መንገድ (በኦፊሴላዊ አጠራሩ የአፍሪካ ጎዳና) ሲጓዙ በትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እንዲመለሱ መታዘዛቸውን አስረድተዋል።

"ዝርዝር የማስፈፀሚያ ህግ ባልወጣበት እንዲህ አይነት እገዳ መጣሉ የህግ የበላይነት አለመኖሩን ማሳያ ነው" ያሉ አንድ እገዳው ያጋጠማቸው አሽከርካሪ ድርጊቱን ኮንነዋል።

ሌላ አሽከርካሪ ደግሞ "አላማው ምንድነው? ዜጎቻችን በሙሉ የሚነዱት ዘመናዊ ተሽከርካሪ ነው የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ይሆን?" በማለት ጥያቄያቸውን ሰንዝረዋል።

እገዳውን እየጣሉ ያሉት የትራፊክ ፖሊሶች ዝርዝር ማስፈፀምያ ደርሷቸው ይሆን ወይስ በራሳቸው ተነሳሽነት የፈፀሙት ነው የሚለውን ለማጣራት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

በአዲስ አበባ አሮጌ መኪናዎች በተለይ የኮሪደር ልማት በተሰራባቸው ቦታዎች እንዳይንቀሳቀሱ ክልከላ ሊደረግባቸው እንደሚችል በመጀመርያ የተሰማው የዛሬ አመት ገደማ ነበር።

በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ የአሮጌ መኪና ባለቤቶች መኪናቸውን መቀየር ካልቻሉ በለሙ የኮሊደር መንገዶች ላይ እንዳይንቀሳቀሱ ክልከላ ሊደረግባቸው ይችላል ብለው ለሚድያዎች ተናግረው ነበር።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

22.9k 0 104 39 436

ከ890 በላይ እስረኞች በምግብ እና ውሀ ብክለት ታመሙ፣ ሟቾችም እንዳሉ ተሰምቷል

(መሠረት ሚድያ)- በደቡብ ወሎ ኮምቦልቻ ከተማ አቅራቢያ 'ጮሬሳ' ተብሎ በሚጠራው ካምፕ ውስጥ ከ890 በላይ የፖለቲካ እስረኞች በምግብ እና በውሃ ብክለት ምክንያት መታመማቸው ታውቋል።

መሠረት ሚድያ ከእስረኞች ቤተሰቦች የደረሰው መረጃ እንደሚጠቁመው እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ እስረኞች መሞታቸውም ተረጋግጧል።

በሽታው የተቀሰቀሰው በዚህ ሳምንት የካቲት 6/2017 ዓ/ም መሆኑን የተናገሩት የታሳሪ ቤተሰቦች ለእስረኞቹ የሚቀርበው ውሃ ከወንዝ እየተቀዳ በመሆኑ ለበሽታው ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ብለዋል።

ወደ እስረኞች ካምፕ ከፌደራል ፖሊስ እና ከመከላከያ ሰራዊት አባላት ውጭ መግባት የተከለከለ በመሆኑ  የሕክምና አገልግሎት ማገኘት እንዳልቻሉም ቤተሰቦቻቸው ጨምረው ተናግረዋል።

እስረኞቹ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰውን የፋኖን ኃይል ትደግፋላችሁ በሚል ከመስከረም ወር ጀምሮ ከተለያዩ የአማራ ክልል ወረዳዎች በማሰባሰብ ከኮምቦልቻ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኛው ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።

ከእስረኞቹ ውስጥ 220ዎቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ዋስትና የተፈቀደላቸው ቢሆንም ታሳሪዎቹን የተረከበው የፌደራል ፖሊስ እስረኞቹን መልቀቅ የሚችለው መከላከያ እንጂ ፍርድ ቤት አይደለም በሚል ሊለቃቸው ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል ተብሏል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

26.5k 0 41 14 454

በአየር መንገድ ግቢ ውስጥ ከአመራሮች እውቅና ውጪ ተነሳ የተባለው ፎቶ በእውቅና መደረጉን የሚያሳይ ደብዳቤ ወጣ

(መሠረት ሚድያ)- ከቀናት በፊት ሲያነጋግር የነበረው የአየር መንገድ ግቢ ውስጥ የተነሳው ፎቶ እንደተባለው "ከተቋሙ አመራሮች እውቅና ውጪ" ሳይሆን በእውቅና መደረጉን የሚያሳይ ደብዳቤ ለመሠረት ሚድያ ደርሷል።

የአየር መንገዱ የአዲስ አበባ ሽያጭ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ግሩም አበበ ለሲቪል አቪዬሽን ደህንነት ዋና መምሪያ ዳይሬክተር ታህሳስ 25/2017 ዓ/ም በፃፉት ደብዳቤ አርቲስት ምህረት ታደሰ በአየር መንገድ የአየር ክልል ውስጥ የፎቶ ፕሮግራም እንድታደርግ መጠየቋን ያሳያል።

ደብዳቤው አክሎም የፎቶ ፕሮግራሙ ለአየር መንገዱ ማስታወቂያነት ስለሚጠቅም ታህሳስ  27/2017 ዓ/ም ቅጥር ግቢ ውስጥ ገብተው ፎቶ እንዲነሱ ይጠይቃል።

የፎቶ ፕሮግራሙ በዚህ ሁኔታ በተቋሙ እውቅና ቢካሄድም ተቋሙ ከትናንት በስቲያ በፌስቡክ ገፁ "የግለሰቧ የአየር መንገድ ግቢ ውስጥ የልደት ምስል ቀረጻ ከተቋሙ አመራሮች እውቅና ውጭ የተደረገ ነው" ማለቱ ግርታን ፈጥሯል።

በተጨማሪም የፎቶ ፕሮርግራሙ የግል የልደት ፕሮግራም መሆኑን አርቲስቷ በሶሻል ሚድያ ገጿ ላይ የገለፀች ቢሆንም ይህ በምን መልኩ ለአየር መንገዱ በማስታወቂያነት እንደሚጠቅም ግልፅ አልሆነም። 

ተቋሙ ለፎቶ ፕሮግራሙ ከአርቲስቷ ገንዘብ አለመቀበሉን እና ምንም አይነት ውል እንደሌለው በመግለጫው ላይ ገልፆ ነበር።

በርካታ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ድርጊቱን ከአየር የበረራ ክልል ደህንነት ጋር በማንሳት ጥያቄ ሲያቀርቡ ሌሎች ደግሞ በምን መስፈርት አንድ ግለሰብ የግል ልደት ከፍ ያለ ደህንነት በሚያስፈልገው አውሮፕላን ላይ ዲኮር በመስራት ተከበረ የሚል ጥያቄ አንስተዋል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ክስተቱ ለአየር መንገዱ ጥሩ ማስታወቂያነት ውሏል ብለው ሀሳብ የሰጡም አልጠፉም።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

47.7k 0 121 66 591


41.3k 0 173 5 147

የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ መቃረቡን ተከትሎ አገልግሎት ላይ እንዳይውል በታገደ መርዝ በርካታ ሺህ ውሻዎች አዲስ አበባ ውስጥ እየተገደሉ መሆኑ ታወቀ

- መርዙ ወንዝ ዳር የሚበቅል ምግብ ሊበክል እንደሚችል ተሰግቷል

(መሠረት ሚድያ)- በአለም ጤና ድርጅት አገልግሎት ላይ እንዳይውል በታገደ መርዝ በርካታ ሺህ ውሻዎች አዲስ አበባ ውስጥ እየተገደሉ መሆኑን ከተለያዩ ቦታዎች የሚደርሱን ጥቆማዎች ያሳያሉ።

በኮሪደር ልማት ምክንያት እንደ ፒያሳ እና ካዛንችስ ያሉ ቦታዎች መፍረሳቸውን ተከትሎ መንገድ ላይ የቀሩ በርካታ ውሻዎች መኖራቸው ይታወቃል።

ይሁንና ቀጣዩን የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶች "ጎዳና ላይ እንዳያዩዋቸው" በሚል ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በርካታ ሺህ ውሻዎች በመርዝ እየተገደሉ እንደሆነ ታውቋል።

ባለፈው ወር የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ሊመጡ ሲልም ሲባልም በተመሳሳይ ብዙ ውሻዎችን በመርዝ መገደላቸው ታውቋል።

"መርዙ በአለም ጤና ድርጅት አገልግሎት ላይ እንዳይውል የታገደ ነው፣ እንዴትስ ወደ ሀገራችን ገባ የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ነው" ያሉት አንድ ጉዳዩን የሚከታተሉ ግለሰብ መርዙ ሰዎች እጅ ቢገባ በአንድ የሻይ ማንኪያ እሩብ በታች ሆነ መጠን ሺህ ህዝብ ሊጨርስ ይችላል ብለዋል።

"መርዙ ሽታ የሌለው በመሆኑ በምግብም ሆነ መጠጥ ውስጥ ሊገባና ሰዎችን ለመጉዳት ሊውል ይችላል። በዚህ መርዝ ያለ ሃጢያታቸው እየተገደሉ ያሉ ውሾች የሚጣሉበት ቦታ ሌላው አውሬ ምግብ ያገኘ መስሎት የሞተውን በድን ሲበላ እንደሚሞት፣ ተያይዞም አሞራዎች በልተውት የተረፋቸውን ወንዝ ላይ ቢጥሉት ውሃው የሚመረዝ መሆኑ ሊታወቅ ይሀገባል" በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል።

አክለውም ውሃው የከተማም ሆነ የገጠር የወንዝ ዳር አትክልት ልማት ላይ ሊውል ስለሚችል ተያያዥነቱ ረጅም በመሆኑ ህዝብ ሁሉ ይህንን ድርጊት እንዲኮንን ተማፅነዋል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

42.5k 0 132 58 706



የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአርማውን ቀለም የመቀየር ፍላጎትና እቅድ እንደሌለው ለመሠረት ሚድያ አሳወቀ

- የድርጅቱ አዲስ አጥር ላይ በአረንጓዴ ቀለም ብቻ የሰፈረው አርማ መልሶ ሊቀባ መሆኑ ታውቋል

(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ በርካታ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ በቪ አይ ፒ መግቢያ አካባቢ ባሰራው አጥር ላይ የሚታወቅበት አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለም ቀርቶ በአረንጓዴ ቀለም ብቻ አርማው (ሎጎው) ተቀብቶ በመመልከታቸው የተለያየ አስተያየት ሲሰነዝሩ ተስተውሏል።

አንዳንዶች አየር መንገዱ ቀስ በቀስ የአርማውን ቀለም እየቀየረ እንደሆነ የገመቱ ሲሆን ድርጊቱን በተለያየ መልኩ ሲገልፁት ታይቷል።

መሠረት ሚድያ በዚህ ዙርያ አየር መንገዱን ያነጋገረ ሲሆን ተቋሙ አርማውን የመቀየር ፍላጎትና እቅድ እንደሌለው አሳውቋል።

"ይሄ የእኛ እቅድም፣ ፍላጎትም አይደለም" ያሉን አንድ የአየር መንገዱ ሀላፊ አዲሱ አጥር በአረንጓዴ ብቻ የተቀባው ገፅታውን 'ቀለል ያለ' እንዲሆን ለማድረግ ነው ብለዋል።

"በዚህ ዙርያ ተወያይተንበታል፣ ብዙ ግርታም እንደፈጠረ አስተውለናል። ወደቀደመው እና ወደ ኦፊሴላዊው የአርማ ቀለሞች መልሶ በቅርቡ ይቀባል" በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።

አንድ ሌላ የዘርፉ ባለሙያ በሰጠን አስተያየትም አንዳንድ ግዜ ባለ ቀለም ሎጎዎች ቀለል ያለ መልክ እንዲኖራቸው ሲፈለግ ቅርፃቸውን ጠብቀው ቀለማቸው ሊቀየር እንደሚችል ጠቁሟል።

"ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በታላቁ ሩጫ ቲሸርቶች ላይ ያለውን ሎጎ ብናይ ወይ ነጭ ወይ ሌላ ቀለም ነው፣ አላማው ዲዛይኑ የማይረብሽ እና ቀለል ያለ እንዲሆን ነው። ይህ አሰራር እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገራት በጣም የተለመደ አሰራር ነው" በማለት ሙያዊ አስተያየቱን ሰጥቷል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

43k 0 43 39 449

"ጠበቃዎችን እያነጋገርኩ ነው፣ በአቪዬሽን ህግ ሊከለክሉኝ እንደማይችሉ ተነግሮኛል"- አቶ ልደቱ አያሌው ለመሠረት ሚድያ

(መሠረት ሚድያ)- ዛሬ ጠዋት ከአሜሪካ ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ለመጓዝ በአትላንታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቢገኙም እንዳይሳፈሩ የተደረጉት ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው ጉዳዩን በህግ ሊይዙት እንደሚችሉ ተናገሩ።

"አየር ማረፊያው ስገኝ ሰራተኞቹ የ boarding pass ማውጣት እምቢ አላቸው፣ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ያሉኝ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲን አነጋግሬ የተለየ ፈቃድ ካልተሰጠኝ በስተቀር ወደ ኢትዮጵያ መጓዝ እንደማልችል ነው" ብለው ለመሠረት ሚድያ የተናገሩት አቶ ልደቱ ዋሽንግተን ወደሚገኘው ኤምባሲ ስልክ ቢደውሉም ጥሪ የሚያነሳ ማሽን እንጂ የኤምባሲው ሰራተኖችን ማነጋገር እንዳልቻሉ ጠቅሰዋል።

"ወደ ሀገሬ መሄድ ማንም ሊከለክለኝ አይችልም፣ ሀገሬ ከሄድኩ በኋላ ግን ማሰር ይችላሉ። በአሸባሪነት ወንጀል ሊከሰኝ እንደሚፈልግና በቁጥጥር ስር እንድውል ከኢንተር-ፖል ጋር ጭምር እየተነጋገረ እንደሆነ ሲገልፅ የነበረው የኢትዮዽያ መንግስት ዛሬ በራሴ ፈቃድ ወደ አገሬ ለመመለስ ስሞክር በእኔ ላይ ህገ-ወጥ ክልከላ ማድረጉ አስገርሞኛል" ያሉት ፖለቲከኛው ከአመታት በፊት ለህክምና ከሀገር ሲወጡ ከልክሏቸው እንደነበር፣ አሁን ደግሞ ሊመለሱ ሲፈልጉ መከልከሉ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ጨምረው ተናግረዋል።

"መሄድ አለብኝ፣ በመብቴ ጉዳይ አልደራደርም። ጠበቆችም እያነጋገሩኝ ነው፣ በአቪዬሽን ህግ ሊከለክሉኝ እንደማይችሉ ተነግሮኛል" በማለት ወደ ሀገር ቤት በመመለስ በሀገራቸው የፖለቲካ ምህዳር ላይ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸው ለሚድያችን ተናገረዋል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

30.6k 0 24 15 396

በዱባይ በተደረገው የፖሊስ SWAT ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ 101ኛ መውጣቱ ታወቀ

(መሠረት ሚድያ)- ላለፉት ጥቂት ቀናት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ዱባይ ከተማ በተካሄደው እና የ103 ሀገራት የSWAT ፖሊስ ቡድን አባላት በተሳተፉበት ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ 101ኛ መውጣቱ ታውቋል።

ይህ Special Weapons And Tactics (የልዩ መሳርያዎች እና ታክቲኮች) የቡድን ውድድር ላይ የቻይና B ቡድን በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ፣ የካዛክስታኑ ሱንካር ፖሊስ ሁለተኛ እንዲሁም የቻይና C ቡድን ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል (ሊንክ: https://uaeswatchallenge.com/?page_id=11727)

በ SWAT ውድድሩ ላይ ሲወዳደር የቆየው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ቡድን ከሁለት ቀን በፊት በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ስትራቴጂክ አመራሮች አቀባበል ተደርጎለታል።

በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል፤ እንደ ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የፖሊስ ተቋም በተባበሩት ዐረብ ኢምሬቶች SWAT ውድድር ላይ መሳተፉ ለሀገራችን ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ጠቀሜታ ከማስገኘቱም ባሻገር ዓለም አቀፍ የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነትን ለማዳበር ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የፖሊስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ውድድር ላይ መሳተፍ መቻላችን ልምድና ተሞክሮ እንድናገኝ ያስቻለን ነው ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም እ.ኤ.አ 2026 በሚካሄደው ውድድር ላይ አስፈላጊውን ስልጠና በመውሰድ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትጋት እንሠራለን ሲሉም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወደ ስፍራው ሲጓዝ እና ውድድሩን አጠናቆ ወደ ሀገር ሲመለስ በስፋት በመንግስት ሚድያዎች ቢበገብም ያስመዘገበው አነስተኛ ውጤት ግን ለህዝብ አልተገለፀም።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

32.1k 0 118 92 1.1k



በኢቢሲ ውስጥ ያለውን የአንዳንድ ሰራተኞች የፎርጅድ ዶክመንት ያጋለጠው ሰራተኛ የሽብር ክስ ቀረበበት

(መሠረት ሚድያ)- የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) አንዳንድ ሰራተኞች ፎርጅድ ወይም እውቅና የሌለው የትምህርት ማስረጃ እንዳላቸው ያጋለጠው የተቋሙ ሰራተኛ ሌላ የሽብር ክስ ቀርቦበት ለእስር ተዳርጎ እንደነበር ታወቀ።

አቶ ወገን አበበ የተባለው የቀድሞው የተቋሙ ሰራተኛ ክሱ ቀርቦበት 52 ቀን ታስሮ ጥር 26/2017 ዓ/ም መለቀቁን ለመሠረት ሚድያ ተናግሯል።

"የተያዝኩት ተወልጄ ባደግኩባት ዲላ ከተማ ነው፣ ከላይ በመጣ ትእዛዝ ተብሎ ቤቴ ተበረበረ። ዲላ 5 ቀን ከታሰርኩ በኋላ ወደ ወላይታ ሶደ ተወሰድኩ፣ 3 ቀን ታስሬ ወደ ሀዋሳ የፌደራል ምርመራ ተወሰድኩ፣ ከዛም አንድ ሳምንት ሀዋሳ ታስሬ ወደ አዲስ አበባ ፌደራል ምርመራ ሜክሲኮ ተወሰድኩ" በማለት ያለፈበትን የእስር ሂደት አስረድቷል።

መሠረት ሚድያ የተመለከተው የክስ ወረቀት እንደሚለው አቶ ወገን በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ቡድን አባሎች ጋር በመቀናጀት እና ቡድኑን በመምራት መጠርመሩን ይገልፃል።

ክሱ አክሎም "በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት ለማድረስ ተልእኮ በመቀበል እና ቡድኑን በገንዘብ በማገዝ" እንዲሁም "በመላው ሀገራችን ሰላም እንደሌለ በማስመሰል ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳሳና ለሽብር ተግባራት የሚቀሰቅሱ የሀሰት ቪድዮ እና የድምፅ መልዕክት በማዘጋጀት እና በማህበራዊ ሚድያ በማሰራጨት" የሚሉ ውንጀላዎችን አካቷል።

ይሁንና አቶ ወገን ከ52 ቀን እስር በኋላ በ40 ሺህ ብር ዋስ ተለቀዋል።

"እኔ አማራ ክልል ሄጄ እንኳን አላውቅም፣ ዘመድም የለኝም" የሚለው አቶ ወገን እንኳን ለተለያዩ ቡድኖች የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግ ኢቢሲ ከስራው ካባረረው በኋላ ስራ እንኩዋን እንደሌለው ገልጿል።

ግለሰቡ ከወራት በፊት የአንዳንድ የኢቢሲ ሰራተኞች የፎርጂድ ዶክመንትን በተመለከተ ካጋለጠ በኋላ ተቋሙ መረጃውን ያወጣብኝ የቀድሞ ሰራተኞዬ "ተአማኒነቴ እንዲቀንስ አድርጓል" በማለት 10 ሚልዮን ብር ካሳ ይክፈለኝ ብሎ ክስ መስርቶ ነበር።

ይሁንና ራሱ ኢቢሲ ከወራት በፊት በተቋሙ ሰራተኞች ላይ ባደረገው የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ ሂደት የ400 ሰራተኞቹ ሰነድ ፎርጂድ/ሀሰተኛ መሆኑን እንዳረጋገጠ አንድ ሾልኮ የወጣ ዶክመንት ጠቁሞ ነበር።

ይህ ሆኖ እያለ የተቋሙ ሀላፊዎች እርምጃ እንዳይወሰድ ይህን መረጃው እንደደበቁ፣ በጥቆማ አቅራቢዎች ላይም ዛቻ እና ማስፈራርያ እያደረሱ እንደኮነ በወቅቱ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ለጠቅላይ አቃቤ ህግ የፃፈው ደብዳቤ አሳውቆ ነበር።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

37.5k 0 51 13 592



#የህዝብድምፅ ከህዝብ በጥቆማ መልክ ደርሰውን ትክክኝነታቸው የተረጋገጡ 5 መረጃዎች

1. በቅርቡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የታሪፍ ማሻሻያ እንዲሁም የቫት (VAT) ክፍያ መጀመሩን ተከትሎ በተለይ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ አስደንጋጭ ክፍያ እየተጠየቁ እንደሆነ አንዳንድ ዜጎች እየተናገሩ ይገኛሉ። ደምበኞች እንደሚሉት ለምሳሌ በቅድመ ክፍያ ካርድ የሚጠቀም አንድ ሰው 1,000 ብር ቢሞላ ቆጣሪዉ ላይ የሚታየዉ የተሞላዉ የብር መጠን 353.3 ብር ነው። የድርጅቱን ሰራተኞች ለማጋነር ጥረት ሲደረግ የቫት ክፍያ ነዉ እንደሚሉ፣ ቫቱ እንዴት እና በምን ስኬል እንደሚሰላ ግን ማስረዳት እንደማይችሉ ታውቋል። በሀገራችን የቫት አዋጅ መሰረት የቫት ስኬሉ የአገልግሎቱ 15% መሆኑ ይታወቃል፡፡

2. በአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ውሳኔ ምክንያት የኤችአይቪ ክትትል የሚያደርጉ ከ 500,000 በላይ ኢትዮጵያውያን አደጋ እንደተጋረጠባቸው ታውቋል። ውሳኔው ኤችአይቪን እንደማይመለከት ተገልፆ የነበረ ቢሆንም የጤና ሰራተኞች ግን መድሀኒት እና ቁሳቁስ ለማዘዋወር እንደተቸገሩ ተሰምቷል። ገና ከአሁኑ ለበሽታው የሚወሰደውን መድሀኒት በህገወጥ መልኩ ለመሸጥ ሙከራዎች እየታዩ እንደሆነ ታውቋል። የኢትዮጵያ የጤና እና የሰብአዊ እርዳታ ሴክተሮች ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ እርዳታ ባስተላለፉት ውሳኔ ክፉኛ መጎዳቱ እየታየ ነው።

3. የኢትዮጵያ ማሪታይም ትሬኒንግ ኢንስትትዩት ተማሪዎች ትምህርቱን ተከታትለው ከጨረሱ በኋላ 36,000 ዶላር እየጠየቀ እንደሆነ ታውቋል። መርከበኞችን አሰልጥኖ ማስቀጠር ከጀመረ ከአስር አመት በላይ የሆነው ተቋሙ በ Marine Engineering and Electrotechnical Officer አስተምሮ ወደ ስራ የሚያሰማራቸው ዜጎችን የሚጠየቀው የገንዘብ መጠን በጣም የተጋነነ እና ከሌሎች ሃገራት አንፃር ሲታይ በብዙ እጥፍ እንደሚበልጥ ታውቋል። ለምሳሌ በተመሳሳይ ትምህርት የተማሩ ሰዎች በህንድ 5,000 ዶላር እንዲሁም በፊሊፒንስ 10,000 ዶላር ብቻ ይጠየቃሉ።

4. በሸገር ከተማ አስተዳደር ለመንግስት ቢሮ ማሰርያ ብር አምጡ እየተባሉ እንደሆነ ዜጎች ለመሠረት ሚድያ ጠቁመዋል። "በተጨማሪም ቤት ለቤት እየዞሩ የቴሌቪዥን ግብር ክፈሉ ይላሉ፣ የቴሌቪዥን ግብርን በተመለከተ EBC   ከመብራት አገልግሎት ጋር ደረስኩት ባለው ስምምነት ላለፋት 3 ዓመታት መብራት ስንሞላ የቴሌቪዥን እየተቆረጠብን ነው የኖርነው፣ አሁን ሸገር ከተማ ከነቅጣቱ ክፈሉኝ እያለ ነው" ብለው ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ። አክለውም የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ከውሀና ፍሳሽ ጋር በመሆን ከነዋሪዎች የቆሻሻ ቢሰበስብም የወረዳ አስተዳደሩ የራሱን ማህበር አደራጅቶ በየወሩ ከነዋሪው በድጋሜ እንደሚያስከፍል ታውቋል።

5. በመጨረሻም፣ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ቤታቸው ፈርሶባቸው ወደሌላ ቦታ የተዛወሩ ሰዎችን በፈረሰው ቤት ስም የቤት ግብር እንዲከፍሉ የቴክስት መልዕክት እየላከላቸው እንደሆነ ታውቋል። "ቤቴ ካዛንችስ ነበር፣ ቤቴም ሰፈሩም ከፈረሰ 3 ወራት አለፉ። ለፈረሰው ቤቴ ነው ግብር ክፈል የተባልኩት" ያሉት አንድ ግለሰብ "መሬት እና የቤት መስሪያ ወደፊት እንሰጣችኋለን ስላሉን የምንጠብቀው እሱን ነበር። በአሁን ሰአት ከነቤተሰቤ  ቱሉ ዲምቱ ኮንዶሚንየም ተከራይተን እየኖርን ነው። ዛሬ ታድያ ላፈረሱት ቤቴ ግብር ክፈል ይሉኛል!" በማለት ለሚድያችን ተናግረዋል።

መረጃን ከመሠረት!
 
 @MeseretMedia

39.8k 0 104 41 807



በኮሪደር ልማት የተሳተፉ ከ400 በላይ ኮንትራክተሮች መንግስት ክፍያ ሊፈፅምላቸው እንዳልቻለ ተናገሩ

(መሠረት ሚድያ)- በኮሪደር ልማት ምክንያት እንደ ካዛንችስ ካሉ ቦታዎች ለተነሱ ሰዎች በፍጥነት የተዘጋጁ የጋራ መኖርያ ቤቶችን ያዘጋጁ ከ400 በላይ ኮንትራክተሮች ክፍያቸውን መንግስት እንደያዘባቸው ገልፀው ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳሉ ተናገሩ።

ኮንትራክተሮቹ ለመሠረት ሚድያ በሰጡት መረጃ መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ኮንትራክተሮቹ በግዴታ ከ3 ሺህ በላይ ቤቶችን ለኮሪደር ተነሺዎች እንዲገነቡ ካደረገ በኋላ ክፍያ መፈፀም አልቻለም።

"በጥቃቅን እና አነስተኛ የተደራጀን እኛ ኮንትራክተሮች ከ3 ሺህ በላይ የ40/60 የጋራ መኖርያዎች ውስጥ ያሉ ለንግድ ተብለው የተሰሩ ክፍሎችን ወደ መኖርያነት ቀይረን ገንብተን ብንጨርስም መንግስት ክፍያችንን ከልክሎናል" የሚሉት ኮንትራክተሮቹ አብዛኞቹ በብድር ወስደው ስራውን ቢሰሩም አሁን ትርፉ ቀርቶ ብድራቸውን ለመክፈል ተቸግረው እንዳሉ አብራርተዋል፣ አንዳንዶቹ ብድሩን ለመክፈል የግል ንብረታቸውን ለመሸጥ እየተገደዱ እንደሆነ ተናግረዋል። 

እነዚህ ለተነሺዎች በኮንትራክተሮቹ የተዘጋጁ  ቤቶች በአያት፣ አራብሳ፣ ቡልቡላ እና አስኮ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

"ቤቶች ልማት እና ፋይናንስ ቢሮዎችን ስንጠይቃቸው ምላሻቸው ገንዘብ የለንም ነው፣ ታድያ ገንዘብ ከሌላቸው ለምን እኛን አሰሩን?" የሚል ጥያቄ የሚያነሱት እነዚህ አነስተኛ እና ጥቃቅን ኮንትራክተሮች አንዳንዶቹ ቤተሰባቸው ጭምር ችግር ላይ እንደወደቀ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ከኮንትራክተሮቹ ጋር መረጃ ይለዋወጥበት የነበረ የቴሌግራም ግሩፕን ስራው ካለቀ በኋላ ሰው መረጃ እንዳይቀያየርበት መቆለፉን ለማየት ችለናል።

የቤቶች ልማት ኮንትራክተሮቹን ወደ ስራ ሲያስገባ ምንም አይነት ቅድመ ክፍያ እንዳይጠይቁ አስፈርሞ እንደነበር መሠረት ሚድያ የተመለከተው አንድ ሰነድ ያሳያል።

"ወደን ሳይሆን በግዴታ ነው ካለ ቅድመ ክፍያ ተስማምተን የገባነው፣ እንደዛ ካልተስማማን ወደፊት ምንም ስራ ከተማ ውስጥ መስራት አትችሉም ተብለን ማስፈራርያ ተሰጥቶን ነበር" ያሉት ግለሰቦቹ አሁን ላይ ለሁሉም ስራ ሳይከፈል የተከማቸው ገንዘብ 4.4 ቢልዮን ብር ገደማ እንደሆነ ጠቁመዋል።

መሠረት ሚድያ በዚህ ዙርያ ባደረገው ተጨማሪ ከ3 ሚልዮን ብር እስከ 42 ሚልዮን ብር የተያዘባቸው ኮንትራክተሮች እንዳሉ የተረዳ ሲሆን ከነዚህ ኮንትራክተሮች ውጪም በኮሪደር ልማት ዙርያ የመንገድ ግንባታ የተሳተፉ አቅማቸው ከፍ ያለ ኮንትራክተሮችም ክፍያ ተነፍጓቸው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችላል።

መረጃን መሠረት!

@MeseretMedia

43k 0 244 27 525



#የምርመራዘገባ አለም ባንክ በዲጂታል ፋውንዴሽን በኩል ለኢትዮጵያ የሰጠው 200 ሚልዮን ዶላር ምን ላይ እየዋለ ነው?

- በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ስር በግል አማካሪነት በአመት 120 ሺህ ዶላር የሚከፈለው ግለሰብ አለ

(መሠረት ሚድያ)- በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ይፋ ተደርጎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተጀመረው በ2013 ዓ/ም ነበር። በዚህ ወቅት ነበር የኢትዮጵያ ዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክት ብሄራዊ ኮሚቴ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስር ሆኖ መንቀሳቀስ የጀመረው።

ፋውንዴሽኑ ዋና አላማው የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎትን ማስፋፋት፣ የህዝብ ተቋማት ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ዝርጋታ፣ የብሄራዊ መታወቂያ ስራ፣ የግል የቴክኖሎጂ ተቋማትን አቅም መገንባት በስራው ውስጥ የተካተቱ ነበሩ።

እንቅስቃሴው ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ በመንግስት በይፋ ቢገለፅም አንዳንድ አነጋጋሪ ድርጊቶች ግን መታየት ጀምረዋል።

ለምሳሌ የአለም ባንክ የዛሬ አራት አመት 200 ሚልዮን ዶላር መድቦለት ስራ በጀመረው የዲጂታል ፋውንዴሽን ውስጥ በአማካሪነት ተቀጥረው እየሰሩ ከሚገኙት መሀል ዶ/ር ስሜነው ቀስስ ሲሆኑ የትምህርት መስካቸው የእንስሳት ህክምና ቢሆንም በዚህ የዲጂታል ዘርፍ በአማካሪነት ተቀጥረው በአመት 130,000 ብር በአማካሪነት እንደሚከፈላቸው ለመሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ ያሳያል።

በሌላ በኩል አቶ ሰለሞን ካሳ፣ ወይም ኢቢኤስ ቴሌቭዥን ላይ 'ቴክ ቶክ' በሚል ስያሜው የሚታወቀው ግለሰብ በተመሳሳይ በማማከር ቅጥር በአመት 120,000 የአሜሪካ ዶላር መቀጠሩ አነጋጋሪ እንደሆነባቸው ጉዳዩን የሚያውቁ ምንጮች ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል፣ ሰለሞን በአመት በርካታ ወራትን በአሜሪካ የሚያሳልፍ መሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ አስገራሚ እንደሚያደርገው ይገልፃሉ።

ይህ ብቻ ሳይሆን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር "Internet Exchange Point" በተባለ ፕሮግራም የኢንተርኔት ፍሰት በሀገር ውስጥ የዳታ ማእከል እንዲያልፍ የሚያደርገው ፕሮጀክት በጀት ተይዞ የነበረ ቢሆንም ስራውን ይዞ የነበረው ተቋም ከቢሮው እንዲለቅ ተደርጎ በሌላ እንዲተካ እንደተደረገ እና ይህም ከገንዘብ ጥቅም ጋር የተያያዘ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

"አይቲ ፓርክ" ተብሎ በሚጠራው ማእከል ውስጥ በዶላር እየከፈሉ የተከራዩ በርካታ ተቋማት እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ገቢ ግን ወደየት እየገባ እንደሆነም እንደማይታወቅ እነዚህ ምንጮች ያስረዳሉ።

"በሸገር ከተማ ቡራዩ ውስጥ ለሚገኝ አንድ የአዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች 'የቴክኖሎጂ ክህሎት ስልጠና ለመስጠት' በሚል ፋሪስ ለተባለ ድርጅት 21 ሚልዮን ብር በዲጂታል ፋውንዴሽን በኩል ተከፍሏል" የሚሉት እነዚሁ ምንጮች ይህም የተከናወነው በጨረታ ስም ሆኖ ሌሎች አቅም ያላቸው ተቋማት ገለል ተደርገው መሆኑን ጠቁመዋል።

የፋሪስ ድርጅት ባለቤት በቅርቡ የቴስላ 'ሳይበርትራክ' መኪና ካለቀረጥ ወደ ሀገር በማስገባቱ የሚታወቅ ሲሆን የዚህን መኪና ወደ ኢትዮጵያ መግባት ባለቤቱ አቶ ኤልያስ ይርዳው ማህበራዊ ሚድያ ላይ ለሀገሪቱ ትልቅ "የኢኖቬሽን" እምርታ ብሎ የገለፀበት መንገድ ብዙዎችን አነጋግሮ ነበር።

በዚህ ዙርያ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩን ዶ/ር በለጠ ሞላን እንዲሁም የዲጂታል ፋውንዴሽን ሀላፊውን አቶ ተሰማ ገዳን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

54.9k 0 306 42 865


Показано 20 последних публикаций.