ጋሽ ዘሌ ይህችን መጽሐፍ በሶፍት ኮፒ ከለቀቀ ትንሽ ቆይቷል ዛሬ እንደ ድንገት ስልኬ ውስጥ ያሉ ፋይሎችን ስበረብር ይህችን መጽሐፍ ከፈትኩኝ።
በጋሽ ዘሌ መጽሐፎችና ጽሁፎች እጅግ ከተጠቀሙ መካከል አንዱ እኔ ነኝ። ስለ ጋሽ ዘሌ ብዙ ብዙ ማለት እችላለሁ ግን የዚህ ጽሁፍ አላማዬ ስላልሆነ ዛሬ ውስጤ ሳሰላስል ወደነበረው እና ትልቅ ትምህርት ስለሆነኝ ስለዚህ መጽሐፍ ትንሽ ልበላችሁ።
መጽሐፉ 100 ገጾች ያሉት ሲሆን ርዕሱ ሳቢና ትንሽ አደናጋሪ ነው፤ "ክርስትና በቅናሽ" ይላል፥ ከርዕሱ ስር ደግሞ ይሄን መጽሐፍ ብታነቡ ምንም ዋጋ የማያስከፍልና ረካሽ ክርስትናን እንዴት መኖር እንደሚቻል ታውላችሁ የሚል ይመስላል።
ይሄን ጥበብ ሁሉም ቢያውቀው ይመኛልና መጽሐፉን ከፍቶ ለማንበብ እጅግ ያጓጓል። ምክንያቱም እውነተኛው ክርስትና ገና ከመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ጀምሮ ዋጋ የሚጠይቅና የሚያስከፍል መሆኑን ነው መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና የምንረዳው። ከዚያም ባለፈ እውነተኛ የክርስትናን ህይወት ለመኖር በምናደረገው የየዕለት ልምምዶቻችን የምናውቀው ክርስትና ዋጋ ሲያስከፍል ነው።
ታዲያ ጋሼ ምን እያለን ነው?
የሚገርመው በዚህ ጥያቄ ውስጥ እያለሁ ነበር መጽሐፉን ማየት የቀጠልኩት የመጽሐፉ ገጽ 2 ባዶ ነው። ገጽ 3ም ምንም የተጻፈ ነገር የለውም። ገጽ 4 ምን ይኖር ይሁን... ምንም የለም። አሁን ቶሎ ቶሎ የመጽፉን ገጾች ወደታች ማድረጌን ቀጠልኩኝ... ቀጣዮቹም ገጾች ባዶ ሆኑብኝ።
እኔ ያወረድኩት ፕዲኤፍ (pdf) የሆነ ችግር ያለበት ስለመሰለኝ ድጋሚ ላወርድ ወደ ጋሼ ቴሌግራም ገጽ አመራኹ... ድጋሚ አውርጄ ሳይም ያው ተመሳሳይ ነበር።
ጋሽ ዘሌ ፖስት ሲያደርግ የተሳሳተ መሰለኝና ለማንኛውም ብዬ እስከ መጨረሻ ድረስ ገጾቹን ለማየት አሰብኩና ከአንዱ ገጽ ወደ አንዱ ቀጠልኩኝ... እስከ 99ኛው ገጽ ከመጽሐፉ ርዕስና ከገጽ ቁጥር ውጭ ምንም የተጻፈ ነገር የለም። ምን አልባት ጋሼ ጋር ባለው ሶፍት ኮፒ ተጽፎ ይሁን አላውቅም። ከገጽ 99 በኋላ ግን የመጨረሻው 100ኛ ገጽ ብቻ ደብዘዝ ባለ ጽሁፍ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል "ርካሽ ክርስትናን ለመኖር ምንም መደረግ የለበትም።
ከውስጡ ዋጋ ጠያቂ ንጥረ ነገሮችን መቀነስ ብቻ ነው።
እነዚህም፤
እግዚአብሔር
ክርስቶስ
መንፈስ ቅዱስ
መስቀል
ቅድስና
ራስን መካድ
ደቀ መዝሙርነት
ወንጌል
ቃሉ
ጸሎት
ኅብረት
አገልግሎት"
ይሄን ሳነብ ነው ታዲያ ለህይወቴ እጅግ ትልቅ ትምህርት የወሰድኩት... ወዳጆቼ ክርስትና ክርስቶስን መምሰል ነው። ክርስቶስ በምድር እንዴት እንደኖረ እናውቃለን ያንን የእርሱን ፈልግ መከተል ነው ክርስትና። ክርስትናን በእኛ ጥበብ በቅናሽ መኖር አይቻልም የክርስትና ዋጋም በቅናሽ የለም ልኩ የኢየሱስ ህይወት ነው።
ስለዚህ ምንም ዋጋ ቢጠይቅም የተጠራነው እርሱን መስለን እንድንኖር ነውና እግዚአብሔር ይህንን ህይወት ያብዛልን እላለሁ። ተባረኩ።
✍ቢኒ
መጽሐፉ፦
https://t.me/zelalemmengistu/387