ኤ.ቲ.ኤም ማሽን ያለባቸው ቦታዎች ላይ በመገኘት ገንዘብ ሊያወጡ የሚመጡ ግለሰቦችን የሚረዳ መስሎ ሚስጥር ቁጥራቸውን በማየትና ሌላ ካርድ በመቀየር የማጭበርበር ወንጀል ይፈፅም የነበረን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 08 ቀን 2017 ዓ/ም (አዲስ ፖሊስ)፦ ተጠርጣሪው አለማየሁ የስጋት ይባላል፡፡ የወንጀል ድርጊቱን የሚፈፅመው ኤ.ቲ. ኤም ያለባቸው ቦታዎች በመገኘት ገንዘብ ሊያወጡ የሚመጡ በተለይም ደጋግመው የሚሞክሩ ሰዎችን ሲያይ የካርዳቸውን የሚስጥር ቁጥር በማየትና የሚረዳ በመምሰል ካርዳቸውን ወዲያው በሌላ በመቀየር እና ከአካባቢው በፍጥነት በመሰወር ከሌላ ማሽን ገንዘባቸውን አውጥቶ የሚሰወር ነው፡፡
ግለሰቡ በተመሳሳይ የወንጀል አፈፃፀም ሚያዚያ 7 ቀን 2017 ዓ/ም በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው ፈረንሳይ ማዞሪያ አካባቢ ከሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀኑ7:30 ሠዓት በመገኘት አንዲት ግለሰብ ገንዘብ ለማውጣት ሲሞክሩ ከኋላቸው ሆኖ የካርዱን ሚስጥር ቁጥር ካየ በኋላ የሚረዳ መስሎ በመቅረብ ማሽኑ እምቢ ብሏል እስኪ በሌላ ይሞክሩ በማለት ካርዳቸውን ይዞ ይሄዳል፡፡ ግለሰቧም እውነት መስሏቸው ካርዱን ተቀብለው ደጋግመው ሲሞክሩ የተመለከታቸው የባንኩ ማናጀር ካርዳቸውን ተቀብሎ ሲያረጋግጥ የግል ተበዳይ አለመሆኑን በማወቁ ተከሳሹ ከአካባቢው ሳይርቅ በፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል።
ተከሳሹ ኪሱ ሲፈተሽም 4 የንግድ ባንክና 3 የአቢሲኒያ ባንኮች ኤ.ቲ.ኤም ካርዶች ከኪሱ የተገኘ ሲሆን ተጠርጣሪው ከ6 ወራት በፊት መርካቶ አካባቢ ከሚገኝ አንድ ባንክ በተመሳሳይ የማጭበርበር ወንጀል 7ሺህ ብር እንዳወጣም በምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን ምርመራውም ቀጥሏል።
በተለያዩ ቦታዎች ተመሳሳይ ወንጀል የተፈፀመባቸው ግለሰቦች ካሉ የካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመቅረብ ለፖሊስ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጡ እያሳሰበ ህብረተሰቡ ገንዘብ ለማውጣት በተለይም በባንኮችና የገንዘብ ማውጫ ማሽኖች በሚገኙባቸው ቦታዎች ሲገኝ የሚረዱ ወይም የባንክ ሠራተኛ በመምሰል የሰዎችን የኤ.ቲ.ኤም ካርድ የሚስጥር ቁጥራቸውን በማየት የማጭበርበር ወንጀል በሚፈጽሙ ግለሰቦች ሠለባ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙም በአቅራቢያ ለሚገኝ ፖሊስ መረጃ በመስጠት ተባባሪ መሆን እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።
@Sheger_Press@Sheger_Press