❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #የካቲት ፲፪ (12) ቀን።
❤ እንኳን #ለመላእክት_አለቃ ለከበረ #ለቅዱስ_ሚካኤል ወደ ረዓይታዊ ወደ ሶምሶን ተልኮ ኃይልን ሰጥቶት ጠላቶቹን ድል እንዲያደርግ ለረዳበት ወራዊ መታሰቢያ በዓል፣ ተጋዳይ ፍጹም የዋሕና ትሑት ለሆነው ለከበረ አባት #ለአባ_ገላስዮስ ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ #ከዶርቃስ ከመታሰቢያው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #የከበረ_ቅዱስ_ሚካኤልን በዚች ዕለት እግዚአብሔር ወደ ረዓይታዊ ወደ ሶምሶን ላከው የፍልስዔም ሰዎች ሊገድሉት በጠላትነት በተነሡበት ጊዜ ድል እስከ አደረጋቸውና እስከ ገደላቸው ድረስ ረዳው ኃይልንም ሰጥቶ በአህያ መንጋጋ ከእርሳቸው አንድ ሺህ ሰዎችን ገደለ። ተጠምቶም ለሞት በተቃረበ ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ተገለጠለትና አጸናው እግዚአብሔር ከአህያ መንጋጋ አጥንት ውኃን አፈለቀለትና ጠጥቶ ዳነ።
❤ ዳግመኛም ከሚስቱ ጋር ተስማምተው ዐይኖቹን አሳውሩ የራሱንም ጠጒር ላጩ አሠሩትም ከዚያም በኋላ ለጣዖቶቻቸው በዓልን በአዘጋጁ ጊዜ ሶምሶንን ወደ ጣዖቶቻቸው ቤት ወሰዱት በዚያም ሦስት ሽህ ያህል ሰዎች ተሰብስበው ነበር የከበረ ቅዱስ ሚካኤልም ተገለጠለትና ኃይልን መላው የዚያንም ቤት ምሰሶዎች ነቀላቸው ቤቱም በላያቸው ወድቆ ከእርሱ ጋር ሁሉንም ገደላቸው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_ገላስዮስ፦ የዚህ ቅዱስ ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ምዕመናን ናቸው በጥበብንና የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተማሩትና ዲቁና ተሾመ። ከታናሽነቱም ጀምሮ ይህን ዓለም ንቆ ተወ የክብር ባለቤት የሆነ የክርስቶስንም ቀንበር በመሸከም በምንኵስና ሁኖ በትጋት እየጾመ እየጸለየና እየሰገደ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ እግዚአብሔር መርጦት በአስቄጥስ ገዳም ባሉ መነኰሳት ላይ ቅስና ተሾመ። ተጋድሎውንና አገልግሎቱን እየፈጸመ ሳለ ለአባ ጳኵሚስ እንደ ተገለጠ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና መነኰሳትን ሰብስቦ ፈሪሀ እግዚአብሔርን የምንኵስናንም ሕግ ያስተምራቸው ዘንድ አዘዘው በዚያንም ጊዜ ብዙዎች መነኰሳትን ሰበሰበ መንፈሳዊ የሆ የአድነት ማኅበርራዊ ኑሮንም ሠራላቸው እርሱ በመካከላቸው እንደ መምህር አልሆነም ከእርሳቸው እንደሚያንስ አገልጋይ እንጂ።
❤ ይህ አባት የዚህ ዓለም ጥሪት ሁሉ ንቆ የተወ ሆነ እጅግም የዋህና ቸር ሆነ ከብሉይና ከሐዲስ መጻሕፍቶችም የተሰበሰበ አንድ ታላቅ መጽሐፍን አጻፈ ለማጻፊያውም ዋጋ ዐሥራ ስምንት የወርቅ ዲናር አወጣ ከርሱ ሊጠቀሙ በሚፈልጉ ጊዜ መነኰሳቱ እንዲያነቡት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአትሮንስ ላይ አኖረው። አንድ መጻተኛ ሰውም አረጋዊ አባ ገላስዮስን ሊጎበኝ በገባ ጊዜ ያንን መጽሐፍ አየውና አማረው በጭልታም ከዚያ ሰርቆ ወጣ ወደ ከተማ ውስጥም በገባ ጊዜ ሊሸጠው ወደደ አንድ ሰውም ዋጋው "ምን ያህል ነው" አለው እርሱም "ዐሥራ ሰባት የወርቅ ዲናር ስጠኝ" አለው። ያ የሚገዛውም ሰው "ያልከውን እሰጥሃለሁ ነገር ግን ለወዳጄ እስካሳየው ታገሰኝ" አለው ያሳየውም ዘንድ ወደ አባ ገላስዮስ ወሰደውና "ተመልከትልኝ መልካም ከሆነ እገዛዋለሁ" አለው አባ ላስዮስም "ያመጣውን ሰው ከአንተ ምን ያህል ፈለገ" አለው "ዐሥራ ሰባት የወርቅ ዲናር" አለው ቅዱስ ገላስዮስም "መጽሐፉ መልካም ነው ዋጋውም ቀላል ነው ግዛው" ብሎ መለሰለት። ወደ ሌባውም በተመለሰ ጊዜ አባ ገላስዮስ የነገረውን ሠውሮ "ለአባ ገላስዮስ አሳየሁት እርሱም ዋጋው በዝቷል አለኝ" አለው፡ሌባውም "ያ ሽማግሌ ሌላ የተናገረህ ነገር የለምን" አለው "አዎን የለም" አለው። ሌባውም "እንግዲህ እኔ አልሸጠውም" ብሎ ወደ አባ ገላስዮስ ሒዶ ከእግሩ በታች ወድቆ ለመነው "ሰይጣን አስቶኛልና ይቅር በለኝ መጽሐፍህንም ውሰድ" አለው የከበረ ገላስዮስም "እኔ መጽሐፉን መውሰድ አልሻም" አለው። ሌባውም በፊቱ እያለቀሰና እየሰገደ ብዙ ለመነው በብዙ ድካምም መጽሐፉን ተቀበለው ማንም ያወቀ የለም። እግዚአብሔር ትንቢት የመናገርን ሀብት ሰጥቶት ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ።
❤ በአንዲትም ዕለት ለገዳሙ መነኰሳት ዓሣ አመጡ ባለ ወጡ ዓሣን አብስሎ በቤት ውስጥ አኑሮ አንዱን ብላቴና ጠባቂ አድርጎ ወደ ሥራው ሔደ ብላቴናውም ከዚያ ዓሣ በላ። ባለ ወጡ በመጣ ጊዜ ተበልቶ አገኘውና በብላቴናው ላይ ተቆጥቶ "አረጋዊ አባቶች፡ ሳይባርኩት እንዴት ደፍረህ በላህ" አለው የቊጣ መንፈስም በልቡ አደረና ብላቴናውን ረገጠው ወዲያውኑ ሞተ እንደሞተም አይቶ ደነገጠ ታላቅ ፍርሀትንም ፈራ ሒዶ ለአባ ገላስዮስ የሆነው ሁሉ ነገረው እርሱም "ወስደህ ከቤተ መቅደሱ ፊት አስተኛው" አለው ሰውየውም እንዳዘዘው አደረገ ወደ ማታ ጊዜም አረጋውያን መነኰሳት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሰብስበው የማታውን ጸሎት አድርሰው ወጡ አረጋዊ አባ ገላስዮስም በወጣ ጊዜ የሞተው ብላቴና ተነሥቶ በኋላው ተከተለው ከመነኰሳትም ማንም አላወቀም እርሱም የገደለውን ባለ ወጥ ለማንም እንዳይናገር አዘዘው።
❤ የተመሰገነ አባ ገላስዮስም ያማረ ትሩፋቱንና ተጋድሎውን ፈጽሞ አድርሶ እግዚአብሔርንም አገልግሎ ይህንንም በጎ መታሰቢያን ትቶ ከዚህ ከኃላፊው ዓለም የሚለይበት ሲደርስ የካቲት12 በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ገላስዮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ለዘላለሙ ትኑር አሜን። ምንጭ፦የየካቲት12 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤#የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዐውዶሙ። ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ። ጠዐሙ ወታእምሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር"። መዝ 33፥7-8። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 25፥31-ፍ.ም።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ወበኀቤየሰ ፈድፋደ ክቡራን አዕርክቲከ እግዝኦ። ወፈድፋደ ፀንዑ እምቀደምቶሙ። እምኌቆሙ እምኆፃ ይበዝኁ"። መዝ 138፥17-18። የሚበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 5፥6-ፍ.ም፣ ይሁ 1፥9-19 እና የሐዋ ሥራ 28፥30-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 20፥24-29። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ሚካኤል በዓል፣ የአቡነ ሠርዘ ጴጥሮስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
@sigewe https://t.me/joinchat/AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886 https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKw