በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን ያሉ የጦር ትብብሮች ቀጠናው ላይ ምን ያስከትላል?
በሱዳን በቀጠለው የእርስ በእርስ ጦርነት እየተደረጉ ያሉ የጦር አጋርነቶች ሱዳንና ደቡብ ሱዳንን ብሎም ቀጣናውን ወደ አደገኛ ነገር እንደሚመራው ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ነው።
የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ባለሙያው አለን ቦስዌል በደቡብ ሱዳን ነገሮች በዚህ የሚቀጥሉ ከሆነ የደቡብ ሱዳንን ጦርነት ከሱዳን ጦርነት ለይተን ማየት ከባድ መሆኑን ተናግሯል።
ባለፈው የካቲት የሰሜን የሱዳን ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ(SPLM-N) እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ(RSF) መካከል ትብብር መፈጠሩ ይታወሳል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ(RSF) ከ2023 ጀምሮ በጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ከሚመራው የሱዳን ጦር ጋር ጦርነት ውስጥ ሲሆን በምስራቅ እና ማዕከላዊ ሱዳን ያለውን ቁጥጥር ማጠናከር ይፈልጋል።
የሰሜን የሱዳን ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ አብድላዚዝ አልሂሉ በሚባሉ ሰው ሲመራ ሱዳን ከደቡብ ሱዳን በምትዋሰንባቸው የብሉ ናይልና ደቡብ ኮርዶፋን አካባቢዎች እንቅስቃሴ የሚያደርግና ባለፉት 10 ዓመታት ከሱዳን ጦር ጋርም እየተዋጋ የሚገኝ ነው።
የሰሜን የሱዳን ህዝቦች ንቅናቄጰ(SPLM-N) ደቡብ ሱዳንን ከሱዳን የገነጠለውን እንቅስቃሴን የመራው የሱዳን ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ(SPLM) አካል የነበረ ሲሆን የሱዳን መንግስትም እነዚህን ታጣቂዎች ሲዋጋ ቆይቷል።
ደቡብ ሱዳን ተገንጥላ ስትወጣ የብሉ ናይል እና ደቡብ ኮርዶፋን አካባቢዎች በሱዳን ውስጥ የቀሩ ሲሆን ታጣቂዎቹ ከደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ድጋፍ እየተደረገላቸውም በዚህ አካባቢ ከሱዳን መንግስት ጋር ሲዋጉ ቆይተዋል።
በዚህ ታሪካዊ ትስስር የተነሳም ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ሳልቫ ኪር የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉንና የሰሜን የሱዳን ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄን ይደግፋሉ ብለው እንደሚያምኑ አለን ቦስዌል ይናገራል።
ታዲያ በሁለቱ ጦሮች መሃል ስምምነት ከተደረሰ በኋላ በምላሹ በጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ሁለቱን ጦሮች እንዲዋጉለት እያስታጠቀ መሆኑ ተነግሯል።
ተንታኞች የሰሜን የሱዳን ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር የተጣመረው በአንድ ጊዜ ከሱዳን ጦር እና ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር መዋጋት ስለማይችል ነው ብለዋል።
የአብድልአዚዝ ጦር የደበብ ኮርዶፋን እና ብሉ ናይል አካባቢዎችን የተቆጣጠረ ሲሆን የደቡብ ኮርዶፋ የሱዳንን ማዕከላዊ ቦታዎች ለመቆጣጠር ከሚያስችለው ኋይት ናይል ጋር ሲዋሰን ብሉ ናይል ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ይዋሰናል፤ ይህም ቦታዎቹን ስትራቴጂካዊ አድርጎታል።
እንደ አለን ቦስዌል ገለፃ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከነፃነት ንቅናቄው ጋር መጣመሩ በቀላሉ መሳሪያዎችን ከደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ እንዲያስገባ ያግዘዋል።
አለን አክሎም ጦሩ ወደ ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ ድንበሮች ገብቶ እየወጣ የሱዳን ጦርን መዋጋት እንደሚችል ተናግሯል።
በደቡብ ሱዳን ደግሞ ከሰሞኑ በሁለቱ መሪዎች መካከል ግጭት ያለ ሲሆን የሁለቱ መሪዎች ግጭት ግን ደቡብ ሱዳን ነፃ ሃገር ከመሆኗ በፊት እንደሚጀምር ተነግሯል።
ደቡብ ሱዳን ነፃ ሳትሆን ሪክ ማቻር በወቅቱ የሱዳን ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄን ለመዋጋት እና የንቅናቄው መሪ የነበሩትን ጆን ካራንግን ለማስወገድ ከካርቱም መንግስት ድጋፍ የተቀበሉ ሲሆን በ2005 ካራንግ በሄሊኮፕተር አደጋ ሲሞቱ ሳልቫ ኪር የንቅናቄው መሪ ሆነው ብቅ አሉ።
የማቻር ጦር በአብዛኛው የኑዌር ጎሳ ሲሆን ሪሳቸውን በሳልቫ ኪር ከሚመራው ንቅናቄ ወይም SPLM ለመለየትም ስማቸው ላይ In Opposition የምትል ጨምረው SPLM-IO ብለው ስማቸውን ሰየሙት።
በአንፃሩ ሳልቫ ኪር የዲንካ ጎሳ ሲሆኑ በሁለቱ መካከልም ግጭት ተነስቶ ከ400,000 በላይ ሰዎች ህይወት አለፈ።
በዚህ ወርም በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉና በSPLM-IO መካከል ግጭት መነሳቱ ተዘግቦ የነበረ ሲሆን በብሉ ናይል ግዛቶችም ውጊያ ተደርገው እንደነበር ተዘግቧል።
አለን ቦሶዌል በደቡብ ሱዳን ያለው ውጥረት በዚሁ ከቀጠለ አብዛኞቹ ደቡብ ሱዳናዊያን የሱዳን ቅጥረኛ ተዋጊዎች እንደሚሆኑ ይናገራል። ለማሳያነትም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ደቡብ ሱዳናዊያንን ለጦር እየመለመለ መሆኑን ተናግሯል።
አለን አክሎም ደቡብ ሱዳን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ከገባች ከሱዳን ጦር በላይ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሊጠቀም እንደሚችል ተናግሯል።
ትንታኔው ሲጠቃለልም ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና የሰሜን የሱዳን ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄን እንደሚደግፉ ሲገመት የሱዳን ጦር በምላሹ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎችን እያስታጠቀ ነው የሚል አንድምታ አለው።
ሱዳን ባለፉት ሁለት አመታት ከፍተኛ የተባለውን የሰብዓዊ ቀውስ ያስተናገደ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ስትሆን ከሰሞኑ የሱዳን ጦር ዋና ከተማዋን መያዙ ሲታወስ የሱዳን የጦር አመራሮችም ደቡብ ሱዳን፣ ቻድና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ይደግፋሉ ብለው ሲከሱ ነበር።
በቀጣናው የሁለቱ ሃገራት የፖለቲካ ግጭቶች ውስጥ መግባት በአካባቢው ሌላ ቀውስን እንዳይፈጥርም ተሰግቷል።
Published On : Al Jazeera
@Tikvahethmagazine @tikvahmagbot