ደብረ ዘይት ሚዲያ


Гео и язык канала: Эфиопия, Амхарский
Категория: Религия


ቤተክርስቲያን ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ።

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Гео и язык канала
Эфиопия, Амхарский
Категория
Религия
Статистика
Фильтр публикаций


+ ድንገት የተበጠሰ ገመድ +

የደብረ ዳሞ ገዳም በገመድ ብቻ የሚወጣ እጅግ ጥንታዊ ገዳም ነው:: ይህንን አቡነ አረጋዊ በዘንዶ የወጡትን ታላቅ ገዳም ለመውጣት በግንባታው ወቅት በአፄ ገብረ መስቀል የተሠራ ደረጃ ነበረው:: ሆኖም አቡነ አረጋዊ ደረጃውን ዳህምሞ (አፍርሰው) ብለው በማዘዛቸው እስከ አሁን ድረስ በገመድ የሚወጣበት ገዳም ሆኖአል::

የደብረ ዳሞ መውጫ ገመድ እጅግ ወፍራም ሲሆን እስከ አሁን ድረስ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተንጠላጥለው ወጥተው ወርደውበታል:: ይህ እጅግ ወፍራም ገመድ ለዘመናት ሲያገለግል ተበጥሶ ሰው ጥሎ አያውቅም:: በታሪክ የማይዘነጋና መሃል ላይ የተበጠሰበትና ሰው የጣለበት ቀን አለ:: (የዲያቢሎስ መተናኮል ነው የሚል አለ)

በዚያ ቀን በተበጠሰው ገመድ ላይ የወረደው መንገደኛ ጻድቁ አባ ተክለ ሃይማኖት ነበሩ:: መነኮሳቱን ተሰናብተው በዚያ ገመድ ሲወርዱ ተበጥሶ የማያውቀው ገመድ ድንገት ተበጠሰ:: ከላይ የሚያዩት አባቶች ቁልቁል እያዩ በድንጋጤ ጮኹ:: ሆኖም እግዚአብሔር ለጻድቁ የብርሃን ክንፍ ሠጥቶአቸው ከተበጠሰው ገመድ ተለይተው እንደ መልአክ በርረው ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ወርደው መሬት ላይ አረፉ:: ባረፉባት ሥፍራም ቤተ ክርስቲያን ተሠራባት::

ወዳጄ በሕይወትህ ድንገት የተበጠሰ ገመድ የለም? ሳትጠብቀው የተበጠሰ ገመድ ማንም ላይ ሳይበጠስ አንተ ላይ የጨከነ ገመድ የለም? ምን ዓይነት ገመድ አትበለኝ:: የእንጀራ ገመድ የኑሮ ገመድ የትምህርት ገመድ የፈለግኸው ገመድ በለው:: እሱን ተጠምጥመህ ይዘህ ወደ አንዳች ቦታ ለመድረስ የተማመንክበት ተስፋህን ሙሉ በሙሉ የጣልክበት ገመድ የለም? ድንገት ተበጥሶ ዙሪያው ገደል አልሆነብህም? ሰዎች ማንም ላይ ያልተበጠሰ ገመድ አንተ ላይ ሲበጠስ አይተው "ምኑ ዕድለ ቢስ ነው?" ብለው የተደነቁብህ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ "ከባሕር አደጋ ተርፎ ዕባብ የነደፈው እንዴት ኃጢአተኛ ቢሆን ነው?" ብለው በትዝብት ዓይን እንዲያዩህ ያደረገ በሕይወትህ ሳታስበው ተበጥሶ ዙሪያው ገደል የሆነ ሥፍራ ላይ የጣለህ የሕይወት ገመድ ይኖር ይሆናል::

በዕድልህ አትማረር በሕይወትህ ድንገት የሚበጠስብህ ገመድ የምትወድቅበት ሳይሆን ክንፍ አውጥተህ የምትበርበት ነው:: ፈጣሪ የተማመንክበትን የምታየውን ገመድ እንዲበጠስብህ ከፈቀደ ያላየኸውን ክንፍ ሊሠጥህ እንጂ ሊጥልህ አይደለም:: የሕይወትህን ገመድ የተበጠሰበትን ቀን "እግዚአብሔር ለመልካም አሰበው" ብለህ እንደ ዮሴፍ ታመሰግንበታለህ::
ገመድህን የሚበጥሰው ከገደል ሊጥልህ ሳይሆን በክንፍ አብቅሎ ሊተክልህ ነው:: የሚተክልህ በበረሃ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ነው:: ተራ ተክል የምትሆን እንዳይመስልህ:: የሃይማኖት ተክል (ተክለ ሃይማኖት) ትሆናለህ:: ተክለ መንፈስ ቅዱስ ተክለ ወልድ ተክለ አብ ትሆናለህ:: አብ የተከለው ደግሞ አይነቀልም!

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 24 2013 ዓ ም

ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-
ዩቱብ
https://www.youtube.com/@12Samual

ቴሌግራም
https://t.me/tsidq






+ ጊዮርጊስ ሆይ ከእኛ ወገን ነህን? +

ወደ አድዋ ከዘመተው ሕዝብ አብዛኛው ባዶ እግሩን ነበር:: ዳዊት ጎልያድን ሊዋጋ ሲወጣ ከያዛት በትር በቀር አብዛኛው ሰው መሣሪያ አልታጠቀም:: አብዛኛው ዘማች ባዶ እጁን የዘመተው ሁለት ነገር አስቦ ነው:: መሣሪያ ባይኖረውም በውጊያው መካከል ከጠላት ጦር መሣሪያ ነጥቄ እዋጋለሁ አለዚያም ከሚወድቁት ላይ መሣሪያ አንሥቼ እዋጋለሁ ብሎ ነበር:: በውጊያው መድፍ በጎራዴ እስከመማረክ ያደረሳቸውም ይህ ቆራጥነታቸው ነበር::

ለመንፈሳዊ ጥንካሬያቸው ደግሞ ምሥጢሩ አብራ የዘመተችው የቤተ ክርስቲያን ጸሎት እና ንጉሡ በድንግል ማርያም ስም ምለው የሠጡት አደራ ነበር:: ለተገፉ የሚቆመው ሰማዕቱ ጊዮርጊስም በግፍ ባሕር አቁዋርጠው በደሃ ሕዝብ ላይ እሳት ከሚያዘንቡት ከአባቱ ዘመዶች ከሮማዊያን ጋር ሳይሆን እንደ ዳዊት በትር ይዘው በእግዚአብሔር ስም ከወጡት ባለማተቦች ጋር በምልጃው ተሰልፎ ዋለ::

በዚያች ዕለት አንድ ጣሊያናዊ ቅዱስ ጊዮርጊስን አግኝቶ ኢያሱ ቅዱስ ሚካኤልን እንደጠየቀው "ከእኛ ወገን ነህ ወይንስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ? " ብሎ ቢጠይቀው ኖሮ "እኔ አሁን ከእግዚአብሔር ተልኬ መጥቻለሁ ይልቅስ የቆምክባት መሬት ኢትዮጵያ የተቀደሰች ናትና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ" ባለው ነበር::

የዐድዋ ዘማቾች ጾመኞች ነበሩ:: እንግሊዝም ጣሊያንም ሰይጣን ይመስል ኢትዮጵያን የተዋጉአት በዐቢይ ጾም ነበር:: "ወድቀህ ብትሰግድልኝ መንገድና ፎቅ እሰራልሃለሁ" ያለንን ጣሊያን አባቶቻችን "ሒድ አንተ ጣሊያን የራስህን እንጂ የእኔን አታስብምና" ብለው ድል ነሡት::

ዘማቾቹ የምግብ እጥረት ቢኖርም እንኩዋን ጾሙን ትተን ካልበላን አላሉም:: ድንገት መሞቴ አይቀር ብበላ ይሻለኛል ሳይሉ ተዋግተው ድል ተቀዳጁ:: እኛ በሰላም ጊዜ የምንተወውን ጾም እነርሱ በጦርነት ላይም ሆነው አልተዉትም:: በዚያ ድል ሀገሪቱ ለዐርባ ዓመት ከጦርነት ስታርፍ ለዕድሜ ዘመንዋ ደግሞ ከቅኝ ግዛት ዐረፈች::

ቅኝ ግዛት ብንገዛ ኖሮ ደሃ አንሆንም ነበር የሚል ሰው አይጠፋም:: ይህንን አሳብ የብዙ አፍሪካውያን ሀገራት ጆሮ አይስማው:: ዛሬ ነጻ ከወጡም በኁዋላ በባርነት ሕሊና የሚሰቃዩ ብዙ ናቸው::

ብዙ በፈረንሳይ የተገዙ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ዛሬም ድረስ በአደራ አስተዳደር በፈረንሳይ በእጅ አዙር ይተዳደራሉ:: በተባበሩት መንግሥታት ሳይቀር ቅኝ ገዢዎቻቸውን ተወካይ ሁነኝ ብለው የሚልኩ ሀገራት አሉ::

ዛሬም ድረስ በአንዳንድ አፍሪካ ሀገራት ጥቁሮች ሊስተናገዱ በተሰለፉበት ሱፐር ማርኬት አንድ ነጭ ከመጣ ሰልፍ ሳይይዝ ቅድሚያ ይስተናገዳል:: (በዓይኔ ያየሁት ነው)

ዛሬም ድረስ ብዙ አፍሪካዊያን ጥቁር በአስተሳሰብ ከነጭ በታች ነው ብለው ያምናሉ:: በዜኖ ፎቢያ የገዛ ወንድሞቻቸው አፍሪካውያንን የሚያሰቃዩ ደቡብ አፍሪካውያን ነጭ ሰፈር ግን ዝር አይሉም:: ሂሳብ ስታሰላ ሲያዩህ እንኩዋን አንተ ጥቁር ሆነህ እንዴት ያለ ካልኩሌተር መደመር ቻልክ የሚሉ ሰዎች ተፈጥረዋል::

በአውሮፓ በአሜሪካ ተወልደው አድገው ስኬታማ የሆኑት ጥቁሮች እንኩዋን የቤተሰብ ስማቸው ላይ አያቶቻቸውን በባርነት የገዛው ነጭ ገዥ ስም አብሮ ስለሚለጠፍ የዕድሜ ልክ የበታችነት ይሰማቸዋል:: አባቶቻችን ከብዙ ጣጣ አድነውናል አሁን ራሳችን የምንፈጥረውን ችግር ቢያዩ ለማመን የሚቸገሩ የሚሆኑትም ዘር ሳይለዩ አብረው የተዋደቁት ጀግኖች ናቸው:: ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬም ቤሩታዊት ኢትዮጵያን ከዘረኝነትና ጥላቻ ከመጨካከን ደራጎን ይታደጋት ዘንድ የምንማጸንበት ጊዜ ነው::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
የካቲት 23 2012 ዓ ም
ወላይታ ሶዶ ኢትዮጵያ

ፎቶ :- ሊባኖስ ቤሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤሩታዊትዋን ያዳነበትን ሥፍራ ተሳልሜ የተነሣሁት ነው::

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ!
ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-
ዩቱብ
https://www.youtube.com/@12Samual

ቴሌግራም
https://t.me/tsidq


+ አምናለሁ እና አላምንም +

ልጁ የታመመበት አባት ነው:: ጌታን "ቢቻልህስ ልጄን ፈውስልኝ" አለው:: ኢየሱስም፦ ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል፡ አለው።

ይህን ጊዜ ሰውዬው "ወዲያውም የብላቴናው አባት ጮኾ፦ አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው፡ አለ" ማር. 9:24

የዚህ ሰውዬ ንግግር ፍቺ የሚፈልግ ቅኔ ይሆንብኛል "አምናለሁ አለማመኔን እርዳው"

ይኼ ሰውዬ ያምናል ወይንስ አያምንም?

ያምናል እንዳንል "አለማመኔን" ይላል ፤ አያምንም እንዳንል "አምናለሁ" ይላል:: የቸገረ ነገር ነው? ሁሉን አዋቂው መድኃኔዓለም ምን ለማለት እንደፈለገ ገብቶት ልጁን ፈወሰለት:: እኔ አላዋቂው ግን "አምናለሁ አለማመኔን እርዳው" የሚለውን ቃል እየደጋገምኩት ቀረሁ::

እያመኑ አለማመን እንዴት ያለ ነው? ብዬ መላልሼ ሳጤነው ግን ሰውዬው የእኔኑ ድክመት እየተናገረ እንደሆነ ገባኝ::

አምናለሁ እላለሁ:: በእርግጥም በፈጣሪ መኖር አምናለሁ:: ሁሉን እንደሚችልም አምናለሁ::
ግን ደግሞ በእርሱ ታምኜ አላውቅምና በሥራዬ እክደዋለሁ:: ኑሮዬ "በሥራቸው ይክዱታል" ከተባሉት የሚመደብ ነው:: (ቲቶ 1:16) አቅዋሜ የማመን ኑሮዬ ያለማመን ነውና አምናለሁ አለማመኔን እርዳው ብል ለእኔ የሚገባ ጸሎት ነው::

ወረደ ተወለደ ተጠመቀ ተሰቀለ ሞተ ተነሣ ዐረገ ብዬ አምናለሁ:: በትሕትና መውረድን ፣ በንስሓ መወለድን ፣ በታናሽ እጅ ዝቅ ብሎ ጽድቅን መፈጸምን ፣ መከራን በትዕግሥት መቀበልን ፣ ከመከራ ሞት ወዲያ ተነሥቶ በክብር ከፍ ማለትን ግን እኔ ሕይወት ላይ አላውቀውም:: የምተርከው ክርስቶስ እንጂ የሚተረክ ክርስትና የለኝም:: ስለዚህ አምናለሁ አለማመኔን እርዳው በልኬ የተሰፋ ጸሎት ነው::

መች በዚህ ያበቃል::

እጾማለሁ አለመጾሜን እርዳው::
ከምግብ እጾማለሁ ከኃጢአት ግን አልጾምም:: ሥጋ መብላት ትቼ የሰው ሥጋ በሐሜት የምበላ ነኝና እጾማለሁ አለመጾሜን እርዳሁ እላለሁ::

እጸልያለሁ አለመጸለዬን እርዳው::
ቆሜ የማደርሰው ጸሎትስ አለኝ:: ግን ልቤ ሠላሳ ቦታ ደርሶ ይመለሳል:: የምጸልየው ማናገር የማልፈልገውን ሰው በግድ የማናግር ያህል የግብር ይውጣ እንጂ ነፍሴ እርሱን ሽታ አይደለምና እጸልያለሁ አለመጸለዬን እርዳው እላለሁ::

እሰግዳለሁ አለመስገዴን እርዳውስ?
ላቤ እስኪወርድ ሰግጄ አውቃለሁ:: ልቤ ግን አንዴ አልሰገደም::

ጌታ ሆይ እመጸውታለሁ አለመመጽወቴን እርዳው:: እዘምራለሁ አለመዘመሬን እርዳው:: አስቀድሳለሁ አለማስቀደሴን እርዳው:: እማራለሁ አለመማሬን እርዳው:: ሆኜ ያልሆንሁትን አድርጌ ያላደርግሁትን ሁሉ አንተ ታውቀዋለህና እርዳኝ::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጳጉሜን 3 2015 ዓ.ም.

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)

ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-
ዩቱብ
https://www.youtube.com/@12Samual

ቴሌግራም
https://t.me/tsidq




++ እንዴት ወድቀን እንዴት ተነሣን? ++ በዲ.ን ሄኖክ ኃይሌ ++
ኦሪት ዘፍጥረት ስለሰው ልጅ ውድቀት ሲናገር ዕባብና ሔዋን ያደረጉትን ቃለ ምልልስና በዕባብ ምክር ሠጪነት የሰው ልጅ እንዴት ከገነት እንደተባረረና ጸጋውን እንደተገፈፈ ያስረዳል፡፡
ይህንን የዕባብና የሔዋን ቃለ ምልልስን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብናወጣው ወይም ኦሪት ዘፍጥረት የአዳምና ሔዋንን ከገነት መባረር ብቻ የሚናገር ቢሆን ኖሮ ‹ምን አጥፍተው ነው የተባረሩት?› ወደሚል ግራ መጋባት ውስጥ እንገባ ነበር፡፡
ወዳጄ የዕባብና ሔዋንን ቃለ ምልልስ መስማት ሳይችል የአዳምና ሔዋንን ከገነት የመባረር ታሪክ ለመረዳት የሚችል እንደሌለ ሁሉ የእመቤታችንንና የቅዱስ ገብርኤልን ቃለ ምልልስ ሳያነብ የሰው ልጅን ወደ ገነት የመግባትና የመዳን ታሪክ ለመረዳት የሚችል ሰው ማንም የለም፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በአዳምና በክርስቶስ ተምሳሌት (Christ-Adam analogy) አድርጎ ጻፈ:: ክርስቶስን ‹ኋለኛው አዳም› ብሎ ጠርቶታል፡፡ (1ቆሮ. 15፡45) አዳምንም ‹አዳም ይመጣ ላለው ለእርሱ አምሳሉ ነው› በማለት የክርስቶስ ምሳሌ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ (ሮሜ. 5፡14) የሰው ልጅ ተፈጥሮ ታሪክ የተጀመረው ከአዳም ታሪክ እንደነበር የሰው ልጅ አዲሱ ተፈጥሮ ታሪክም የተጀመረው በዳግም ፍጥረት (Recaptulation) በተፈጠርንባት በቀራንዮ ነው፡፡
ይህም ንጽጽርም በኁዋላ ዘመን ለተነሡ እንደሰማዕቱ ዮስጦስና እንደ ያዕቆብ ዘሥሩግ ያሉ ሊቃውንት የማርያምና ሔዋን ተምሳሌትን (Mary eve analogy) እንዲያመሠጥሩ መነሻ ሆናቸው:: ያነጻጸሩት ሔዋንን ከማርያም ብቻ ሳይሆን እንዴት ወደቅን እንዴት ተነሣን የሚለውን ነው::
ሔዋን ለውድቀታችን መነሻ ነበረች ማርያም ግን ለመነሳታችን ምክንያት ሆነች:: ሔዋንን ሰይጣን በዕባብ ተመስሎ አነጋገራት:: ማርያምን ግን እግዚአብሔር በገብርኤል ሆኖ አነጋገራት:: ሔዋን የዕባቡን ቃል በመስማትዋ ከገነት ወጣን : ማርያም የገብርኤልን ቃል በመስማትዋ ወደ ገነት መለሰችን::
የዕባብና የሔዋንን ቃለ ምልልስ በቁጭት እናነበዋለን:: የድንግልና የገብርኤልን ምልልስ ግን በደስታ እንጸልየዋለን:: ያ ቃለ ምልልስ እኛን ወደ ሕይወት የመለሰ ቃለ ምልልስ ነው:: የ15 ዓመትዋ ብላቴና ማርያም ምድራዊያንን ሁሉ ወክላ ከሰማያዊው መልእክተኛ ጋር ተነጋግራ ዕርቃናችንን አለበሰችን:: የድሆች ልጅ የሆነችው ብላቴና የመላእክትን አለቃ በጥያቄ አስጨንቃ መርምራ ከጭንቃችን ገላገለችን::
ሔዋን የዕባብን ምክር ሳትመረምር ተቀበለች:: ድንግል ማርያም ግን የገብርኤልን ብሥራት መረመረች:: ለሔዋን ዲያቢሎስ "እግዚእብሔር እንደርሱ እንዳትሆኑ ብሎ ከለለላችሁ" ብሎ ከፈጣሪ አጣላቸው:: ሔዋን ሁሉን አዋቂ ለመሆን ቸኩላ ከባልዋ ጋር ፈጠነች:: ድንግል ማርያም ግን ሁሉን አዋቂ ልሁን አላለችም :: "ወንድ ስለማላውቅ እንዴት ይሆንልኛል? ብላ ጠየቀች : ሔዋን አምላክ ለመሆን ተታለለች:: ትሕትና የሞላባት ድንግል ግን "እነሆኝ የጌታ ባሪያው ነኝ" ብላ ተቀበለች::
ይህች ድንግል ገብርኤልን ሰምታ የሕይወትን ዛፍ አበላችን:: ይህች ድንግል ይሁንልኝ በማለትዋ የተጠመቅን ሁላችን ክርስቶስን ለበስን:: በእርስዋ ይሁንልኝ ማለት ኪሩብ ሰይፉን ጣለ : ከጥበቃም ተገላገለ:: እኛም ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ ታደልን::
ብዙ ሰው " ሔዋን ለመውደቃችን ምክንያት ናት " ሲባል ይስማማል:: ድንግል ማርያም ግን ለመዳናችን ምክንያት ሆነች የሚለውን ግን አንዳንዶች ለመቀበል ይቸገራሉ:: ሔዋን ለመውደቃችን ካደረገችው ይልቅ ድንግል ማርያም ለመነሣታችን ያደረገችው ይበልጣል!
የድኅነታችን መጀመሪያ የሆነችውን ይህችን ድንግል ክብርዋን በሕሊናችን እንሳለው:: እሳታዊ መልአክ ቆሞ የዘመረላት ድንግል : አባትዋ ዳዊት ከሩቅ ሆኖ እያያት "ልጄ ሆይ ስሚ እዪም ጆሮሽን እዘንብዪ" እያለ የገብርኤልን ቃል እንድትሰማና ከሲኦል እንድታወጣው የሚማጸናትን ድንግል : ወንድምዋ ሰሎሞን "እኅቴ ሙሽራ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ነውርም የለብሽም" እያለ የቀረበላትን 'የተባረክሽ ነሽ' የሚል ምስጋና እንድትቀበል የሚዘምርላትን : በእጆችዋ ሐርና ወርቅን : በማኅጸንዋ ሰውና አምላክን : በመውለድዋ ሰውና መላእክትን አስማምታ የፈተለችና ያዋሐደችዋን ይህች ድንግል እስቲ ለአፍታ እናስባት:: የባቢሎንን ሰባት እጥፍ የነደደ እሳት ያቀዘቀዘው ገብርኤል በፊትዋ በትሕትና አደግድጎ የቆመላትና ዘካርያስን ዲዳ ትሆናለህ ባለበት አንደበቱ "አንቺ የተባረክሽ ነሽ " እያለ የሚማጸናትን የዐሥራ አምስት ዓመት ብላቴና እስቲ እናስባት! ዓላማ ይዞ እንደተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ ይህች ማናት?
ሽማግሌ አባትዋን ቅጠል ከለበሰበት ዛፍ አውጥታ ልጅዋን ሸማ አድርጋ ያለበሰች : እናትዋን ሔዋንንም የሚጎዳ ማሠሪያዋን ፈትታ ቁስልዋን ያከመች የሔዋን መድኃኒት ይህች ድንግል ማን ናት? የእርስዋን ክብር በኃጢአተኛ ብዕር እንደምን እጽፈዋለሁ?
ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ያለውን ብዬ ብዘጋው ይሻለኛል
"የድንግል ማርያምን ክብር ከመግለጽ ፀሐይን ከነብርሃንዋና ከነሙቀትዋ መሣል ይቀልላል"
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-
ዩቱብ
https://www.youtube.com/@12Samual

ቴሌግራም
https://t.me/tsidq








ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-
ዩቱብ
https://www.youtube.com/@12Samual

ቴሌግራም
https://t.me/tsidq


ለነገሩ ለወላዋዩ ናቡከደነፆር ምን መልስ ይሠጣል፡፡ ታሪኩን ስናነብ እንደ ናቡከደነፆር ተገለባባጭ ሰው የለም፡፡ ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ሁለት ላይ ለፈጣሪ መሰከረ ፣ ምዕራፍ ሦስት ላይ ካደ ፣ ምዕራፍ ሦስት መጨረሻ ላይ አምኖ መሰከረ ፣ ምዕራፍ አራት መጀመሪያ ላይ ለፈጣሪ እንደ መዘመር ቃጣው በሕልሙ መልአክ እስከማየት ደርሶ ስለ ፈጣሪ ኃያልነት መሰከረ ፣ ምዕራፍ አራት መጨረሻ ላይ ግን ‹‹ይህች በጉልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?›› ብሎ ተኮፍሶ እንደ እንስሳ ሣር እስኪግጥ ድረስ ተቀጥቷል፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ‹አምላካችሁ ማን ነው?› ሲላቸው መልስ ልንሠጥህ አያስፈልገንም ፤ አንተው ማን እንደሆነ ሣር ስትግጥ ታየዋለህ አሉት፡፡ እግዚአብሔር ማን ነው ያሉ እነፈርኦን የደረሰባቸው ባይገባህ አንተ ላይ ደርሶ ታየዋለህ ሲሉ ‹እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም› አሉት፡፡

ሦስቱ ወጣቶች አምላካችሁ ማን ነው የሚለውን ባይመልሱም ይህንን ግን አሉ ‹‹ንጉሥ ሆይ አምላካችን ከሚነድደው ከእቶኑ እሳት ያድነን ዘንድ ይችላል ከእጅህም ያድነናል› ንጉሥ ሆይ አምላካችን ኃይሉ ከእሳት በላይ ነው፡፡ ያለ እሳት ማንደድ ያለ ውኃ ማብረድ ይችላል፡፡ ከእሳቱ ያድነናል ፤ ‹ከእሳቱ ቢያድናችሁ ምን ዋጋ አለው ፤ ከእሳት ብታመልጡ ከእኔ አታመልጡም› ብለህ ታስብ እንደሆን ‹‹ከእጅህም ያድነናል›› አሉት፡፡

‹‹ነገር ግን ንጉሥ ሆይ እርሱ ባያድነንም አማልክትህን እንደማናመልክ እወቅ›› አሉት፡፡ ወጣቶቹ ‹ባያድነንም› ያሉት ተጠራጥረው አይደለም፡፡ ለጣዖት ከመስገድ ሞት ይሻለናል ፣ ለጣዖት በመስገድ የምንጎዳው ጉዳት በእሳት ተቃጥለን ከምንጎዳው አይብስም ፣ የዘላለም እሳት ከሚፈጀን የአንተ እሳት ቢፈጀን እንመርጣለን ለማለት ነበር፡፡ በዚያ ላይ ሦስቱ ወጣቶች ‹ያድነን ዘንድ ይችላል› አሉ እንጂ ‹እንድናለን› አላሉም፡፡ የፈጣሪያቸውን የማዳን ኃይል በእርግጠኝነት ተናገሩ እንጂ ከዚህ እሳት እንደሚድኑ በእርግጠኝነት አልተናገሩም፡፡ ይህም ከትሕትናቸው የተነሣ ነበር፡፡ እግዚአብሔር መላእክቱን ስለ እኔ ያዝዝልኛል ያድነኛል ብሎ ወደ ሞት ራስን መሥጠት ጌታችን ለዲያቢሎስ እንዳለው ጌታ አምላክን መፈታተን ነው፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ‹ባያድነን እንኳን› ሲሉ ምግባራችን ከልክሎት ባያድነን እንኳን ያልዳነው በኃጢአታችን ነው እንጂ አምላካችን ማዳን ተስኖት እንዳይመስልህ አሉት፡፡

እነዚህ ወጣቶች ምንኛ ያስደንቃሉ ፤ ስለ ትንሣኤ ሙታን ባልተሰበከበት በዚያ ዘመን ፣ ምንም እንኳን ሥቃይ የማይነካቸው ቢሆንም እንኳን ጻድቃንም ቢሆኑ ወደ ሲኦል በሚወርዱበት በዚያ ዘመን ተስፋ ሳይኖር ተስፋ አድርገው እንደ ሐዲስ ኪዳን ሰው ወደ ሞት የሔዱት እነዚህ ወጣቶች ምንኛ ክቡራን ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ሰማዕቱ ዮስጦስ (Justine the martyr) ‹‹ከክርስቶስ በፊት የነበሩ ክርስቲያኖች›› (Christians before Christ) የሚላቸው፡፡

★ መርጦ የሚያነድ እሳት

ናቡከደነፆር በወጣቶቹ መልስ እጅግ ተበሳጨ ፤ የሚነድደውን እሳት ሰባት እጥፍ እንዲያደርጉት አዘዘ፡፡ ልፋ ሲለው ነው እንጂ እሳቱ ሰባት እጅም ቢሆን ፣ አንድ እጅም ቢሆን ለሦስቱ ወጣቶች መቃጠል ያው መቃጠል ነው፡፡ የባቢሎንን ማገዶ ከማባከን በቀር ሦስቱ ወጣቶች የሚሞቱት ሞትም ያው አንድ ሞት ነው፡፡ የተፈለገው ግን እንዲፈሩ ነበር፡፡ ሰይጣን አሠራሩ እንዲህ ነው ፤ እምነታችን ሲጨምር እሳቱ ሰባት እጥፍ ይጨምራል፡፡ ‹ያድነናል› የሚለው ምስክርነታችን ናቡከደነፆሮችን ያስቆጣል፡፡ በሥልጣናቸው የሚነድደውን እሳት መጨመር እንጂ የእኛን እምነት መቀነስ አይችሉም፡፡ ሦስቱን ወጣቶች ከሰናፊላቸው ፣ ከቀሚሳቸውና ከመጎናጸፊያቸው ከቀረው ልብሳቸውም ጋር እንዲታሠሩ ተደረገ፡፡ ያ ሁሉ ልብስ አብሮአቸው እንዲታሰር የተፈለገው ሥቃያቸውን የበለጠ ለማብዛት ፣ እግራቸው መታሰሩም ሳይንፈራገጡ እንዲቃጠሉ ለማድረግ ነበር፡፡ በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ ሦስቱን ወጣቶች ወደ እሳት ጨመሯቸው፡፡ ከእሳቱ ኃይል የተነሣ ‹የጣሏቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን ገደላቸው›

ሦስቱን ወጣቶች እሳት ውስጥ ሲገቡ ከእስራቸው ተፈትተው ሲመላለሱ ታዩ ፤ ናቡከደነፆር ባላዋቂ አነጋገር ‹የአማልክት ልጅ› ያለውን ‹የእግዚአብሔር ልጆች› ተብለው ከሚጠሩት መላእክት አንዱ የሆነውን መልአኩን ልኮ የእሳቱን ኃይል አጠፋ፡፡ ‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ዙሪያ ይሠፍራል ያድናቸውማል› የተባለውም ተፈጸመ፡፡ ‹የአማልክት ልጅ› የተባለው የመልአኩ መውረድ የወልደ እግዚአብሔር የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ፣ የመምጣቱና የሰውን ልጅ ከሲኦል እሳት የማዳኑ ሥራ ምሳሌ ሆኖ ይኖራል፡፡

ሦስቱ ወጣቶች ልብስ አልብሰው የጨመሯቸው እንዲሰቃዩ ነበር ፤ ሆኖም ለሥቃይ የለበሱት ልብስ ለዝማሬ ሆናቸው፡፡ መቼም ዕርቃን ሆኖ ዝማሬ የለም፡፡ አልብሰው ባይከቷቸው ኖሮ ሲወጡ ዕርቃናቸውን በወጡ ነበር፡፡ የሚያስደንቀው እነዚህ ሦስት ዕፀ ጳጦሶች እንኳን ሊቃጠሉ ጭስ ጭስ እንኳን አይሉም ነበር፡፡
የባቢሎን እሳት አስደናቂ እሳት ነው፡፡ ከእሳቱ ውስጥ እያሉ እሳቱ ያቃጠለው የታሰሩበትን ገመድ ብቻ ነበር፡፡ ከዚያ ውጪ የጣሏቸውን ሰዎች ወላፈኑ ገደላቸው፡፡ ሰዎችን ወደ እሳት መገፍተር ቀላል ነው፤ እሳቱ ግን ገፍታሪዎቹን ሊያቃጥል ይችላል፡፡ ‹‹እሳት በላዒ ለአማፅያን ለእለ ይክህዱ ስሞ ፤ ወእሳት ማኅየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ›› (ስሙን ለሚክዱ ለአመጸኞች የሚባላ እሳት ነው ፤ፈቃዱን ለሚሠሩ ልባቸው ለቀና የሚያድን እሳት ነው) የሚለው የአባ ሕርያቆስ ቅዳሴ በብሉይ ኪዳን ቢሆን ለባቢሎን እሳት ይሠራ ነበር፡፡

ሦስቱ ወጣቶች እሳት ውስጥ ገብተው የመውጣታቸው ታሪክ በጥላቻና በዘረኝነት እሳት እየነደድን ባለንበት በዚህ ዘመን ሆነን ስንመለከተው መልእክቱ ብዙ ነው፡፡ በሚነድደው እሳት ላይ የእያንዳንዳችን ድርሻ ምንድር ነው? አንዳንድ ሰው ‹ይለይለት ካልደፈረሰ አይጠራም› ይላል፡፡ በስድብ በጥላቻ በነቀፋ ከሩቅም ከቅርብም ሆኖ የሚያባብስ ሰው እንግዲህ እሳቱን ሰባት እጥፍ ከሚጨምሩት የናቡከደነፆር አሽከሮች አይለይም፡፡ በዚያ ላይ ይለይለት ብለህ የምትጨምረው እሳት ወላፈኑ አንተኑ ማቃጠሉ አይቀርም፡፡ ያለነውም የምንኖረውም እሳቱ ውስጥ ሆነው ‹‹የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል›› ብለው በሚጸልዩ ሰዎች ነው፡፡ ጸሎት መፍትሔ ነው ሲባል በሚያስቀን በናቡከደነፆሮች ሳይሆን ዳዊቱን በማያስታጉሉ አናንያ አዛርያና ሚሳኤሎች ነው፡፡

እሳት ውስጥ ገብተው የወጡት እነዚህ አርበኞች ከጸሎቱ ባሻገር አንድ ልብ ነበሩ፡፡ በሙሉ ትንቢተ ዳንኤል ላይ ‹አናንያ እንዲህ አለ ፤ አዛርያም እንዲህ አለ› የሚል አልተጻፈም፡፡ ሦስት ሲሆኑ እንደ አንድ ሰው ሲናገሩ ሲሰሙ ፣ አብረው ሲጾሙ ፣ አብረው ሲሾሙ ፣ አብረው ሲታሰሩ ፣ አብረው ከእሳት ሲገቡ አብረው ሲወጡ ፣ አብረው ሲዘምሩ ነው ያየናቸው፡፡ አንድ ልብ ሳይሆኑ ከእሳት መውጣት አይቻልም፡፡ አናንያና አዛርያ ተፋቅረው ሚሳኤልን ቢጠሉት ኖሮ በሃሳብ ባይስማሙ ኖሮ ተቃጥለው ይቀሩ ነበር፡፡ ‹‹መልአኩን የላከ በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ የአናንያ የአዛርያ የሚሳኤል አምላክ ይባረክ›› (ዳን. 3፡28)

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 19/2011 ዓ.ም.
ኦስሎ ኖርዌይ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!


+ መርጦ የሚያቃጥል እሳት +

★ የቆሎ ተማሪዎች

ንጉሥ ናቡከደነፆር እስራኤልን ድል ነሥቶ በግዞት ወደ ባቢሎን በወሰዳቸው ጊዜ ሕዝቡን ለአመጽ እንዳያነሣሡበት ከነገሥታትና መሳፍንት ወገን የሆኑትን ፣ መልከ መልካሞቹን ፣ ወጣቶቹንና ብሩሕ አእምሮ ያላቸውን መርጦ ከሕዝቡ ለይቶ በቤተ መንግሥቱ ሰበሰበ፡፡ ዓላማው ወጣቶቹ የሀገሩን ቋንቋ ከተማሩና በቤተ መንግሥት በምቾት ከኖሩ የወገኖቻቸው መከራ እንደማይሰማቸው በማሰብ ነበር፡፡ ከሰው ልጅ የሚበዛው እርሱ እስከተመቸውና ጥቅሙ እስካልተነካበት ድረስ የሌላው ወገኑ ጩኸት ስለማይሰማው ናቡከደነፆር እስራኤልን ለማፈን የተጠቀመው አደገኛ ስልት ነበረ፡፡ ይህ ስልት ግን በሦስቱ ወጣቶች በአናንያ በአዛርያና ሚሳኤል ላይ አልሠራም፡፡ ገና ከጅምሩ በቤተ መንግሥት የቀረበላቸውን ‹ጮማና ጠጅ አንበላም ጥሬ ይሠጠን› ብለው በድብቅ ‹የቆሎ ተማሪዎች› ሆኑ፡፡

መቼም የቤተ መንግሥትን እንጀራ አንዴ አትልመደው እንጂ የለመድከው እንደሆነ ንጉሡ ምንም አድርግ ቢልህ ታደርጋለህ፡፡ የቤተ መንግሥት ምግብ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ‹‹ኦርዮም ከንጉሡ ቤት ሲወጣ ማለፊያ እንጀራ ተከትሎት ሄደ›› ተብሎ እንደተጻፈ እንኳን የናቡከደነፆር ቤተ መንግሥት ምግብ ይቅርና የንጉሥ ዳዊት ቤተ መንግሥት ምግብም እንደ ኦርዮ ሞትን ሊያስከትልም ይችላል፡፡ ከቤተ መንግሥት የሚሠጥህን ምግብ አገኘሁ ብለህ ደስ ቢልህም ያ ምግብ የመጨረሻ ራትህ ሊሆን ይችላል ወይም ደግሞ ነገ ክፉ ነገር አድርግ ቢሉህ እምቢ ለማለት ትቸገራለህ፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ጥሬ ቆርጥመው ሊማሩ ወሰኑ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ሦስቱን ወጣቶች ከንጉሡ ጋር የሚያጋፍጥ ነገር የመጣው፡፡

ከዚህ በኋላ ናቡከደነፆር ሕልም አለመ ፤ ሆኖም ሕልሙ ጠፋበት፡፡ አስማተኞቹን ሰብስቦ ‹ሕልሜን ከነፍቺው ንገሩኝ› ብሎ አፋጠጣቸው፡፡ ግራ ገባቸው ፤ ሕልሙን ተናግሮ ቢሆን ‹ሲሳይ ነው ፣ ዕድሜ ነው ፣ ጸጋ ነው› ብሎ ማለፍ ይቻል ነበር፡፡ አሁን ግን ‹ሕልሜን ውለዱ› አለ፡፡ አልነግር ሲሉት ሊገድላቸው ወሰነ፡፡ በዚህ መካከል ሦስቱ ወጣቶች ከአጎታቸው ዳንኤል ጋር ሆነው መፍትሔ አመጡ፡፡ እነርሱ በጸሎት ሲተጉ እግዚአብሔር ሕልሙን ከነትርጓሜው ለዳንኤል ገለጠለት፡፡
ንጉሡ በዘነጋው ሕልሙ ያየው ‹ራሱ የወርቅ ፣ የቀረው አካሉ የብር ፣ የናስ ፣ የብረትና ሸክላ የሆነ ትልቅ ምስል ነበር› ዳንኤል ሕልሙን ለንጉሡ ከነገረው በኋላ እንዲህ ብሎ ፈታለት፡፡ ‹ንጉሥ ሆይ ባየኸው ሕልም ላይ በሥልጣን ከሁሉ በላይ አድርጎሃልና የወርቁ ራስ አንተ ነህ ፤ ከዚያ በታች ያየኻቸው ደግሞ ከአንተ በኃይል የሚያንሡ ከአንተ በኋላ የሚነሡ ነገሥታት ናቸው›› ብሎ እርሱና ከእርሱ በኋላ የሚነሡ ነገሥታት እንዴት መንግሥታቸው እንደሚያልፍ ሕልሙን ከነዝርዝር ፍቺው ነገረው፡፡ በዚህም ንጉሡ ደስ አለውና ዳንኤልን ከፍ ከፍ አደረገው ፤ ሦስቱን ወጣቶችም በአውራጃ ሥራ ላይ አዛዦች አድርጎ ሾማቸው፡፡

★ እንደ ንጉሡ አጎንብሱ

ናቡከደነፆር ዳንኤል ከፈታለት ረዥም ሕልም ውስጥ ግን ከአእምሮው ያልጠፋችው ‹ወርቁ አንተ ነህ› የምትለው ዓረፍተ ነገር ነበረች፡፡ መቼም እኛ ወርቅ የሆንንበት ቅኔ ከልባችን አይጠፋም፡፡ ስለዚህ ራስ ወዳዱ ናቡከደነፆር ከረዥሙ ሕልም ውስጥ ‹ወርቁ አንተ ነህ› የምትለዋ ብቻ ልቡን ነካችው፡፡ ባልንጀራህን ‹እንደ ራስህ ውደድ› ስለሚል ራስን መውደድ ጥፋት አይደለም፡፡ ራስን መውደድ በጣም ከፍ እያለ ሲመጣ ግን ‹ፀሐይ የምትወጣው እኔን ለማየት ነው› እስከማለት ያስደርሳል፡፡

ናቡከደነፆር በራሱ ፍቅር ወደቀ ፣ ራሱን አቅፎ ለመሳም ቃጣው ፤ በመጨረሻም ‹እኔ ወርቅ ነኝ› የምትለው አሳቡ አድጋ በዱራ ሜዳ ላይ ትልቅ የወርቅ ሐውልት ሆነች፡፡ ‹ለዚህ ጣዖት የማይሰግድ ሰው ወደ እሳት ይጣላል› የሚል አዋጅ አወጀ፡፡ የመለከትና የእንቢልታ የመሰንቆና የክራር የበገናንና የዋሽንት የዘፈን ድምፅ በሀገሩ ተሰማ፡፡ ሕዝቡ ወደ ዕቶን እሳት ትጣላለህ ከሚል ማስፈራሪያ ጋር ስሜቱን የሚነካ ሙዚቃም ሲሰማ ያለማመንታት ታዘዘ፡፡ በዚህ አዋጅ ምክንያት በድፍን ባቢሎን የሚኖሩ እስራኤላዊያንም ጭምር ሁሉም ለወርቁ ምስል ሰገዱ፡፡

የአውራጃ ሹመኞች የሆኑት የቤተ መንግሥት ጾመኞች ሦስቱ ወጣቶች ግን አልሰገዱም፡፡ ሁሉም ሲሰግድ አለመስገድ ፣ ሁሉም ሲያጨበጭብ እጅን መሰብሰብ ፣ ሁሉ ሲስቅ መኮሳተር ጽናት የሚጠይቅ ነው፡፡ ‹ከሀገሩ የወጣ ሰው እስኪመለስ ድረስ ፤ ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ› ብለው መተረት አልፈለጉም፡፡ ሀገሩ ሁሉ ከሰገደ በእነዚህ ወጣቶች ለይቶ የሚፈርድባቸው ሰው አልነበረም፡፡ ከእስራኤል ወገን ብዙ ሽማግሌዎች ብዙ መጽሐፍ አዋቂዎች አገጎንብሰው ቢሰግዱም እነዚህ ወጣቶች አልሰገዱም፡፡ ‹‹ከእኛ ብዙ የሚያውቁት እነ እገሌ እነእገሌ ከሰገዱ እኛ ለምን እንጠቆራለን? ከሰው ተለይተን ምን እንፈጥራለን? የአውራጃ ገዢ አድርጎ ሾሞን የለ አሁን እንቢ ብንል ውለታ ቢስ መሆን አይሆንብንም? ስገዱ ያለው ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው እንጂ ጣዖት አምልኩ አላለንም ፤ እሳት ውስጥ ከምንገባ ይህችን ቀን አጎንብሰን ብናልፋትስ ፣ ዋናው ልብ ነው›› ብለው ራሳቸውን ሊያሞኙ አልፈለጉም፡፡ ሁሉ ባጎነበሰበት ቀን አንሰግድም ብለው ቆሙ፡፡

★ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው?

ናቡከደነፆር ሦስቱ ወጣቶች እንዳልሰገዱ ሲነገረው ቁጣው ነደደና አስጠራቸው፡፡ ‹‹የምሰማው እውነት ነውን?›› አለ ፤ እንዲያስተባብሉ ዕድል ሲሠጥ፡፡ ‹አሁንም የመለከትና የእንቢልታ የመሰንቆና የክራር የበገናንና የዋሽንት የዘፈን ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ብትሰግዱ መልካም ነው›› አለ፡፡ መቼም በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ናቡከደነፆር የሙዚቃን ስሜት ቀስቃሽነት የተረዳ ሰው ያለ አይመስልም፡፡ ‹‹በሉ ሙዚቃው ድጋሚ ይከፈትልሃል ትጨፍራላችሁ›› የሚል ይመስላል፡፡ ስገዱ ከማለቱ ሙዚቃውን ስትሰሙ ማለቱ ይገርማል፡፡ ከዚያ ማስፈራሪያ ጨመረበት ‹‹ተደፍታችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው።

ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ለሚለው ለንጉሡ ጥያቄ ሦስቱ ወጣቶች ‹‹ናቡከደነፆር ሆይ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም›› አሉት፡፡ ምን ማለታቸው ነው? ለምን አይመልሱለትም? ይህንን ያሉበት ምክንያት ናቡከደነፆር ከጥቂት ጊዜ በፊት ሕልም አልሞ በተፈታለት ጊዜ ደስ ብሎት ‹‹አምላካችሁ የአማልክት አምላክ የነገሥታትም ጌታ ምሥጢርም ገላጭ ነው›› ብሎ መስክሮ ስለነበር ነው፡፡ (ዳን 2፡47) አሁን ደግሞ ተገልብጦ ‹ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው?› አላቸው፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ትናንት ያመሰገነውን አምላክ እንደማያውቀው ሲሆን ላንተ መልስ አያስፈልግህም አሉት፡፡ አንዳንድ ሰዎች ትናንት ያመለኩትን አምላክ ዛሬ እንደማያውቁ ሆነው ሲጠይቁ ፣ ትናንት ያመኑበትን ዛሬ ክደው ሲያናንቁ ‹‹በዚህ ነገር እንመልስላቸው ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም››




+ አልቆም ያለ ደም+

"በኋላውም ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፥ የደምዋም ፈሳሽ በዚያን ጊዜ ቆመ" ሉቃ. 8:44

ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥ ትዳርዋንም ሁሉ ለባለመድኃኒቶች ከስራ ማንም ሊፈውሳት አልተቻለውም።

ደምዋ ፈስሶ አያልቅም ወይ? ዓሥራ ሁለት ዓመት ሙሉ? እንዴት ያለ ሕመም ነው?! ሰው በክፉ ሽታዋ እስኪርቃት ድረስ የማይቆም ደም::

ባለ መድኃኒቶች ሊያቆሙት ያልቻሉትን የደም ጎርፍ የናዝሬቱ ባለ መድኃኒት በቀሚሱ ብቻ አቆመው:: በልብሱ ጫፍ ብቻ::

ሳያያት ሳይነካት እጁን ሳይጭንባት በልብሱ ጫፍ ብቻ የደምዋን ዝናብ እንዲያባራ አደረገው:: የሕመምዋን ማዕበል ገሠጸው::

በልብሱ ጫፍ ብቻ የሚፈውስ ሐኪም እንዴት ያለ ነው? ቀጠሮ ሳይሠጥህ ሳያናግርህ ቀና ብሎ ሳያይህ ስትነካው ብቻ የምትድንበት ከሆነ እርሱ መድኃኒት የሚያዝ ሐኪም ሳይሆን ራሱ መድኃኒት ነው:: የልብሱን ጫፍ የነካ ከዳነ ሥጋውን የበሉ ደሙን የጠጡማ ምንኛ ይድኑ ይሆን?

ሊፈውሳት አስቦ አልነበረም የዐሥራ ሁለት ዓመት ሴት ልጅ ከሞት ሊያስነሣ መንገድ ሲሔድ ግን እግረ መንገዱን የዓሥራ ሁለት ዓመት የቁም ሙትዋን ፈወሳት::

መድኃኔዓለም እንዲህ ነው:: ወደ በሽተኛው ሳይሔድ በቃሉ ብቻ ተናግሮ ይፈውሳል ፤ በሽተኛው ቤት ገብቶ በአልጋው ላይ ይፈውሳል:: ሊፈውስ ሲሔድም ይፈውሳል:: እናም የሴቲቱ አልቆም ያለ ደም በልብሱ ጫፍ ብቻ ቀጥ አለ::

ጌታዬ ሆይ የእኔንስ ደም የምታቆመው መቼ ነው?

ምን ደም ፈስሶህ ያውቃል ካልከኝ ኃጢአት የሚባል ደም ሲፈሰኝ አይታይህም? አንተስ በቃልህ "ኃጢአታችሁ እንደ ደም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች" ብለህ የለ? እንደ ደም የቀላው የእኔ ኃጢአት ነው:: ይኸው ሲፈስ ከሴቲቱ በላይ ቆየ::

ላቆመው ብል አልቆም አለኝ:: ያላሰርኩበት ጨርቅ ፣ ያልሞከርኩት ቅባት ፣ ያልሔድኩበት ባለ መድኃኒት የለም:: ገንዘቤን ከሰርኩ እንጂ ኃጢአቴ ግን መቆም አልቻለም:: እንዲያውም መጠኑ እየጨመረ ነው:: ባሕር ሆኖ ሊያስጥመኝ የደረሰ የኃጢአት ደም ከብቦኛል::

ለእኔ የሚሆን የቀሚስ ጫፍ ታጣ ይሆን? እኔ እንደ ሴቲቱ ታላቅ እምነት የለኝም ቀሚስህ ግን አሁንም ኃይል አለው:: ልትፈውሰኝ ና አልልህም ስታልፍ ግን ልዳስስህና ልዳን:: ጉዞህን ሳላሰናክል ሰው ሳይሰማ በልብስህ ጫፍ ብቻ ደሜን አቁምልኝ:: የእኔን ደሜን መግታት ላንተ ምንህ ነው? ደምህንስ አፍስሰህልኝ የለ?

እባክህን ደሜ ሳይቆም ሌላ ዓመት አልሻገር::
እኔ ኃጢአቴን "ያለፈው ዘመን ይበቃል" ማለት ቢያቅተኝም አንተ ግን ይበቃሃል በልልኝ::
በእምነት ማጣት የታጠፈውን እጄን ወደ ልብስህ ጫፍ ዘርጋልኝ:: እኔ ማቆም ያልቻልኩትን የበደል ደም ጸጥ አድርገህ "አንድ ሰው ዳስሶኛል ኃይል ከእኔ ወጥቶአል" በል:: እነጴጥሮስም ይደነቁ እኔም በሰላም ልሒድ::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጳጉሜን 2015 ዓ.ም.

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)

ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-
ዩቱብ
https://www.youtube.com/@12Samual

ቴሌግራም
https://t.me/tsidq






Видео недоступно для предпросмотра
Смотреть в Telegram


+ የሐሰት መገለጦች ፣ ራእዮችና ሕልሞች +

በተሳሳተ አስተሳሰብህ እንድትቀጥል ለማድረግ አንዳንድ ጊዜ ዲያቢሎስ ነገሮችን ከመሆናቸው በፊት እንድታውቃቸው ሊያደርግህ ይችላል፡፡ ወይም የሌሎች ሰዎችን ሐሳብ እንድታውቅ ሊያደርግህ ይችላል፡፡

ዲያቢሎስ እንዴት ይህን ማድረግ ይችላል? በጣም ቀላል ነው! ለምሳሌ ሀገር ቤት ያሉ አያትህ በጠና እንደታመሙ ያውቃል ፤ ስለዚህ ይህንን ሐሳብ በአንተ ኅሊና እንዲታሰብ ያደርጋል፡፡አንተም ደንገግጠህ ስልክ ትደውላለህ ፤ በዚህ ጊዜ አያትህ በጣም እንደታመሙ ይነገርሃል፡፡ ይህንን ስታምን ሌሎች ነገሮችንም እየነገረህ እግዚአብሔር የገለጠልኝ ነው ብለህ እንድታስብ ያሳምንሃል፡፡

በትእቢትና ራስን እንደ ጻድቅ በማየት ኃጢአትም
እንድትሞላ ያደርግሃል፡፡ ዮሐንስ ዘሰዋስው ደግሞ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡ ዲያቢሎስ ሐሳቦችን በአንድ ሰው ኅሊና ላይ ከተከለ በኋላ ይህንኑ ሐሳብ ለሌላ ሰው በመንገር ራሱን የሰውን አእምሮ የሚያነብ እንደሆነ እንዲሰማው ያደርገዋል፡፡ ጠንቋዮች የሚያውቁትን ነገር ከየት የሚያገኙት ይመስላኋል? ከዲያቢሎስ እኮ ነው! በእርግጥም አብዛኞቹ ጠንቋዮች በትክክል በአጋንንት የተያዙ ናቸው፡፡

ሦስት መነኮሳት አንድ ነገር ተገልጦላቸው የተገለጠው ነገር ከእግዚአብሔር ነው ወይንስ ከዲያቢሎስ እያሉ ይከራከሩ ነበር፡፡ በመጨረሻም ወደ ቅዱስ እንጦንስ ሔደው ሊጠይቁት ወሰኑ፡፡ ወደ ቅዱስ እንጦንስ ሲሔዱ በመንገድ ላይ ይዘውት ሲሔዱ የነበረ አህያ ሞተባቸው፡፡

መንገዳቸውን ቀጥለው ወደ ቅዱስ እንጦንስ ሲደርሱ
‹‹አህያችሁ መሞቱ በጣም ያሳዝናል!›› አላቸው፡፡
እነርሱም ‹‹ስለ አህያው እንዴት ልታውቅ ቻልህ?›› ሲሉ ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹‹ሰይጣን ነገረኝ!›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ሳንጠይቅህ ጥያቄያችንን መለስህልን!›› አሉት፡፡

አንዳንድ ሰዎች መላክትንና ቅዱሳንን በራእይ ያያሉ፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉትን ራእዮች ከመቀበል በፊት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ፤ ምክንያቱም ዲያቢሎስ መንፈሳዊ ሕይወታችንን ለማፈራረስ ሲል ሊያስመስል ይችላል፡፡ የበረሃ አባቶች ታሪክ ራእይና ሕልምን ከእግዚአብሔር መሆኑንና ከሰይጣን መሆኑን ሳይለዩ ስለተቀበሉ ሰዎች በሚናገሩ አስፈሪ ታሪኮች የተሞላ ነው፡፡

ከእነዚህ ታሪኮች አንዱ የሄሮን ታሪክ ነው፡፡ ይህ መነኩሴ ለሃምሳ ዓመታት በብሕትውና የኖረ ሲሆን ለረዥም ጊዜ ይገለጥለት በነበረ የሐሰት መልአክ እየወደቀ የመጣ ነው፡፡ መልአክ ስለተገለጠለት ወደ ቤተ ክርስቲያን መሔድ አቆመ ፣ ለአበምኔቱ እንዲነግራቸው ሌሎች መነኮሳት የመከሩትንም ምክር አልተቀበለም፡፡
በመጨረሻም ‹‹መልአኩ›› ለዚህ አባት በሕይወቱ እያለ እንደ ኤልያስ ወደ ሰማይ እንደሚወሰድ ነገረው፡፡ ይህ ምስኪን መነኩሴም ወንድሞቹ መነኮሳትን ሊሰናበት ሔደ፡፡ ነገሩ ከዲያቢሎስ ቢሉትም አልሰማቸውም፡፡ መልአክ ነኝ ባዩም ይህንን አባት ወደ ተራራ ይዞት ወጣ፡፡ እንዲዘልልም ነገረው ፤ ይህ አባትም በተባለው አምኖ ሲዘልል ወድቆ ተከስክሶ ሞተ፡፡ አበምኔቱ ይህ መነኩሴ ራሱን እንዳጠፋ በመቁጠር ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግለት እንኳን አልፈቀደም፡፡

ሌላ መልአክ ነኝ ባይ ደግሞ ለሌላ መነኩሴ ለሦስት ዓመታት ተገለጠለት፡፡ በዚህ መልአክ ብርሃን ይህ አባት የሚኖርባት በአቱ ታበራ ነበርና ሻማዎችን ማብራት አያስፈልገውም ነበር፡፡ ከሦስት ዓመታት በኋላ ይህ በራእይ በ‹‹ገነት›› አይሁዳውያን በአብርሃም እቅፍ ሆነው ክርስቲያኖች ደግሞ በሲኦል ሲሰቃዩ አስመስሎ አሳየው፡፡ ይህ መነኩሴ ክርስትናን ትቶ አይሁዳዊ ሆነ፡፡

በሰይጣን የማይታለሉ ጥበበኛ የሆኑ መነኮሳትም ነበሩ፡፡

ለአንዱ መነኩሴ ‹‹ገብርኤል›› ነኝ ባይ ጋኔን ከእግዚአብሔር ተልኬ መጣሁ አለው፡፡ መነኩሴውም ‹‹የመጣኸው ወደ ትክክለኛው በአት አይደለም ፤ እኔ ገና ራእይ ለማየት የማይገባኝ ኃጢአተኛ ነኝ! ከዚህ ቀጥሎ ያለው መነኩሴ ግን ጻድቅ ሰው ነው›› ሲል መለሰለት፡፡ ገብርኤል ነኝ ባዩም እንደ ጢስ ተነነ!

ለሌላ አባት ደግሞ ዲያቢሎስ ‹ክርስቶስ ነኝ› ብሎ ተገለጠለትና የአምልኮት ስግደት እንዲያቀርብለት ነገረው፡፡ ይህ አባት ግን ‹‹እኔ ክርስቶስን በሰማይ እንጂ በምድር ላይ ለማየት አልፈልግም!›› አለው፡፡ ይህም ክርስቶስ ነኝ ባይ እንደ ጢስ ተንኖ ጠፋ፡፡

እነዚህ ነገሮች ከዘመናት በፊት በመነኮሳት ላይ የተፈጸሙ ናቸው፡፡ ነገር ግን ዲያቢሎስ ዛሬም ይህንኑ ስልት እየተጠቀመ እና እየተሳካለት ነው፡፡

ከዓመታት በፊት ነው ፤ አንድ አገልጋይ ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣት እንዳቆመና ለረዥም ጊዜም ሥጋ ወደሙ መቀበል እንደተወ ተረዳሁ፡፡ መጠየቅ እንደሚገባኝ በማመን ወደ እርሱ ሔጄ ምክንያቱን ልጠይቀው ሞከርሁ፡፡ ቀለል አድርጎ መለሰልኝ ፡- ‹‹እሑድ እሑድ አቡነ ቄርሎስ ይገለጡልኛል ፤ ሥጋ ወደሙም ያቀብሉኛል!›› ከሌላ ቦታ የመጣ አንድ አገልጋይ ደግሞ ወደ እኔ መጥቶ ኅሊናውን የሚረብሸው ነገር እንዳለ ነገረኝ፡፡ እኔም የንስሐ አባቱ ባለመሆኔ የንስሐ አባቱን እንዲያናግርና እንዲናዘዝ መከርሁት፡፡ በማግሥቱ ጠዋት መጥቶ ጠራኝና በሕልሙ ‹‹አቡነ ቄርሎስ››

መጥተው ተናዘዝ እንዳሉትና ጸሎተ ንስሐ እንዳደረጉለት ነገረኝ፡፡ ከዚያም ይህ ይበቃው እንደሆነ ጠየቀኝ ፤ እኔ ግን አሁንም ወደ ንስሐ አባቱ ሔዶ እንዲናዘዝና ስላየው ሕልምም እንዲነግራቸው ነገርሁት፡፡

ትክክለኛ ገንዘብ አለ ፤ የሐሰት ገንዘብ ደግሞ አለ፡፡ እንዲሁም እውነተኛ መገለጥ አለ ፣ የሐሰትም መገለጥ አለ፡፡ ሕልሞችን ፣ ራእዮችና መገለጦችን ለማስተናገድ ትክክለኛው መንገድ የንስሐ አባትን ማማከር ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው ሁልጊዜም ራሱን ሕልም ራእይ ለማየት የማይገባው አድርጎ ማየት ይገባዋል፡፡ በተለይ ሕልሞች በዲያቢሎስ ሙሉ ቁጥጥር ሥር ናቸው ማለት ይቀላል፡፡ እግዚአብሔር ለአንዳንድ ሰዎች ጋር በሕልም ተናግሯል፡፡ ሆኖም እነዚህ በጣት የሚቆጠሩ ሲሆኑ እነርሱም ነቢያትና ቅዱሳን ነበሩ እንጂ እንደ እኛ ኃጢአተኞች አልነበሩም፡፡ ለሕልሞችም ይህን ያህል ክብደት መስጠት የለብንም፡፡

አንድ ጊዜ ቅዱስ እንጦንስ እንዲህ ብሏል፡-
‹‹በሕልሞች የሚያምን የዲያቢሎስ መጫወቻ ነው››

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሚያዝያ 26 2012 ዓ ም
(ተግባራዊ ክርስትና ከተሰኘው መጽሐፍ የተወሰደ
አቡነ አትናስዮስ እስክንድር እንደጻፉት
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ እንደተረጎመው

ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-
ዩቱብ
https://www.youtube.com/@12Samual

ቴሌግራም
https://t.me/tsidq


++ በሰንበት መፍረስ ++

የኢያሪኮ ሰዎች የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ኃይል በመናቃቸው ምንኛ ተጎዱ?! እርሱ ዓለምን የፈጠረ መሆኑን ስላላመኑ እንዳልተፈጠሩ የሆኑት የኢያሪኮ ሰዎች መጨረሻ እጅግ አሳዛኝ ነበር፡፡

ቅጥራቸው ከመፍረሱ በፊት እስራኤል የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው ለስድስት ቀናት ያህል በዝምታ ኢያሪኮን ዞሯት፡፡ ዓለምን በስድስት ቀናት የፈጠረውን ጌታ እንዲያስተውሉ ስድስት የዝምታ ቀናት ተሠጧቸው፡፡ በሰባተኛው ቀን ግን ጮኹ የኢያሪኮም ቅጥር ፈረሰ፡፡

ሰባተኛ ቀን የዕረፍት ቀን ነው፡፡ ለኢያሪኮ ግን የመፍረስ ቀን ሆነባት፡፡ ሰባተኛ ቀን ፈጣሪን ለሚያምኑ የተቀደሰ ቀን ነበር ፤ ለኢያሪኮ የመረገም ቀን ሆነባት፡፡
እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም እንደሆነ ባየበት ሰባተኛ ቀን ኢያሪኮ ግን ከፉ እንደሆነች ታየባት፡፡

እግዚአብሔር የሌለበት ሕይወት እንዲህ ነው፡፡ ወዳጄ እግዚአብሔር በሕይወትህ ውስጥ ከሌለ የሰንበት ቀን የነፍስህ ዕረፍት ቀን መሆኑ ይቀርና እንደ ኢያሪኮ የመፍረስ ቀን ይሆናል፡፡ በዚያ ቅዱስ ቀን ቅጥርህን በመጠጥ ፣ ብስካር ብዝሙት ስታፈርስ ትውልና ታድራለህ፡፡ ራስህን አንድደህ ትሞቃለህ ፤ እያራገብህ ትቃጠላለህ፡፡ ታቦት ይዘው ቢዞሩህም የኃጢአት ግንብን አጥረሃልና አትሰማም፡፡ በላይህ ላይ ቢቀደስብህም እንደ ኢያሪኮ ሰዎች ካህናቱን እያየህ ‘ዝም ብሎ መዞር ምንድር ነው?’ እያልክ ትስቃለህ፡፡ የካህናቱ የቅዳሴ ዜማ ለአንተ የሚያፈርስ ጩኸት ይሆንብሃል፡፡ የኢያሪኮ ሰው ከመሆን ፣ በሰንበት ፈራሽ ከመሆን ያድንህ!

ቅዳሴያችን መካከል ካህኑ ዕጣን እያጠኑ ዞረው ሲመለሱ የዚህች አጭር ጽሑፍ መነሻ ሃሳብ የሆነውን ይህንን ጸሎት ይጸልያሉ፦ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ አስቀድመህ በባሪያህ በነዌ ልጅ በኢያሱ እጅ የኢያሪኮን ግንብ እንዳፈረስከው የእኔንና የሕዝብህን የኃጢአታችንን ግንብ አፍርሰው፡፡

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥቅምት 9 /2012 ዓ.ም.
ቪክቶሪያ
ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-
ዩቱብ
https://www.youtube.com/@12Samual

ቴሌግራም
https://t.me/tsidq

Показано 20 последних публикаций.