በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
የዐቢይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት(ኒቆዲሞስ)
በዲያቆን ያሬድ መለሰዮሐ፫፥፩
"ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል ሠው ነበር።የኒቆዲሞስን ነገር ያነሳው ለምንድን ነው ቢሉ፦ በእምነት ጸንቶ እስከ መጨረሻው የሚከተለው ነውና፡፡ ሉቃ ፳፬፥፲፫ ፣ ዮሐ፲፱፥፴፱
አንድም ፦ በእርሱ አምኖ በኋላ የሚመሰክር ነውና፡፡ ዮሐ፯፥፶
አንድም፦ ያልተማሩ መጽሐፍት የማያውቁ ብቻ ሳይሆን ከተማሩ ከአዋቂዎች ከአለቆችና ከመምህራንም ወገን በእርሱ ያመኑ እንዳሉ ለመግለጥ
አንድ ሠው ነበር ያለው ታሪክ አያይዞ ነው ቢሉ፦ ብዙዎች በስሙ አመኑ ከተባሉት መካከል ነው ሲል ነው፡፡
ከምዕራፍ ፪ ጋር ሲያያዝን ነው፡፡ በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ ያደረገውን ምልክት/ገቢረ ተአምራት/ ባየ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ ብሎ ስለነበር፡፡
ከዚህ ጋር ሲያያዝ ነው ዮሐ፪፥፳፫ አመኑ ከተባሉ ሲደምረው ከፈሪሳውያን ወገን የሚሆን ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሠው ነበር አለ፡፡ ካመኑት መካከል አንዱ ኒቆዲሞስ ነውና
አንድም፦ ታሪክ አላያያዘም ቢሉ፦ የቃሉን ትምህርት ገቢረ ተአምራቱን ተመልክቶ በእርሱ ያመነ ከፊሪሳዊያን ወገን የሚሆን በትምህርቱ በሀብቱ በሹመቱ የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሠው ነበረ ሲል ነው፡፡
የአይሁድ አለቃቸው ሲል፦ አለቅነቱ በሶስት ወገን ነው በትምህርት/ሊቅ ኦሪት/በሹመት በባለፀግነት (በሀብት)
ዮሐ፫፥፪
"እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን እነዚህን ምልክቶችን ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን አለው።"በግዕዝ "ወውእቱ መድአ ሃበ እግዚአ ኢየሱስ ቀዲሙ ሌሊቱ።" ትርጉሙ "አስቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታ የመጣ"
አማርኛው ከግዕዙ ጋር ሲነጻፀር ቀዲሙ /አስቀድሞ/ የሚለው ይገኝበታል ።"እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ አስቀድሞ መጥቶ
አስቀድሞ ወደ እርሱ የመጣ አለ ከምን አስቀድሞ?፦ ሲለው በስቅለት ጊዜ ሥጋውን ከመስቀል ከማወረዱ በፊት ለትምህርት በሌሊት መጣ ሲል ነው።
አስቀድሞ የሚለው ሥጋውን ከማውረዱ በፊት አስቀድሞ ለመማር መጣ ለማለት ነው፡፡ ዮሐ ፲፱
አንድም፦ ከመዓልት ከሚመጡት አስቀድሞ በሌሊት መጣ ሲል ነው
አንድም፦ ከማመን አስቀድሞ የመጣ ሲል ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ኋላ ላይ አምኗል ከማመኑ በፊት ነው ለትምህርት የሚመጣ ነበር። ዮሐ ፯፥፵፱
በሌሊት ለምን መጣ?
በሌሊት ለምን መጣ ቢሉ ለወንጌል የተጋ የእግዚአብሔር በረከት እንዳይከፈልበት የሚፈልግ ነውና፡፡
አንድም፦ ውዳሴ ከንቱ ሽቶ መምህር ነኝ እያለ ገና ይማራል ብለው እንዳይንቁት ነው።
አንድም፦ ጨለማ የተባለ ድንቁርናን ይዞ አለማወቅንም ለብሶ ሲል ነው፡፡ ጨለማ የተባለች
አንድም፦ የቀን ልቡና ባካና ነው፡፡ የሌሊት ልቡና የተሰበሰበ ነውና፡፡ በተሰበሰበ አእምሮ ለመማር የሌሊቱ ጊዜ የተመቸ ነው፡፡
አንድም፡- አይሁድን ፈርቶ ነው፡፡ ዮሐ፱፥፳፫
በሌላ በኩል ኒቆዲሞስ የጌታን መምህርነት የመሰከረለት አምኖ ነው ወይስ ሳያምን ነው የሚለው መመልከት ይገባል።
ፍጽም አምኗል ቢሉ፦ አምኖ ነው ቢሉ፦ በህልውና በባሕርይ በመለኮት በሥልጣን ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ከሆነ በቀር ማንም ሰው ይህንን ሥራ ሊሠራው አይችልም ሲል ነው፡፡ ዮሐ፩፥፶
ፍጹም አላመነም ቢሉ፦ እግዚአብሔር ያደረበት ሠው ካልሆነ በቀር ይህንን ተዓምራት ማንም ሊሰራው አይችልም ሲል ነው፡፡
ዮሐ፫፥፫
"ኢየሱስም መልሶ እውነት እውነት እልሃለሁ ሠው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔር
መንግስት ሊያይ አይችልም አለው፡፡"የእግዚአብሔር መንግስት ያለው፦ ሃይማኖትን ነው፡፡ መንግስተ ሰማያት ሃይማኖት ትባላለች ለምን መንግስት ሰማያት በሃይማኖት ነውና የምትወረሰው ደግሞ ወልድ ዋሕድ በምትባል ሃይማኖት የምትወረስ ናትና፡፡
አንድም፦ መንግስተ ሰማያትን ነው
ጻድቃን ከረፍታቸው በኋላ እንደ ከዋክብት ብርሃናዊያን ሆነው ይወርሷታል፡፡
ሠው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርስም ሲል ያልተጠመቀ ርኩስ ነው የረከሠ ያልተጠመቀ ሁሉ መንግስተ ሰማያትን አይገባባትም፡፡ አይወርሳትም አያያትም።
ሰው በጥምቀት ዳግም ካልተወለደ በቀር መንግሥተ ሰማያትን አይወርሳትም ሲል ነው፡፡ ዮሐ፩፥፲፩-፲፫
ዳግም ልደት ያለው ጥምቀት ነው፡፡
ለልደት ሥጋ ነው ቢሉ፦ ከእናት ከአባት የምንወለደው አንድ ልደት ሲሆን በጥምቀት ከእግዚአብሔር ሲወለዱ (የምንወለደው) ዳግም ልደት ነው፡፡/ያልተካከለ ንጽጽር/
ለልደት ነፍስ ቢሉ፦ ሰው ሁለተኛ በጥምቀት ከእግዚአብሔር የሚወለደውን ነውና።/የተሰተካከለ ንጽጽር/ ዮሐ፩፥፲፩-፲፫
ጥቅል ትርጉም፦ ያልተጠመቀ/ዳግም ያልተወለደ/ ወልድ ዋሕድ የምትለውን ሃይማኖት አያውቃትም፡፡ መንግስት ሰማያትን አይወርስም ሲል ነው፡፡
ዮሐ፫፥፬
"ኒቆዲሞስም ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል ዳግመኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው።"ሰው ወደ እናቱ ማኅፀን ወደ አባቱ አብራክ ተመልሶ ዳግም ሥጋዊውን ልደት ይወለድ ዘንድ እንዴት ይችላል? ሲል ነው፡፡
አንድም፦ ዳግም ካልተወለደ ክብር አብራክ ተመልሶ ዳግም ሥጋዊውን ልደት ይወለድ ይገባዋል ሲል ነው
ዮሐ ፫፥፭
"ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ሲል እውነት እውነት እልሃለሁ ሠው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡"ኒቆዲሞስ ጌታን ዳግም መወለድ ይቻላል ግዴታ ነው ብሎ ጠይቆ ነበርና ለጠየቀው መልስ ሲሰጥ ነው፡፡
ይቻላልን፦ ብሎ ለጠየቀው ልደቱን ነገሮች መወለጃውን አልነገረውም ነበርና ሁለተኛ ከአብራከ መንፈስቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ካልተወለደ መንግሥተ ሰማያት መግባት አይችልም የሚለውን የመወለጃውን መንገድ ሲገልጥ ነው።
ይገባዋል፦ ላለው ደግሞ የሚያሰጠውን ክብር ነገረው ሲል ነው።
ዮሐ፫፥፮
"ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው፡፡በሥጋዊ ግብር የሚወለድ ግዙፍ ሥጋ ነው ልደቱም ሥጋዊ ነው ከረቂቅ መንፈስቅዱስ የምትወለድ ነፍስ ግን ረቂቅ ናት፡፡
አንድም፦ ከሥጋ የተወለደ ሥጋዊውን ክብር ያገኛል ከመንፈስ የተወለደ ግን መንፈሳዊውን ክብር ያገኛል ሲል ነው።
ዮሐ፫፥፯
"ዳግመኛ ልትወለድ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ፡፡ዳግመኛ መወለድ ይገባል ግዴታ ነው ሲለው ነው።
አንድም፦ የምትወለድበት መንገድ ይሄ ነው ብዬ ስለነገርኩህ ቃል አታድንቅ ሲለው ነው፡፡
ዮሐ፫፥፰
"ነፋስ ወደ ወደደው ይነፍሳል ድምጹንም ትሰማለህ ነገር ግን ከወዴት እንደመጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅምን ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው፡፡"ንፋስ ወደ ወደደው ይነፍሳል ከወዴት እንደመጣ ወዴትም እንደሚሄድ ግን አይታወቅም የንፋስ መኖር ባህር ሲገሥጽ ዛፍ ሲያናውጽ ይታወቃል፡፡ ከመንፈስቅዱስ የሚወለዱትም ልደት የማይታይ በሥራቸው የሚታወቅ ሲል ነው እንዲሁ በእምነት ተቀብለውት በሚሠራው ሥራ ይታወቃል፡፡