በጫማ መስገድና ተያያዥ ነጥቦች
~
[ሀ] በጫማ መስገድ ይቻላል?
አንዳንድ ሰዎች በጫማ መስገድ የማይፈቀድ ይመስላቸዋል። ለዚህ ያደረሳቸው ጉዳዩ በዑለማእ ሲፈፀም ወይም ሲነገር ስላላጋጠማቸው ይሆናል። ነገር ግን በጫማ ከመስገድ የሚከለክል አንድም ማስረጃ የለም። ይልቁንም በተቃራኒው በጫማ መስገድ የማያሻማ ሸሪዐዊ መሰረት ያለው ሱና ነው። ይህንን ከሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ውስጥ ከፊሉን ብናይ፡-
1. አቡ መስለማ ሰዒድ ብኑ የዚድ አልአዝዲ ረሒመሁላህ እንዲህ ብለዋል፡-
سَأَلْتُ أَنَسَ بْنَ مَالِكٍ: أَكَانَ النَّبِيُّ ﷺ يُصَلِّي فِي نَعْلَيْهِ؟ قَالَ: «نَعَمْ»
“አነስ ኢብኑ ማሊክን ‘ነብዩ ﷺ በጫማዎቻቸው ይሰግዱ ነበርን?’ ብዬ ጠየቅኩት። ‘አዎ’ አለኝ።” [ቡኻሪና ሙስሊም]
2. ዐብዱላህ ብኑ አቢ ሐቢባ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ብለዋል፡-
جاءنا رسول الله ﷺ في مسجدنا ب(قباء فجئت وأنا غلام (حدث) حتى جلست عن يمينه (وجلس أبو بكر عن يساره) ثم دعا بشراب فشرب منه ثم أعطانيه وأنا عن يمينه فشربت منه ثم قام يصلي فرأيته يصلي في نعليه
“የአላህ መልእክተኛ ﷺ ቁባእ ወዳለው መስጂዳችን መጡ - እኔ ለጋ ልጅ ነኝ በጊዜው መጣሁና በቀኛቸው በኩል ተቀመጥኩ። አቡበክር በግራቸው ተቀመጡ። ከዚያም የሚጠጣ ነገር ጠየቁና ከሱ ጠጡ። ከዚያም በቀኛቸው ላለሁት ለኔ ሰጡኝና ከሱ ጠጣሁ። ከዚያም ሊሰግዱ ተነሱ። በጫማዎቻቸው ሲሰግዱ አየኋቸው።” [አሶሒሐህ፡ 2941]
3. ከዐምር ብኑ ሹዐይብ ከአባታቸው፣ ከአያታቸው ተይዞ እንዲህ ብለዋል፡-
رأيت رسول الله ﷺ يصلي حافيا ومنتعلا.
“የአላህ መልእክተኛን ﷺ በባዶ እግራቸውም ተጫምተውም ሲሰግዱ አይቻቸዋለሁ።” [ሶሒሕ አቢ ዳውድ፡ 660]
4. አቡ ሰዒድ አልኹድሪ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ብለዋል፡-
“አንድ ቀን የአላህ መልእክተኛ ﷺ አሰገዱን። በከፊል ሶላታቸው ላይ ሳሉ ጫማዎቻቸውን አወለቁና በግራቸው በኩል አስቀመጧቸው። ሰዎች ይህንን ሲያዩ ጫማዎቻቸውን አወለቁ። ሶላታቸውን ሲያጠናቅቁ ‘ምን ሆናችሁ ነው ጫማዎቻችሁን ያወለቃችሁት?’ አሉ። እነሱም ‘ጫማዎችህን ስታወልቅ ስናይህ ጫማዎቻችንን አወለቅን’ አሉ። በዚህን ጊዜ እሳቸው ﷺ እንዲህ አሉ፡-
"إن جبريل أتاني، فأخبرني أن فيها قذراً؛ فألقيتهما، فإذا جاء أحدكم إلى المسجد؛ فلينظر في نعليه: فإن رأى فيهما قذراً؛ فليمسحهما، ولْيصلِّ فيهما"
‘ጂብሪል ከኔ ዘንድ መጥቶ በነሱ (በጫማዎቼ) ላይ ቆሻሻ እንዳለባቸው ሲነገረኝ አወለቅኳቸው። አንዳችሁ መስጂድ ሲመጣ ጫማዎቹን ይመልከት። ቆሻሻ ካየባቸው ይጥረጋቸውና ይስገድባቸው።’” [ሲፈቱ ሶላት፡ 80]
5. ከሸዳድ ብኑ አውስ ረዲየላሁ ዐንሁ ተይዞ ነብዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡-
«خالفوا اليهود فإنهم لا يصلون في نعالهم ولا خفافهم»
“አይሁዶችን ተፃረሩ። እነሱ በጫማዎቻቸውና በኹፎቻቸው አይሰግዱምና።” [ሶሒሑል ጃሚዕ፡ 3210]
ማሳሰቢያ፡-
ባሳለፍናቸው አምስት ሐዲሦች በጫማ መስገድ እንደሚቻል አይተናል። ስላሳጠርኩት እንጂ ማስረጃዎቹ ከዚህም በላይ ናቸው። ትንሽ ሰፋ ያለ ነገር የፈለገ የሸይኽ ሙቅቢልን ረሒመሁላህ “ሸርዒየቱ ሶላቲ ፊኒዓል” ኪታብ ይመልከት። ነገር ግን:-
1ኛ፡- የሚሰገድበት ጫማ ንፁሕ መሆን አለበት።
2ኛ፡- በጫማ የሚሰገደው ለመታወቅ ወይም ተለይቶ ለመታየት አይነት ኒያ እንዳይሆን
3ኛ፡- ዛሬ ሰዎች ለሱናው ባይተዋር ሆነዋል። ስለሆነም በጫማ በመስገድ የሚነሳ ፈተና ካለ መታቀብ ያስፈልጋል። ጉዳትን ማስወገድ የሚወደድን/ የሚፈቀድን ነገር ከመፀም ይቀድማልና። በዚህን ጊዜ ወደ ተግባር ከመግባት በፊት ማስተማር ይቀድማል ማለት ነው።
4ኛ፡- በሶላትም ውስጥ ይሁን ከሶላት ውጭ ከአውሬዎች ቆዳ የተዘጋጀ ጫማ መልበስ አይቻልም።
[ለ] በጫማ መስገድ የተፈቀደ ወይስ የተወደደ?
በጫማ መስገድ እንደሚቻል ካለፉት ማስረጃዎች አይተናል። ግን ከነጫማ መስገድ የሚፈቀድ ብቻ ነው ወይ የሚወደድም ጭምር ነው? ሸይኽ ኢብኑ ዑሠይሚን ረሒመሁላህ በዚህ ጉዳይ ላይ ከጥንት ጀምሮ ውዝግብ እንደተከሰተ ከጠቀሱ በኋላ “የሚያደላው ይሄ ከሸሪዐዊ ድንጋጌዎች መሆኑ ነው፤ ስለሆነም የተወደደ ነው” ብለዋል። ለዚህም “አይሁዶችን ተፃረሩ። እነሱ በጫማዎቻቸውና በኹፎቻቸው አይሰግዱምና” የሚለውን ሐዲሥና ሌላም ማስረጃ ጠቅሰዋለል። [መጅሙዑ ፈታዋ ኢብን ዑሠይሚን]
[ሐ] በዘመናችን ባሉ መስጂዶች ውስጥ በጫማ መስገድ
በአሁ ሰዓት መስጂዶች ውድ ውድ ምንጣፎች ተነጥፎባቸዋል። ሰው ሁሉ ከነጫማው ቢገባ ምንጣፎቹ በቆሻሻ ይሞላሉ። ይሄ ደግሞ ሰጋጆችን ያስቸግራል። በዚህም የተነሳ ምንጣፍ በተነጠፉ መስጂዶች ውስጥ ከነጫማ መግባት አይገባም። ነገር ግን ከዚህ ሁኔታ ውጭ ከሆኑ (በቤታቸው ወይም ምንጣፍ በሌለባቸው ቦታዎች) ፍላጎታቸው ከሆነ ከነጫማቸው መስገድ ይችላሉ።
[መ] ሶላት ሊሰግድ ሲል ጫማውን ማውለቅ ከፈለገ የት ያድርግ?
በቀኙ በኩል ማስቀመጥ የለበትም። ስለዚህ በግራው በኩል ማድረግ ይችላል። በግራው በኩል ሌላ ሰጋጅ ከኖረ በግራ በኩል ማድረግ የለበትም። ምክንያቱም ለሱ በቀኝ በኩል ይሆንበታልና። በዚህን ጊዜ በእግሮቹ መሀል ያድርግ። ነብዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡- “አንዳችሁ መስገድ ካሰበ ጫማዎቹን በቀኙ በኩል አያድርግ። በግራውም አያድርግ፣ በሌላ ሰው ቀኝ በኩል ይሆናልና - በግራው በኩል ማንም ከሌለ ነው እንጂ። (በግራ ሰው ከኖረ ግን) በእግሮቹ መሀል ያድርጋቸው።” [ሶሒሑል ጃሚዕ፡ 645]
@yasin_nuru @yasin_nuru