“ማግባት ለሚሹ”
የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ምክር
ከምንም በፊት የጋብቻ ዓላማን ማወቅ አለባችሁ፡፡ በሕይወታችን ለምን ጋብቻ እንደሚያስፈልገን መረዳት አለባችሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ ነገርን አትጠይቁ፡፡ እናስ የጋብቻ ዓላማው ምንድነው? ለምንድነው እግዚአብሔር ጋብቻን የሰጠን? ብጹዕ ጳውሎስን እናድምጠው፤ እንዲህ ያለውን፦ "ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑሮው፤ ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራሷ ባል ይኑራት" (1ኛ ቆሮ.7፥2)። "ከድህነት ይወጣ (ትወጣ) ዘንድ" ነው የሚለውን? ወይስ "ሀብት ለማግኘት ሲባል" ነው የሚለውን? አይደለም፡፡ ታዲያ ምንድነው የሚለው? ከዝሙት እንጠበቅ ዘንድ፤ ራሳችንን መቆጣጠር እንችል ዘንድ፤ ንጽህናን ገንዘብ እናደርግ ዘንድ፤ በትዳር አጋራችን ደስ ተሰኝተን እግዚአብሔርን እናመሰግን ዘንድ፡፡ አያችሁ ይኼ ነው የጋብቻ ስጦታው ይኼ ነው የጋብቻ ፍሬው፤ ይኼ ነው የጋብቻ ጥቅሙ፡፡
ስለዚህ ልጆቼ! እማልዳችኋለሁ ትልቁን ጥቅም ዘንግታችሁት ዓይናችሁን በትንሹ ላይ አታሳርፉ፡፡ የትዳር አጋርን ስትመርጡ የሀብት ጉዳይ የእናንተ ትልቅ አጀንዳ ሊኾን አይገባም፡፡ ስለ ሀብት ብሎ የትዳር አጋርን መምረጥ ድንቁርና ነው፤ ሀብት ነገ ሊጠፋ ይችላልና፡፡ ስለዚህ ለትዳር የምትመርጡት ሰው ከምንም በላይ መንፈሳዊ ሀብቱን ተመልከቱ፡፡ በዚህም ዓለም በወዲያኛውም ዓለም ይበልጥ የሚጠቅማችሁ ይኼ ነውና፡፡
አባቶች ሆይ! አብርሃምን ምሰሉት፡፡ አብርሃም ለልጁ ለይስሐቅ ሚስትን ሲፈልግለት፦ ሀብትን አላየም፤ የንጉሣውያን ቤተሰብን አልተመለከተም፤ አፍአዊ ውበትን መመዘኛ አላደረገም፤ ወይም ይህን የመሰለ ሌላ መስፈርትን አልደረደረም፡፡ የነፍስ ንጽህናን እንጂ፡፡
እናቶች ሆይ! ሴት ልጆቻችሁን እንደ ርብቃ አሳድግዋቸው፡፡
እናንተ ማግባትን የምትሹ ወጣቶች ሆይ! ይስሐቅን ምሰሉት፦ ዘፈንን፣ ዳንኪራን፣ ሳቅና ስላቅን፣ የከበሮንና የዋሽንት ጫጫታን፣ ሌላውንም የዲያብሎስ ትርኢት በሰርጋችሁ ቀን አታስቡ፡፡ ከዚህ ይልቅ በምታደርጉት ኹሉም ላይ እግዚአብሔር እንዲቀድማችሁ ለምኑት፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደኾነ ትዳራችሁ ፍቺ፣ ዝሙት፣ ቅናት፣ ጭቅጭቅ፣ ንትርክ የሌለበት ኾኖ ይፀናላችኋል፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደኾነ፥ ሌላው በረከትም ተትረፍርፎ ይመጣላችኋል፡፡ የአውሎ ነፋስ ዓይነት በዙሪያችሁ ቢነፍስም፥ አትነዋወፁም፡፡
እናንተ ልጃገረዶች ሆይ! ርብቃን ምሰሏት፡፡ የትዳር አጋራችሁን ፍጹም ለማፍቀር የተዘጋጃችሁ ኹኑ፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደኾነ ቤታችሁ ፍጹም ሰላማዊ ባሎቻችሁ የምትልዋቸውን የሚያደርጉና በፍቅራችሁ የሚንበረከኩ ይኾናሉ፡፡ ትዳር እንዲህ ኾኖ ሲጀመር፥ እግዚአብሔርንና ወላጆቹን ደስ የሚያሰኝ ልጅ ይገኝበታል፡፡
የቤት ዕቃዎችን መግዛት ስንፈልግ፥ በጣም እንጠነቀቃለን፡፡ የሻጮቹን ማንነት አይተን፣ የዕቃዉንም ጥንካሬ አገላብጠን ተመልክተን ነው የምንሸምተው፡፡ ሚስት ስናገባም ከዚህ የበለጠ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡ የገዛነው ዕቃ ችግር ቢኖርበት ለሸጠልን ሰው መመለስ እንችላለን፡፡ ሚስት ስናገባ ግን ወደ ቤተሰቦቿ መመለስ አንችልም፤ እስከ ዕድሜአችን ፍጻሜ ድረስ ከእኛ ጋር ነው የምትኾነው፡፡ ክፉ ናት ብለን ብንመልሳት፥ በሕገ እግዚአብሔር መሠረት አመንዝራ እንኾናለን፡፡ ስለዚህ፥ ሚስት ስትመርጡ የሀገራችሁን ሕገ መንግሥትን ብቻ አታንብቡ፤ ከኹሉም በፊት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን አንብቡ እንጂ፡፡