ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal


Гео и язык канала: Эфиопия, Амхарский
Категория: Новости и СМИ


The best fiction is far more true than any journalism
📢 ተዓማኒ የመረጃ ምንጭ ፤ ለሙያው ስነምግባር ተገዢ በሆኑ ጋዜጠኞች ብቻ
👉 በፌስቡክ ገፆቻችን https://www.facebook.com/simon.dereje.56
👉 https://www.facebook.com/mik0Man

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Гео и язык канала
Эфиопия, Амхарский
Категория
Новости и СМИ
Статистика
Фильтр публикаций


ገንዘብ ለመቆጠብ በሚል ኑሮዋን በመስርያ ቤቷና በጂምናዜየም ዉስጥ ያደረገችዉ ግለሰብ እያነጋገረች ነው

አነጋጋሪውን ታሪክ የተመለከቱ አስተያየት ሰጪዎች የ2025 ዓመት ቤት አልባነት ከከዚህ ቀደሞቹ የሚለይ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።በማህበራዊ ትስስር ገፆች የተጋራው ምስል እንደሚያሳየው ከሆነ እንስቷ በስራ ቦታዋ ባለ አንድ አነስተኛ ክፍል ውስጥ የጠረጴዛ መብራት፣ የእቃ ማጠብያ ማሽን፣ እንዲሁም አነስተኛ ፍሪጅ የሚታዩ ሲሆን ይሄው በመስርያ ቤቷ የሚገኘው አነስተኛ ክፍል መኖሪያዋ እንደሆነ ተገልጿል። ይህ ወጣ ያለ የአኗኗር ዘይቤን ያሳያል የተባለለት ተንቀሳቃሽ ምስል በተለቀቀ በአጭር ጊዜ ውስጥ የበርካቶችን ቀልብ ለመግዛት የቻለ ሲሆን የተለመደውን የአኗኗር መንገድ በማስቀረት የቤት ኪራይ ወጪን የሚያስወግድና ገንዘብ ለመቆጠብ የሚያስችል ፍቱን መፍትሄ ነው ተብሎለታል።

ዴስቲኒ የተባለችው ይህቺ እንስት ቤት አልባ ለመሆን ወስና በመስርያ ቤቷ ውሰጥ መኖር መጀመሯን በቲክቶክ ላይ ይፋ ያደረገች ሲሆን ቲክቶክ ላይ በለቀቀቺው ቪድዮ በየወሩ ለቤት ኪራይና ተያያዥ ወጪዎች ከ2ሺ የአሜሪካ ዶላር በላይ ማውጣት እንዳሰለቻት ስትናገር ተደምጣለች። በዚህ በመማረር እንስቷ ወጪዎችን ለመቀነስ ስትል ቤት ተከራይታ መኖር ያቆመች ሲሆን ይህም ገንዘቧን እንድትቆጥብ እምዳስቻላት ትገልፃለች።

በኢንስታግራም ላይ ከፍተኛ ትኩረት በሳበው የዲስቲኒ ቪድዮ እነስቷ ቤት ላለመከራየት ከወሰነች በኃላ በመኪና ውስጥ ለመኖር ሞክራ እንደነበረች የተናገረች ሲሆን ይሄው አማራጭ የቤት ኪራይ ወጪ የከበዳቻው በርካታ አሜሪካውያን የሚከተሉት መንገድ ነው። ነገር ግን ዴስትኒ መኪናዋ መበላሸቱን ተከትሎ ለረዥም ጊዜ በመኪጋዋ ውስጥ ለመኖር ሳትችል ቀርታለች። ከዚህ በመቀጠልም እንስቷ ሰለገጠማት ችግር ከአሰሪዋ ጋር በነፃነት የተነጋገሩ ሲሆን የስራ አለቃዋ እንስቷ በመስርያ ቤቱ ውስጥ ማደር መጀመሯን ብትነግረውን ድርጊቷን እንድታቆም ወይንም ስራ እንድትለቅ ሳያደርጋት ቀርቶ ችግሯን በመረዳት እዛው ማደሯን እንድትቀጥል እንደፈቀደላት ተገልፆል።

እንስቷ ኑሮዋን በመስርያ ቤቷ ውስጥ ከማድረጓ በተጨማሪ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ማለትም ገላዋን መታጠብና ሌሎች ተዛማጅ ነገሮችን መከወን ስትፈልግ ደግሞ ስፖርት በምታዘወትርበት ጂምናዝየም ሻወር ወስዳና ተዘገጃጅታ ወደ ስራ እንደምትገባ ተናግራለች። ከዚህ በተጨማሪ አንድ አንድ ንብረቶቿን ለማስቀመጥ ደግሞ በወር 75 ዶላር የሚከፈልበት አነስተኛ መጋዝን መከራየቷን ኢንስታግራም ገፆ ላይ ባጋራችው ተንቀሳቃሽ ምስል አስታውቃለች።

ታድያ እንስቷ ይህንን ታሪኳ ለሰዎች በምታጋራበት ሰዓት በርካቶች ከቆሻሻ ማጠራቀምያ ምግብ እየለቃቀምኩ የምኖር ነው የሚመስላቸው ነገር ግን እንደዛ አይደለም እኔ እነሱ በየወሩ ለቤት ኪራይ ለመብራትና ውሃ ክፍያ የሚያወጡትን ወጪ በባንክ አካውንቴ እየቆጠብኩ የተሻለ ህይወት እየኖርኩ ያለሁ ሰው ነኝ ስትል እንደምትመልስላቸው ትናገራለች። ታድያ ይህ ታሪክ በርካቶች የአውሮፓውያኑ 2025 ዓመት አዲስ አይነት ጎዳና ተዳዳሪነት እያስመለከትን ይገኛል የሚል አስተያየት እንዲሰጡ አስገድዷቸዋል።

በሚሊዮን ሙሴ
#ዳጉ_ጆርናል




ለ18 ወራት የሚያገለግል የኢንሱሊን በቂ ክምችት እንደሚገኝ ተገለፀ

የኢንሱሊን መድኃኒት ለቀጣይ አንድ አመት ከስድስት ወር የሚያገለግል ምርት ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ በክምችት ውስጥ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ንጉሴ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ተናግረዋል።

የኢንሱሊን መድኃኒቱን ለመንግስት የጤና ተቋም  እንደሚያቀርቡ ገልፀው እንደ ከነማ ፋርማሲዎች፣ በየመንግስት ጤና ተቋም ስር የሚደራጅ የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶች እንዲሁም አሁን ላይ ለግል ሆስፒታሎች ማቅረብ መጀመሩን በማንሳት ለግል ፋርማሲዎች መድኃኒቱን እንደማያቀርቡ ገልፀዋል። በመሆኑም ከነማ ፋርማሲ እና የኮሚኒቲ ፋርማሲ የኢንሱሊን መድኃኒት በሚፈልጉት መጠን አቅርቦቱን እያገኙ እንደሆነም ተናግረዋል።

በመንግስት የጤና ተቋም በበቂ መጠን አገልግሎቱን ስለቀረበ ማህበረሰቡ እንደማይቸገር አክለዋል። ሶስቱም አይነት ኢንሱሊን፣  የአዋቂ እና የህፃናት ስሪንጅ አንድ አመት ከ ስድስት ወር የሚያቆይ በቂ የሆነ መድሀኒት ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን ገልፀዋል። በቀጣይ አንድ አመት ግዢ በማያስፈልግበት ሁኔታ አስተማማኝ የሆነ አቅርቦት  መኖሩን ገልፀው እንደሁኔታው እየታየ ግዢ እንደሚፈፀምም አቶ ሰሎሞን ንጉሴ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ጨምረው ተናግረዋል፡፡

በሰመኃር አለባቸዉ
#ዳጉ_ጆርናል


የካቲት 18-2017 - ኢትዮጵያ በመለያ ምቶች 5-4 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች።

🇪🇹 ኢትዮጵያ 2-0 ዩጋንዳ 🇺🇬

መለያ ምቶች
🇪🇹 ✅ ✅ ✅ ✅❌✅
🇺🇬 ✅ ✅ ❌ ✅✅❌


  #ዳጉ_ጆርናል


ሉሲዎቹ ቀጣዩን ዙር ተቀላቅለዋል !

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ አቻው ጋር ያደረገውን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በመለያ ምት በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር ተቀላቅለዋል።

የመልስ ጨዋታውን አበበ ቢቂላ ስታዲየም ያደረገው ብሔራዊ ቡድኑ በመደበኛ ሰዓት ጨዋታውን 2ለ0 አሸንፏል።

የሉሲዎቹን የማሸነፊያ ግቦች አረጋሽ ካልሳ እና እፀገነት ግርማ ከመረብ ማሳረፍ ችለዋል።

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በድምር ውጤት 2ለ2 መሆናቸውን ተከትሎ በተሰጠ የመለያ ምት ሉሲዎቹ አሸናፊ ሆነዋል።

ሉሲዎቹ በሁለተኛው ዙር ከታንዛኒያ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ አሸናፊ ጋር ይገናኛሉ።

#ዳጉ_ጆርናል


በደቡብ ኮሪያ ልጅ ለሚወልዱ ወላጆች ክፍያ መስጠት መጀመሩን ተከትሎ በዘጠኝ ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ወሊድ ጨመረ

በዓለም ላይ ዝቅተኛው የደቡብ ኮሪያ የወሊድ ምጣኔ በ 2024 ለመጀመሪያ ጊዜ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ጨምሯል ፣ ምክንያቱ ደግሞ ቀጣሪ ድርጅቶች እና ኮሪያውያን ወላጅነትን እንዲቀበሉ ለማበረታታት የፖሊሲ ለዉጥ መደረጉን ተከትሎ ወላጆች ልጆችን ሲወልዱ እና አሰሪ ተቋማት ክፍያ እንዲያገኙ በመደረግ ላይ ይገኛል።ባለፉት አስርት አመታት ውስጥ ሴቶች ከጋብቻ ወይም ከወላጅነት ይልቅ የስራ እድገትን በማስቀደማቸዉ ሀገሪቱ የወሊድ ምጣኔዋ እያሽቆለቆለ መምጥቷል፡፡

ይህም የሀገሪቱን 51 ሚሊዮን ህዝብ በዚህ ክፍለ ዘመን መጨረሻ በግማሽ ይቀንሰዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡በርካታ ጥንዶች በትዳሮች ውስጥ ለመግባት መፈለግ እና የመንግስት ፖሊሲዎች በስራ እና በቤተሰብ ሚዛን ፣ በህፃናት እንክብካቤ እና በመኖሪያ ቤት ውስጥ ፍላጎት እያሳየ ይገኛል፡፡የስታስቲክስ ኮሪያ ባለሥልጣን ኃላፊ ፓርክ ህዩን-ጁንግ እንደተናገሩት ስለ ጋብቻ እና ልጅ መውለድ የበለጠ አዎንታዊ አመለካከቶች በማህበራዊ እሴት ላይ ለውጥ ታይቷል ብለዋል፡፡

የፖሊሲ ለውጦች ሁለቱም ወላጆች የወላጅነት ፈቃድ ከወሰዱ ደመወዛቸው 100 በመቶ ለስድስት ወራት የሚከፈላቸው ይሆናል፡፡ከዚህ አመት ጀምሮ መንግስት ለቀጣሪ ኩባንያዎች ከህጻናት እንክብካቤ ጋር የተገናኘ ስታቲስቲክስን በተቆጣጣሪ ሰነዶች ውስጥ እንዲያካትቱ እና ለመንግስት ፕሮጀክቶች ማበረታቻ እና ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግን አስገዳጅ እያደረገ ይገኛል፡፡የደቡብ ኮርያ መንግስት በዚህ አመት ወሊድን ለማበረታታት 19.7 ትሪሊየን ዎን ወጪ ለማውጣት አቅዷል፣ ይህም ከ2024 ጋር ሲነጻጸር 22 በመቶ ብልጫ አለው።

በሰምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል


ሁለት ጓደኛሞች የ10 ሚሊዮን ብር የሎተሪ እድለኛ ሆኑ

ጓደኛሞቹ የገና ስጦታ ሎተሪን የ1ኛ ዕጣ 10 ሚሊዮን ብሩን ለሁለት ተካፍለውታል፡፡

ጓደኛሞቹ ገደፋው ከበደ እና ሙላቱ መንግስቴ በስራ ቦታቸው አካባቢ ካዛንችስ ብዙውን ጊዜ ቁርስ በሚበሉበት ምግብ ቤት ቁርስ እየበሉ ሎተሪ አዟሪ ወዳሉበት ይመጣል፡፡

ሙላቱ መንግስቴ ለረጅም አመታት የሎተሪ ደንበኛ ሲሆን ገደፋው ሎተሪ አልፎ አልፎ እንደሚቆርጥ ይናገራል፡፡ ሙላቱ በኪሱ ያለው 20 ብር ብቻ በመሆኑ የገና ስጦታ ሎተሪ አንድ ትኬት ብቻ ገዝቶ የተቀሩትን ሁለት ትኬቶች ጓደኛውን ቁረጥ ይለዋል፡፡ ገደፋው እያንገራገረ 40 ብር ከፍሎ ሁለቱን ትኬት ይወስዳል፡፡

የገና ስጦታ ሎተሪ ታህሳስ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ሲወጣ ገደፋው ከበደ በሁለቱ ትኬት የ6.66 ሚሊዮን ብር፣ ሙላቱ መንግስቴ በአንድ ትኬት የ3.33 ሚሊዮን ብር እድለኛ መሆናቸዉን ዳጉ ጆርናል ከኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ያገኘዉ መረጃ ያመላክታል፡፡ ገደፋው ከበደ ህንፃ በሚገነባበት አንድ ጥግ ቦታ በምትገኝ አነስተኛ የሽሮ ቤት የሚተዳደር ሲሆን ሙላቱ መንግስቴ በጎዳና እየተዘዋወረ መጽሐፍ ይሸጣል፡፡

ጓደኛሞቹ የደረሳቸውን ገንዘብ በምን ስራ ላይ እንደሚያውሉት ለጊዜው እንዳላቀዱ፤ሆኖም ተመካክረን የኛንና የቤተሰብን ህይወት የሚለውጥ ስራ እንጀምራለን ብለዋል፡፡

#ዳጉ_ጆርናል


ዛሬ የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ-ከተማ ወረዳ 2 ካራ ቆሬ በተለምዶ ቢቂላ መናፈሻ እየተባለ በሚጠራዉ አካባቢ የእሳት አደጋ ተከስቷል።

የእሳት አደጋዉን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችና የጸጥታ አካላት እንዲሁም የአካባቢዉ ህብረተሰብ ርብርብ እያደረጉ ነዉ።

በዚህም እሳቱን ወደሌላ ቦታ እንዳይዛመት ማድረግ የተቻለ ሲሆን አስቀድሞ የተያያዘዉን እሳትም መቆጣጠር ይቻላል።
በአደጋዉ  በሰዉ ላይ የደረሰ ጉዳት የለም።

በትግስት ላቀው/ ብስራት ሬዲዮ
#ዳጉ_ጆርናል


ከሚመለከተው አካል ፍቃድ ውጪ ከ100 በላይ ሰዎችን ቀጥረዉ ወርቅ በማዉጣት ሲያሰሩ የነበሩ 16 ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

በኢሊባቡር ዞን ነዲ ወረዳ ጀዊ ቀበሌ ውስጥ ከሚመለከተው አካል ፍቃድ እና እውቅና ውጪ በማዕድን ቁፋሮ ላይ የተሰማሩ 16 ግለሰቦች በእስራት ሲቀጡ ለቁፋሮ የተጠቀሙበት ቁሳቁስ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን መወሰኑን የኢሊባቡር ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታዉቋል።

የኢሊባቡር ዞን ፖሊስ መምሪያ የኮምኒኬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ለማ ቦይዶ ለብስራት እንደተናገሩት አስራ ስድስቱ ግለሰቦች ካለማንም ፍቃድ እና እውቅና ውጪ ራሳቸውን አደራጅተው በስሮቻቸው ከ መቶ ሰዎች በላይ ቀጥረው በህገወጥ መንገድ የወርቅ ማዕድን ሲያወጡ በመገኘታቸው በእስራት ሊቀጡ ችለዋል።

ፖሊስ በደረሰው መረጃ መሠረት አስራ ስድስቱን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር በማዋል ከአቃቤ ህግ ጋር በመሆን የምርመራ መዝገባቸውን በማጣራት አቃቤ ህግ የኦሮሚያ ክልል የማዕድን ውጤቶችን ለማስተዳደር እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ድንጋጌ ቁጥር 223/2012 አንቀፅ 8 መሠረት ክስ የመሠረተ መሆኑን ገልፀዋል።

በአቃቤ ህግ የተመሠረተውን ክስ ሲከታተል የነበረው የነዲ ወረዳ ፍርድ ቤትም አስራ ስድስቱ ግለሰቦች ጥፋተኛ በማለት በ አራት ወር ቀላል እስራት የተቀጡ ሲሆን በቁፋሮ የተገኘ 131 ኪሎግራም ወርቅ እና 153 ሺህ ጥሬ ገንዘብ እንዲሁም 3 ጄነሬተር ፣ 16 ዲጂኖ ፣15 የወርቅ ማንጠሪያ ገበቴ እና  3 የወርቅ ሚዛን ለመንግስት ገቢ እንዲሆን መወሰኑን ምክትል ኢኒስፔክተር ለማ ቦይዶ ጨምረው ለብስራት ተናግረዋል።

በሰመኃር አለባቸዉ
#ዳጉ_ጆርናል


በአዲስአበባ ፤ አገልጋዮች በቅዳሴና ለሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎት ሰዓት ሞባይል ስልክ ይዘው ወደ ቤተክርስቲያን እንዳይገቡ ታገዱ

አገልጋዮች በቅዳሴና ለሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎት ሰዓት ሞባይል ስልክ ይዘው ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ መከልከሉን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስታወቀ።

ሀገረ ስብከቱ የዐቢይ ጾምን አስመልክቶ አገልግሎቱ እንዴት መከናወን እንዳለበት ከሁሉም ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎችና ሰባክያነ ወንጌል እንዲሁም ቄሰ ገበዞች ጋር ባደረገው ውይይትና ስምምነት መነሻነት የተለያዩ መመሪያዎች መተላለፋቸው ተገልጿል።

ከመመሪያዎች አንዱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚከናወኑ የጸሎተ ቅዳሴና ሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች የእጅ ሞባይል ስልክ ይዞ መግባት በጥብቅ የተከለከተለ መሆኑን ለሁሉም ገዳማትና አድባራት በተላከው የመመሪያ ደብዳቤ ለማወቅ ተችሏል።

በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት መሠረት ቅዳሴ የሁሉም ጸሎታት ማጠናቀቂያ ፣ ቀራንዮ ላይ ምንገኝበት፣ የበጉ ሠርግ ላይ የምንታደምበት፣የጌታችንን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን በአንድነት ለሓጢአት ሥርየት፣ ለነፍስ ሕይወት፣ ለሃይማኖት ጽንዐትና ለመንግሥተ ሰማያት መውረሻ ይሆነን ዘንድ የምቀበልበት ታላቅ የጸሎት ሰዓት ነው ብሏል ሀገረ ስብከቱ።

በመሆኑም አላስፈላጊ የእጅ ስልክ አጠቃቀም ጎልጎታን ከሚያስረሱ ፣በረከትን ከሚያሳጡና ጸጋን ከሚያስወስዱ ድርጊቶች መካከል አንዱ በመሆኑ እንደተከለከለም ተገልጿል።

ይህንን መመሪያም የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ሰበካ ጉባኤያት ጥብቅ ክትትል በማድረግ እንዲያስፈጽሙ መታዘዛቸውን በተጻፈ ደብዳቤ ለማወቅ ተችሏል።

Via አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
#ዳጉ_ጆርናል


በአውስትራሊያ አንዲት ነርስ ለእስራኤላውያን ታካሚዎች ህክምና እንደማትሰጥ በመናገሯና በመዛቷ ክስ ተመሰረተባት

በአውስትራሊያ የምትኖር አንዲት ነርስ የሆስፒታሉ ሰራተኞች ለእስራኤል ታማሚዎች ህክምና እንዳይሰጡ እና የግድያ ዛቻ ስትፈፅም የሚያሳይ ቪዲዮ መሰራጨቱን ተከትሎ ክስ ተመስርቶባታል። የኒው ሳውዝ ዌልስ ፖሊስ ረቡዕ ዕለት እንዳስታወቀው የ26 ዓመቷን ሴት በሶስት ወንጀሎች ክስ እንደተመሰረተባት ይፋ አድርጓል።

የኒው ሳውዝ ዌልስ ፖሊስ ኮሚሽነር ካረን ዌብ እንዳሉት ሴትየዋ ሳራ አቡ ሌብዴህ የምትባል ሲሆን አውስትራሊያን ለቅቃ እንዳትወጣ እና ማህበራዊ ትስስር ገጾችን እንዳትጠቀም ተከልክላለች። ዌብ እንደተናገሩይ ሴትየዋ በመጋቢት 19 በሲድኒ ፍርድ ቤት ትቀርባለች ብለዋል። ይህ እርምጃ የተወሰደው በሲድኒ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ ሁለት የእስራኤል ታማሚዎችን ለመጉዳት ስትፎክር የሚያሳይ ምስል በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በመሰራጨቱ የተነሳ ሲሆን ሰፊ ውግዘት አስከትሏል።

በእስራኤላዊው የይዘት ፈጣሪ ማክስ ቬፈር በተጋራ የቪዲዮ ውይይት ላይ አቡ ሌብዴህ ህክምና የሚፈልጉ እስራኤላውያንን እንደማታከም እና "እንደምትገድላቸው ስትናገር ትታያለች። በቪዲዮው ላፕ በተጨማሪም አንድ ወንድ የሆስፒታል ባልደረባ ብዙ እስራኤላውያን ታካሚዎችን ወደ ሲኦል እንደላከ ሲናገር ይታያል። በሀገር ውስጥ በወጡ ዘገባዎች አህመድ ረሻድ ናዲር የተባለው ግለሰብ በድርጊቱ ክስ አልተመሰረተበትም።

የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ “አስጸያፊ ፣ አሳፋሪ ” በማለት አውግዘዋል። የጤና ባለሥልጣናት ሁለቱ የሆስፒታል ሠራተኞች በጤና አጠባበቅ ውስጥ “በማንኛውም ሁኔታ” እንዳይሠሩ አግደዋል ። የጤና ባለሥልጣናቱ እስራኤላውያን የሆኑ ሕመምተኞች ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚያሳይ ምንም ማስረጃ እንዳላገኙ ተናግረዋል።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል




በኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር በተፈጠረው ግጭት ከ13 በላይ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ህይወት አለፈ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዳሰነች እና በሰሜን ኬንያ ቱርካና የድንበር አከባቢ የኢትዮጵያን ድንበር ዘልቀው የገቡ የቱርካና ታጣቂ የሚልሻ አባላት አርብቶ አደሮች ባደረሱት ጥቃት የ13 ንፁሀን ዜጎች ህይወት ሲያልፍ 3 ሰዎች በከፍተኛ የህክምና ክትትል ላይ እንደሚገኙ የደቡብ ኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት እና ገጽታ ግንባታ ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር አሸናፊ ኃይሌ ለብስራት ሬዲዮ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

"ከየካቲት 12 ቀን 2017 ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ የኢትዮጵያን ድንበር ዘልቀው የገቡ የተደራጁ ታጣቂ የሚልሻ አባላት ተከታታይነት ባለው ሁኔታ በተለያዩ አካባቢዎች ባደረሱት ጥቃት በአከባቢው ከፍተኛ ውድመት ደርሷል"።

ይህንን ተከትሎ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሚዋሰኑበት የድንበር አከባቢ በንፁሀን ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ላይ የደረሰው የህይወት መጥፋትና የንብረት ዘረፋን አስመልክቶ ከአካካቢው ማህበረሰብ ጋር ተወያይተዋል።

በተደጋጋሚ ድንበር ዘልቀው የሚገቡ ታጣቂዎች በሚያደርሱት ጉዳት ለከፍተኛ ችግር መጋለጣወን ነዋሪዎች የገለፁ ሲሆን መንግሥት በድንበር አከባቢ ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን ከጎረቤት ሀገር ኬንያ መንግሥት ጋር ሊሰራ ይገባል ሲሉ መናገራቸውን ኮማንደር አሸናፊ ኃይሌ ለብስራት ሬዲዮ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በሳምራዊት ስዩም
#ዳጉ_ጆርናል


"እንዳለሁ አበራለሁ" የተሰኘና ኦቲዝም ላይ ትኩረቱን ያደረገ መፅሀፍ በአሜሪካን ሃገር ተመረቀ

በደራሲ ማክዳ አርሺ Shining As I am በእንግሊዝኛ ግጥም ተፅፎ በታገል ሰይፉ ወደ አማረኛ የተተረጎመው "እንዳለሁ አበራለሁ" የተሰኘው መፅሃፍ የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም በአሜሪካን ሃገር ሲልቨር ስኘሪንግ ሜሪላንድ ቬተራንስ ፕላዛ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ተመርቋል::

"እንዳለሁ አበራለሁ" ለልጆች ኦቲዝም ምን እንደሆነ በቀላል ቋንቋ የሚያስረዳ ሲሆን ታሪኩ አንድ የኦቲዝም ተጠቂ የሆነ ልጅ ቀኑን ሙሉ የሚገጥመውን ነገር የሚገልፅበት እና በልዩነት ውስጥ ያለን ውበት አጉልቶ የሚያሳይ ስለመሆኑ ታውቋል፡፡ ለልጆችም ትዕግስትን፣ ሌሎችን መቀበልን እና ርህራሄን ያስተምራል ተብሏል፡፡

በምርቃቱ ላይ የመፅሃፉ ደራሲ ማክዳ አርሺ ኦቲስቲክ ልጆች አለምን የሚገነዘቡበት መንገድ ልዩ ነው ያሉ ሲሆን ሆኖም በሃገራችን እንደሚታሰበው ኦቲዝም “ እብደት” ወይም “እርግማን” ሳይሆን በተፈጥሮ የሚከሰት ሰዎች ከማያስተውሉት አነስተኛ የባህሪ ልዩነት አንስቶ እጅግ በጣም ከፍተኛ እገዛና እርዳታ የሚያስፈልገው የአዕምሮ እድገት ልዩነት መሆኑን ተገንዝቦ ልጆቹ የፈጣሪ ስጦታ መሆናቸውን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፤ እስከዛሬ ግን ይህን በቅጡ አልተረዳነውም ሲሉም አክለዋል።

ብዙ ወላጆች ከማህበረሰብ የሚደርስባቸው መገለልና እነሱም ስለ ህመሙ በቂ መረጃ ስለማይኖራቸው ለከፍተኛ ስቃይና እንግልት እንደሚዳረጉም አንስተዋል።ኑሯቸውን በሃገረ አሜሪካ ያደረጉት ማክዳ አርሺ ከዚህ ቀደም "የአለም መብራቶች" የተሰኘ የልጆች መፅሃፍ ደራሲ ሲሆኑ በዚሁ መፅሃፍ moms choice award የተሰኘ አሜሪካን ሃገር የሚገኝ ሽልማትን ጨምሮ የአምስት ሽልማቶች አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል::

"እንዳለሁ አበራለሁ" በአሁኑ ወቅት Amazon ላይ እየተሸጠ ሲሆን Shining As I am “Amazon Best seller” መሆኑም የሚታወቅ ነው::በቅርብ ጊዜ በሃገር ውስጥ ለሚገኙ አንባቢያን ይደርሳልም ተብሏል::


#ዳጉ_ጆርናል




ለመቄዶንያ የሚደረገዉ የገቢ ማሰባሰቢያ 554 ሚሊዮን ብር በላይ ደረሰ

ለመቄዶንያ የሚደረገዉ የገቢ ማሰባሰቢያ 18ኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን 554 ሚሊዮን ብር በላይ እንደደረሰ ዳጉ ጆርናል ታዝቧል።

ለሊቱን የፕሮቴስታንት እምነት ዘማሪያን እና ፓስተሮች ገቢ ማሰባሰቡን ያገዙ ሲሆን በዛሬው እለት ደግሞ ከአሜሪካ አትላታ እና ከአዲስ አበባ የተሰባሰቡ ጓደኛሞች ስቱዲዮ ድረስ በመገኘት 500,000 ብር ለመቄዶንያ ለግሰዋል፡፡

በገቢ ማሰባሰቢያዉ በግለሰቦች እና በሀይማኖት ተወካዮች በኩል የሚደረጉ ድጋፎች በብዛት የተስተዋሉ ሲሆን ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ድጋፍ ዉጪ የባንኮች እና ሌሎች ትልልቅ ተቋማት የድጋፍ እንቅስቃሴ ግን እስካሁን አልታየም።

#ዳጉ_ጆርናል


ዩክሬን ያላትን ማዕድን ለአሜሪካ ለመስጠት ተስማማች

ዩክሬን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በዋና ማዕድን ልማት ስምምነት ላይ ደርሳለች ሲሉ የኪዬቭ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናግረዋል። ባለሥልጣኑ ምንም ተጨማሪ ዝርዝር መግለጫ ሳይሰጡ "በርካታ ጥሩ ማሻሻያዎች ተስማምተናል እናም እንደ አወንታዊ ውጤትም ተመልክተናል" ብለዋል። የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ዋሽንግተን የተፈጥሮ ሀብቱን ከመጠቀም ሊገኝ የሚችለውን 500 ቢሊዮን ዶላር የማግኘት መብትን የመጀመሪያ ጥያቄዎች የተወች ሲሆን ነገር ግን በጦርነት ለተጎዳችው ዩክሬን ጠንካራ የደህንነት ዋስትና የማትሰጥ ይሆናል።

የዩናይትስ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዩክሬን አቻቸው ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በዋሽንግተን በዚህ ሳምንት ስምምነቱን ይፈራረማሉ ብለው እንደሚጠብቁ ስማቸው ያልተገለፀ የዩክሬን ባለስልጣን ተናግረዋል ።
ስምምነት ላይ መድረሱን ሳያረጋግጡ ትራምፕ ማክሰኞ እለት እንደተናገሩት ለስምምነቱ ምላሽ ዩክሬን "የመዋጋት መብት" ታገኛለች ብለዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ገንዘብ እና ወታደራዊ መሳሪያዎቿ ባይኖሩ ኖሮ ይህ ጦርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ያበቃ ነበር ሲሉ አክለዋል።

ለዩክሬን የአሜሪካ መሳሪያዎች እና ጥይቶች አቅርቦቶች ይቀጥላሉ ወይ ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ “ምናልባት ከሩሲያ ጋር ስምምነት ላይ እስክንደርስ ድረስ ድጋፍ ማድረግ አለብን፣ ስምምነቱ ካልተደረሰ ግን ይቀጥላል” ብለዋል። ማንኛውንም የሰላም ስምምነት ተከትሎ በዩክሬን ውስጥ “አንዳንድ የሰላም ማስከበር ዓይነቶች” እንደሚያስፈልግ ትራምፕ አክለው ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ትራምፕ ዜለንስኪን “አምባገነን” ሲሉ የገለፁት ሲሆን ጦርነቱን የጀመረችው ዩክሬን ናት ማለታቸው ይታወሳል። የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት የአሜሪካን የ500 ቢሊዮን ዶላር የማዕድን ሀብት ጥያቄ ውድቅ ካደረጉ በኋላ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሩሲያ በፈጠረችው የሃሰት የመረጃ ውስጥ እንደሚኖሩ ጠቁመዋል። ትራምፕ ሞስኮ ሙሉ ወረራ ከጀመረች ከሦስት ዓመታት በፊት ጀምሮ ዋሽንግተን ላደረገችው ወታደራዊና ሌሎች ድጋፎች የዩክሬን ማዕድን ለማግኘት ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል




ሰሜን ኮሪያ የአሜሪካን፣ ጃፓን እና ፈረንሳይን የጋራ የባህር ኃይል ጦር ልምምዶችን አወገዘች

ሰሜን ኮሪያ ዛሬ ማክሰኞ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ጃፓን እና ፈረንሳይ በጋራ የባህር ኃይል ልምምዶችን ማድረጋቸዉን በመቃወም የወታደራዊ ወረራ ፍላጎታቸውን ለማደስ ያደረጉት ሙከራ ብላለች።

በመንግስት የሚተዳደረው የኮሪያ ማእከላዊ የዜና አገልግሎት (KCNA) ጃፓንን “በኤዥያ-ፓሲፊክ ክልል ያለውን የሃይል ሚዛን ስጋት እና አዲስ የግጭት መዋቅር በመፍጠር” ሲል ከሷል።

የጋራ ልምምዱ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በፊሊፒንስ አቅራቢያ በሚገኙ ውሃማ አካላት ላይ በሶስቱ አጋሮች የተካሄደ ሲሆን የአሜሪካ እና የፈረንሳይ አውሮፕላኖች እንዲሁም የጃፓን የጦር መርከብን ያሳተፈ ነበር።

"የጃፓን አውሮፕላን ተሸካሚ ከመከላከያ አቀማመጡ ጋር ግንኙነት በሌለው ራቅ ወዳለ ቦታ የማሰማራቱ እውነታ እና ከውጭ ወራሪዎች ሃይሎች ጋር መቀላቀል የወታደራዊ ሃይሎች የባህር ማዶ ወረራ ምኞት ወደ ትግበራ ደረጃ መግባቱን ያሳያል" ሲል  የኮሪያ ማእከላዊ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል


የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባ የነዋሪነት አገልግሎት የወረዳ ጽ/ቤት አመራር በ10ሺ ብር  ተደራድረው የዲጂታል ምዝገባ ሲያከናውኑ በቁጥጥር  ስር ዋሉ

የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ በደረሰው የተገልጋይ ጥቆማ የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አያለው እንዲሁም የነዋሪ መርጃ፣ ህትመት ስርጭት እና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ መንግስቱ እጅጉ  በቁጥጥር  ሥር  ውለዋል።

ተከሳሾቹ በጋራ በመመሳጠር ላልተገባ ሰው አገልግሎትን በገንዘብ ለመሸጥ በ10ሺ ብር ተደራድረው የዲጂታል ምዝገባ በማከናወን ላይ ሳሉ በተደረገው ክትትል እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት  ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን  ተናግረዋል።

የተቋሙ የስነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ክፍል ከፖሊስ ጋር በመተባበር ላለፉት ሶስት የስራ ቀናት ክትትል ሲያደርግ በመቆየት ተጠርጣሪዎቹ  የካቲት 17 ቀን በጽ/ቤቱ ውስጥ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል። ተቋሙ በክትትሉ የተደራጁ የድምፅ ቅጂ እና ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለፖሊስ አስረክቧል።

ተቋሙ  ከህገ-ወጥነት ለመከላከል የስነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና የስራ ክፍል የመረጃ አቅምን እያጠናከረ ያለና የዲጂታል አገልግሎቱም ኦዲት የሚደረግበት ስርዓት በመዘርጋት  ከህገ-ወጥ ደላሎች እና አገልግሎትን በገንዘብ ከሚሸጡ ሰዎች ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው አቶ ዮናስ ዓለማየሁ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በኤደን ሽመልስ
#ዳጉ_ጆርናል

Показано 20 последних публикаций.