EBC (Ethiopian Broadcasting Corporation)


Гео и язык канала: Эфиопия, Амхарский
Категория: Новости и СМИ


Ethiopian Broadcasting Corporation (EBC)

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Гео и язык канала
Эфиопия, Амхарский
Категория
Новости и СМИ
Статистика
Фильтр публикаций




"ከቭላድሚር ፑቲን ጋር በቅርቡ እገናኛለሁ"፦ ዶናልድ ትራምፕ
********

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ከሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተገናኝተው ሊያደርጉ እንደሆነ ተገልጿል።

ትራምፕ "ከቭላድሚር ፑቲን ጋር በቅርቡ እገናኛለሁ፤ መቼ እንደሆነ ግን አላውቅም" ማለታቸውን ስፑቲንክ አስነብቧል።

አክለውም፥ የሩስያ - ዩክሬን ግጭትን ለማስቆም ከፑቲን ጋር ተገናኝተው በመምከር የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

ይህ መቼ እንደሚሳካ መገመት የሚቻለው ግን ከፑቲን ጋር ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ ብቻ መሆኑን ትራምፕ አመላክተዋል።

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ከሩስያ ጋር ስምምነት በመፈረም ሰላም ለማውረድ ዝግጁ መሆናቸውንም ነው ትራምፕ የጠቆሙት።

በሜሮን ንብረት




በሰሜን ምዕራብ ቱርክ ቦሉ ግዛት በሆቴል ውስጥ በተነሳ የእሳት አደጋ ቢያንስ 66 ሰዎች ሕይወታቸው አለፈ
*************

በሰሜን ምዕራብ ቱርክ ቦሉ ግዛት በሆቴል ውስጥ በተነሳ የእሳት አደጋ ቢያንስ 66 ሰዎች ሞተው 55 ሰዎች መጎዳታቸውን የግዛቲቱ ባለስልጣናትን ጠቅሶ አልጀዚራ ዘግቧል።

"በአደጋው የ66 ዜጎቻችንን ሕይወት አጥተናል፤ በጥልቅ ሀዘን ውስጥ ነን" ሲሉ የቱርክ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ዬርሊካያ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።

የሀገሪቱ የጤና ሚኒስትር ከማል ሜሚሶግሉ፥ ከተጎጂዎቹ መካከል ቢያንስ አንዱ በአስጊ ሁኔታ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የሀገሪቱ የፍትሕ ሚኒስትር ይልማዝ ቱንክ፥ ከአደጋው ጋር በተያያዘ የሆቴሉን ባለቤት ጨምሮ 4 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው በዋና ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ምርመራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

የቦሉ ግዛት አስተዳዳሪ አብዱልአዚዝ አይዲን በበኩላቸው፥ እሳቱ በባለ 11 ወለሉ ሆቴል 4ኛ ፎቅ ላይ ከሌሊቱ 9:30 ገደማ መነሳቱን ተናግረዋል። 4ኛው ፎቅ የሆቴሉ ምግብ ቤት መሆኑንም አክለዋል።

በአደጋው ከሞቱት ሰዎች መካከል ሁለቱ ከሕንፃው ወደ ውጭ ከዘለሉ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን ጠቅሰዋል።

የእሳት አደጋው በተከሰተበት ወቅት 234 እንግዶች በሆቴሉ ውስጥ እንደነበሩ አስተዳዳሪው አብዱልአዚዝ አይዲን ለአናዶሉ የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

የአደጋው ምስሎች የሕንጻው ጣሪያና የላይኛዎቹ ወለሎች በእሳት ሲጋዩ ያሳያሉ።

በወቅቱ የሆቴሉ የአደጋ ጠቋሚ ሥርዓት ከጥቅም ውጭ ሆኖ እንደነበር የዓይን እማኞችን ጠቅሰው መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ፕሬዚዳንት ሬሺፕ ታይፕ ኤርዶዋን መንግሥታዊ ተቋማት የአደጋውን መንስዔ ለማጣራት እየሰሩ ነው ብለዋል።


ኢትዮጵያ በቱርክ በቦሉ ግዛት በሆቴል ውስጥ የተነሳ እሳት ባስከተለው የሰዎች ጉዳት እና የሕይወት መጥፋት የተሰማትን ሀዘን ገለፀች
**************

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቱርክ በቦሉ ግዛት በሆቴል ውስጥ የተነሳ እሳት ባስከተለው የሰዎች ጉዳት እና የሕይወት መጥፋት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል።

ሚኒስቴሩ በመግለጫው በአደጋው ለሞቱ ሰዎች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል። የአደጋው ተጎጂዎችም በቶሎ እንዲያገግሙ ሚኒስቴሩ መልካም ምኞቱን ገልጿል።

ሚኒስቴሩ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለቱርክ ሕዝብና መንግሥት ያለውን አጋርነትም በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ስም ገልጿል።


የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአፋር ክልል በርዕደ መሬት የተጎዱ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ተመለከቱ
*********

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት እንዲሁም ከውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የተውጣጣ ቡድን በአፋር ክልል በርዕደ መሬት የተጎዱ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ተመልክቷል።

በምልከታውም በክልሉ በተከሰተው ርዕደ መሬት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለው ጥረት በቂ አለመሆኑን ቡድኑ ተመልክቷል።

ከሰብዓዊ እርዳታ ጋር በተያያዘ የመጠለያ፣ የምግብና የውሃ አቅርቦት እንዲሁም የጤና አገልግሎት አሰጣጥ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከተመለከተ በኋላ፤ በቀጣይ መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች አመላክቷል።

ለዜጎች የሚደረገው ድጋፍ መጠናከር እንዳለበትና በየደረጃው ያሉ የክልሉ አመራር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው የቡድኑ አባላት አስገንዝበዋል።

የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው፥ ጉዳቱ ቅፅበታዊ ቢሆንም፤ በአደጋው የተጎዱ ዜጎችን ለማገዝ እየተሰራ መሆኑን ማስረዳታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል።


የብሔራዊ ታክስ ሪፎርም ግብረ-ኃይል የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ገመገመ
*********

የብሔራዊ ታክስ ሪፎርም ግብረ-ኃይል የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በጉምሩክ ኮሚሽን ዋና መ/ቤት አካሂዷል።

ግብረ-ኃይሉ በታክስ አስተዳደሩ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት በሚያስችሉ የታክስ ፖሊሲ፣ የሀገር ውስጥ ታክስ አስተዳደር፣ የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ አስተዳደር ጉዳዮች ዝርዝር ዕቅድ በማዘጋጀት አፈፃፀሙን በየወሩ እየገመገመ ይገኛል።

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው 6 ወራት የገቢ አሰባሰብ በዕቅዱ መሰረት በተሳካ ሁኔታ የተፈፀመ መሆኑን እና በቀሪ 6 ወራት በዕቅድ የተያዘውን የገቢ ዕቅድ ለማሳካት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ግብረ-ኃይሉ አቅጣጫ ማሰቀመጡን የጉምሩክ ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።

በተጨማሪም ለገቢ አሰባሰቡ አጋዥ የሆኑ የስጋት ስራ አመራር ሥርዓትን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የውዝፍ ዕዳ ክትትልን ማጠናከር፣ የጉምሩክ ዋጋን ወቅታዊ ማድረግ፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ልማት ሥራዎችን ማጠናከር፣ አዳዲስ ታክስ ከፋዮች ወደ ታክስ ሥርዓቱ እንዲገቡ ክትትል ማድረግ፣ የደረሰኝ እና የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ቁጥጥር እና ክትትልን ማጠናከር ግብረ-ኃይሉ በውይይቱ ያስቀመጣቸው የቀጣይ ወራት አቅጣጫዎች ናቸው።

የብሔራዊ ታክስ ሪፎርም ግብረ-ኃይል ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከጉምሩክ ኮሚሽን በተወጣጡ ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ ግብረ-ኃይል ነው።





Показано 9 последних публикаций.