HAKIM mini-journal club: hot off the press update in diabetes
የአለም የስኳር ህመም ሳምንትን እያከበርንበት ባለበት ሁኔታ ላይ በላንሴት የህክምና መጽሄት ላይ ዛሬ ታትሞ የወጣ አንድ ጥናት በስኳር ህመም ዙሪያ በቸልታ የማይታለፉ አሳሳቢ እውነታዎችን አስነብቧል። ይህ ሰፊ ጥናት ብዙ አስደንጋጭ መረጃዎችን ይዟል።
በ200 አገሮች ውስጥ የሚገኙ ከ141 ሚሊዮን በላይ ወካይ ተሳታፊዎችን የሚያካትት ሆኖ ከ1,000 በላይ ጥናቶች የተውጣጡ መረጃዎችን የሚሸፍን ጥልቅ ትንታኔ ስለሆነ እስከዛሬ ከተሰሩ የዳሰሳ ጥናቶች በተሻለ ሁኔታ ስለስኳር ህመም ስርጭትና አዝማሚያዎች አለም አቀፋዊ ምስል ምን እንደሚመስል አሳይቷል።
የዚህ ጥናት ቁልፍ ግኝቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፤ የስኳር ህመም ስርጭት መጨመር፡ በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ800 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች (እንቅጩን ለመናገር 828 ሚሊዮን) በስኳር ህመም እንደሚሰቃዩ ያሳያል። በሚያስገርም ሁኔታ ይህ ቁጥር እኤአ በ1990 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከአራት እጥፍ በላይ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።
የስኳር ሕክምና ሽፋን ዝቅተኛ መሆን፡ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ስኳር ያለባቸው ሰዎች በቂና ጥራት ያለው ሕክምና አያገኙም። ይህ የሕክምና ክፍተት በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገሮች ይብሳል።
የስኳር ህመም ስርጭትና ህክምና ኢፍትሃዊነት፤ በስኳር ህመም ስርጭት እና ህክምና ላይ ጉልህ የሆነ የጂኦግራፊያዊ ልዩነቶች አሉ። ሪፖርቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በስኳር በሽታ ስርጭት ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እያጋጠማቸው መሆኑን አጉልቶ ያሳያል።
የስኳር ህመም መብዛት ምክንያቶች፡ ዋነኛው መንስኤ ከመጠን ያለፈ ውፍረት መጨመር እንደሆነ ተጠቅሷል።
የጉዳዩ አሳሳቢነት፤ የስኳር ህመም ስርጭት በዚህ ፍጥነት መጨመር በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የጤና ጉዳት የሚያመጣ አስቸኳይ ጉዳይ እንደሆነ አመላክቷል።
የስኳር ህመም ስርጭት ለመግታት የግለሰብ ሚና የስኳርን ህመም መስፋፋት ለመቀነስ በየደረጃው የጋራ እርምጃ መውሰድን ይጠይቃል። እያንዳንዱ ግለሰብ የስኳር ህመምን በመዋጋት ረገድ ወሳኝ ሚና አለው።
የስኳር ህመምን ስርጭት ለመግታት የሚረዱ ቁልፍ የፖሊሲ ምክሮች፡✍️ የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
✍️ የስኳር ህመም ተያያዥ የሆኑ የጤና ጠንቆችን የሚቀንሱ ጥራት ያላቸው መድሃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ማድረግ ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ነው።
✍️ የስኳር ህመም ዙሪያ የሚሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች በስፋትና በጥራት መስጠት ይመከራል።
✍️ በስኳር ህመም ዙሪያ የሚሰሩ ጥናትና ምርምሮችን መደገፍ ለነገ የማይባል ኢንቨስትመንት ነው።
✍️ ብሄራዊ ፖሊሲዎች ጤናማ አመጋገብን፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እና ሌሎች ጤናማ ልማዶችን ለማዳበር የሚያበረታቱ መሆን አለባቸው።
ማጠቃለያይህ አዲስ የጥናት ውጤት የስኳር ህመም አስቸኳይ ንቅናቄ መፍጠር እና የተጠና እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ አጉልቶ ያሳያል። ይህንን ዓለም አቀፍ የጤና ፈተና ለመቅረፍ ከግለሰቦች፣ ከጤና ባለሙያዎች እና ፖሊሲ አውጪዎች የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል።
ዋቢ
Zhou, Bin et al. Worldwide trends in diabetes prevalence and treatment from 1990 to 2022: a pooled analysis of 1108 population-representative studies with 141 million participants. NCD Risk Factor Collaboration (NCD-RisC). Lancet, 2024.
የዚህን ጽሁፍ ሙሉ መረጃ በዶ/ር መላኩ ታዬ ብሎግ
https://melakutaye.com/global-diabetes-crisis-action/ ማንበብ ይችላሉ።
ቴሌግራም
https://t.me/hakimmelakuቲክቶክ
https://www.tiktok.com/@hakimmelaku WhatsApp/Telegram consults at +251921720381
Dr. Melaku Taye (Endocrinologist, Lipidologist, Health advocate practicing at Tikur Anbessa Specialized Hospital, Addis Ababa University)
Get social with Hakim on Youtube:
http://www.youtube.com/@Hakim207 @HakimEthio