ምህላ ፩
ሁሉም ነገር የድምጽና የንዝረት ውጤት የመሆኑን ነገር እያሰላሰልኩ በደንብ አየር ሳብኩና ደወሉንም ደወልኩት፡፡ ከመቅደሱ የሚወጣው የደወል ድምጽ በመንደሯ በሙሉ ተሰማ፡፡ በጫካው ውስጥ የከተመች ታላቂቱ የገዴ ወፍ ለደወል ድምፁ ምላሽ ሠጠች፡፡ ከዚህች የተቀደሰች ገዴ ወፍ የወጣው ድምጽ ግን የሕማም፣ የድንጋጤ አይመስልም፡፡ የመንደሯ ውሾች የደወል ድምጹን መስተጋባት ተከትሎ በደስታ ጮኹ፡፡ የደወሉ ድምጽ በተራሮች ገመገም አማካኝነት ከተስተጋባ በኋላ ወደ ሞገድ ተለውጦ ከሰመ፡፡ ደወሉን ደግሜ ደጋግሜ ደወልኩት፡፡ ጊዜውን ጠብቆ ደወሉን መደወል ልጅ እያለሁ ዘወትር የማከናውነው ተግባር ነበር፡፡ የደወሉ ድምጽ ንዝረት ሰውነቴንም በረቂቅ ሁኔታ ይንጠው ጀመር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህ የደወል ድምጽ ልክፍት ጎንደር በሕዝብ መሃል ስረማመድ፣ በማንቸስተር ከተማ የደቡብ ሕንድን ምግብ ቤቶች ስታደም፣ ወይ በሰንሪ ቹኦ የባቡር ጣቢያ በኩል ሳልፍ ይይዘኛል፡፡ ድምፁ ቀጭንና ሰርሳሪ ነው፡፡ ግን ደግሞ የለምለም አረንጓዴ ሸለቆን ሽታ፣ የትኩስ አፈርን ጠረን፣ የወንዝ ዳርን መዓዛ እየነዛ ያልፋል፡፡ ገመዱን በሁለት እጆቼ ይዤ ደወሉን የደወልኩበት የገመዱ የመሰርሰር ስሜት እጆቼ ላይ ይሰማኛል፡፡
ልጅ እያለሁ ሴት አያቴ ስለ ወንድ ቅድመ አያቴ የነገረችኝ የሆነ ታሪክ ትዝ ይለኛል፡፡ አያቴ በሁሉም የሚወደድ ንቁ መነኩሴ ነበር አሉ፡፡ የዚህ ቅድመ አያቴ ታላቅ ወንድም ጃፓን ከሩሲያ ጋር ባደረገችው ጦርነት ተገደለ፡፡ ቀድሞ ባይሞት ኖሮ ከቅድመ አያቴ ይልቅ የቤተመቅሱ ጠባቂ የሚሆነው እርሱ ነበር፡፡ ልክ ከምሽግ አንገቱን ብቅ ሲያደርግ ጭንቅላቱን እንደተመታ ይነገራል፡፡ እና የቤተ መቅደሱን አገልጋይነት የተቀበለው ቅድመ አያቴ የነተበ የምንኩስና ልብሱን ለብሶ በባዶ እግሩ እየተመላለሰ በአካባቢው በእጅጉ የሚወደደውን ሱትራ (የዘወትር ጸሎት) ያነበንብ ነበር፡፡ ወንዙን ሲሻገር የጸሎት መነባበንቡን አቁሞ ከንጹሁ ውኃ ጠጥቶ ወደ ሌላኛው አጎራባች ጎጥ ይጓዛል፡፡
በአብዛኛው በሚሄድባቸው ቦታዎች የሚያከናውናቸው የጸሎተ ፍታት ሥርዓቶች እስከ እኩለ ሌሊት ያቆዩታል፡፡ በውድቅት ወደ መኖሪያ ቤቱ ሲመለስ ግን ብቻውን አይመጣም፡፡ ያማ እያለ የሚጠራውን ከውሻ ትንሽ ከፍ ያለ እንሰሳ አስከትሎ ይመጣል፡፡ ያማ በጃፓንኛ ተራራ ማለት ነው፡፡ አያቴ እንደነገረችኝ እንሰሳው አስፈሪ ጭራቅ የሚያስመስለው ከአፉ እስከ ጆሮው የዘለቀ ከባድ ሽንትር ጠባሳ አለበት፡፡ ቀስ በቀስ እንሳሰው ቅድመ አያቴን ተለማምዶ ቤተኛ ሆነ፡፡ ቅድመ አያቴ እንሰሳውን ሲጠራው ራሱ ‹ያ› የምትለው ቃል ላይ ጠንከር ያለ አጽዕኖት ይሰጣል፡፡ ይህ እንሰሳ የዱር ውሻ ዝርያ ይሁን የተኩላ የሚታወቅ ነበር አልነበረም፡፡
የቅድመ አያቴንና የያማን ታሪክ የነገረችኝ አያቴ በአሁኑ ጊዜ አልጋ ላይ ውላ ኑሮዋ በአዛውንቶች መጦሪያ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያ ወንድ ልጇን አባቴን እንኳን አታስታውሰውም፡፡ የቅርብ ወዳጇ የሆነች እኩያዋ ሴት ግን አሁንም በመንደራቸው አቅራቢያ ትኖራለች፡፡ የአዛውንትነት ዕድሜ ላይ ብትሆንም አሁንም በእርሻ ማሳዎች ላይ አንዳንድ ሥራዎችን ታከናውናለች፡፡ ይህችን ሴት ስለ ያማ ታሪክ የምታውቀው ነገር ካለ ብጠይቃት ምንም የምታስታውሰው ነገር እንደሌለ ነገረችኝ፡፡ ያኔ ቅድመ አያቴ ለአገልግሎት ወደ አጎራባች መንደሮች ይረማመድበት የነበረው ተራራ ምናልባት ዛሬ ለኮንክሪት የሚያገለግል ማዕድን ፍለጋ በግራቨል ማይኒንግ የሚቆፈረው ተራራ ሳይሆን አይቀርም፡፡
ቅድመ አያቴ አንድ በጣም ያረጀ እና የደበዘዘ ፎቶ ብቻ አለው፡፡ ፎቶው ወደ ፓስፊክ ለጦርነት የዘመተውን የጦር ጓድ ተከትሎ የቤተመቅደሱ ደወልም አብሮ ሲዘምት ለማስታወሻ የተነሳ ነበር፡፡ ከደወሉ ጎን የቤተመቅደሱ ግድግዳ ላይ የተጻፉ የቡድሂስት ጽህፈቶችና ምልክቶችም አብረው ይታያሉ፡፡ ከደወሉ ፊት ለፊት ሁለት መነኮሳት ቆመዋል፡፡ አንደኛው ቅድመ አያቴ ሲሆን ሁለተኛው ከአጎራባች ቤተ መቅደስ የመጡ መነኩሴ ናቸው፡፡ እኒህ ጽኑ እና ኃያል የሚመስሉ ውብ የመነኮሳት አልባሳትን የተጎናጸፉ ግዙፍ ሰው አሮጌ የተሸበሸበ የመነኩሴ አልባሱን ለብሶ አንጎንብሶ የተዳከሙ የሚመስሉ ዓይኖቹን ሩቅ ተክሎ ከቆመው አያቴ ጎን ተሰትረዋል፡፡
በፎቶው ላይ እንደማየው የቅድመ አያቴ የመኖር ምኞት የሰለለ የነበረ ይመስላል፡፡ እናም ጦርነቱ ከማብቃት ጥቂት ዓመታት በፊት ድንገት ተዝለፍልፎ ወደቀና ሞተ፡፡ እንግዲህ ይህ ፎቶ ምናልባት በዕድሜው አመሻሽ የተነሳ መሆን አለበት፡፡ ፎቶው ላይ ከደወሉ ጀርባ የእርሱ ጎረቤት የነበሩ ሀምሳ ያህል መንደርተኞች ይታያሉ፡፡ በልጅነቴ አንዳንዶቹን ደርሼባቸዋለሁ፡፡ በዚያ ጊዜ እኔ ሳውቃቸው ፎቶው ላይ የሚታየው ወዘናቸው ተሟጧል፡፡ በእርግጥ ዘመኑ ብዙ ነበርና እንዲያ ቢሆን የሚገርም አይሆንም፡፡
በዚህ ፎቶ ላይ የምትታየው ሴት የሴት አያቴ ጓደኛ ናት፡፡ አያቴ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለች እዚህች ወዳጇ ቤት ትመላለስ ነበር፡፡ ሴት አያቴ በሜጂ ዘመን ነበር የተወለደችው፡፡ ስሟ ዩሳን ይባላል፡፡ አንድ ምሽት ለቤተ መቅደስ በስለት የተሰጠሁ ልጅ ስለመሆኔ ነገረችኝ፡፡ በእያንዳንዱ ምሽት የቤተመቅደሱን ደወል ስሰማ አንገቴን እሰብራለሁ፡፡ አንገቴን ድፍቼ ዓይኖቼን ጨፍኜ ድምፁ ወደሚመጣበት ዞሬ እጆቼን ለፀሎት አገጣጥሜ ጸሎቴን አነበንባለሁ፡፡ ልጅ እያለሁ ከእርጅና የተነሳ ፊቷ የተሰረጎደ አንዲት አሮጊት ሴት የደወሉን ድምጽ ተከትላ በመጸለይዋ ጸሎቷ እንደሚሰምር በማሰብ ወደ ደወል ድምጹ ዞራ ስትጸልይ ማየቴን አስታውሳለሁ፡፡
አንዳንድ ጊዜ የቤተመቅደሳችን ደወል ተራራ፣ ወንዝ፣ ሀይቅ፣ ውቅያኖስ አቆራርጠው ተሸክመውት ወስደው አቅልጠውት ሰዎችን ለመግደል ለጦር መሳሪያነት አውለውት ይሆን እያልኩ አስባለሁ፡፡ የፓስፊክ ጦርነት ካበቃ በኋላ ለቤተመቅደሳችን አዲስ ደወል ተሰርቶ መጣ፡፡ ደግሜ ደጋግሜ የደወልኩት፣ የተወዳጀሁት፣ አብሬው ማለቂያ የሌለውን የሙሪዮጁኮ ሱትራን ያነበነብኩበት ይህ ደወል እንደ ቀደመው ደወል ዓይነት ዕጣ እንዳይገጥመው ምኞቴ ነው፡፡
.
.
.
(የፒያሳ ቆሌዎች ገጽ 58-61 )