ዕውቀት እና የዕውቀት ባለቤቶች ደረጃ ክፍል - 12
የማያውቁትን “አላውቅም” ማለት የእውቀት ግማሽ ነው ጅብሪል ቂያማ ቀን የሚቆምበትን ሰዓት ለረሱል ﷺ በጠየቃቸው ጊዜ
“ከጠያቂው ተጠያቂው የበለጠ አዋቂ አይደለም” የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት፡፡ ይህ የሚጠቁመው አንድ አሊም የሆነ ሰው በአንድ ጉዳይ ሲጠየቅ ስለጉዳዩ የማያውቅ ከሆነ
“አላውቅም” የሚል ምላሽ መስጠት እንደሚገባው ነው፡፡
በጅብሪል ሐዲስ የአላህ መልክተኛ ﷺ
“ጠያቂውን ታውቀዋለህን?” ብለው ኡመርን ሲጠይቁት ፣
“አላህና መልክተኛው አዋቂ ናቸው” በማለት የሰጠው ምላሽም ተመሳሳይ ነበር፡፡
አንድ አሊም ሲጠየቅ
“አላውቅም” የሚል ምላሽ መስጠቱ ደረጃውን የሚቀንስ ሳይሆን አላህን ፈሪ ፣ የዲን ሰው መሆኑን ነው የሚያመላክተው፡፡
አንድ ሰው የማያውቀውን “አላውቅም” ማለቱ ዲኑን ከሚያሟለበት መንገድ አንዱ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡
አላህ ለመላኢካዎች የሚከተለውን ጥያቄ ሲጠይቃቸው የሰጡትን መልሰ እስኪ እናስተውል፡
قَالُوا سُبْحَانَكَ لَا عِلْمَ لَنَا إِلَّا مَا عَلَّمْتَنَا ۖ إِنَّكَ أَنتَ الْعَلِيمُ الْحَكِيمُ
«ጥራት ይገባህ፤ ከአስተማርከን ነገር በስተቀር ለኛ ዕውቀት የለንም፡፡ አንተ ዐዋቂው ጥበበኛው አንተ ብቻ ነህና» (አሉ)፡፡ (በቀራ ፡ 32)
ሸእብይ - ረሂመሁሏህ - ስለአንድ ጉዳይ ተጠየቀና “አላውቅም” የሚል ምላሽ ሰጠ፡፡
“የኢራቅ አሊም ሆነህ አላውቅም ስትል አታፍርም?” በማለት ከጎኑ የነበሩ ሰዎች ጠየቁት፡፡
((“ጥራት ይገባህ አንተ ያሳወቀከን እንጅ ለእኛ እውቀት የለንም” በማለት መላኢካዎች ለጌታቸው ምላሽ ሲሰጡ አላፈሩም፡፡)) በማለት ምላሽ ሰጣቸው።
(ኢብን አብዱል በር “ጃሚኡ በያኒል ኢልም” 2/51)
ነፍሱን ያወቀ ሰው አላህ ለታማኙ ነብይ ﷺ የተናገረውን ያስተውል፡፡
قُلْ مَا أَسْأَلُكُمْ عَلَيْهِ مِنْ أَجْرٍ وَمَا أَنَا مِنَ الْمُتَكَلِّفِينَ
"በላቸው «በእርሱ ላይ ምንም ዋጋ አልጠይቃችሁም፤ እኔም ከተግደርዳሪዎቹ አይደለሁም፡፡"(ሷድ ፡ 86)
ማለትም : የኔ ያልሆነውን "የኔ ነው" ፤ ለእኔ የሚወረድልኝን ወህይ እንጅ በቅጥፈት የማላውቀውን "አውቃለሁ" ብየ የምሞግትም አይደለሁም።
አብደሏህ ብን መስኡድ የሚከተለውን ተናግሯል ፡“እውቀት ከእርሱ ዘንድ ያለ ይናገር፡፡ ከእርሱ ዘንድ እውቀት የሌለው “አሏሁ አእለም” ይበል፡፡ አላህ ለነብዩ የሚከተለውን ተናግራል ፡
قُلْ مَا أَسْأَلُكُمْ عَلَيْهِ مِنْ أَجْرٍ وَمَا أَنَا مِنَ الْمُتَكَلِّفِينَ
"በላቸው «በእርሱ ላይ ምንም ዋጋ አልጠይቃችሁም፤ እኔም ከተግደርዳሪዎቹ አይደለሁም፡፡" (ሷድ ፡ 86)
እንዲህ አይነት ተወዳጅ የሆነ ባህሪ ፣ ከፍተኛ የሆነ ስነምግባር ፣ ምርጥ የሆነ አነጋገር ከሰለፎች ፣ ከሶሃቦች ፣ ከታብእዮች እና የእነርሱን ጎዳና ከተከተሉትም በብዛት ተገኝቷል፡፡
አቡበክር ሲዲቅ ከአላህ ቁርዓን አንድ አንቀጽ ተጠየቀ፡፡ የሚከተለውን ምላሽ ነበር የሰጠው፡
"أية أرض تقلني ، وأية سماء تظلني إذا قلت في آية من كتاب الله بغير ما أراد الله سبحانه وتعالى" “የትኛው መሬት ይሸከመኛል ፣ የትኛው ሰማይ ያጠልለኛል፡፡ ከአላህ መጽሐፍ በአንድ አንቀጽ አላህ ያልፈለገውን በተናገርሁ ጊዜ” ኢብን ኡመር ተጠየቀ ፡ “የአባት እህት ትወርሳለች?”
“አላውቅም” አለ፡፡ ጠያቂውም “አንተ አታውቅም?! ፣ አንተ አታውቅም?!” አለው፡፡
ኢብን ኡመርም ፡ “አዎ” ፤ “ሂድና የመዲናን ኡለሞች ጠይቅ” አለው፡፡
የሚከተለውን ተናግሮ ዘወር ብሎ ሄደ
"نعما قال أبو عبد الرحمن ، سئل عما لا يدريه ، فقال : لا أدري" “አቡ አብዲረህማንን ምን ያማረ (ሰው) አደረገው ፤ ስለማያውቀው ነገር ተጠየቀ እርሱም አላውቅም አለ፡፡”
(ኢብን አብዱል በር ፡ ጃሚኡ በያኒል ኢልም” 2/52)
የሶሃቦች ባህሪ ይህ ነበር፡፡ እያንዳንዳቸው ሲጠየቁ ፈትዋውን ጓደኛቸው ቢመልስላቸው ይመኙ ነበር፡፡
በራእ ብን አዚብ የሚከተለውን ተናግሯል ፡ "لقد رأيت ثلاثمائة من أهل بدر ما منهم أحد إلا وهو يحب أن يكفيه صاحبه الفتوى"
“ከበርድ ጦርነት (ዘማች ሶሀቦችን) ሶስት መቶ የሚሆኑትን ተመልክቻለሁ፣ ከአነርሱ አንድም አካል የለም ፣ ፈትዋው በጓደኛው እንዲብቃቃ የሚወድ ሆኖ እንጅ”
(አልፈቂህ ወልሙተፈቂህ” 2/165)
ታብዕዮችም ይህን ባህሪ ከሶሃቦች ወርሰዋል፡፡
አብዱረህማን ብን አቢ ለይላ የሚከተለውን ተናግሯል ፡ “ከአላህ መልክተኛ ባልደረቦች ከአንሷሮች አንድ መቶ ሀያ የሚሆን አግኝቻለሁ አንዱ ጥያቄ ሲጠየቅ ወደዚያኛው ይመልሰዋል ፤ ያኛው ሲጠየቅ ወደዚያኛው ይመልሰዋል መጨረሻም ጥያቄዋ መጀመሪያው ወደተጠየቀው ሰው ትመለሳለች፡፡” (ዳረሚይ 1/53 ፤ ኢብን አልሙባረክ “ዙህድ” 58)
ቃሲም ብን ሙሀመድ አንድ ቀን ተጠየቀ፡፡ “አላውቅም” ብሎ መለሰ፡፡ ከዚያም የሚከተለውን ተናገረ ፡
"والله لأن يعيش الرجل جاهلا بعد أن يعلم حق الله عليه خير من أن يقول مالا يعلم"
أخرجه الدارمي : 1\48
“ወሏሂ ፣ አንድ ሰው የአላህን ሀቅ ካወቀ በኋላ የማያውቀውን ከሚናገር ለእርሱ ጃሂል ሆኖ ቢኖር ይሻለዋል፡፡”
ኢብን አባስ የሚከተለውን ተናግረዋል ፡ "إذا ترك العالم لا أدري أصيبت مقالته" “አሊም 'አላውቅም' የሚለውን ከተወ ንግግሩ ፈተና ይደርስባታል”
(ኢብን አብዱል በር ፡ ጃሚእ በያኑል አልኢል” 2/54)
አቡዘያል የሚከተለውን ተናግሯል ፤ "تعلم لا أدري ولا تعلم أدري ، فإنك إن قلت لا أدري علموك حتى تدري ، وإن قلت أدري سألوك حتى لا تدري"
“'አላውቅም' የሚለውን ተማር ፣ 'አውቃለሁ' የሚለውን አትማር ፤ አንተ 'አላውቅም' ካልህ እስከምታውቅ ድረስ ያስተምሩሃል ፤ 'አውቃለሁ' ካልህ ግን እስከማታውቅ ድረስ ይጠይቁሃል፡፡
“ጃሚኡ በያኑል ኢልሚ ወፈድሉህ” 2/55)
https://t.me/alateriqilhaq كن على بصيرة