Фильтр публикаций


በመኖር ትርምስ ያለ እርጋታ ያህል
በህይወት መቀዝቀዝ የሞቀ ፍቅር ያህል
ህመም እንደሚያቀል
የበሰለ አባባል
ጥሎብኝ ’ወዳለሁ
"የአባቱ ልጅ!" መባል።

አማን@amadonart


         ተስፋ

ወደታች ወደላይ ባክኖ ያየ አንድ ሰው
የኢትዮጲያን ነገር እንዲህ ሲል ተቀኘዉ

‘እኔን ከሀገሬ መውደድ አያስረኝም
ደርሶ የመጣም ነፋስ አይነጣጥለኝም
ይሄ መንታ መንገድ ያልተፈታ ገና
እያዞረ ወስዶ ይጥለኛልና
እያሽከረከረ የወሰደኝ ‘ነገር’
ዘረፍኩ ባልኩት ቅኔ እንደዚህ ስቸገር
እደርስ ስል ስሮጥ ያልያዝኩት ቢበዛም
የሀገሬ ርቀት ከክፋት አልገፋም።’
 
        አማን@amadonart


          ‘ክፈሉ’
የሚያካፋው ዝናብ ተው ደም ይሆናል
የተዘራ አንድላይ ለየቅል ይበቅላል
ግጥም ስብከት አልባ
                   ስሜት ነው እንዲሉ
ማለቂያ የሌለው ነገር አትኮልኩሉ
ፍቅር ሰምሮ ባያቅ
እንዲህ አንዳላችሁ ጥላቻን ‘ክፈሉ’
ጥልም ልናፈርበት
ሰዉነት ይታሰር ፍቅርን ‘ክፈሉ’።
Aman


       መንገድ

ገሽልጦ የሚጥል ነገር እየጠጣሁ
ህሊናን የሚያስንቅ ኑሮ እየገዛሁ
ኮረንቲ 'ሚያስረሳ ኩራዝ እየፈጀሁ
እዉቀት የሚሸፍን ጉልበት እያበጀሁ
ከእልፍ ምኞቴና ከምንም እምነት ጋር
እጠብቃለሁኝ ነፃነት 'እስቲማር'።

አማን@amadonart


         ህገ–ስጋ
  (የታመመ ትዉልድ ቅኔ)

አትዩ ግዴለም
ባለመመልከቱ ያጣ ሀበሻ የለም።
      (*)
አትመራመሩ እንተኛ ግዴለም
አሸወይና ይሁን ፍቅር ነው መጋደም
ገድሎ–እስኪያበቃ ተጠርጣሪ የለም ።
       (**)
ጀግንነትም ይፈር እንኳንስ ምንሽር
ያዳም ዘር በሙሉ ይኮልኮል ከሰል ስር
ህይወት ስትራገብ መንደድ ነው ምስጢሩ
ባለ ምድጃውን አይገፋም አየሩ።
       (***)
‘አዋቂ ብላችሁ ማንንም አትስሙ፥
          በፅሁፍ ስላለ በሁሉ አትመሩ’
በህይወት መተብተብ–
     የመደሰት ጣሪያን እናንተዉ አኑሩ፥

ምክንያቱም...
ለማያንሰራራ_ተስፋውን እንዳለ
አሟጦ ለጣለ

ምን ምክር ይገኛል ሀሰት ያላዘለ?

አይዟችሁ ዘንድሮ –ከችግሩ በላይ
ጠፍቷል የበቀለ።

         አማን @amadonart


            ንጋት

ሲጨልም ዝም ሲል_
ምድር ገፁን ሲያጣ
ሰማይ እኔን ሲመስል _ ወዶ ሲገረጣ
ህያዋን ሲደክሙ_ ወየው ያሉ ለታ
የጦቢያ ፍቅር ንድፍ የ ደመቀ ለታ
ያኔ አንቺ ሀገሬን÷ያኔ እኔን አያርገኝ...
ታውሮ የቆየ ቤት ብርሃንን ሲያገኝ!

Aman @amadonart


(በዉሸትሽ እምላለሁ)


ደጉ ባልነው ዘመን ‘ውዴ ትቅደም!’ ብሎ
አንቺና ክፋትሸን አምኖ ተቀብሎ

ሲኖር አንዳልነበር
‘መሄድሽ’ ሲነገር

ያንቺ መጥፎነት ላይ ገኖ የነበረ
የዋህነት ግብሬ ከላዬ በረረ::

ያው እንደምታውቂው...

ከዛን ቀን ጀምሮ ራሴን አይደለሁም
                       አለሁ እል ይሆናል

‘ይንሳኝ ዉሸትሽን’ –ሀቅ’ማ እኔን ሆኖ
                          መች ያማምለናል 

 
               አማን
      @amadonart


                 አምላኬና እናቴ

ፊቴ ተዘብጐ ከማየው ሞት ይልቅ
                       ያ ህይወት ይበልጣል

ከሰውነት በላይ ረቂቅ ማንነቴ
                            ኩራቴን ይሰብራል

ከጥፋቴ ገዝፎ ፍፁም ቸርነቱ
ሀሳቤን ይገዛል

የተሰጠኝ ፀጋ ከዓለም ፍትህ በላይ
እጅጉን ይልቃል

ተመስገን ለእናቴ ለእርሷ በኔ ኗሪ
እሩቅ ሳይ ከእንቅፋት ጠብቃኝ አዳሪ!

                Aman


       ( ወኔ ¡)

ዝቅ አትበል  አንተ በግ-
ልረድህ ያሉህ 'ለት

አንገትህን ደፍተህ ዛሬ በቆምክበት

የስንቱ እምቢ ባይ ነው ደም የፈሰሰበት!!


Aman

@amadonart


          ህልምና ቅኔ

ንጋትን ፍለጋ ወደዚያ ስማትር
አየሁኝ ተገፍቶ የጣሉትን ፍቅር

ማሰብ ሀጥያት ሆኖ_
ምዕመን መክኖ ሲቀር
አየሁኝ ተጠበው_  ያቆሙትን መንደር

በዚያ የሚናገር – የሚሰማም የለም
በየራሱ እዉነት – መሽጐ እንዲታመም
           ...
"ለምን እኔ ብቻ?"  በሚባል መፈክር
ይታየኛል ‘በእንቅልፍ–የተተወች ሀገር’።



              Aman

       @amadonart


        አላስቀድምሽም

ከውበትሽ ይልቅ እድፍሽን ማጐላው
ከእንከን አልባነትሽ ስህተትሽን የምሻው
ብዕሬ አንቺን ትቶ ሀገሬን ’ሚጠራው

ወድጄ አይደለም...

የኔና አንቺ ነገር ፍቅር ተባለ እንጂ...
ነፍሴን ከምድሬ ጋር አንድ ላይ ብትወስጂ
በኔ ዓለም_ ላፍታ ገብተሽ ብትወጪ
መሬቴ ’ምላትን ከልብሽ ብትረግጪ


ትረጂልኝ ነበር የሚነዝረኝ ነገር
ካንቺ እንደሌለ

ሲፈጥረኝ ጀምሮ በእርሱው የተኳለ

የሀሴቴም አድማስ
የእንባዬም ሙቀት ጦቢያን እንዳዘለ!

አማን

@amadonart


                  የፍቅር ጥግ

ይኸው እኔና አንቺ_ መቀስቀሱ ከብዶን
                     _ ያልሞተን ህሊና

  አዶናይ ተዋርዷል እኛኑ ሊያቀና

  በዚህ ግፍ ባለበት ምህረት እንዲፀና

Aman

@amadonart


                ፍርሃት

ልተንፍሰው ብዬ ኑሮዬን ብምገዉ

‘የህይወት አቀበት’ ብሎ
የፃፈ ሁሉ –እንደሚከበረው
ከሀዘን ላይ
ውበት እንደሚጨመቀው
ያልኖረውን ዓለም
ረሃብ እንዳስፃፈው
ማስተጋባት ብልሀት
እንደሚመስለው ሰው...
 
ላወጣሁት ብሶት ምፀት አቀበሉ
ጩኸት ሲያጨምተኝ ያላዩ ዓይኖች ሁሉ
ነፃነት ያቀናው ሰላም አለው አሉ

Показано 13 последних публикаций.

123

подписчиков
Статистика канала