✔️መልስ፦ በጥልቀት ተቆፍሮ የወጣ ጉድጓድ በበጋም በክረምትም ከውሃ እንደማይደርቅ ሁሉ ጥልቅ ጥበብም በብልህ ሰው ልቡና ይኖራል ማለት ነው። ፈሳሽ ወንዝ ሲፈስስ ደስ እንደሚያሰኝ ጥበብም ከጥበበኛ አፍ ስትነገር ደስ ታሰኛለች ማለት ነው።
▶️፲፮. "የሰው ሆድ ከአፉ ፍሬ ይሞላል። ከንፈሩም ከሚያፈራው ይጠግባል" ይላል (ምሳ.18፥20)። የሰው ሆድ ከአፉ ፍሬ ይሞላል ሲባል ምን ማለት ነው?
✔️መልስ፦ በሆድ ሁሉንም ሕዋሳት መናገሩ ነው እንጂ ሰው ከአፉ ፍሬ ማለት በአፉ ጸልዮ ከሚያገኘው ጸጋ፣ በከንፈሩም በጸለየው ጸሎት ሁለንተና ሰውነቱ ጸጋን፣ ክብርን ያገኛል ማለት ነው።
▶️፲፯. "የሚገዛ ሰው ክፉ ነው ክፉ ነው ይላል። በኼደ ጊዜ ግን ይመካል" ይላል (ምሳ.20፥14)። ለማለት የተፈለገው ሀሳብ ምንድን ነው?
✔️መልስ፦ እህልን ወይም ሌላ ነገርን የሚገዛ ሰው ዋጋው እንዲረክስለት ነገሩን ያክፋፋዋል ማለት ነው። ከገዛው በኋላ ግን ጥሩ ነገር ገዛሁ እያለ ለሁሉ ያወራል ማለት ነው። የሚገዛ የሚለው እህልን የሚገዛ ለማለት ነው እንጂ ሰውን የሚያስተዳድር ለማለት አይደለም። እንግሊዘኛው ለይቶታል Buyer ይለዋል። ለሰው ቢሆን Governor ይል ነበርና። ሙሉው “It is not good, it is not good” says the buyer; then off he goes and boasts about his purchase ይላል።
▶️፲፰. "ዐሳብ በምክር ትጸናለች። በመልካምም ምክር ሰልፍ አድርግ" ይላል (ምሳ.20፥18)። በመልካምም ምክር ሰልፍ አድርግ ሲል ምን ማለት ነው?
✔️መልስ፦ በመልካም ምክር ሰልፍ አድርግ ማለት ንጉሥ በጠላቶቹ ላይ ጦርነትን ሲያውጅ በተጠና ምክር ሊሆን ይገባል ማለት ነው። አጋንንትን ስንገጥምም በጥሩ ምክር ሆነን በፈሊጥ በጥበብ መዋጋት እንደሚገባን የሚያመለክት ቃል ነው።
▶️፲፱. "ዘዋሪ ሐሜተኛ ምሥጢርን ይገልጣል። ከንፈሩን የሚያሞጠሙጥ ሰውን አትገናኘው" ይላል (ምሳ.20፥19)። ዘዋሪ የተባለው ወዴት የሚዞር ነው?
✔️መልስ፦ ዘዋሪ ሐሜተኛ ማለት በየመንደሩ እየዞረ (እያውደለደለ) ሰውን የሚያማ ማለት ነው። እገሌማ እንዲህ አደረገ፣ እገሌማ እንዲህ ነው እያለ ምሥጢር የሚያወጣ ማለት ነው።
▶️፳. "ጠቢብ ንጉሥ ኃጥኣንን በመንሽ ይበትናቸዋል። መንኰራኵሩንም በእነርሱ ላይ ያንኰራኵርባቸዋል" ይላል (ምሳ.20፥26)። ለማለት የተፈለገው ሀሳብ ምንድን ነው?
✔️መልስ፦ መንሽ ገለባውን ከፍሬው እንደሚለይ ሁሉ ጠቢብ ንጉሥም ወንጀለኛውን ሰውና ንጹሕ ሰውን በፍርዱ ይለያቸዋል ማለት ነው። መንኰራኵር ማለት እንደመኪና የሚገለባበጥ ነገር ነው። ወንጀለኞችን በዚህ ይቀጣቸዋል ማለት ነው።
▶️፳፩. ምሳ.16፥4 ላይ "በዐመፃ እጅን በእጅ የሚመታ አይነጻም" ይላል። ንባቡን ቢያስረዱን።
✔️መልስ፦ እጅን በእጅ መምታት የመሐላ ምልክት (ትእምርተ መሐላ) ነው። ስለዚህ ሰዎች ሌላውን ለመጉዳት በዐመፅ መማማል አያነፃም ማለት በደለኛ ተብሎ በእግዚአብሔር ይፈረድበታል ማለት ነው።
▶️፳፪. "ኀጥእ ለክፉ ቀን ይጠበቃል" ይላል (ምሳ.16፥9)። ምን ማለት ነው?
✔️መልስ፦ ኃጥእ ለክፉ ቀን ይጠበቃል ማለት ኃጥእ ሰውን ክፉ ቀን ያገኘዋል ማለት መከራ ይገጥመዋል ማለት ነው። መከራ ሥጋ መከራ ነፍስ ይገጥመዋል ማለት ነው።
▶️፳፫. ምሳ.20፥16 ላይ "ለማያውቀው ከተዋሰ ሰው ልብሱን ውሰድ። ለእንግዳ የተዋሰውንም እርሱን አግተው" የሚለው ሀሳቡ ምን እንደሆነ አልገባኝም።
✔️መልስ፦ አንድ ሰው ለማያውቀው ሰው ዋስ ሆኖ ሳለ የተዋሰው ሰው መልሶ ወንጀል ሠርቶ ቢጠፋ የተዋሰው ሰው መክፈል ይገባዋልና ይህን ለመግለጽ ልብሱን ውሰድ ይላል። ለእንግዳ የተዋሰውንም እርሱን አግተው ማለት እንግዳው ቢጠፋ እንግዳው ሊከፍለው የሚገባውን ነገር ዋሱ ይክፈል ማለት ነው።
▶️፳፬. ምሳ.17፥9 ሌሎች የሠሩትን በደል የሚሰውር እንጅ የራሱን በደል የሚሰውር (ንስሓ የማይገባ) እንዴት ነው እርቅን የሚሻ?
✔️መልስ፦ እውነት ነው የራሱን በደል ከንስሓ አባቱ የሚሰውር ሰው በደል ይሆንበታል። ነገር ግን ከዚህ የተጠቀሰው ሌላ ሰው በድሎት እያለ ለዕርቅ ብሎ በደሉን ትቶ ተበድሎ ሳለ አልተበደልኩም የሚል ዕርቅን ይወዳል ለማለት ነው።
▶️፳፭. ምሳ.16፥10 ሰው የሆነ ንጉሥ እንዴት የማይሳሳት (infallible) ይሆናል? የቱንም ያህል ጥበብ ቢኖረው በፍርድ አይሳሳትምን? his mouth does not err in judgment ይላልና።
✔️መልስ፦ ሥጋዊ ንጉሥ ፍጹም ስላልሆነ ሊሳሳት ይችላል። ፍርዱም ፍጹም እውነት ነው የሚባል አይደለም። ይህ የሚነገር ለእግዚአብሔር ብቻ ነው። በተቻለ አቅም ግን ተቀብቶ የሚነግሥ ንጉሥ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ስለሚያድርበት ከሌላው በተሻለ ጥሩ ፍርድ ይፈርዳል ማለት ነው። his mouth does not err in judgment ማለቱም በፍጹም ሳይሆን በአንጻራዊ ነው።
▶️፳፮. ምሳ.18፥22 ላይ "ሚስትን ያገኘ በረከትን አገኘ" ይላል። ይህ እንዴት ይታያል? የሁሉ ሚስት አንድ ይሆናል እንዴ?
✔️መልስ፦ ሚስት ያገባ ሁሉ በረከትን አገኘ አይባልም። ደግ ሴትን ያገኘ ሰው በረከትን ያገኛል ማለት ነው። ግእዙ የተሻለ ገልጾታል። "ዘረከበ ብእሲተ ኄርተ ረከበ ሞገሰ" ይላል።
▶️፳፯. ምሳ.18፥14 ላይ "የሰው ነፍስ ሕመሙን ይታገሣል። የተቀጠቀጠን መንፈስ ግን ማን ያጠነክረዋል" ይላል። የተቀጠቀጠ ሲል ምን ማለት ነው?
✔️መልስ፦ የተቀጠቀጠ ነገር ደካማ እንደሚሆን ሁሉ ደካማ ልብ ያለው ሰው ለማለት ነው። መንፈስ ያለው ከዚህ ልብን ነው። የተቀጠቀጠ መንፈስ ያለው ሰው ማለት ልበ ደካማ፣ አእምሮ ደካማ ሰው ማለት ነው።
▶️፳፰. ምሳ.20፥30 ላይ "የሰንበር ቁስል ክፉዎችን ያነጻል" ይላል። የሰንበር ቁስል ማለት ምንድን ነው?
✔️መልስ፦ ክፉዎችን ያነጻል ማለት ይጥላል ማለት ነው። ያነጻል ከዚህ ይጥላል ተብሎ ይተረጎማል። የሰንበር ቁስል ማለት የሆድ ቁስል፣ የጨጓራ ቁስል ማለት ነው። ይህ ከባድ በሽታ ስለሆነ ይጥላል ማለት ነው።
▶️፳፱. መዝ.17፥12 ላይ "ሰነፍን በስንፍናው ከመገናኘት ልጆቿ የተነጠቁባትን ድብ መገናኘት ይሻላል" ይላል። ልጆቿ የተነጠቁባት ድብ እንዴት ያለች ናት?
✔️መልስ፦ ልጆቿ የተነጠቁባት ድብ በጣም ቁጡ ስለሆነች ትገድላለች። ነገር ግን ሰነፍ ሰውን በስንፍናው ከማግኘት እርሷን መገናኘት ይሻላል አለ። ቁጡ ድብ ብትጎዳን ሥጋችንን ነው። ሰነፍ ሰው ግን ሥጋንም ነፍስንም ይጎዳልና ይህን ለመግለጽ ነው።
© በትረ ማርያም አበባው
✝️የዩቲዩብ ቻናሌ:- ንሕነ ዘክርስቶስ
https://youtube.com/@edenawizechristos?si=6V4y-73OM3LTzhAf ነው።
🌻የፌስቡክ ገጼ Betremariam Abebaw
https://www.facebook.com/profile.php?id=100075547015721 ነው።